Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዘርፍ ምክር ቤት አገር አቀፍ ኤሌክትሮኒክ ማውጫ ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት አገር አቀፍ ኤሌክትሮኒክስ የኢንዱስትሪ ስልክ ማውጫ  (ዳይሬክቴሪ) በማዘጋጀት ጥቅም ላይ አውሏል፡፡

እስካሁን ከተለመዱትና በወረቀት ኅትመት ውጤቶች አማካይት ከሚዘጋጁት የቢዝነስ አድርሻ ማውጫዎች ለየት ተደርጎ የተዘጋጀው የኤሌክትሮኒክስ የኢንዱስትሪ ማውጫ፣ በሞባይል ስልኮችም መተግበሪያው ተጭኖ አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ ሐሙስ፣ መጋቢት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሔደው ሥነ ሥርዓት  ወቅት አገልግሎቱን ይፋ አድርጓል፡፡

አገር አቀፍ የኤሌክትሮኒክ የኢንዱስትሪ አድራሻዎች ማውጫው እስካሁን አገልግሎት ከሚሰጡት የሚለየው፣ ማንኛውም ተጠቃሚ በፈለገው ጊዜና ቦታ በተንቀሳቃሽ ስልኩና በኢንተርኔት አማካይነት ሊጭነውና ሊጠቀምበት መቻሉ እንደሆነ የምክር ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ጉርሙ ገልጸዋል፡፡

የአድራሻ ማውጫው በዚህ መንገድ መዘጋጀቱ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ የንግድና የኢንቨስትመንት ኩባንያዎችም ቢሆኑ በኢትዮጵያ ካሉ አምራቾች ጋር ያለ ሦስተኛ ወገን እገዛ በቀጥታ ሊነጋገሩና የንግድ ሽርክና መጀመር እንዲችሉ መንገዱን የሚያመቻች ዘመናዊ ማውጫ እንደሆነም አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡ ተደራሽነቱም መጠነ ሰፊና አገራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆሙት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ይኼንን አገልግሎት የሚሰጠውን መተግበሪያ በሞባይል ስልኮች ላይ በመጫን በቀላሉ መገልገል ይቻላል ብለዋል፡፡

ለአምራች ዘርፉ በአጠቃላይ ለንግዱ ማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል የመረጃ ማዕከል ማቋቋምና ማደራጀት አንዱ ዓላማው በማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የሚያመላክተው የምክር ቤቱ መረጃ፣ በዚህ የመረጃ ማዕከል ከሚደራጁ መረጃዎች ውስጥ የአምራች ዘርፉ መሠረታዊ መረጃዎችን የሚይዘው የኢንዱስትሪ ማውጫ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ አምራቾችን መረጃ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች በስፋትና በፈለጉት ጊዜና ቦታ ማቅረብ መቻሉ የውጭ ኩባንያዎች የአገር ውስጥ አምራቾችን በቀላሉ እንዲያገኙ ማስቻሉ አንዱ ጠቀሜታ ነው ተብሏል፡፡ የትኛውም የኅበረተሰብ ክፍል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን መረጃ ለማግኘት የእርስ በርስ ግንኙነት በመፍጠር ረገድም እንዲህ ያሉ ዘመናዊ የመረጃ መለዋወጫ ሥልቶች አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆኑ ከተሰጠው ማብራርያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

አሁን ባለው ደረጃ ይኼ ዳይሬክተሪ ከ12 ሺሕ በላይ በሆኑ ማኅበራትንና   ኩባንያዎችን መረጃና አድራሻዎቻቸውን አካትቶ የያዘ ሲሆን፣ በቀጥታ ከማውጫው ላይ ወደ የኩባንያዎች ስልክ መደወል የሚያስችል ፕሮግራም ያለው ነው፡፡ ይኼ የኤሌክትሮኒክስ ማውጫ በየጊዜው እየታደሰና ተጨማሪ ኩባንያዎችን እንዲያካትት ተደርጎ እንደሚቀጥል ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

 በቀጣዩ ምክር ቤቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው መስፋፋት አጋዥ የሚሆኑ መረጃዎችን በማቋቋም ላይ የሚገኘው የመረጃ ማዕከሉ፣ በጥራዝና በኢንተርኔት ተደራሽ በሚሆን መልኩ ለአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ለማሰራጨት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም የቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ ያስረዳል፡፡

ይኼንን ኤሌክትሮኒክስ ማውጫ ያዘጋጀው ካቫሊንክ ኢቨንትና መልቲ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ኃይሌ እንደገለጹት፣ እስካሁን በመጽሐፍ መልክ ይቀርብ የነበረው ማውጫ ወደ ሞባይል አፕሊኬሽን ተቀይሮ ቢሠራበት ውጤታማ ይሆናል ተብሎ የተተገበረ ሥራ ነው፡፡

የቢዝነስ ማውጫዎች ከመጽሐፍ ይልቅ በሞባይል መጠቀሙ የበለጠ ተደራሽ በመሆን የሚፈለገውን ዓላማ መምታት ይቻላል፡፡ እነዚህ መረጃዎች ከየትኛውም በተለይ በመጽሐፍ መልክ ከሚዘጋጁት ቢዝነስ ማውጫዎች በተሻለ ጠቀሜታ ይሰጣሉ፡፡ ተጨማሪ መረጃዎችንም ለማስተላለፍ ተመራጭ ናቸው ይላሉ፡፡

የግል ባለሀብቱ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዋነኛ ሞተር መሆኑን የገለጹት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሴክቶሪያል ግንኙነትና ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገለልቻ በኩላቸው፣ የዘርፉ ምክር ቤቶች ከዓላማዎቹ መካከል የምርት መረጃዎችን ማጠናከርና ለአባሎቻቸው ማሰራጨት፣ ቴክኖሎጂና የገበያ መረጃዎችን ጠቁመዋል፡፡ ይኼ ማውጫም ምክር ቤቱ የተቀመጠለትን ዓላማ እየተወጣ መሆኑን ማሳያ ነው በማለት እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም መሸጋገሪያ መንገድ ስለሆነ ለዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 341/1995 የተቋቋመና በአሁኑ ወቅት ከ27 በላይ የተደራጁ የዘርፍ ማኅበራትና 11 የክልል ዘርፍ ምክር ቤቶችን ያቀፈ አገራዊ የንግድ ተቋም ነው፡፡ ምክር ቤቱ በአባላት አቅም ብዛት፣ በአድቮኬሲና ኢንቨስትመንት በማስፋፋት ረገድ በርካታ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በአገር ውስጥና በውጪ በሚዘጋጁ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ትርዒቶችና ዝግጅቶች ላይም አምራቾችን በመወከል በስፋት በመንቀሳቅ ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች