የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሚቀጥለው ዓመት ከኅዳር 8 እስከ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በጋና ለሚያከናውነው የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ፣ የማጣሪያ ውድድሮችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከሜዳቸው ውጭ ከሊቢያ ጋር በገለልተኛ ሜዳ ግብፅ ካይሮ ላይ ረቡዕ ይጫወታሉ፡፡
በአሠልጣኝ ሰላም ዘርዐይ እየተዘጋጀ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) እሑድ መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካይሮ ያመራል፡፡ ቡድኑ የሊቢያ አቻውን የሚያሸንፍ ከሆነ ሁለተኛውን ማጣሪያ ከሴኔጋልና አልጀሪያ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡
ሉሲዎቹ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በየወሩ ይፋ ከሚያደርገው የአባል አገሮች የእግር ኳስ ደረጃ ውጪ አድርጎት መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ምክንያት ተብሎ የቀረበው አገሮች በፊፋ ወርኃዊ ደረጃ ውስጥ ለመካተት፣ ቡድኖች በዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ መሥፈርት መሠረት ሉሲዎቹ ለ19 ወራት ያህል ምንም ዓይነት ውድድሮችን ማድረግ ሳይችሉ መቆየታቸው ከፊፋ የአገሮች የእግር ኳስ ወጪ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል፡፡