Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጃፓን ለዓመታት የዘገየውን የካይዘን የሥልጠና ማዕከል ለመገንባት 750 ሚሊዮን ብር ለገሰች

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባለአራት ፎቅ ሕንፃው በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚገነባ ይጠበቃል

ተገንብቶ በመጠናቀቂያውና ሠልጣኞችን በመቀበያው ወቅት እንደ አዲስ በተደረገ ስምምነት፣ የጃፓን መንግሥት ከኢትዮጵያም ባሻገር ለአፍሪካ አገሮች የካይዘን ሥልጠና የሚሰጥበትን ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል የ27.5 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ750 ሚሊዮን ብር ለግሳለች፡፡

ዓርብ፣ መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በተከናወነ ሥነ ሥርዓት የጃፓን መንግሥትን በመወከል፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ሚስተር አኪራ ዩቺዳ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ጋር የገንዘብ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

የስምምነቱ ዋና ዓላማም የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ሥር ለሚመራው የኢትዮጵያ ካይዘን የሥልጠና ዘርፍ አጋዥ ይሆን ዘንድ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ እንደሚገነባበት ጉዳይ ፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡

የሥልጠና ማዕከል የሚሆነው ሕንፃ ልደታ ክፍለ ከተማ ውስጥ ከብሔራዊ ትንባሆ ድርጅት ጀርባ በሚገኝ አካባቢ እንደሚገባና የግንባታ ሥራውም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የካይዘን ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነትና የኢንፎርሜሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሙሉቀን ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት ስምምነት የተደረገበት የካይዘን የሥልጠና ማዕከል እስካሁን ስለዘገየበት ምክንያት ሲያብራሩም፣ ለማዕከሉ ግንባታ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ እንዲለቀቅ ያጸደቀው በቅርቡ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ሕንፃው የሚገነባበትን ቦታ የማቅረብ ችግሮች ለመጓተቱ ሰበብ ሆነዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሕንፃው የሚውሉ ቁሳቁሶችን ከውጭ በማስመጣት ወቅት መከፈል ያለበትን የጉምሩክ ቀረጥ ከሁለቱ መንግሥታት ማናቸው ይክፈሉ የሚለውም ሌላው ምክንያት ተደርጓል፡፡

ይሁንና እ.ኤ.አ. በ2020 ግንባታው እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ይህ የካይዘን ማዕከል፣ 60 መኝታ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ 80 ሠልጣኞችን የሚያስተናግድ ካፊቴሪያ፣ 120 ሰዎችን የሚይዝና ፈርጀ ብዙ አገልግሎቶች የሚስተናገዱበት አዳራሽ፣ አንድ 60 ሠልጣኞችን የሚያስተናግድ ክፍል፣ እያንዳንዳቸው 20 ሠልጣኞችን መያዝ የሚችሉ ስምንት ክፍሎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራት የሚናከናወኑባቸው የሕንፃው ክፍሎች በካይዘን የአሠልጣኝነት ሥልጠና ለሚሳተፉ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ እግረ መንገዱንም ለካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ በመሆን ያገለግላል ተብሏል፡፡ አቶ ሙሉቀን እንደሚሉት፣ ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት ተከራይቶ በሚገለገልበት አነስተኛ ሕንፃ ውስጥ 24 ዳይሬክቶሬቶችን ጨምሮ በርካታ የሥራ ዘርፎችን የሚመሩ ባለሙያዎችና ሠራተኞች በተጣበበ አኳኋን የዕለት ተዕለት ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ጃፓን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅ የምትፈልገውን የማኔጅመንት ፍልስፍና ካይዘን በማለት የሰየሙት ከቻይና በተዋሷቸው ‹‹ካይ›› እና ‹‹ዜን›› በተሰኙ ሁለት ቃላት ሲሆን፣ የማያቋርጥ ለውጥ፣ ለጥራት የሚል አቅራብ ትርጉም የሚሰጡ ቃላት ናቸው፡፡

በ2004 ዓ.ም. በተወጣው የሚኒስትሮች ደንብ መሠረት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት፣ በአገሪቱ ሁሉም መስክ ካይዘን እንዲተገበር እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ በአዲሱ ስምምነት መሠረት የካይዘን ሥልጠና ማዕከል ‹‹የቶኪዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ) የሰው ሀብት ልማት ማዕከል›› በሚል መጠሪያ ስምምነት ተፈርሞበታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች