ኢትዮጵያን አይድል ለኢትዮጵያ የተሰጥኦ ውድድሮች ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ እውቁን አሜሪካን አይድል ጨምሮ የበርካታ አገሮች የተሰጥኦ ውድድሮች የዝግጅቱ መነሻ ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ በያኔው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የአሁኑ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በየሳምንቱ ይተላለፍ የነበረው ዝግጅቱ፣ አንድ ለእናቱ እንደመሆኑም በርካታ ተመልካች ነበረው፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ቴሌቭዥናቸው ላይ አይናቸውን ተክለው፣ ቀልባቸውን የገዛውን ተወዳዳሪ የሚደግፉ፣ ውድድሩንም በራሳቸው ምልከታ የሚዳኙ ተመልካቾች ጥቂት አልነበሩም፡፡ በውድድሩ የድምፃውያንንና ተወዛዋዦችን ብቃት የሚለኩ ዳኞችም በተመልካቾች ሚዛን ይቀመጣሉ፡፡
ዛሬ የተሰጥኦ ውድድሮች ቁጥር ጨምሮ በየቴሌቪዥን ጣቢያው አንድ ወይም ሁለት የተሰጥኦ ውድድር ይተላለፋል፡፡ በኢቢሲ ኢትዮጵያን አይድልን ተከትሎ የመጣው ባላገሩ አይድል አንዱ ነው፡፡ ከድምፃውያን ውድድሮች መረዋና ኮካኮላ ሱፐር ስታርስ፣ ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ያወዳደረው ኢትዮ ታለንት ሾው፣ በሥራ ፈጠራ ዘርፍ ባለ ራዕይ፣ በትወና የማለዳ ኮከቦችና በሥነ ውበት ኢትዮጵያን ቢውቲ ታለንት ሾው ይጠቀሳሉ፡፡
የተሰጥኦ ውድድሮች በሙያ ማኅበሮች አንዳንዴም በድርጅቶች ተነሳሽነት ቢካሄዱም፣ ቴሌቪዥን ካለው መጠነ ሰፊ ተደራሽነት አንፃር በቴሌቪዥን ስለሚተላለፉት አያሌ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡ የውድድሮቹን ዳኞች በተመለከተ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ ስለ ተወዳዳሪዎች ብቃት ያሏቸውን የተለያዩ አስተያየቶች በተለይም አስተያየታቸው ያልተገናኘ ሲመስል የሚያስታርቁበት መንገድ ነው፡፡ ይህ በዳኝነት የሚቃረን ሐሳብ ሲኖር እንዴት ይደረጋል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት የሚጠቀሙበት መንገድም ይነሳል፡፡ በተለይም አንድ ዙር አልቆ ቀጣዩ ሲተካ የተወዳዳሪዎችን እጣ ፈንታ በሚወስኑ ዳኞች ላይ ያለው ጫና እየጨመረ፣ ከተመልካቾችና ተወዳዳሪዎች የሚነዳው የፍትሐዊነት ጥያቄም እየጨመረ ይሄዳል፡፡
በኢትዮጵያን አይድል ይዳኙ ከነበሩ አንዱ ሙሉ ገበየሁ፣ ዳኞች የሚሰጡት አስተያየት ባላቸው ልምድና ዕውቀት እንደሚለያይ ይናገራል፡፡ አንድ ተወዳዳሪ ሲመዘን በዳኛው አረዳድ ልክ እንዲሁም የሙዚቃ ወይም ውዝዋዜ መሥፈርቶችን በተገነዘበው መጠን ጥሩ ወይ መጥፎ ይባላል፡፡ የዳኞች ምልከታ ቢለያይም፣ ሚዛናዊ ፍርድ ላይ የሚደረሰው በጋራ በሚስማሙባቸው መሥፈርቶች መሆኑን ያስረዳል፡፡ በውድድሩ የእያንዳንዱ ዳኛ ውጤት ተደምሮ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፈው ወይም የሚያሸንፈው ይለይ ነበር፡፡
በዚሁ ውድድር ዳኛ የነበረው አሁን ደግሞ በመረዋ እየዳኘ ያለው ሠርፀ ፍሬስብሃት የሙሉን ሐሳብ በተወሰነ መልኩ ይጋራል፡፡ እሱ እንደሚለው እያንዳንዱን ዳኛ የሚስበው ዓይነት ድምፅ አለ፡፡ ስለ አንድ ተወዳዳሪ ብቃት አሻሚ አስተያየት ሲኖር መለኪያቸው ሁሉም የሚስማሙበት መሠረታዊ የሙዚቃ ቀመሮች ይሆናሉ፡፡ ልዩነታቸው የሚታረቀውም የሙዚቃ ቀመሮቹን በመከተል በሚሰጡት ውጤት ድምር ይሆናል፡፡ የጥበባዊ ሥራዎች ውበት እንደየተመልካቹ ስለሚለያይ፣ የማያወላዱትን መለኪያዎች መከተል የተሻለ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ከአንድ ዙር ወደ ሌላው ሲሸጋገሩ መስፈርቶች እየጨመሩና እየተጠናከሩ መሄድ አለባቸውም ይላል፡፡
እንደ እሱ አስተያየት፣ በመረዋ ዳኞቹ በሙዚቃው ውስጥ በተለያዩ ክፍሎች ያሉ መሆናቸው ለዳኝነቱ ሚዛናዊነት ይረዳል፡፡ ከሙዚቃ ውጪ ያሉ እይታዎችን ለማካተት ፊልም ሠሪዎችና ሌሎችም ሕዝቡን የሚወክሉ ባለሙያዎች ይጋበዛሉ፡፡ በሌሎች አገሮች ከተወዳዳሪዎች የቴክኒክ ችሎታ አልፈው በገበያው የሚኖራቸውን ተቀባይነት ከግምት የሚያስገቡ ዳኞችም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ውድድሩ ብዙ እንደሚቀረው ይናገራል፡፡
አንዳንዴ ተወዳዳሪዎች ችሎታ ቢኖራቸውም ውድድሩ የሚጠይቀውን ባለማሟላት ይወድቃሉ፡፡ ‹‹አንዳንዴ እየሳሳሁላቸው የሚወድቁ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም፣ ዳኝነት ጭካኔ ይጠይቃል፤›› የሚለው ሠርፀ፣ ተወዳዳሪዎችን በማባበል አያምንም፡፡ የተወዳዳሪዎቹ ክፍተቶች ላይ ያተኮረ አስተያየት መሰጠት አለበት ይላል፡፡ አንዳንዶች ምንም ነገር የማይጥመው አድርገው ቢወስዱትም፣ ዳኝነት እንዲከበርና ተወዳዳሪዎች የተሻለ ሥራ እንዲያቀርቡ ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡
የአንድ ተወዳዳሪ ውጤት ቤተሰቡን፣ ዘመድ አዝማዶቹን፣ ጓደኞቹን፣ የሰፈሩን ሰዎችና ሌሎችንም በተወሰነ መልኩ የሚነካ መሆኑ፣ ዳኞች በሚሰጡት ውሳኔ ከብዙዎች ጋር እንዲጋፈጡ ያስገድዳል፡፡ ከብዙ ሺሕ ተወዳዳሪዎች መካከል ብቁዎችን ለይቶ የማውጣት ኃለፊነት ሌላው የዳኝነት ፈተና ሲሆን፣ ትክክለኛውን ውሳኔ የማስተላለፍ ጫና ደግሞ ሠርፀን፣ ‹‹ወንበሩ ላይ ከመቀመጥ በፊት ፀሎት ያስፈልጋል›› እንዲል አድርጎታል፡፡
ብዙ ውድድሮች ውጪ አገር ካሉት ጋር በመመሳለላቸው ይተቻሉ፡፡ መረዋ የአሜሪካውን የተሰጥኦ ውድድር ‹‹ዘ ቮይስ››ን መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ የሌሎችም ውድድሮች አካሄድ ከተለያዩ ውድድሮች ጋር መመሳሰሉ የተመልካችን ስሜት እያቀዘቀዘው እንደመጣ ይነገራል፡፡ እሱ በበኩሉ፣ መነሻቸውን ሙሉ በሙሉ ከውጪ ያደረጉ ውድድሮች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ኢትዮጵያዊ ገፅታ እንዳልተላበሱ ይናገራል፡፡ በተቃራኒው ባላገሩ አይድል በተሻለ መልኩ አገርኛ ገፅታ የተላበሰ ነው ይላል፡፡ በዳኝነቱ ረገድ ግን በመረዋ ለዳኝነት የሚመጥኑ ሙያዊ አገላለጾች እንደሚጠቀሙ ያስረዳል፡፡
በባላገሩ አይድል ላይ የውዝዋዜ ዳኛ የነበረው ጌታነህ ፀሐዬ ከሠርፀ የተለየ ሐሳብ አለው፡፡ ዳኞች የተለያየ ሐሳብ ማቅረባቸው ለውድድር ውበት ይሰጣል ይላል፡፡ ሁሉንም የሚያስማሙ ተወዳዳሪዎች እንዳሉ ሁሉ ልዩነት የሚፈጥሩ መኖራቸውም አይቀሬ ነውና ዳኞች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት እንደያዙ መቀጠላቸው ዳኝነቱን ሚዛናዊ ያደርገዋል ብሎ ያምናል፡፡
ዳኞች የተሰማቸውን ፊትለፊት መናገር አለባቸው ቢልም አስተያየት ሲሰጥ ከበጎ ጎን መጀመር እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ጥሩ ከሠሩ ተወዳዳሪዎች በበለጠ መጠነኛ ሙከራ ላደረጉት የተጋነነ አስተያየት ይሰጣል፡፡ ባለሙያዎች በአካሄዱ ቢተቹትም ከተመልካቾች በጎ ምላሽ ያገኛል፡፡ በባለሙያዎችም ይሁን በሌሎች ተመልካቾች ዘንድ የሚሰጠው ቦታ እንደማያሳስበው ገልጾ፣ ‹‹ተወዳዳሪው ጥሩም ይሥራ መጥፎ በመልካም ቃላት ተገንብቶ መሄድ አለበት፤›› ይላል፡፡
በእሱ እምነት፣ ዳኞች ተወዳዳሪዎች በሚያቀርቡበት ትዕይንት የተሰማቸውን በዛው ቅጽበት ማሳየት አለባቸው፡፡ ተወዳዳሪውን ማቀፍ፣ ተወዛውዞ ማሳየትና ሌሎችም ትጽበታዊ ምላሾች መኖር አለባቸው ይላል፡፡ በሌላ በኩል ከዳኞች በተጨማሪ የሕዝብ ዳኝነት የተወዳዳሪዎችን ዕጣ ፈንታ ስለሚወስን ሚዛናዊ መሆን ይገባዋል ይላል፡፡ ችሎታ ሳይኖራቸው በቲፎዞ ብዛት ጥሩ ውጤት የሚያመጡ ተወዳዳሪዎች እንዳሉም ይጠቅሳል፡፡
በባላገሩ አይድል የመጨረሻው ዙሮች የተወሰነ ልዩነት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ሲወድቁ ማየቱን ጠቅሶ፣ በሕይወቱ ካደረጋቸው ከባድ ነገሮች ዋነኛው በዳኝነት ወንበር መቀመጥ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ወደ ባላገሩ አይድል ከመምጣቱ በፊት በሌሎች የተሰጥኦ ውድድሮች የሚመለከታቸውን የዳኝነት መንገዶች ይተች ነበር፡፡ ዳኛ የመሆን ፍላጎቱ ባይኖረውም በአብርሃም ወልዴ ግፊት ዳኝነቱን ከተቀላቀለ በኋላ፣ ሙሉ በሙሉ የሚያስበውን ዓይነት ዳኛ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ተሳክቷል ይላል፡፡
በኢትዮጵያ ብሮካስቲንግ ሰርቪስ (ኢቢኤስ) ከሚተላለፉ የተሰጥኦ ውድድሮች አንዱ የኢትዮጵያ ቢውቲ ታለንት ሾው ነው፡፡ ከተወዳዳሪዎች መካካል ምርጥ አሥር የተባሉት የተለዩት በቅርቡ ነበር፡፡ የፀጉር ሥራና ገፀ ቅብ ውድድሩ ፕሮዲውሰርና ዳኛ ጎልያድ ሚካኤል፣ የውድድሩ ዳኞች በዘርፉ የዓመታት ልምድና ዕውቀት ያካበቱ መሆናቸው መሥፈርት እንደነበር ይገልጻል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ተወዳዳሪዎች ችሎታ እንዳላቸው አምነው መግባታቸው አንዳንድ የዳኞችን ውሳኔዎች በቀና እንዳይመለከቱ አድርጓቸዋል፡፡ የዳኞችን አስተያየት በመቃወም ውድድሩን ጥለው የወጡም ነበሩ፡፡ በመጀመርያው ዙር ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶች ተወዳዳሪዎች ድክመታቸውን እንዲያስተካክሉ መንገድ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ለተወዳዳሪዎች የሚሰጡ ፈተናዎች እየጠነከሩ ሄደዋል፡፡
የውድድሩ ቋሚ ዳኞች እንዲሁም ተጋባዦች የሚከተሉት ሳይንሳዊ መሥፈርት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ዕይታቸው የተወሰነ ልዩነት ቢሮረውም ሰፊ ልዩነት አይገጥማቸውም፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ዕይታችን እኩል ነው፤ ክፍተት ቢፈጠር እንኳን የሁላችንም ድምፅ ድምር መለያ ይሆናል፤›› ይላል፡፡
ውድድሩ እየተለመደ ሲሄድ ተወዳዳሪዎች የዳኞችን መሥፈርቶች ስለሚገነዘቡ እንደሚሻሻሉ ያምናል፡፡ እስካሁን ከተመልካቾችና ከተወዳዳሪዎች ዳኝነትን በተመለከተ የቀረቡ ብዙ ቅሬታዎች ባይኖሩም፣ በቀሩት አሥር ተወዳዳሪዎች መካከል ያለው ፉክክር ዳኝነቱን እንደሚያከብደው ይገምታል፡፡
በተመሳሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያ የትወና ውድድር የሚካሄድበት የማለዳ ኮከቦችን ከሚዳኙ አንዱ ሚካኤል ሚሊዮን፣ በዳኝነት ሳይንሳዊ መሥፈርቶችን መከተል በሚለው ሐሳብ ከጎልያድ ጋር ይስማማል፡፡ ትወና እንደየተመልካቹ ስለሚወሰን ስለ አንድ ተወዳዳሪ ትዕይንት የተለያየ ሐሳበ ሊሰነዘር ይችላል፡፡ ተወዳዳሪዎች የሚፈተኑባቸውን ገፀ ባህሪዎች ዳኞች በኅብረት ቢያዘጋጁም፣ መድረክ ላይ ሲቀርቡ ምልከታቸው ይለያያል፡፡ ይኼኔ ሁሉም ወደሚስማሙባቸው የትወና ንድፈ ሐሳቦች ፊታቸውን ያዞራሉ፡፡
ሚካኤል በዳኞቹ መካከል የሐሳብ ልዩነት መፈጠሩ ብዙ ሰዎችን እንዲወክሉ እንደሚያደርጋቸው ያምናል፡፡ ዳኞች ተመሳሳይ ሐሳብ ከሚኖራቸው ቢለያዩ የሚመርጠውም ለዚሁ ነው፡፡ ዳኞቹ ከትምህርት ተቋም፣ ከቴአትር ቤትም የተውጣጡ መሆናቸው ሚዛናዊነታቸውን እንደሚጠብቅ ገልጾ፣ ‹‹እርስ በርስ መጨቃጨቃችን የውድድሩን ተዓማኒነትም ያሳያል፤›› ይላል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡን ሌሎች ዳኞች ጋር የሚስማማበት ሐሳብ ተወዳዳሪዎችን ትችላላችሁ ወይም አትችሉም ብሎ መፈረጅ ያለውን ጫና በሚመለከት ነው፡፡ ለዳኝነት በሚሰጠው አጭር ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ ለማስተላለፍ ጥረት ቢደረግም ስህተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ይናገራል፡፡ ተመልካች ወይም ተወዳዳሪዎች ስህተት ተሠርቷል ቢሉም እንኳን ካለፈ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለ ያስረግጣል፡፡
ከኮካ ኮላ ሱፐር ስታርስ የተሰጥኦ ውድድር ዳኞች አንዷ ብሌን ዮሴፍ በውውድሩ የአብላጫ ድምፅ መንገድ እንደሚከተሉ ትናገራለች፡፡ አንድ ዳኛ ክፍተቶችን ሲናገር ሌሎቹ ደግሞ የታዩዋቸን በጎ ጎኖች ይገልጻሉ፡፡ ከጎልያድ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ የምትጋራው ዳኞች በመጀመርያው ዙር ለስለስ ማለታቸውን በሚመለከት ነው፡፡ ዳኞች ሚዛናዊ ፍርድ ቢያስተላልፉም እንኳን ከወቀሳ አይድኑም፡፡ የሚሰጡት ውሳኔ ሙያዊ ሳይሆን ግላዊ የሚመስላቸውም አሉ፡፡
እሷ እንደምትለው፣ ለአንድ ውድድር ዳኞች ሲመረጡ በሙያዊ ብቃታቸው መሆን አለበት፡፡ ውድድሮች አዳዲስ ባለሙያዎች የሚፈጠሩባቸው በመሆናቸው ወንበሩ የሚሰጠው ባለሙያ ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡ በአንድ ሙያ የሚታወቁ ሰዎች ታዋቂ ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደ ዳኛ ተመዝነው መምጣት አለባቸው የምትለው ብሌን፣ ‹‹ዳኞች የሚመረጡት ውድድርን እንዲያሳምሩ ሳይሆን ለውጥ ማምጣት የሚችሉና ተፅዕኖአቸው የሚታይ መሆን አለባቸው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