Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርትሴካፋ ያጎላው የእግር ኳሱ ችግር

  ሴካፋ ያጎላው የእግር ኳሱ ችግር

  ቀን:

  38ኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) የእግር ኳስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ወደ ሩብ ፍጻሜ የገቡት ስምንት ቡድኖችም ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያከናወኑት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ጨዋታዎቹ በሐዋሳ ስታዲየም እንዲጠናቀቁ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑም ተነግሯል፡፡ ወትሮም ቢሆን ብዙ ትኩረት እንደማያገኝ በሚነገርለት ውድድር፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአካባቢው አገሮች አንፃር ያስመዘገበችው ስኬት ያን ያህል በመሆኑና በሌሎች ዓለም አቀፍ ማጣሪያዎች ላይ በሚያደርሰው ጫና የተነሳ ብዙ ትኩረት አላገኘም፡፡ ለዚህ ደግሞ የዞኑን እግር ኳስ የሚመራው ሴካፋ ችግሩን በደንብ ተረድቶ ሻምፒዮናው በተመልካች ዘንድ አርኪና ሳቢ ሆኖ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅበታል የሚሉ አስተያየቶች ይደመጣሉ፡፡

  ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ባዘጋጀችውም ሆነ አሁን እያዘጋጀችው ባለው የሴካፋ ሻምፒዮና እግር ኳስ ውድደሩ ተመልካቾች ጨዋታዎችን በስታዲየም ተገኝተው ከመመልከት ባሻገር እርስ በእርሳቸው ውይይት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል፡፡ ዘንድሮ ውድድሩ በአጋጣሚም ሆነ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ሲቀጥል ልዩ ያደረጉት ምክንያቶች ናቸው ከተባሉት የአዲሶቹ ስታዲየሞ መከፈትና የክልል ተመልካቾች ለውድድሩ የሰጡት ድምቀት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አብዛኛው የእግር ኳስ ቤተሰብ በብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ አቋም ላይ ያለው ስሜት የተቀዛቀዘ መሆኑና ይህም በተለይ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑን ወቅታዊ አቋምና ብቃት ተከታትሎ ጥንካሬውንም ሆነ ድክመቱን የመገምገምም ሆነ የማስገምገም ኃላፊነት የተሰጠው ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ትኩረት የነፈገው ጉዳይ መሆኑ የእግር ኳስ አፍቃሪ ቤተሰቡንም ሆነ በአንድም ሆነ በሌላ የሚመለከታቸውን አካላት እያነጋገረ ይገኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ከተረከቡት በኋላ ቡድኑ አሁን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የሴካፋ እግር ኳስ ሻምፒዮናን ሳይጨምር ተደራራቢ ጨዋታችን ማለትም እ.ኤ.አ. ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ ለሩሲያው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንዲሁም ለአፍሪካ አገሮች (ቻን) ማጣሪያ ጨዋታና ለአቋም ማጠናከሪያ ተብሎ የተረጉትን የወዳጅነት ጨዋታዎች ጨምሮ ከአሥራ አንድ በላይ ግጥሚያዎችን አድርጓል፡፡

  ይህ ሁሉ ሲሆን የቡድኑን ወቅታዊ ብቃትና አቋም የመገምገምና የማስገምገም ኃላፊነት ያለበት በፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ የሚመራ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ዝምታን መምረጡ የሚተቹ አሉ፡፡ የአገሪቱን እግር ኳስ የሦስት አሠርታት የተሳትፎ እንቆቅልሽ ‹‹የፈቱ›› ተብሎ የሚወሰዱት የአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን የነበረውን ጠንካራና ደካማ ጎን አስመልክቶ፣ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴና ባለድርሻ አካላት መድረኮችን እየፈጠሩ ይገመግሙ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው አሠራር በባሪያቶና ዮሐንስ የዝግጅት ወቅት የለም፡፡ ከአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቀጥሎ ብሔራዊ ቡድኑን ተረክበው ሲያሠለጥኑ የነበሩት ፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ በሥራ ላይ በነበሩበት ወቅት፣ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴውን የሥራ ድርሻና ከእሳቸው ጋር የነበረው የሥራ ግንኙነትን አስመልክቶ ሁሌም ይተቹ እንደነበርና ችግሩ ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንላቸውም፣ ነገር ግን የብሔራዊ ቡድኑን ወቅታዊ ብቃትና አቋም የመገምገም፣ ክፍተቶችን የማመላከት ድርሻ የተሰጠው ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ በብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ ቀርቶ የግል ውይይት እንኳ ለማድረግ ዕድል ሳይሰጣቸው ለወራት የቆዩበት አጋጣሚ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

   እሳቸውን ተክተው ብሔራዊ ቡድኑን እያሠለጠኑ የሚገኙት ዮሐንስ ሳሕሌም በተመሳሳይ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል እንደማይደረግላቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አሠልጣኙ እንደ ማሪያኖ ባሬቶ ሁሉ ስለ ብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ አቋምና ብቃት ባለድርሻ አካላት በተካተቱበት መድረክ ተፈጥሮ ለግምገማ የተቀመጡበት ጊዜ የሌለ መሆኑን ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እየተከናወነ በሚገኘው የሴካፋ እግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መውረድ እየተስተዋለበት መሆኑ በሚዲያው አማካይነት ተመልካቹ እየተናገረ ይገኛል፡፡ ችግሩ ምን እንደሆነ ሊታወቅ እንደሚገባ ጭምር ጠንካራ ትችቶች እየተሰሙ ነው፡፡

