‹‹በቂም በቀል እየታሰርን ነው›› የሚል አቤቱታ ቀርቧል
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ በአዋጁ መሠረት በአገር አቀፍ ደረጃ በኮማንድ ፖስቱ የታሰሩት 1,108 ሰዎች መሆናቸውን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አስታወቀ፡፡ ከታሳሪዎቹ ውስጥ 20 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡
መርማሪ ቦርዱ ቅዳሜ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ኮማንድ ፖስቱ በአዋጁ መሠረት ያሰራቸው አጠቃላይ ታሳሪዎች 1,108 ናቸው፡፡ ማንነታቸውንና የታሰሩበትን ቦታ የሚገልጽ ዝርዝር ለሁሉም ክልሎች ከሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚልክና ክልሎችም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ ቦርዱ አስታውቋል፡፡
በኮማንድ ፖስቱ ታስሮ ነገር ግን ይፋ በሚደረገው ዝርዝር ውስጥ ያልተገኘ ሰው ካጋጠመ፣ ለቦርዱ በአድራሻው ጥቆማ ማቅረብ እንደሚቻል የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ተናግረዋል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ ለፀጥታ ማስከበር ይመቸው ዘንድ አገሪቱን በስድስት የፀጥታ ቀጣናዎች በመክፈል ዕዞችን ያቋቋመ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ አዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳዎች በኮማንድ ፖስቱ ቀጣና አንድ ዕዝ ሥር ይገኛሉ፡፡ በዚህ ቀጣና 450 ሰዎች ሲታሰሩ፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ 137 ሰዎች መታሰራቸው ተገልጿል፡፡ ይህም በዚህ ቀጣና ከታሰሩት ትልቁ ቁጥር መሆኑን የቦርዱ መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህ ቀጣና ውስጥ ከታሰሩት 450 ሰዎች መካከል ስምንቱ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የቀጣና ሁለት ዕዝ መቀመጫ ሐዋሳ ሲሆን ሮቤ ከተማ፣ ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ አዳማ ከተማ፣ ምሥራቅና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ይካተታሉ፡፡ በዚህ ቀጣና በድምሩ 39 ሰዎች ታስረዋል ተብሏል፡፡
በቀጣና ሦስት ሐረርና ድሬዳዋ የተካተቱ ሲሆን፣ በድምሩ 178 ሰዎች መታሰራቸውን ይፋ የተደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡ በቀጣና አራት የተካተቱት ደግሞ ጅማና ነቀምት ሲሆኑ፣ በድምሩ 388 ሰዎች መታሰራቸውን የኮማንድ ፖስቱ መርማሪ ቦርድ መግለጫ ያሳያል፡፡
በቀጣና አምስት ማለትም በባህር ዳር 43 ሰዎች ሲታሰሩ፣ በቀጣና ስድስት አፋር ክልል ሰመራ ደግሞ ዘጠኝ ሰዎች ታስረዋል፡፡ በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የግድያ ወንጀል ፈጽመዋል፣ ቤትና ንብረት አውድመዋል፣ መንገድ ዘግተዋል፣ የመማር ማስተማር ሒደትን አደናቅፈዋል፣ የንግድ እንቅስቃሴ ዘግተዋል፣ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋውረዋል፣ ብሔርን ከብሔር አጋጭተዋል በሚሉ ወንጀሎች በመጠርጠር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሞያሌ የተከሰተውን ግድያ በቀጣይ ወደ ሥፍራው በመጓዝ አጣርቶ፣ በተጠያቂዎች ላይ የተወሰደውን ዕርምጃ ጭምር ቦርዱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ የተለያዩ ጥቆማዎችን ለቦርዱ እያቀረበ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢው አቶ ታደሰ፣ አመዛኙ ጥቆማና አቤቱታ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገላችን በቂም በቀል እየታሰርን ነው›› የሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከታሰሩት መካከል የወረዳና የዞን አመራሮች እንደሚገኙበት መረጃ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የተገለጸው መረጃ ኮማንድ ፖስቱ አጠናቅሮ የላከው እንጂ ቦርዱ በምርመራ ያረጋገጠው አለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