Wednesday, February 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር መውደድ ማለት ምንድነው ትርጉሙ?

የአገር ፍቅር ጉዳይ ሲነሳ በጥልቀት ትርጉሙን መረዳት ካልተቻለ፣ አሁን በደምሳሳው እየተስተዋለ እንዳለው መቀጠል አይቻልም፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት በሙዚቃ፣ በፉከራ፣ በሽለላ፣ በተውኔትና በመሳሰሉት ሲገለጽ የብዙዎቹን ልብ ያማልላል፡፡ ነገር ግን ይህ ፍቅር ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ መለካት ካልተቻለና ሳይረፍድ ማስተካከያ ካልተደረገለት ለችግር ያጋልጣል፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ትውልድ የአገር ፍቅር ስሜት እንዴት ነው እየተገለጸ ያለው? ብሎ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ የድል በዓላት ሲከበሩ ከሚሰማው ዲስኩር በላይ ትውልዱ ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል? ያለፉት ትውልዶች አገራቸውን ከወራሪዎች ለመመከት ካደረጉት ተጋድሎ አንፃር አሁን ያለው ስሜት እንዴት ይገለጻል? ለአገራችን በተለያዩ የሙያ መስኮች አኩሪ ተግባር ለፈጸሙ ቀደምቶች የምንሰጠው ክብርስ ምን ያህል ነው? አገርን ከወራሪዎች ከመመከት በተጨማሪ በሌሎች ተግባራት መወደስ ያለባቸው አኩሪ ዜጎች የሉንም ወይ? በዓለም ዙሪያ የአገር ፍቅር ስሜት እንዴት ነው የሚታየው በማለት ለማማተር እንሞክራለን ወይ? ስንል ብዙ ሐሳቦችን መምዘዝ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ዘመን አይሽሬ የሆኑ አርዓያነትን ጥለውልን ያለፉ የበርካታ ዜጎች አገር ናት፡፡ ከጦር ሜዳ ውሎች በተጨማሪ በሥነ ጽሑፍ፣ በዕደ ጥበብ፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በንግድ፣ በእርሻ፣ ወዘተ ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ አርዓያ የሚሆኑ አኩሪ ዜጎች ተፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በዘመናቸው ለአገር የሚበጁ በርካታ ተግባራትን አከናውነው አልፈዋል፡፡ ጨቋኞችና አምባገነኖች የሚፈነጩባቸው ሥርዓቶች ተወግደው ሕዝብን የሚያገለግል ሥርዓት እንዲመጣ መስዋዕት የሆኑ እጅግ በጣም ብዙ ወጣቶች ተሰውተዋል፡፡ እነዚያ የአምባገነኖች ሰለባ የሆኑ ወጣቶች መስዋዕትነት የከፈሉት ለአገራቸው በነበራቸው የጋለ ፍቅር ነው፡፡ ከእነሱ ያልተናነሱም በየእስር ቤቱ መከራቸውን አይተዋል፡፡ ይህ ለአገር ፍቅር የተከፈለ ዋጋ ነው፡፡ ወገኖቻቸውን ከመኃይምነት ለማላቀቅ በእግርና በከብት ጀርባ እየተጓዙ የታሪክ አደራቸውን የተወጡ መምህራን መቼም አይዘነጉም፡፡ ምንም ዓይነት መሠረተ ልማቶች ባልነበሩባቸው ሥፍራዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሕክምና አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ወገኖችም እንዲሁ፡፡ በተለያዩ መስኮችም በርካቶች በመሳተፍ የሚያኮራ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለእናት አገር ፍቅር ሲሉ፡፡

