Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ማንም ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መኖሩ አያስደስተውም››

ሚስ አሁና ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ ተጠሪ

ሚስ አሁና ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ቋሚ ተጠሪ፣ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪና በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ፕሮግራም ቋሚ ተጠሪ በመሆን በኢትዮጵያ ተመድበው መሥራት ከጀመሩ ሦስት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ኢትዮጵያ በመምጣት የተመድ ተጠሪ ሆነው በቆዩባቸው በእነዚህ ዓመታት፣ አብዛኛውን ጊዜ በአስቸኳይ የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታዎች ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ለማድረግ የተገደዱባቸውን ተከታታይ ሦስት የድርቅ ዓመታትን ታዝበዋል፡፡ ለኢትዮጵያ መደረግ ስለሚገባቸው አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታዎችና ለልማት ስለሚያስፈልጉ ድጋፎች በበርካታ መድረኮች ከለጋሾች ጋር ሲነጋገሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየተነጋገሩ ይገኛሉ፡፡ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ድርቅ ስምንት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ለአስቸኳይ ዕርዳታ መዳረጉ ብቻም ሳይሆን፣ በዓለም ዙሪያ በሚታዩ ልዩ ልዩ ቀውሶች ሳቢያ የሚፈለገውን የዕርዳታ መጠን ማግኘት አዳጋች እየሆነ እንደመጣ፣ ዕርዳታ ለማግኘት ያለው ሽሚያም እየጨመረ መምጣቱን ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ ገልጸዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በተመድ ልዩ ልዩ የሰብዓዊና የልማት ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍ የካበተ ልምድ ያላቸው ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፣ በ15 አገሮች ውስጥም እንዲህ ያሉትን ሥራዎች በማስተባበርና በመምራት ይታወቃሉ፡፡ ብርሃኑ ፈቃደ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኮንጎ ሕንፃ በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ውስጥ ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼን በማነጋገር የሚከተለውን አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዳለመታደል ሆኖ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም ለአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ተዳርገዋል፡፡ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቅ የዕርዳታ አቅርቦት ይሻሉ፡፡ የተመድ ቋሚ አስተባባሪ እንደ መሆንዎና እንደ ተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ወኪልነትዎ ሁኔታውን እንዴት ገምግመውታል? ከከፋ ሁኔታ ወደ ባሰ የከፋ ሁኔታ እያመራ ነው ማለት ይቻላል?