  አሠልጣኝ ዮሐንስ ለቡድናቸው የአቋም መውረድ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ማድረግና የልምድ ማነስ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ አሠልጣኙ ከሆነ ይህ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው የምሥራቅ መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ዋንጫ፣ ኢትዮጵያ ዋናውን ቡድን ሊመግቡ የሚችሉ ወጣትና ተተኪ ተጨዋቾች ልምድ ያገኙ ዘንድ ሁለተኛ ቡድን አዘጋጅታ በሻምፒዮናው ብትሳተፍ በተለይ ለወጣቶቹ ጥሩ አጋጣሚ ሊፈጥርላቸው የሚችል መሆኑን ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ አቅርበው እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ በፌዴሬሽኑ በኩል ግን ይኼ ያልሆነበት ምክንያት በግልጽ የተነገረ ነገር የለም፡፡

  አሠልጣኙ በቡድናቸው ካካተቷቸው ተጨዋቾች አንድ ወይም ሁለት ካልሆኑ ብዙዎቹ አዳዲሶችና በእንደዚህ ዓይነት ተደራራቢ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ልምድ የሌላቸው ናቸው፡፡ ከነዚህ ተጨዋቾች አንዱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ ተስፋ ቡድኑን የተጠራው ቢኒያም በላይ ሲሆን፣ ተጨዋቹ በብሔራዊ ቡድን የቋሚ አሰላለፍ ሚናውን እየተወጣ ቢገኝም፣ በክለቡ ግን ለተስፋው ቡድን ካልሆነ ለዋናው ቡድን እንዲጫወት ዕድል እንዳልተሰጠው ነው እየተነገረ የሚገኘው፡፡ ክለቡ ተጨዋቹ ለዋናው ቡድን መጫወት እንዲችል በ‹‹ቢጫ ካርድ አስመዝግቤዋለሁ›› ይላል፡፡ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ ለተጨዋቾች ዝውውር ከፍተኛ በጀት ከመደቡ ክለቦች አንዱና የመጀመርያው እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ የአገሪቱ ክለቦች ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ ወጣት ተጨዋቾች ለማግኘት ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ይልቅ ዕድሜያቸውን ሙሉ ከክለብ ወደ ክለብ በመዘዋወር አንቱ ለተባሉ ተጨዋቾች ትኩረት እንደሚሰጡ ነው የሚሰማው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች በተለይ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አማካይነት የተቋቋሙ ክለቦች ግባቸው ሊሆን የሚገባው፣ ማኅበራዊ ግዴታዎቻቸውን መወጣት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሲታይ ስንቶቹ ለዚህ ተቋማዊ ተልዕኮ ዕውን መሆን እየሠሩ ናቸው? የሚለው አግባብ ባለው የሚመለከተው አካል ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያስፈልግ ጭምር ነው የሚናገሩት፡፡

  የብሔራዊ ቡድኑ የሰሞኑ አቋም ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ የቡድኑ ተጨዋቾች ከበረኛ እስከ አጥቂ ያሉባቸው ክፍተቶች አንድ በአንድ እየተጠቀሱ ትችቶችና ወቀሳዎችን እያስተናገደም ነው፡፡ ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች የሐዋሳ ከተማው ኤልያስ ቸርነት ይጠቀሳል፡፡ እንደ ኤልያስ ከሆነ፣ ‹‹በአገሪቱ በከፍተኛው የፕሪሚየር ሊግ ደረጃ የሚጫወቱት ክለቦች 14 ናቸው፡፡ ከነዚህ ክለቦች አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዳማ ከነማና ሐዋሳ ከነማ የመሳሰሉ የቡድናቸው ቋሚ በረኞች የውጪ ዜጎች ናቸው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ በሁሉም ክለቦች ከተከላካይ እስከ ፊት አጥቂ የወሳኝነት ሚና ያላቸው ተጨዋቾች በተመሳሳይ የውጭ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ እየተሳተፈ የሚገኘው ሲዳማ ቡናው የፊት አጥቂው ኡጋንዳዊው ኤሪክ ሙራንዳ ከ13 ዓመት በፊት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቷል፡፡ በአቋም መውረድ ምክንያት እንዲሰናበት መደረጉም ይታወቃል፡፡ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ድጋሚ ተመልሶ ለሲዳማ ቡና ፈርሞ በ2007 የውድድር ዓመት ከኮከብ ግብ አስቆጣሪ ተጨዋቾች አንዱ ሆኖ አጠናቋል፡፡ የውድድር ዓመቱ ከኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ተሻላሚ የሆነው የደደቢቱ ናይጄሪያዊ ሳሙኤል ሳኑሚ ነው፡፡ ኮከብ ጎል ጠባቂ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሮበርት አዱንካራ ነው፤›› በማለት በአገሪቱ ያለው የእግር ኳስ እንቅስቃሴና ሥርዓቱን በመተቸት ትዝብቱን ይናገራል፡፡

  ብሔራዊ ቡድን የክለቦች ግብዓት እንጂ ራሱን ችሎ ብቻውን የሚቆም እንዳልሆነ የሚናገረው ኤልያስ፣ እራሱን ጨምሮ ስለአገሪቱ እግር ኳስ ‹‹ተቆርቋሪ ነኝ›› የሚል አካል በአጠቃላይ የእግር ኳሱ አደረጃጀቶች ከታች ከመሠረቱ ጀምሮ ክለቦች፣ የክልል ፌዴሬሽኖች፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና መንግሥት ስፖርቱን በበላይነት እንዲመራ ያስቀመጣቸው አካሎች ጭምር በችግሩ ዙሪያ መነጋገርና የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባቸው ጭምር ያስረዳል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img