Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነገ ከዛሬ ካልበለጠ ምኑን ተኖረ?

ሰላም! ሰላም! “እስኪ ልነሳና ልያዘው መንገዴን…” ብዬ ብነሳ የምይዘው መንገድ አጣሁ። ማንጠግቦሽ፣ “መንገዱ ሁሉ ፈርሶ እየተገነባ ምን የሚያዝ መንገድ አለና?” ስትለኝ ነበር። መቼም እናንተ ናችሁ ብዬ ነው የማወራችሁ። ለሌላማ ለማን አወራዋለሁ? መንገድ ሊመራ ሲገባው መንገደኛን አቅጣጫ እያሳተ እንጀራውን የሚጋግረውን ዘንድሮ አልቻልነውም። ለነገሩ እንኳን የሰማነውንና የምናየውን ለመረዳት ለመኖር አቅም የሚያሳጣ ጊዜ ላይ ነን። ዘመኑ የፉክክር ነው ሲባል፣ ፉክክሩ ጤናማ አልሆን እያለ ወገን በወገኑ ጀርባ ላይ ይጋልባል፡፡ አንዱ ሌላውን ዘርጥጦ ካልጣለ ዕድገት አይታሰበውም፡፡ አቋራጭ ፍለጋ ሲባል የሚፈጸመው ኃጢያት ሰው መሆንን ያስጠላል፡፡ አመረርኩ እንዴ? ምን ይደረግ ታዲያ? ዘመኑ እኮ አስፈሪ ሆነ፡፡

ትንሽ ትልቁን ሐሳብ እያነሳን እንደ ፈላስፋ ለመነጋገር ከሞከርን ምን ቀረን? እውነቴን እኮ ነው። እናማ ማንጠግቦሽ እንዳለችው መንገዴን ልያዝ ብዬ የሚያዝ ጎዳና ያጣሁት ቁፋሮ ስለበዛ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ተቆፍሮ የተደመደመው ለቀቅና ቦርቀቅ ተደርጎ ያለቀውን መንገድ እንቁጠረው ብንል ‘ልወደድ ባይነት’ ይመስልብናል (ግን ቢመስልብንስ ምንድነው ነውሩ? የሰው አገር መንገድ እናደንቅ የለም እንዴ?) እንጂ ብዙ ነው። ቁም ነገሩ ማለቅ አለማለቁ አይደለም። ማሳለጫ፣ ባለቀለበት መሆን አለመሆኑም አይደለም። አልጨበጥ ያለኝ መንገዱ ላይ ሰው ስላለ ነው፡፡ አያችሁ? እናንተና እኔ ስላለን። “እና ምን ይጠበስ?›› ይል ነበር አሉ የአዲስ አበባ ሰው ድሮ፡፡ ፓስቲም በአቅሟ በአሥር ዓመት ውስጥ ከሃምሳ ሳንቲም አምስት ብር ሳትገባ በፊት። ዕድገት ስላለ ነው ትሉ ይሆናል እኮ ስኳርና ዘይት እየተቸገራችሁ። እንዲያው እኮ! ብቻ እንደ ዛሬው ለእራቱ የሚጠበስ በቅሎ ፍለጋ ወጥቶ ራሱ በፀሐይ ተጠብሶ በየሳምንቱ ጉንፋንና ራስ ምታት ሳይጫወትበት በፊት፣ አዲስ አበቤው ‘ተጠብሶ መጥበስን’ ይሳለቅበት ነበር። አወይ መንገድና ሰው ብዬ ልለፈውማ። አንዴ እባካችሁ አሳልፉኝ? ምነው ስንት የማይታለፍ ነገር አልፈን አላሳለፍንም እንዴ? አይ ሰውና ሰው!

ትዝ ይለኛል ማንጠግቦሽን የግሌ ለማድረግ የማይረገጥ ስረግጥ፣ አይገቡ ስገባ “ልብህን ጠብቅ” ባይ መካሪ ብዙ ነበር። እስኪ አሁን ልብን ያህል ነገር የሰው ልጅ ጠብቆ ማዳን ቢችል ሕይወት ምን ትርጉም ይኖራት ነበር? ያደለው በምርጫ ያልታደለው በጠመንጃና በመፈንቅለ ሥልጣን መንግሥት ሲቀያይር ይኖር ነበር? የምር! እንጃ ምን ያህል እንገደባንና እንደገባቸው እንጂ ጨዋታው እኮ ልብ ለልብ ነበር። አሁንም ነው ለነገሩ። ነገር አላንዛዛ ብዬ እንጂ የማይጠገኑ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሕይወት ኪሳራዎች በጠቅላላ በልብ ዙሪያ ያጠነጠኑ ቁማሮች ናቸው። እንግዲህ እኔም እንደ አያቴ የሚመራኝ ሳይኖር ነገሮች ስለማይገለጡልኝ የባሻዬን ልጅ፣ “ልብ ብለህ ልባችንን ሰጥተን ስለተገኘንባቸው ጉዳዮች አጫውተኝማ?” አልኩት። አካሄድ!  .  . .  አያቴ ያልኩት የህንደኬ ገንዘብ ሚኒስቴር የነበረውን ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው። እንግዲህ ዘመኑ የግል እምነትና ሐሳብ የሚከበርበት ከሆነ ያን የእምነት አርበኛ ማጠጋጋት መብቴ ነው። ፑሽኪን በአያቱ ተዛመደን ብለን እሪ የማለት መብት እንዳለን ሁሉ ማለት ነው። እንተዛዘብ ስንል ታዲያ እዚህ ጋ ‘ማን እንደ እኛ ያለ ሃይማኖተኛ?’ ባልንበት አፋችን የፑሽኪንን ያህል ጃንደረባውን ስናስታውሰው አንሰማም። ምናልባት ከእምነት ይልቅ ታዋቂ በመሆንና ታዋቂን መተዋወቅን ቁብ ስለምንሰጥም ይሆናል። ምናልባት!

ምን ለማለት ፈልጌ መሰላችሁ? እንደ መልክና ይዘታችን የዛሬ አርባ ዓመት ለለውጥ ከመነሳት ይልቅ፣ በተውሶ ፍልስፍናና በተውሶ አብዮት አብደን የሆንነው ታሪክ ከዚህ ጋር የሚጋራ ስለመሰለኝ ነው። ‘ኮምፕሊኬትድ’ አደረግኩባችሁ? እንግዲህ ጥሬ ቆርጥሜ ስላደግኩ ቻሉኝ። ወደፊት አገራችን በዕድገት ጎዳና ተመንድጋ ዕውቀት ፈትፍታ የምታሳድጋቸው ልጆችዋ ይክሱዋችሁ ይሆናል። ታዲያ አደራ ልባችሁን ጠብቁ። ‘በምን?’ እህ ደላላ እንጂ የደኅንነት አጠባበቅ ‘ኤክስፐርት’ አይደለሁ። ስትፈልጉ ጨለማ ቤት ባደገ ውሻ፣ ቢያሻችሁ በባለ አራት ሜትር ልማታዊ ግንብ፣ እንደ እኔ በመጠን የምትኖሩ ከሆነ በቆርቆሮ አጥራችሁ መጠበቅ ነው። የሕዝብ ሀብት በማባከን ካልተከሰሳችሁ ኮብልስቶንም መጠቀም ይቻላል። ኋላ ግን አጉል ፍትፍት በማንኪያ የምንጎርስበት ዘመን ቅርብ ነው ብላችሁ  . . . ነገርኩ ብቻ። ካርታ ጨዋታ ይመስል ልብ እየጣልን ነው ዛሬ ልበኛ የጠፋው!

ጨዋታ እያነሱ ጨዋታ መጣልን እንግዲህ አንዴ ለምደነዋል። ቁም ነገሩንስ ቢሆን? ያዝ ለቀቅ መታወቂያችን ላይ አለመጻፉን እንደ ዕድል እንቆጥረዋለን መሰለኝ። “በደግ በደጉ እየተገናኝ ያዙኝ ልቀቁኝ ስንል ድል በሜዳውና በደጋፊ ጩኸት የሚቀናው ብሔራዊ ቡድናችን ሳይቀር ስንት ዘመን ያለተመልካች እንደተጫወተ አስበን እናውቃለን?” እያለ የሚነዘንዘኝ አንድ ወዳጅ ነበረኝ። ይኼ ወዳጄ ሁሉም ነገር ሲጠለዝ አብዝቶ የሚወድ ነበር። ኳስም ሆነ ነገር ካልተጠለዘ (ካልጦዘ ነው ወርቁ) ደስ አይለውም። ብሎ ብሎ ታዲያ ሁሉም ነገር እያደር በአንድ ፓርቲ መዳፍ ሥር ውሎ ሲያድር፣ ኳሱም ተስፋ ባስቆረጠበት ሰዓት እሱን ራሱን ‘ዲቪ’ አሜሪካ ድረስ ጠልዞ አሸሸው። እሱን እያስታወስኩ አዕምሮው በአግባቡ ለመሥራት እያመነታ ለመታወክ ዳር ዳር እያለ ካሰጋኝ፣ የረጅም ዘመን ደንበኛዬ ጋ ቀበሌና ክፍለ ከተማ ዘው ዘው ስል ሰነበትኩ።

ይኼኛው ጓዴ ነጋዴ ነው። ቀልጣፋ ነው። ነበር ልበል መሰል አሁን እንኳ። ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ትልቅ ሆቴል አለው። ሰሞኑን፣ “ከየትም ብለህ ከከተማ ወጣ ያለ ሥፍራ ጥሩ መኖሪያ ቤት ውለድ፤” አለኝ። እንደ አጋጣሚ ለገጣፎ አካከቢ አንድ ዳያስፖራ “ጆሮውን በልልኝ” ያለኝ ቤት ነበርና አገናኝቼው ገዝቶታል። ቤት ሲገዛ በሥራው ደስተኛ፣ በገቢው የተማመነ መስሎኝ ነበር መጀመሪያ። ኋላ ሳየው ግን እጅግ ተስፋ መቁረጥ ይታይበታል። እንዳልኳችሁ የአዕምሮ ጤናው እየተቃወሰ ነው። የቤቱን ካርታና ይዞታ በስሙ እያዛወረ ሳለ ምን እንደሆነ ብጠይቀው “ዕዳ” አለኝ። “የምን ዕዳ?” ስለው፣ “ግብር አናቴ ላይ ወጣ፤” አለኝ። “መቼ ዕለት ከፍዬ ጨረስኩ ተመስገን ስትል አልነበር?” እያልኩ ሰቅዤ ስይዘው፣ “የአምናና የካቻምናን ‘ኦዲት’ አድርገው ከአቅሜ በላይ እንደሚጫኑኝ መቼ ጠረጠርኩ?” ብሎ ብቻውን ማውራት ጀመረ። በከንቱ እኮ ነው ለአዲስ ዓመት ክብረ በዓል አላስፈላጊ የርችት ወጪ የምናወጣው ጎበዝ!

በአጭሩ ወዳጄና የዘመናት ደንበኛዬ ዕዳ እያለበት ቤት የገዛው ንግድ ቤቱ እስከ መታሸግ ቢደርስ ደንታ አልሰጠው ብሎ የዕረፍት ኑሮ ተጠምቶ መሆኑን ወዲያው ደረስኩበት። የአዕምሮው መታወክ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ ነጋ ጠባ ወትውተው ይዘውት ሄደው ፀበል ማስጠመቅ ሥራቸው ሆኗል። ውሎ አድሮ ባሻዬም ያውቁት ነበርና የሆነውን ሳጫውታቸው፣ “ግብር መክፈል የውዴታ ግዴታ ስለሆነ አታነካካኝ…” ብለው ዝም አሉ። “ምነው ፈሩ?” ስላቸው ዘራፍ ብለው አቅራሩ። ሳበርዳቸው ደግሞ፣ “ይኼ ዓለም የድካም ዓለም ነው። ብዙ ስታስብ ብዙ ታጣለህ። ብዙ ስታስገባ ብዙ ትከፍላለህ። ትርፍህ ሰላምህ ነው። በመጠን ኑር…” ብለው ዝም አሉ። “ግን እንዴት ነው በመጠን ተኑሮ፣ በጎመን በጤና ብሂል በፈጣን ግስጋሴ ላይ ካለው ኢኮኖሚያችን ጋር መስማማት የሚቻለው?” ብላቸው፣ “እሱን አላውቅልህም። ወይ በግ አርደህ አልያም እንደ በግ ታርደህ ብቻ በመረጥከው መንገድ መስማማቱ ያንተ ፋንታ ነው፤” አሉኝ። “እንቀጥለዋለን…” ብዬ ትቻቸው ሄድኩ። እውነት መስሏችሁ አደራ ቀጥልልን እንዳትሉኝ። እንዲህ ያለ ወሬ ከመቀጠል መጀመሪያ በየሠፈራችሁ እየተቋረጠ ያስቸገራችሁን ኤሌክትሪክ ማስቀጠል ይቅደም። አይሻልም?

 ኋላ ደግሞ መታወቂያዬን አሳድሳለሁ ስል ቀኑ ገፋ። እንደምታውቁት በአገራችን የመታወቂያችን ቀኑ ከሚያልፍበት ቀናችን በከንቱ ቢያልፍ ይቀላል። ሄጄ “አድሱልኝ” ማለት። እነሱም፣ “ሠፈሩ በቅርቡ ስለሚፈርስ ወደምትመራበት ወረዳ መሸኛ ብትወስድ ይቀላል፤” ማለት። እኔ “የሚቀለኝን እኔ አውቃለሁ…” ስል እነሱ “እናውቅልሃለን…” ሲሉ አጋጣሚውን በመጠቀም አንዱ ጠጋ ብሎ በቁራጭ ወረቀት ስልኩን መስጠት። ስደውል፣ “ሦስት ሺሕ ብር ስጠኝና እኔ ልሥራልህ?” ብሎ ቀልቤን ግፍፍ። ዙሪያዬን ባስስ ባስስ የመርሁ ብዛት። ‘ግልጽነት! ተጠያቂነት! ታማኝነት! ቅንነት . . . .!’  ወዘተ፣ ወዘተ። በመርህ ደረጃ ገነት በተግባር፣ ግን ሲኦል ከመገኘት ይሰውረን ብለን ባይሰውረንም ከመመኘት ሌላ ምን ይባላል? ምንም!