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- ድርቁ ዳግመኛ መምጣቱ መጥፎ ነው፡፡ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በአገሪቱ ድርቅ ተከስቷል፡፡ ድርቁ ከአየር ንብረት ለውጥ አኳያ ከከፋ ሁኔታ ወደ ተባባሰ ሁኔታ አምርቷል ወይ ካልን አዎን ትክክል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙውን ጊዜ ድርቅ ሲያጋጥማት ቆይታለች፡፡ ሆኖም በየመካከሉ ግን የዕፎይታ ጊዜያት ነበሩ፡፡ ከአንዱ የድርቅ ዘመን ወደ ሌላው በሚደረግ ሽግግር ወቅት ከድርቅ ዕፎይ የሚባልበት ጊዜ ባለፉት ሦስት ዓመታት አልታየም፡፡ በእነዚህ ዓመታት የተከሰተው ድርቅ በርካታ ሰዎችን ለችግር ዳርጓል፡፡ ባለፈው ዓመት የተከሰተው በዋናነት ያጠቃው የቆላማ አካባቢ ሕዝቦችን ነበር፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት እንዲሁም ካቻምና በኤልኒኖ ሳቢያ የተከሰተው ድርቅ ግን አብዛኛውን የደጋ አካባቢዎች አጥቅቶ ነበር፡፡ በሕዝቡ አሰፋፈር ሳቢያ የደጋው አካባቢ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞታል፡፡ በዚህ ሳቢያ ብቻም ሳይሆን በእነዚህ አካባቢዎች ካለው የአቅም ውስንነት የተነሳም ለችግሩ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ ከባድ አድርጎት ነበር፡፡ በአብዛኛው ኑሯቸውን በአርብቶ አደርነት የመሠረቱ ሰዎች የሚኖሩበት በመሆኑም ጭምር ድርቁ ከባድ ጫና ነበረው፡፡ ለማገገም ዓመታትን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ዓመት በዝናብ ሥርጭቱ ላይ መለስተኛ መሻሻል ቢታይም፣ በርካቶች አሁንም ድጋፍ የሚሹበት ወቅት ከመሆን አልተወጣም፡፡ አንዱ ምክንያትም ካለፈው የድርቅ ችግር ሊያጋግሙ ባለመቻላቸው ጭምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዘንድሮውን ድርቅ ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ሌሎችም ችግሮች መከሰታቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንደኛው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ስደተኞች በአገሪቱ መጠለላቸው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በፖለቲካ ግጭት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎች መኖራቸውም ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ከመጋፈጥ አኳያ የተመድ ኤጀንሲዎች ችግሮቹ ወደ አሳሳቢ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ ምን እያደረጉ ነው?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- ችግሩ በተጠቀሱት ፈታኝ ሁኔታዎች ብቻም ሳይሆን በዓለም ላይ በሚታየውም ሁኔታ ሳቢያ አሳሳቢነቱ የጎላ ነው፡፡ ከፍተኛ የዕርዳታ ፍላጎት በየቦታው እየታየ ነው፡፡ ከጄኔቭ በቅርቡ ነው የተመለስኩት፡፡ ከብሔራዊ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ ጋር በመሆን፣ ኢትዮጵያ ስለሚያፈልጋት ዕርዳታ ለለጋሾች ገለጻ አድርገናል፡፡ ገለጻውን ባቀረብንበት በዚያኑ ዕለት በሶሪያ ጉዳይ ላይ ከሚነጋገሩ ለጋሾች ጋር ተገናኝተናል፡፡ ለሰብዓዊ ዕርዳታ የሚውል ጥሪት ፍለጋ ላይ ከፍተኛ ሽሚያ አለ፡፡ በዓለም ዙሪያ ይህ ፈተና አለብን፡፡ ያለው ሀብት በርካታ ቀውሶች ላይ እንዲውል ስለሚፈለግ፣ በየቦታው ተበጣጥሶ የሚያስፈልገውን ያህል ለማግኘት አዳጋሽ እየሆነ ነው፡፡ ከምናበረታታቸው ጉዳዮች መካከል መንግሥት ለችግሩ መቋቋሚያ አስተዋጽኦ ለማድረግ መነሳቱ ነው፡፡ ለቀረበው የዕርዳታ ጥሪ የመጀመርያውን ምላሽ የሰጠው መንግሥት ሲሆን፣ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህ አጋሮቻችን የበኩላቸውን እንዲያወጡ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ምክንያቱም አገሪቱ ራሷ ኃላፊነቷን ለመወጣት የተነሳች መሆኗን