ዛሬስ? የእናት አገር ፍቅር ስሜትን ከሙዚቃና ከአጉል ዲስኩር በላይ የማይመለከቱ ሞልተዋል፡፡ የገዛ ወገኑን እንደ ወንድሙና እንደ እህቱ በተቆርቋሪነት መንፈስ የሚመለከት ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ አገርን መውደድ ግን ወገንን እንደ ራስ መውደድ ማለት ነው፡፡ መንገድ ላይ ፀጥታ ለማስከበር የተሰማራ ሰው የገዛ ወገኑን እየገላመጠ ወይም እያንገላታ፣ ለባዕድ ግን ጉዝጓዝ ላንጥፍ ሲል ይስተዋላል፡፡ የገዛ ወገኑን በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ማገልገል የሚገባው የመንግሥት ሠራተኛ፣ ጉቦ ወይም መማለጃ ካልተቀበለ ማስተናገድ እርሙ ነው፡፡ በዓላት በመጡ ቁጥር ስለባህል፣ ወግና ልማዶች እየጠረቀ ‹አገሬ ኢትዮጵያ› እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው በአዘቦቱ ግን ጥላቻ ውስጥ ሆኖ አገሩንና ወገኑን ይረግማል፡፡ የተሰጠውን ኃላፊነት ላልተገባ ዓላማ የሚያውል የመንግሥት ሹመኛ ነጠላ ዜማው ‹አገሬ› ነው፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት በእንዲህ ዓይነት ግራ የሚያጋባ አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ ትርጉሙ እየጠፋ ነው፡፡ አገር መውደድ ማለት ጥልቅ ትርጉም ያለው ጽንሰ ሐሳብ መሆኑ ግንዛቤ እየጠፋ የአጭበርጫሪዎች ማላገጫ እየሆነም ነው፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ያለፉት ትውልዶች በንፁኅ ህሊና በአገር ፍቅር ስሜት ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ዕድሜያቸውን በሙሉ አገራቸውን በታማኝነት አገልግለዋል፡፡ አሁን ግን በአቋራጭ መክበር የሚባል አጉል ድርጊት ውስጥ እየተገባ አገርን መዝረፍና ማዘረፍ ተለምዷል፡፡ ወጣቶች ከትምህርት ተቋማት ተመርቀው ሲወጡ በሚሰማሩበት የሙያ መስክ ሥነ ምግባራቸውን ጠበቀው ማገልገል ሲገባቸው፣ በብዙ ሥፍራዎች እንደሚስተዋለው በአቋራጭ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ይሯሯጣሉ፡፡ ማንም ዜጋ እሴት እየጨመረ በድካሙ መጠን መበልፀጉ የሚደገፍ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ አሁን ግን መጪውን ትውልድ ሳይቀር የሚመርዝ እላፊ ፍለጋ መሯሯጥ ፋሽን ሆኗል፡፡ ይህ እላፊ የሚገኘው ግን አገር ለልማቷ ከሚያስፈልጋት በስንት መከራ ከሚገኝ በጀት ላይ ነው፡፡ ግዥ ላይ፣ ጨረታ ላይ፣ ግንባታና በመሳሰሉት ለዝርፊያ ያሰፈሰፈው ያስደነግጣል፡፡ አገሩን እየዘረፈ ‹አገሬ. . . አገሬ. . .› እያለ የሚያላዝን በዝቷል፡፡ አገሩን በቅንነት ለማገልገል የሚታትር ዜጋ እየተኮረኮመ አፈ ጮማው በአቋራጭ ወደ ሀብት ማማ ይተኮሳል፡፡ የዘፈኑና የግርግሩ ጊዜ ደግሞ መድረኩን ይቆጣጠረዋል፡፡ የአገር ፍቅር ንፁህ ስሜትን ይበክለዋል፡፡

ስደትን ስናስተውል አስተዛዛቢ ጉዳዮች ይገጥሙናል፡፡ በአገራቸው ሁሉም ነገር ጨለማ የሆነባቸው ዜጎች የግንዛቤ ችግሩም ተጨምሮበት እግራቸው በመራቸው በረሃ አቆራርጠው ይሰደዳሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚደርስባቸው ሰቆቃና እንግልት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ እነዚህን ወገኖች ለመታደግ ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦች ሲቀርቡ ይታያል? በፍፁም፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጀምሮ እስከ የሚመለከታቸው አካላት ድረስ ሁሉም በሩን ዘግቶ ቁጭ ብሏል፡፡ እነዚህን ወገኖች መታደግ የአገር ፍቅር ስሜት አንዱ መገለጫ መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ያሳዝናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በጋብቻ ብዙ ሺሕ ዶላሮችን እየከፈሉ ከሚኮበልሉት ጀምሮ፣ በተለያዩ ምክንያቶች አውሮፓና አሜሪካ የሚገቡ ወገኖች ጉዳይ እዚህ ላይ መነሳት አለበት፡፡ አገር መውደድ ሌላ፣ ሥርዓት መጥላት ሌላ መሆኑ የማይገባቸው ወይም የማይፈልጉ አንዳንድ ወገኖች የጥገኝነት ወረቀት ለማግኘት ሲሉ ብቻ በሚያወሩት ውሸት አገሪቱን ገሀነም ያደርጓታል፡፡ የሚሸሹትን መንግሥት ማብጠልጠል መብታቸው ቢሆንም አገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈጸም ግን፣ ክርስቶንስ በ30 ዲናር ከሸጠው ይሁዳ ጋር የሚወዳደር ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ያለምንም ኃፍረት የሸሿትንና ያዋረዱዋትን አገር ለማንቆለጳጰስ ማንም አይቀድማቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ወገኖቻቸው ተርበው የዕርዳታ ያለህ ሲሉ ለማስከልከል ሲራወጡም ይታወቃሉ፡፡ እነሱ በርቀት ሆነው አገራቸው እንደ ጧፍ ስትነድ ለማየት ሲጓጉም እንዲሁ፡፡ ይኼንን ለመታዘብ ማኅበራዊ ሚዲያውን መጎብኘት በቂ ነው፡፡ ያውም ለማይረባ የፖለቲካ አጀንዳ፡፡ አገር መውደድ ማለት እንዲህ ሲሆን ያበሳጫል፡፡

ይህ ትውልድ የታሪክ ተጠያቂነት እንዳይኖርበት መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡ ለመጪው ትውልድ ስለአገር ፍቅርና አርበኝነት በጥልቀት ማስተማር ካቃተው አገር ትጠፋለች፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚኮተኩቱበትን መንገድ ደግመው ደጋግመው ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ማኅበረሰቡ ለመጪው ትውልድ መጨነቅና መጠበብ፣ እንዲሁም ለመፍትሔው ጥረት ማድረግ አለበት፡፡ የትምህርት ተቋማት በጥናት ላይ የተመሠረተ የመፍትሔ ሐሳብ ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎችና በተለያዩ ዘርፎች የተደራጁ ወገኖች በያገባኛል መንፈስ ሊነሱ ይገባል፡፡ መንግሥት ደግሞ በፖሊሲ ደረጃ በማሰብ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡  አገር ህልውናዋ አስተማማኝ ሆኖ መቀጠል የሚችለው በእውነተኛ ስሜት ለአገር የሚጠቅም ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ የአገር ፍቅር በመዋደድ፣ በመከባበር፣ በመረዳዳትና ለጋራ ዓላማ በአንድነት በመቆም የሚገለጽ ጥልቅ ስሜት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ መጪው ትውልድ የሚቀረፀው በጭፍን ጥላቻ፣ በቂመኝነት፣ በክፋት፣ በሌብነት፣ በኢሞራላዊ ዝቅጠቶችና በመሳሰሉት አይደለም፡፡ ይልቁንም በከፍተኛ ሥነ ምግባርና ጨዋነት በታጀበና በዕውቀት ላይ በተመሠረተ አርዓያነት ነው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኖ ማሰብ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ከገዛ ልጁ ጀምሮ ወገኖቹን በዚህ መንገድ መቅረፅ አለበት፡፡ የአገር ፍቅር ስሜት በደም ሥር ውስጥ መሠራጨት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ማሟላት ሲቻል ነው አገር መውደድ ማለት ምንድነው ትርጉሙ? ለሚለው ጥያቄ በብቃት ምላሽ መስጠት የሚቻለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...