Tuesday, October 3, 2023

የለንደኑ የሶማሊያ ኮንፈረንስና የኢትዮጵያ አሠላለፍ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት በዋናነት የሚጀምረው ቅኝ ገዥው ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለመውረር ባቀደበት ጊዜ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

አብዛኛው ሕዝቧ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆነባት ሶማሊያ፣ ኮሎኒያሊስቱ ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት በመንደርደር ላይ እያለ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆና እንዳገለገለችው ይነገራል፡፡ የጣሊያን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ለመግባትና የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ማርካት ሲያስብ እንደ መንደርደሪያ ከተጠቀመባቸው አካባቢዎች አንዷ ሶማሊያ ነች፡፡

ጣሊያን በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ያለውን የሶማሌላንድ በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ሞክሯል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የሶማሊያ መሪዎች በገንዘብና በመሣሪያ በመደለል የጣሊያኖችን የበላይነት ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መንገድ ከፍተዋል፡፡ የጣሊያን መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1905 በሶማሌላንድ የጠረፍ ግዛት ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት 144,000 ፓውንድ ስተርሊንግ ከፍሎ እንደተረከበ ይጠቀሳል፡፡ ሶማሊያዊያን መሪዎች ለጣሊያን በራቸውን በመክፈትና ብሎም ወደ ጎረቤት አገሮች ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲሻገሩ በማድረግ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የታሪክ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመከፋፈል አቅደው ወደ አኅጉሪቷ ጎራ ሲሉ፣ መንገድ በመጠቆምና ትብብር በማድረግ ከተሳተፉት መካከል አንዷ ሶማሊያ ነች፡፡

በዚህም የተነሳ ሶማሊያ ከወረራ ያልተናነሰ በደል በኢትዮጵያ ላይ እንደፈጸመች አንዳንድ መጻሕፍት ከትበውት ይገኛል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የሶማሊያ ገዥዎች ለገንዘብና ለሥልጣን በነበራቸው ፍቅር ለቅኝ ገዥዎች ቀኝ እጅ በመሆን ለአፍሪካ  አገሮች ነፃነት ማጣትና መውደቅ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ሁለተኛውና ቀጥተኛ የሆነው የኢትዮጵያና የሶማሊያ ግንኙነት  የሚጀምረው ደግሞ የደርግ መንግሥት በትረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ የዚያድ ባሬ መንግሥት ከደርግ መንግሥት ጋር በነበረው ቅራኔ ደም  አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የነዳጅ ዘይት ይገኝበታል ተብሎ የሚጠረጠረውን የኦጋዴን አካባቢ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከደርግ መንግሥት ጋር አድርጓል፡፡

ምንም እንኳን የዚያድ ባሬ መንግሥት በወቅቱ በውስጣዊ ችግር የተተበተበና በእርስ በርስ ጦርነት የተዳከመ ቢሆንም ከደርግ መንግሥት ጋር ኃይለኛ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ይህ ጊዜ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በከፍተኛ ሁኔታ በቀጥታ የተገናኙበትና ጉልበታቸውን የተፈታተሹበት ጊዜ እንደሆነ ታሪክ ይገልጻል፡፡

ምንም እንኳ ሶማሊያ በእርስ በርስ ጦርነት ለዓመታት የቆየች አገር ብትሆንም፣ በታሪክ አጋጣሚ ኢኮኖሚዋን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ጥረት ያደረገችበት  አጋጣሚም ነበር፡፡ አገሪቷ በዚያድ ባሬ ቁጥጥር ሥር ሆና በንግድና ኢንቨስትመንት የተሻለች ለመሆን ‹‹የገልፍ የትብብር ካውንስል›› እየተባለ በሚጠራው ድርጅት ውስጥ አባል ሆና እንደነበር የታሪክ ማኅደሯ ይጠቅሳል፡፡ በታሪክም የገልፍ ጦርነት እየተባለ ይጠራ በነበረው ጊዜ ተሳትፎ እንደነበራት ተጠቁሟል፡፡ ዚያድ ባሬ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሻሻል ወደ አውሮፓና ወደ ገልፍ የትብብር ካውንስል ፊቷን እንድታዞር ጥረት አድርገዋል፡፡  ይህም ሆኖ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ማሻሻል እንዳልቻሉ ተጠቁሟል፡፡ የዚያድ ባሬ አምባገነናዊ አስተዳደር ሊያበቃ የቻለውም በአገሪቱ በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1991 በሶማሊያ የዚያድ ባሬ ሥርዓት ወደቀ፡፡ ይህ የማዕከላዊ መንግሥት መውደቅም ሶማሊያን በንግድና ኢንቨስትመንት እንድታቆጠቁጥ ዕድል ከፍቶላት እንደነበር አንዳንድ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ጥብቅ የሆነ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሌለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣናው ያለው ሰላም አስተማማኝና እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ፣ በአካባቢው በሚኖሩ አገሮች መካከል  ጠንካራ የሚባል ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት የለም፡፡ አልሸባብ በቀጣናው ውስጥ ባሉ አገሮች ግንኙነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ  እ.ኤ.አ. የካቲት 2 ቀን 2016 ዕትሙ ላይ እንደገለጸው፣ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ አገሮች በኅብረት ለመሥራትና ይህንንም ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማምጣት በኩል ውስንነቶች አሉባቸው፡፡ አገሮቹ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት ቢኖራቸውም በአልሸባብ አማካኝነት ህልማቸው ዕውን ሳይሆን እንደቀረ ይጠቀሳል፡፡