አሳይታለች፡፡ ችግሩ የደረሰበት አገር ለድጋፍ የሚውል ጥሪት ማዋጣቱ ብዙም ያልተመለደ ነገር ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ግን በርካታ ችግሮች በመከሰታቸው ሳቢያ በጥንቃቄ ለችግሩ የሚውለውን ሀብት የምንጠቀምበትን መንገድ እንድንፈልግም አስገድዶናል፡፡ ስምንት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በዚህ ዓመት ለምግብ ዕርዳታ መጋለጣቸው የታወቀ ነው፡፡ ለዚህ ችግር የተጋለጡት ሰዎች በአካባቢያቸው ይህ ነው የሚባል ኢንቨስትመንት ባለመኖሩ ጭምር እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት ከመንግሥት ጋር በመሆን የተለየና ሦስት ማዕቀፎች ያሉት ሞዴል አዘጋጅተን፣ ለጋሾች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እያግባባን ነው፡፡ መከላከልና መቋቋም፣ ምላሽ መስጠትና ተዘጋጅቶ መጠበቅ፣ እንዲሁም ለማገገም የሚያስችል ሥርዓት መፍጠርን ያካተቱ ማዕቀፎችን ነድፈናል፡፡ ሁሉም ተዋናዮች በአንድ ጊዜ በእነዚህ ማዕቀፎች ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጋብዘናል፡፡ የውኃ እጥረት በሚኖርበት ወቅት ቀድመን በመዘጋጀት ለእንስሳት የሚሆነውን መኖ ብናቀርብ ከዕልቂት እንታደጋቸዋለን፡፡ ቀድሞ መኖ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ስምንት ሚሊዮኖች ለምግብ ዕርዳታ ከሚዳረጉ ይልቅ እንዲህ ባለው ሥራ ላይ ኢንቨስት ማድረጉ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ አይሆንም፡፡

በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት የሚሰቃዩ ሰዎችን ቁጥርም ለመቀነስ ያስችለናል፡፡ በአሁኑ ወቅት 2.2 ሚሊዮን ሕፃናት ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተዳርገዋል፡፡ በአስቸጋሪ ወቅት ይህ አኃዝ ወደ ሦስት ሚሊዮን ያሻቅባል፡፡ በዚህ ዓመት 300 ሺሕ ተጨማሪ ሕፃናት ለአስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚዳረጉ እንገምታለን፡፡ ይህ እንግዲህ የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ ደረጃ ከፍተኛ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ሕፃናት እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ከፍተኛ ሥቃይን የሚያስከትል በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መገኘት እጅግ ከባድ ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ እንዲያገግሙ ለማድረግ የሚጠይቀው ወጪ ከሦስት እጥፍ በላይ ነው፡፡ በሰብዓዊ ጉዳዮችና በልማት ተዋናዮች በኩል የጋራ ኢንቨስትመንት እንዲፈጠር በማድረግ ችግሩ እንዳይባባስ ቀድሞ ለመከላከል ይረዳናል፡፡

ሪፖርተር፡- የልማት አጋሮች አስከፊውን ችግር ቢገነዘቡም ተደጋግሞ በሚከሰተው ድርቅና በሚጠየቀው ዕርዳታ ሳቢያ የተሰላቹና ድጋፍ ለመስጠትም የሚያቅማሙ ይመስላሉ፡፡ እነዚህ አካላት በተመድ የሰብዓዊ እንቅስቃዎች ላይ ያላቸው ምልከታ ምን ይመስላል? እውነት ተሰላችተዋል ማለት ይቻላል? የሚጠየቁትን ድጋፍ ከመስጠትስ ሊታቀቡ የሚችሉበት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- ተሰላችተዋል ማለት አልችልም፡፡ ችግሩ እየከበዳቸው እንደመጣ መናገር ግን እችላለሁ፡፡ ሁላችንም በዚህ ስሜት ውስጥ ብንሆንም የተሻለ ለማድረግ ግን እንፈልጋለን፡፡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎቱ ከፍተኛ እንዳይሆንም እንፈልጋለን፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑም ሙሉ በሙሉ ድጋፍ ለማድረግ አላስቻለንም፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች አስጠልላለች፡፡ ከ800 ሺሕ በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡ እነሱም ድጋፍ ይሻሉ፡፡ እንደሰማሁት ለእነሱ የሚያስፈልገውን ዕርዳታ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው ገንዘብ ውስጥ የ22 ሚሊዮን ዶላር ክፍተት አለ፡፡ ይህ እንግዲህ ስደተኞቹን ለመመገብ ከሚያስፈልገው ውስጥ ሲሆን፣ የሚደርሳቸውን ሬሽን ሙሉ በሙሉ እንኳ የማይሸፍን ነው፡፡ የልማት አጋሮች ስደተኞቹም ድጋፍ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም  ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እነሱንም የመደገፍ ግዴታ ስላለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እነዚህን ስደተኞች በማስጠለል የመልካም ተግባር ምሳሌነቷን በማሳየቷም ድጋፍ ትሻለች፡፡ ይህ እንግዲህ የሰብዓዊ ተግባራት ላይ የሚሳተፉትም ሆኑ የልማት ማኅበረሰቡ ሊሸከሙት የሚገባቸው ተግባር ነው፡፡ በዚህ ላይም በአገር ውስጥ አንድ ሚሊዮን ዜጎች በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለዋል፡፡ ይህም ነገሩን ሁሉ የሚያወሳስብ አዲስ ክስተት ነው፡፡ መንግሥት የተፈናቃዮች ችግር እንዲራዘም ወይም ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ አይፈልግም፡፡ ይህም ማለት ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው፡፡ ሰዎች ከመኖሪያቸው አካባቢ በተሰደዱበት ወቅት የቱንም ያህል ብንጣጣር እንኳ ሁኔታዎች በሙሉ የተመቹ እንዲሆኑላቸው ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ለተፈናቃዮች የሚስማማ ሁኔታ በአስቸኳይ መፍጠር እንደሚገባ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ግንባሮች በተከሰቱ አደጋዎች ሳቢያ ከአቅም በላይ የመወጠር እንጂ የመሰላቸት ችግር ተከስቷል ብዬ አላምንም፡፡   

ሪፖርተር፡- ከውጭ የገቡትን 800 ሺሕ ስደተኞች ከማስጠለል ባሻገር በግጭት ምክንያት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ዜጎች በአገሪቱ መታያተቸው፣ በየትኛውም ወቅት የሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትልና የመበታተን አደጋ የሚፈጥር ክስተት የአገሪቱንም የመቋቋም አቅም ምን ያህል በቀላሉ ተጋላጭ እንደሆነ ሊያሳይ የሚችል ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- እውነታው በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች መከላከል ላይ ያመዘነ አካሄድ እንከተላለን፡፡ የተመድ ዋና ጸሐፊም ትኩረታቸው እዚህ ላይ ነው፡፡ ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ ከመረባረብ ቀድሞውኑ መከላከሉ ላይ ማተኮር አለብን፡፡ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ የተከሰቱት ሰው ሠራሽም ሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎችን መከላከል ይቻል ነበር፡፡ ድርቅ የተፈጥሮ ክስተት እንደ መሆኑ መጠን ኢትዮጵያ ላትከላከለው ተችሏል፡፡ ሆኖም ድርቁ የሚያስከትለውን ጉዳት መቋቋም ይቻላል፡፡ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛትም ድርቅ ያጋጥማቸዋል፡፡ ሆኖም ወደ አስቸኳይ ዕርዳታ ደረጃ በጭራሽ አይወስዳቸውም፡፡ ተቋማትና ሥርዓት በዚህ መንገድ መገንባት አለባቸው፡፡ በዚህ አኳኋን የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም የተፈጠረው ሥርዓት ችግሩን ተቋቁሞ ለማለፍ ያስችላል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን ክስተቶች መጋፈጥና መቋቋም የሚችሉበትን አቅም ፈጥረዋል፡፡ የተፈጥሮ ክስተቶችን ማስቀረት ባንችል እንኳ ተፅዕኖአቸውን መቀነስና ቀውስ እንዳያስከትሉም መከላከል እንችላለን፡፡

