Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ላይ ግብፅ ያቀረበችውን ጥያቄ አልቀበልም አለች

  ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ላይ ግብፅ ያቀረበችውን ጥያቄ አልቀበልም አለች

  ቀን:

  የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ እንዲሻሻል ግብፅ ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵያ እንደማትቀበል የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

  የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ግብፅ ወደ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ (NBI) ለመመለስ ዕድል እንዲሰጣት ሐሳብ ያቀረቡ በመሆኑ፣ ስብሰባውም በተፋሰሱ አገሮች መሪዎች ደረጃ እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

  ይህ ቀጠሮ ለዚህ ሳምንት ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ጠያቂነት ለሚቀጥለው ወር መተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ግብፅ ወደ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የመመለስ ፍላጎት ቢኖራትም ለመመለስ የሚያበቃትን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጣለች፡፡ የሪፖርተር ምንጮች ግብፅ በቅድመ ሁኔታነት ያቀረበችው ቀደም ብሎ ክርክር ሲደረግበት የነበረ ሐሳብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  ይህ ያነሳችው ቅድመ ሁኔታ የውኃ ደኅንነት ጉዳይ (ማለትም የውኃ ድርሻዋ) እንዲከበር የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተፋሰሱ አገሮች ተከራክረው፣ የተፋሰሱ አገሮች በሌላ ተጋሪ አገር ላይ ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ የውኃ ሀብቱን መጠቀም እንደሚችሉ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ለግብፅ መንግሥት ዕድል ለመስጠት ይህንን ስምምነታቸውን በሰነዱ ላይ እንዳላካተቱት ይታወቃል፡፡

  በሁለተኛ ቅድመ ሁኔታነት የቀረበው የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች የሚያጋጥማቸውን አለመስማማት መፍታት ያለባቸው በስምምነት ነው የሚል ሲሆን፣ ይህ በትክክል ማዕቀፉ ላይ በድምፅ ብልጫ እንዲሆን ተደርጎ እየተሠራበት ይገኛል፡፡

  የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በዓባይ ውኃና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከተፋሰሱ አገሮች በተለይም ከግብፅ ጋር የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ድርድሮች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተጠይቀው ነበር፡፡

  ለጉዳዩ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ ግብፅ ወደ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ተመልሳ ለመግባት ከፈለገች ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ የለባትም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት አገሮች የናይል ትብብር ማዕቀፉን በፓርላማዎቻቸው አፅድቀው እያለ፣ እንዲሻሻል ግብፆች ቅድመ ሁኔታ ማቅረባቸው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ማዕቀፍ እንዲሻሻል የትኛውም አገር ፍላጎት እንደሌለውም አክለዋል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ1929 እና በ1959 የተፈረሙት ስምምነቶች ከዓባይ ውኃ የመጠቀም መብትን ለግብፅና ለሱዳን በመስጠት ሌሎቹን አገሮች አግልለዋል፡፡ በኢትዮጵያ አነሳሽነት ሌሎች አገሮች ይህን ፍትሐዊ ያልሆነ ስምምነት ለመቀየር ባደረጉት ጥረት፣ የዓባይ የትብብር ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡

  በፍትሐዊና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተው ማዕቀፍ በስድስት አገሮች ተፈርሞ በሦስት አገሮች ፀድቋል፡፡ ስምምነቱ በስድስት አገሮች ከፀደቀ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ እስካሁን ያፀደቁት ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 የተረቀቀው ስምምነት እንዲዘጋጅ እ.ኤ.አ. በ1999 የተቋቋመው ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ትልቅ ሚና መጫወቱ አይዘነጋም ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...