አልሸባብ ምሽጉን በሶማሊያ አድርጎ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ወጣ ገባ እያለ የሽብር ጥቃት የሚያደርስ አሸባሪ ቡድን ነው፡፡ በአልቃይዳ እንደሚደገፍ የሚናገረው ይህ አሸባሪ ቡድን ከዚህ በፊት በኬንያ የዌስትጌት የገበያ ማዕከል ባደረሰው ጉዳት፣ የበርካታ ኬንያውያንን ሕይወትን ቀጥፏል፡፡ በኬንያ በተደጋጋሚ ጊዜ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ሳይቀር ጥቃት በማድረስ አገሪቷን የሽብር መናኸሪያ ለማድረግ ሌት ከቀን ሲሠራ ነበር፡፡ ኬንያ ምንም እንኳ በቀጣናው ካሉ አገሮች የተሻለ ኢኮኖሚ ቢኖራትም፣ ለእንደዚህ ዓይነት የሽብር ጥቃት ተጋላጭ ከመሆን እንዳልዳነች መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኬንያ የደኅንነት ጉዳይ በሙስና ቅሌት የተዘፈቀ መሆን ደግሞ ጉዳዩን እንዳባባሰው መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡

በአፍሪካ ካሉ ዋነኛ አሸባሪ ቡድኖች መካከል በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሸባብ፣ በሊቢያ የሚገኘው አይኤስና በናይጄሪያ የሚገኘው ቦኮ ሐራም ዋነኛዎቹና ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ የእነዚህ  አሸባሪ ቡድኖች ዋነኛ ዓላማ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ ዓለምን የትርምስ መድረክ ሆና ማየት ዓላማቸው እንደሆነ ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው ጠቁሟል፡፡

አልሸባብ በዋናነት ትኩረት ያደረገው በሽግግር ላይ የምትገኘዋን ሶማሊያ ማድቀቅና በሶማሊያ የፀጥታ ሁኔታ ላይ እጃቸውን በሚያስገቡ አገሮች ላይ አፀፋዊ ዕርምጃ መውሰድ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሶማሊያ ዋና ዋና የመንግሥት የትኩረት ቦታዎች በሚባሉት ላይ ማለትም በደኅንነት ቢሮዎች፣ በቤተ መንግሥትና በመረጃ መረብ አውታሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ እነዚህም አልሸባብ እያደረሰ ያለው ቀውስ ከሶማሊያ አልፎ ወደ ጎረቤት አገሮች  እየተስፋፋ መምጣቱን ማሳያ መረጃዎች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ በብሩንዲ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በሌሎች የቀጣናው አገሮች ላይ ትኩረቱን እንዳደረገ ጃኪላ ናካይዞ የተባሉት የኡጋንዳ ከፍተኛ ተመራማሪ ይገልጻሉ፡፡

ጃኪላ ናካይዞ  አልሸባብ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተዋናይ በሆኑ  አገሮች ላይ ሥጋት እየሆነ ከመምጣቱ ባሻገር፣ የአሸባሪ ቡድኑን አከርካሪ መትቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጣል እንዳልተቻለ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ ገልጸዋል፡፡

በሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ወቅት በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ዋና ተዋናይትና በአሜሪካና በአውሮፓ መንግሥታት የገንዘብ ድጋፍ አልሸባብን ከሶማሊያ ጠራርጎ የማስወጣት ዕቅድ ቢኖርም እንዳልታሳካ የናካይዞ ጽሑፍ ያስረዳል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ጥላ ሥር የሚገኘው የቀጣናው አገሮች የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጥረት ታክሎበት  ሶማሊያን ከአሸባሪ ቡድኑ ነፃ የማውጣት ውጥን ቢኖርም ሊሳካ እንዳልቻለ ጽሑፉ ያብራራል፡፡

በሶማሊያ የአሚሶም ጥበቃ እንደሚፈለገው አለመሆን ደግሞ በቀጣይ የአሸባሪ ቡድኑ ሰለባ ከሚሆኑ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ልትሆን እንደምትችል ገልጿል፡፡ ምንም  እንኳ ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች ችግር ጣልቃ መግባት እንደሌለባትና ድንበሯን ከአሸባሪ ቡድን በመጠበቅ ብቻ መኖር እንዳለባት የሚመክሩ ወገኖች ቢኖሩም፣ በቀጣናው ሰላም መስፈን የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣች እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የአልሸባብን ስብስብ ከኢትዮጵያ  ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ የዓረብ አገሮች ድጋፍ እንደሚያደርጉለት በተደጋጋሚ ጊዜ ይደመጣል፡፡ በተጨማሪም ይህን ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች መካከልም ኤርትራ አንዷ እንደሆነች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በተደጋጋሚ ጊዜ በሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡

በኢትዮጵያ ዋነኛ ተዋናይነትና በአሜሪካ የገንዘብ  ድጋፍ ይመራ የነበረው የሽግግር መንግሥቱን  የማጠናከርና አሸባሪ ቡድኑን የማጥፋት ዘመቻ በሶማሊያ የተወሰኑ ለውጦችን ቢያሳይም፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ እንዳልቻለ ግን በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል፡፡

ሶማሊያ በዋነኛነት በኦሚሶም ጥላ ሥር በሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር በመታገዝ የካቲት ወር ላይ ምርጫ በማካሄድ አዲስ ፕሬዚዳንቷን መርጣለች፡፡ ሶማሊያን ከገባችበት አረንቋ ያወጣሉ ተብለው የተመረጡት አዲሱ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በሶማሊያ  ሕዝብ ላይ ከበሮ እየመታ ያለውን  አል-ሸባብ ከአገሪቱ ነቅሎ ለማስወጣት የማይፈነቀሉት ድንጋይና የማይገቡበት ጉድጓድ እንደሌለ ገልጸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሥልጣን ከያዙ ሳምንት  ሳይሞላቸው አልሸባብ በሞቃዲሾ ባደረሰው የአጥፍቶ መጥፋት የበርካታ ንፁኃን ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ አሁንም ቢሆን ብቅ ጥልቅ እያለ ጉዳት ከማድረስ እንዳልተቆጠበ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡

ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ የሽግግር መንግሥቱን ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ በሕዝቡ ዘንድ አንፃራዊ መረጋጋት ታይቷል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአገሪቱ የድርቅ አደጋ ቢጠብቃቸውም፣ ችግሩን ለመፍታት ከላይ ታች ሲሉም ታይተዋል፡፡

አዲሱ ፕሬዚዳንት ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ለሶማሊያ መንግሥት አሜሪካና የአውሮፓ አገሮች ሳይቀር ድጋፍ ችረውታል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ  ሊሆን የሚችለው ደግሞ እንግሊዝ በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ያሳየችው እንቅስቃሴ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ፎርማጆ ወደ ሥልጣናቸው ከመጡ ሁለት ወራት ሳይሞላቸው፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን  እ.ኤ.አ. መጋቢት 15 ቀን 2017 ሶማሊያን ጎብኝተዋል፡፡ የቦሪስ ጆንሰን  የሶማሊያ ጉብኝት ሳይታሰብና ድንገተኛ እንደሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ ቢሰነብትም፣ በሶማሊያ የደኅንነትና የፀጥታ ጉዳይ ላይ ከፎርማጆ ጋር እንደተወያዩ ተገልጿል፡፡ ቦሪስ ጆንሰን በሞቃዲሾ ለሰባት ሰዓታት በነበራቸው ቆይታ፣ ከአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ወደ ምሥራቅና ምዕራብ አፍሪካ እየተስፋፋ ስላለው ድርቅና የሶማሊያ የፀጥታ ሁኔታ ተነጋግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሶማሊያና እንግሊዝ ወደፊት ስለሚኖራቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት አንስተው መክረዋል፡፡

ቦሪስ ጆንሰን በነበራቸው አጭር የሶማሊያ ቆይታ የእንግሊዝ ጦር ለአዲሱ የሶማሊያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ድጋፍ የጎበኙ ሲሆን፣ ወደፊትም ይህንን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የሽግግር መንግሥቱን ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ  አገሮች ጎራ በማለት፣ አዲሱ መንግሥታቸው የሚጠናከርበትንና ለአገሪቱ ድጋፍ በሚያደርጉበት ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት እንዳልነበራችው ቢገለጽም፣ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደሚሉት፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት  የላቸውም የሚለው ግምገማና ድምዳሜ ከጥርጣሬ ያለፈ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ ለመግባት ምንም ፍላጎት  እንደሌላትና በሶማሊያ  ሕዝብ ከተመረጠው አካል ጋር  ተባብሮ መሥራት፣ የኢትዮጵያ መርህ  እንደሆነ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ ለሦስት ቀናት ይፋዊ  የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ጉብኝታቸውን ሳይጨርሱ ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ በቅርብ ካዋቀሩት ካቤኔ አዳዲስ  አመራሮች አንዱ የሆኑት ወጣት ሚኒስትር በአሸባሪዎች መገደላቸውን ሲሰሙ ጉብኝታቸውን  ሳይቋጩ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ይህን ድርጊት አልሸባብ ለዚች አገርና ለአፍሪካ ቀንድ መቼም ቢሆን ሊተኛ እንደማይችል አንዱ ማሳያ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ሶማሊያን ወደ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ዓለም አቀፍ ስብሰባም በለንደን ተካሂዶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በለንደን የተካሄደው የሶማሊያ ኮንፈረንስ ለሶማሊያዊያን  ትልቅ  ተስፋ  ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና  የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ጸሐፊና ሌሎች የዓለም መሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡ ለአንድ ቀን የቆየው ይህ የለንደኑ የሶማሊያ ኮንፈረንስ በአልሸባብ የጥፋት እጅ እየተደበደበች ያለችውን ሶማሊያን ነፃ በማውጣት ስትራቴጂና 6.2 ሚሊዮን ሶማሊያዊያንን ለችግር በዳረገው ድርቅ ላይ መሪዎች ተወያይተዋል፡፡ ኮንፈረንሱ በዋናነት የሶማሊያ አዲሱ መንግሥት የሚጠናከርበትን ዘዴ አበጅቶ ያለፈ እንደሆነ፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡

ወደ እንግሊዝ ዋና ከተማ ለንደን ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በኮንፈረንሱ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፣ በአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ ላይ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦርና የአሚሶም ኃይሎች በጋራ እያካሄዱ ስላለው ዘመቻ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በዚህም አልሸባብ እየተዳከመ መምጣቱንና ይህንን ዘመቻ ከግብ ለማድረስ ግን እየተደረገ ያለው ድጋፍ መቀነሱን አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አልሸባብን በተፈለገው ጊዜ አከርካሪውን መስበር እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ የአሸባሪ ቡድኑ አቅም ካለፈው ጋር ሲነፃፀር እንደተዳከመ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ አሁንም ግን በሶማሊያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሽብር ጥቃት ለማድረስ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አሚሶምንና የሶማሊያን ብሔራዊ ጦር በመደገፍ በቡድኑ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሶማሊያን ከአሸባሪ ቡድኑ ነፃ አውጥቶ የተረጋጋች አገር እንድትሆን ዓለም  አቀፉ ማኅበረሰብ ለአሚሶምና ለሶማሊያ ብሔራዊ ጦር የፖለቲካ፣ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፎችን ሊያርግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በሶማሊያ ላይ ተጥሎ የነበረው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በከፊል መነሳቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢደግፉትም፣ ሙሉ በሙሉ መነሳት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ባደረጉት ንግግር፣ በሶማሊያ የተከሰተው ረሃብና ያንን ተከትሎ የመጣው የኮሌራ ወረርሽኝ በአካባቢው ላይ ሥጋት  እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡ ከችግሩ መጠነ ሰፊነት የተነሳም ዓለም አቀፍ ተቋማት ጣልቃ መግባት እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ በበኩላቸው፣ በሶማሊያ  የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ለአሚሶም ሠራዊት ያዋጡ አገሮች ከፍተኛ  መስዋትነት እየከፈሉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲና ጂቡቲ እጅግ የተለየና ጠንካራ ሥራ በመሥራታቸውና የላቀ መስዋዕትነት በመክፈላቸው ሊደነቁ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሶማሊያ ፀጥታ የሰፈነባት፣ የተረጋጋችና የበለፀገች አገር እንድትሆን አገራቸው ድጋፏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የሶማሊያ አዲሱ ፕሬዚዳንት መሐመድ አቡዱላሂ ፎርማጆ በበኩላቸው፣ በአገራቸው ላይ የተጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡ የተደራጀውን አልሸባብ ለመዋጋት ከባድ መሣሪያ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ፎርማጆ፣ ‹‹የእኛ የፀጥታ ኃይልና አሸባሪ ቡድኑ እየተዋጉ ያለው ኤኬ 47 ኤስ (AK- 47S) በተሰኘ ቀላል መሣሪያ ነው፡፡ ይህንን የአሸባሪ ቡድን ለመዋጋት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊያ ላይ ጥሎት የነበረውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲያነሳ እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ተመድ በሶማሊያ ላይ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ  የጣለው እ.ኤ.አ. በ1992 የዚያድ ባሬን መንግሥት ለመገልበጥ በተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በርካታ ንፁኃን ሶማሊያዊያን ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ የተሻሻለው ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2013 ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ሞቃዲሾ ቀላል የጦር መሣሪያ ገዝታ እንድትጠቀም መብት ሰጥቷታል፡፡ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች ያለ አካላት ግን ውሳኔውን መልካም ነው ብለው አልተቀበሉትም፡፡