ሌላው መንገድ ሰላምን በማስጠበቅ ረገድም የመከላከል አካሄድን መከተል ይኖርብናል፡፡ ብዝኃነትን ማስተናገድ ይቻላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የአፍሪካ አገሮች በብዝኃነት የታወቁ ናቸው፡፡ አንዳንዴ ይህንን ብዝኃነት የማስተናገድ አካሄድ ላይ የሚፈጠረው ውስብስብነት ነው ወደ ግጭት የሚያመራው፡፡ ግጭቶችን ለመከላከል ደግሞ ተቋማት የዳበረ አቅም ሊኖራቸውና ብዝኃነትን ማስተናገድ የሚችሉበት ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን በማስተዳደር በኩል የሚፈጠር ግጭት አለ፡፡ ለተፈጥሮ ሀብት የሚደረግ ሽሚያ አለ፡፡ እኩልነት የማያሰፍኑ አሠራሮችም መታየት አለባቸው፡፡ ለዚህ ነው ዘላዊ የልማት ግቦች ቁልፍ ድርሻ የሚኖራቸው፡፡ አካታችና ዘላቂ ልማትን የሚያበረታቱ፣ እንዲሁም አንድም ሰው ወደኋላ እንዳይተው ወይም ከልማት ተሳታፊነት ውጭ እንዳይሆን የሚጠይቁ ጽንሰ ሐሳቦችን ያራምዳሉ፡፡ የእያንዳንዱን ፍላጎት የሚያካትት ልማት ላይ ኢንቨስት ካደረግን ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ማስቀረት እንችላለን፡፡ ግጭቶች አሁንም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ብጥብጥ እንዳያመሩ ማድረግ እንችላለን፡፡ ብጥብጥ ነው ወደ መበታተን የሚወስደው፡፡ 

ሪፖርተር፡- በቅርቡ በኬንያ ድንበር ሞያሌ አካባቢ በተከሰተ ግጭት በርካቶች ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ይህም ለተጎጂዎቹ ብቻም ሳይሆን ለተመድም ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም፡፡ ከቀናት በፊት የተመድ ልዑክ ወደ ስደተኞቹ ጣቢያዎች በመሄድ ካምፖቹን ጎብኝቷል፡፡ ሁኔታው ምን ይመስላል? የተደረገ የቅድመ ዳሰሳ ጥናት ይኖር ይሆን?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- የመንግሥት ኃላፊዎችም እንዳረጋገጡት የተከሰተው ችግር አሳዛኝ ነው፡፡ መከሰት የማይገባው ነገር ቢሆንም ተከስቷል፡፡ በሰዎች ላይ ተፅዕኖ አስከትሏል፡፡ እንደተረዳነው 9,000 ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለው በኬንያ ድንበር አካባቢ ስደተኞች ሆነዋል፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ ፍላጎቶቻቸው ተሟልቶላቸው ኤጀንሲዎችም በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ነገር በቻሉት መጠን ለማድረግ እየጣሩ ነው፡፡ በዚያው መጠን ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ወደየአካባቢያቸው መመለስ ስለሚችሉበት ሁኔታ ውይይት ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡ እንደማስበው የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎችም ፍላጎት  ስደተኞቹን ወደየቤታቸው ለመመለስ ነው፡፡ ይህ በሒደት ያለ ነው፡፡ በተቻለ ፍጥነት ተፈናቃዮቹን ወደ መኖሪያቸው በመመለስና አስፈላጊውን በማሟላት ማገዝ ይገባል፡፡

ይህ ቅድመ ሁኔታ ሲሟላም የተመድ ሥርዓት በሚፈቅደው መሠረት ተመላሾቹን በተመድ የስደት ተመላሾች ኮሚሽንና በሌሎችም ተቋማት በኩል በሚደረግ ድጋፍ ማገዝ ይጀመራል፡፡ በሞያሌ ያለው ሁኔታ ውስብስብ የሚሆነው የድንበር አካባቢ በመሆኑ ነው፡፡ እንደ ልብ እነሱን ማግኘት መቻል አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኮማንድ ፖስት ባለፈው ሳምንት ከተመድ ኤጀንሲዎች ለተውጣጣው ልዑክ ድጋፍ በማድረግ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ እንዲመለከት በመፍቀዱ ተደስተናል፡፡ ለተፈጠረው ችግር የምናደርገው ድጋፍ ይኖር እንደሆነ ለማየት የተደረገ ጉብኝት ነበር፡፡ አሁን በተወሰነ ደረጃ የመግባትና የማየት ዕድል በማግኘታችን ደስተኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተመድ የሰብዓዊ ሥራዎችን ለማስፈጸም የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ገድቧል ማለት ነው? ከኮማንድ ፖስቱ ዕውቅና ውጪ በአገሪቱ የትኛውም ክፍል መንቀሳቀስ አልቻላችሁም?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥም ሆነን ሥራችንን መሥራት አለብን፡፡ እንደማስበው ባለሥልጣናቱ ይህንን በመገንዘብ መሄድ በምንፈልግባቸው አካባቢዎች ውስጥ እንድንንቀሳቀስ ፈቅደውልናል፡፡ ሕጉን እስከተከተልን ድረስና ለኮማንድ ፖስቱ ዓላማችንን እስካሳወቅን ድረስ ነገሮች ይመቻቹልናል፡፡ እርግጥ ነው ማንም ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መኖሩ አያስደስተውም፡፡ ሆኖም አዋጁ አለ፡፡ መሄድ ወደ ምንፈልግባቸው ቦታዎች መሄድ ሲያስፈልገን አሁንም ነገሮች እንደሚመቻቸሉን እናስባለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት በእንቅስቃሴያችሁ ወቅት የፀጥታ ጥበቃና ወታደራዊ አጀብ ያስፈልጋችሁ ነበር ማለት ነው?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- አዎን በትክክል፡፡ ነገር ግን በተቻለን መጠን በወታደራዊ አጀብ ላለመጓዝ እንሞክራለን፡፡ ይህ የሰብዓዊ ሥራዎችን ለማከናወን የመጀመርያው ተመራጭ ተግባር አይደለም፡፡ ለሰብዓዊ ሥራዎች የሚጓጓዙ ተሽከርካሪዎች ነፃ ኮሪደር ቢመቻችላቸውና ጥበቃ ማግኘታቸውን ማረጋገጡ ተገቢ ነው፡፡ እስካሁን መሄድ ያለብን ቦታ ከመሄድ ጋር በተያያዘ ያጋጠመን ችግር የለም፡፡ አዎን ሁኔታው ግን የሰብዓዊ ተግባራትን ለማከናወን የሚመረጥ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱን ለሰብዓዊ ቀውስ ከዳረጉ ችግሮች አንዱና ዋናው የውኃ እጥረት ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ የመስኖ እርሻ አይዘወተርም፡፡ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትም በቀላሉ አይገኝም፡፡ ይህ በተመድ በኩል እንዴት ይታያል? ባለሥልጣናቱ ለውኃ አቅርቦት የሚሰጡት ትኩረት ምን ይመስላል?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- ባለፉት ሦስት የድርቅ ዓመታት ከተማርናቸው ነገሮች አንዱ ዘላቂ የውኃ አቅርቦት ልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባን ነው፡፡ በቆላማ አካባቢዎች በተለይ በሌሎችም አካባቢዎች የሚታየውን ሰቆቃ ለመቀነስ ውኃ ዋናው መነሻ ነው፡፡ ይህንን መገንዘባችን ወደ ሌሎች በርካታ ጉዳዮች አድርሶናል፡፡ አንደኛው መንግሥት ራሱ ተነሳሽነቱን በመውሰድ የውኃ፣ የሳኒቴሽንና የኃይጂን (ዋሽ) ፕሮግራም ዘርግቷል፡፡ ስትራቴጂና ፕሮግራም አለ፡፡ አማራጭ መፍትሔዎች አሉ፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አለ፡፡ ከለጋሽ አካላት ጋር በመሆን ከአንድ ወር በፊት አፋር ክልል ውስጥ ወደሚገኘው አፍዴራ አካባቢ ሄጄ ነበር፡፡ አካባቢው ውኃ የሚገኝበት አይመስልም፡፡ ሳይንሳዊ መፍትሔዎች በመኖራቸው ግን እንደ ዩኒሴፍና የጀርመኑ ኬኤፍደብሊው የተሰኘው የልማት ፋይናንስ አቅራቢ ተቋምና ሌሎችም ሆነው፣ በዚያ አካባቢ ሳይንስን በመተግበር ውኃ የት ቦታ እንደሚገኝ ለመለየት ችለዋል፡፡ ከደጋማ አካባቢዎች የሚመጣው ውኃ የትኛው ቦታ ላይ ተከማችቶ እንደሚገኝ ለይተው ማወቅ ችለዋል፡፡ የውኃ ክምችቱ ለረዥም ጊዜ ጥቅም በመስጠት እንደሚቆይ ታውቋል፡፡ የውኃ ልማት ሥራው ከዚህ ቀደም ውኃ ለማግኘት ረዥም ርቀት ይጓዙ በነበሩ ማኅበረሰቦች ዘንድ ያመጣው ለውጥ ትልቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለአንድ ጄሪካን ውኃ እስከ 25 ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ወጪው በእጅጉ ቀንሶ በጄሪካን ሃምሳ ሳንቲም ብቻ ይከፍላሉ፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ቦታዎች በረሃማ ቢመስሉም፣ ብዙና ያልተነካ የከርሰ ምድር ውኃ አለ፡፡ ሳይንስ ውኃው የት እንደሚገኝ እየነገረን ነው፡፡ በፊት በነበረን ተሞክሮ የውኃ ጉድጓድ ለመቆፈር የምናደርገው እንቅስቃሴ ያስከትል የነበረው አሉታዊ ተፅዕኖ አሁን ተቀይሯል፡፡ ጉድጓድ እንዲሁ በጭፍን ቆፍረን ውኃ የምናጣበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አሁን ቴክኖሎጂው አለ፡፡ ዘጠና በመቶ ውኃ የሚገኝበትን ቦታ በትክክል የሚጠቁም ቴክኖሎጂ አለ፡፡ ችግሩ ግን የሚጠይቀው የመነሻ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ እኛ ለማሳመን የምንሞክረው ይህንኑ ኢንቨስትመንት ማካሄድ ወደፊት ሊኖር የሚችለውን ወጪ በእጅጉ ይቀንሰዋል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጄኔቭ ከለጋሾች ጋር በተደረገ ውይይት ምን ያህል ውጤታማ ነበራችሁ? ቃል የተገባ ገንዘብ አለ?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- ስብሰባው የገቢ ማሰባሰቢያ ኮንፈረንስ ሳይሆን፣ ከለጋሾች ጋር የተደረገ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ነው፡፡ በዚህ ዓመት ስለሚያስፈልገው ድጋፍ ግንዛቤ እንዲያገኙ የተደረገበት ስብሰባ ነበር፡፡ የዕርዳታ ድጋፍ የሚደረግበት መግለጫ ይወጣል ብለንም አልጠበቅንም፡፡ ሆኖም ካደረግንላቸው ገለጻ በኋላ ግን ኢትዮጵያ በለጋሾች ዘንድ አሁንም የዕርዳታ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችላት ተቀባይነት እንዳላት ግልጽ ነበር፡፡ አንደኛው ምክንያት አንዳንዶቹ ለጋሾች በልማት ሥራዎች ላይ በአገሪቱ ኢንቨስት ሲያደርጉ የቆዩ በመሆናቸው፣ ሰብዓዊ ችግሩ ካልተፈታ በልማት መስክ የተገኘውን ውጤት ሊቀለብሰው እንደሚችል ይገነዘባሉ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ መንግሥት ኃላፊነቱን ለመወጣት ብሎም ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ብሔራዊ ሥርዓት በመዘርጋት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለዕርዳታ የሚሰጠው ነገር ሁሉ እንደማይባክን በመረዳታቸውም ጭምር አገሪቱ ተቀባይነት አግኝታለች፡፡ እነዚህ ጠንካራ ጎኖች ኢትዮጵያ ጥሩ ምላሽ የምታገኝበትን ዕድል እንደሚፈጥሩ ተስፋ አለን፡፡ የሚፈለገው ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ነው፡፡ እስካሁን የ600 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አስመዝግበናል፡፡ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ይቀረናል፡፡ ከዚህ ውስጥ ካለፈው ዓመትም የተንከባለለ ገንዘብ አለበት፡፡ ይሁንና ለዚህ ዓመት ቀውስ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ቢያንስ ግማሹ እንኳ ሊገኝ ይችላል ብለው ይጠብቃሉ?

ሚስ ኤዚያኮንዋ-ኦኖቼ፡- በሚገባ፡፡ ይህ እንደሚሳካ አምናለሁ፡፡

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....