እንሰነባበት? ሳይሻል አይቀርም። ምክንያቱም ብዙ ልብ የሚያጠፋ ነገር ወሮናል። “አሁን እስኪ ልብ ደም እንጂ ወተት ይረጫል በፈጣሪ? ምነው ታዲያ እያደር ወተት ወተቱን ትተን ደም ደሙን አልን?” ብዬ ባሻዬን ስለገጠመኘ ባጫውታቸው፣ “የቃየል ሥራ ነዋ፤” ብለው ዝም። እሳቸው ዝም ሲሉኝ ወደ ግሮሰሪዬ ሄጄ ቆዘምኩ። ቅድም ‘ልብ ብሎ ልባችን ስለተገኘባቸው ጉዳዮች’ የባሻዬ ልጅ አጫወተኝ ያልኳችሁ እዚያ ነው። “መንግሥታት ለሕዝባቸው የቀን የቀኑን እንጂ የሌት የሌቱን አስበውለት አያውቁም፤” አለኝ። “ምን ማለት ነው?” ስለው “በቃ! እንደምታየው ነው። ሕዝብ ምርታማና ታታሪ ሠራተኛ የሚሆነው ሰላም ሲኖረው ነው። ከሰላምም ደግሞ ትልቁ ሰላም ሰላማዊ የአልጋ እንቅልፉ ነው  . . . ” ሲል ሳለ አንዱ ጣልቃ ገብቶ፣ “ይኼው እኔ አልጋ መስሎኝ አልጋ ቀየርኩ። ፍራሽ መስሎኝ ፍራሽ አሳደስኩ። ትራስ ነው ብዬ በአዲስ ሞከርኩት። እህሳ? ፍጥጥ እንዳልኩ መንጋት። ‘አሁን ነገ ጉዳዬን በቶሎ ይጨርሱልኝ ይሆን? ከአቅሜ በላይ ግብር ቢጣልብኝስ? አቤት ብል ሰሚ አገኝ ይሆን? ያላግባብ ተጥሎብኛል ይቀነስልኝ ከምለው ገንዘብ በላይ ጉቦ እጠየቅ ይሆን?’ ነው በቃ እንቅልፍ የሚነሳኝ። በጥርጣሬና በፍርኃት ዝሎ ልቤ ያለ አንዳች አጋዥ ኃይል መምታቱ ብቻ ይገርመኛል፤” ብሎ በሞቅታ መጠጥ ካልጋበዝኩ አለ።

የባሻዬ ልጅ ወደ እኔ ዞሮ፣ “ጨርሶልሃል። ሥጋትና ተስፋ በልባችን ታዛ መሳ ለመሳ ነግሠው ወደ ፊት መጓዝ ብሎ ነገር የለም። ከጠራ የመንግሥት አቋምና ፖሊሲ በፊት የረጋና የተማመነ የሕዝብ ልብ ሊኖር ያስፈልጋል፤” ብሎ ጋባዣችንን ወደ ማመሥገን ዞረ። ‘ልብ ለልብ’ የሚባል አጀንዳ ፓርላማ ቀርቦ ውይይት ሲደረግ ማየት ናፈቀኝ። ግን ፓርላማ ከመግባታችን በፊት እዚህ . . . እዚህ ጎዳናው ላይ እንደ ሰው፣ እንደ ወገን፣ እንደ ፍጡር . . .  ልብ ለልብ መገናኘት የለብንም መጀመሪያ? አሁንስ ልቤን አመመኝ መሰል፡፡ አንዳንዴ እኮ ወፈፍ ሲያደርገኝ፣ ዛሬ ከትናንት ለምን አይሻልም ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንዶች እንደቆሙበትና እንደሚያምኑበት አቋም ዛሬና ነገን በስሜታቸው ልክ ይመዝኑታል፡፡ እኔ ግን ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም በማለት እንዲህ አስባለሁ፡፡ ‘ትናንትና ከዛሬ ጋር ባይወዳደርም፣ ነገ ግን ከዛሬ መብለጥ አለበት’፡፡ ነገ ከዛሬ ካልተሻለ እኛ ምንድነን? ነገ ዛሬን ካልበለጠ ምኑን ተኖረ? መልሱልኝ! መልካም ሰንበት!           

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት