- ንግድ ባንክ ክሱ እውነት መሆኑን ሲያረጋግጥ ዓቃቤ ሕግ ግን የተሠራ ወንጀል የለም ብሏል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና አቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ያላግባብና ከሕግ ውጪ ፈጽመዋል በተባለ የመጋዘን ጨረታና ሽያጭ፣ በናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የቀረበባቸውን የፍትሐ ብሔር ክስ ላለፉት 13 ዓመታት ሲከራከሩ ከርመው ጉዳዩ ሰበር ሰሚ ችሎት የደረሰ ቢሆንም፣ ችሎቱ ጉዳዩ በሥር ፍርድ ቤት በድጋሚ መታየት እንዳለበት ገልጾና የመከራከርያ ነጥቦችን ለይቶ በማስቀመጥ ውሳኔ ሰጥቶ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ትዕዛዝ ያስተላለፈበት የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ከብድር ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት መጋዘኖችንና አንድ የኢንሹራንስ ቦንድ በመያዣነት ወስዶ ወይም ይዞ ለናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ ግል ማኅበር 35 ሚሊዮን ብር ያበድራል፡፡ ናይል ቡና ላኪ ድርጅት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት የተበደረውን ገንዘብ በውሉ መሠረት መመለስ ባለመቻሉ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዋስትና የያዛቸውን ሁለት መጋዘኖች ጨረታ አውጥቷል፡፡ በወጣው ጨረታ ብቸኛ የነበረው ተሳታፊ አቢሲኒያ ባንክ በመሆኑ፣ ጨረታው ይሰረዝና ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ ይወጣል፡፡
በሁለተኛውም ጨረታ ብቸኛ ተሳታፊ የሆነው በድጋሚ አቢሲኒያ ባንክ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጨረታው አሸናፊ አቢሲኒያ ባንክ መሆኑን በማሳወቅ እንዲረከብ አድርጎታል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ ያሸነፈውን ሁለት መጋዘን ሲረከብ፣ ለክሱ ምክንያት የሆነ ሁለቱ መጋዘኖች በሚገኙበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለ አንድ ሌላ ሦስተኛ መጋዘን መረከቡን የክስ ሒደቱ ያሳያል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በጨረታ ያሸነፈውን ንብረት ሲረከብ ሦስተኛው መጋዘን በጨረታው ውስጥ ያልተካተተ በመሆኑ ‹‹ልትረከብ አትችልም›› በማለት ናይል ቡና ላኪ ድርጅት ክስ መመሥረቱንም የክስ መዝገቦች ያስረዳሉ፡፡
ክሱን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዝርዝር ማስረጃዎችን ካየ በኃላ፣ ሦስተኛው መጋዘን ለጨረታ አለመቅረቡን በማረጋገጥ ለናይል ቡና ላኪ እንዲመለስ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ በመከፋቱ ጉዳዩን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቅርቦታል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎት በበኩሉ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ መርምሮና ተጨማሪ ክርክር ሰምቶ በሰጠው ውሳኔ፣ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክል ባለመሆኑ ሦስተኛው መጋዘን ለናይል ቡና ላኪ ሊመለስ እንደማይገባ ገልጿል፡፡
መሠረታዊ የሕግ ጥሰት እንደተፈጸመበት ያመለከተው ናይል ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጉዳዩን ለፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ሲያቀርብ፣ ችሎቱ ‹‹የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል›› በማለት የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ከመረመረ በኋላ መከራከሪያ ጭብጦችን ለመለየት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጨረታ ለአቢሲኒያ ባንክ ስለተላለፉት መጋዘኖችና በጨረታው ውስጥ አልተካተተም ስለተባለው ሦስተኛ መጋዘን አጣርቶ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የንግድ ባንክ ኃላፊዎች አቢሲኒያ ባንክ መጋዘኖቹን እንዲረከብ ያደረጉት በሕገወጥ መንገድ ነው መባሉን በሚመለከት ደግሞ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት አጣርቶ ውሳኔውን እንዲልክና ሌሎች ነጥቦችን ጨምሮ የሥር ፍርድ ቤት አጣርቶና በድጋሚ መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ሰበር ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ስለመጋዘኑ ጨረታ እንዲያጣራ ትዕዛዝ የደረሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጣርቶ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ባንኩ ባደረገው የኦዲት ጥናት፣ በድምሩ የንብረት ግምታቸው 23,156,204 ብር የሆነና ተያይዘው የተሠሩ መጋዘን ቁጥር 1፣ ቁጥር 2 እና ቁጥር 3 የተባሉ መጋዘኖች መኖራቸውን አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ቢሮና የወርክሾፕ ሕንፃዎች መኖራቸውንም ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለናይል ቡና ላኪ ድርጅት ለሰጠው ብድር ለመያዣ ተደርጎ የተሰጡት መጋዘን 1 እና 2 መሆናቸውን ገልጿል፡፡ መጋዘን ቁጥር ሦስት በግቢው ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ ያልተገመተና ለሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ ላይ ያልተካተተ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ነገር ግን መጋዘኑ የተበዳሪው ንብረት ቢሆንም ለጨረታ አሸናፊው አቢሲኒያ ባንክ ተላልፎ መስጠቱን አረጋግጧል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፎርክሎዠርና ብድር ክፍል ቡድን መሪ ትዕግሥት ገብረ እግዚአብሔርና በንግድ ባንክ ነገረ ፈጅ ኢትዮጵያ ታመነ ተረጋግጦ ለፍርድ ቤቱ የተላከው ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ በመጋዘኖቹ ህልውና ላይ የበላይ ኃላፊዎች እንዲወስኑበት ተጻፈ የተባለው ቃለ ጉባዔ ጠፍቷል በመባሉ፣ የጨረታው አሸናፊ አቢሲኒያ ባንክ ስለመሆኑና የበላይ ኃላፊዎች ስለማፅደቃቸውም ማወቅ እንዳልተቻለ አረጋግጠው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ናይል ቡና ላኪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተበደረው ብድር በመያዣነት ካስያዛቸው በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 27 ቀበሌ 11 የቤት ቁጥር አዲስና በሊዝ ቁጥር 0270 ከተገዛው 22,753 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተሠሩትን መጋዘን 1 እና 2 ብቻ መሆናቸውን ባንኩ አረጋግጧል፡፡ መጋዘን ቁጥር 3 ያለ ቢሆንም እንዳልተያዘ አረጋግጧል፡፡
ሰበር ሰሚ ችሎት በተመሳሳይ ሁኔታ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት፣ የንግድ ባንክ ኃላፊዎች እንዴት አድርገው መጋዘኖቹን በጨረታ አሸንፏል ለተባለው አቢሲኒያ ባንክ እንደሰጡ እንዲያጣራ፣ ተፈጽሟል የተባለውን የሙስና ወንጀል ጥቆማ እንዲያረጋግጥ ትዕዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ በዳይሬክተሩ አቶ መዝሙር ያሬድ ተፈርሞ ለፍርድ ቤቱ የተላከው ምላሽ እንደሚያስረዳው ከሳሽ ናይል ቡና ላኪ ድርጅት የመሠረተው ክስ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን ገልጿል፡፡ በባንኩ ውስጥ ተጠርጥረዋል ስላተባሉት ኃላፊዎች ምንም ያገኘው ነገር እንደሌለ በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ብድር የሰጠው ንግድ ባንክ ግን፣ ጨረታው በበላይ ኃላፊዎች ሳይፀድቅ በቦታው ላይ የሚገኙ ሠራተኞች እንዴት ጨረታ ያልወጣበትን መጋዘን ጭምር ሊያስረክቡ እንደቻሉ እየጠየቀ ነው፡፡ መዝገቡ የተመለሰለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር አንደኛ ችሎት የተቋማቱን ምላሽና ሰበር ሰሚው ችሎት ያስቀመጠለትን ነጥቦች በመመርመርና ከተገቢው ሕግ ጋር በማገናዘብ፣ ተጨማሪ ክርክር ለማድረግ ለግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጥሯል፡፡