ፎርማጆ በወርኃ የካቲት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ፣ ከአልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው የሚባለውን አልሸባብን ለመዋጋትና ድባቅ ለመምታት ቃል ገብተው ነበር፡፡ ዕቅዳቸው እስከ ዛሬ አልሰመረም፡፡ ኢትዮጵያ በአሚሶም ጥላ ሥር ሆና አልሸባብን ለመዋጋትና እስከ መጨረሻው በሶማሊያ መፍትሔ ለማምጣት እንደምትሠራ በተደጋጋሚ ጊዜ ትገልጻለች፡፡ ፎርማጆ በኢትዮጵያ መራሹ የአሚሶም ሠራዊት ታግዘው አልሸባብን በአጭር ጊዜ ለማውደም ቢሞክሩም፣ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ ግን ሚዲያዎች እየገለጹ ነው፡፡

ለአንድ ቀን ያህል ምክክር ባደረገው በለንደኑ የሶማሊያ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም፣ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሥልጣን በያዙ ሳምንት 6.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሶማሊያዊያን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው ነበር፡፡ ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል፡፡

ጉቴሬዝ በሶማሊያ አሁን የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት 900 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ወዲህ በአልሸባብ የአሸባሪ ቡድን፣ ወዲያ  ደግሞ በድርቅ እየተመታች ያለችው አዲሲቷ ሶማሊያ ከችግሮችና ፈተናዎች መላቀቅ እንዳልቻለች የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ  አደጋዎች  እየተፈራረቁ ሶማሊያን የበለጠ የተዳከመች አገር ለማድረግ እየተገዳደሯት መሆኑ ይገለጻል፡፡

ሶማሊያን መነሻው  አድርጎ በአፍሪካ ቀንድ እየተዘዋወረ መጠነ ሰፊ ጥቃት  እያደረሰ ያለው አልሸባብ የመሞቻ ቀኑ ረዥም ሊሆን እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ የተደራጀ መሆኑና ከአንዳንድ የዓረብ አገሮች ኤርትራን ጨምሮ ድጋፍ እየተደረገለት በመሆኑ በቀላል ሊወገድ እንደማይችል በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በአሚሶም ጥላ ሥር ያለው የኢትዮጵያ ሠራዊትም ለብዙ ዓመታት በሥፍራው ቢገኝም፣ አልሸባብን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ እንዳልተቻለ በለንደኑ የሶማሊያ ኮንፈረንስ ተገልጿል፡፡

ለንደን የተካሄደው የሶማሊያ ኮንፈረንስ በአገሪቱ ብዙ ለውጦች ይዞ ይመጣል  ተብሎ ቢገመትም፣ አገሮች አሁንም ገንዘብ በማውጣት የአሚሶምን ጦር የማይደግፉ ከሆነ ጉዳዩ ጉንጭ ከማልፋት ውጭ ትርጉም እንደሌለው እየተነገረ ነው፡፡ አዲሱ የሶማሊያ መንግሥት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ካልተነሳ ችግሩ አሁንም ሊፈታ እንደማይችል ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ የማያደርግ ከሆነ፣ በቀጣናው ያላትን ወታደራዊ አሠላለፍ ልታላላ እንደምትችል ግምቶች ይሰማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -