Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ትኩረት ለመንገድ ትኩረት ለትራፊክ ደኅንነት

በአማን ዘበአማን

በአገሪቱ የሚደርሱ የመንገድና የትራፊክ አደጋዎች በየዓመቱ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያደርሱ እንደነበር እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ሲጠቀስ ሰምተናል፡፡ ከሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ባሻገር በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ ፍጅትም እየጨመረ መጥቷል፡፡

የመንገዶች ዘመናዊነት እያደገ፣ ስፋትና ርዝመታቸውን እየጨመረ ይገኛል፡፡ አሮጌ ለመባል ከበቃው ቀለበት መንገድ ወዲህ የጎተራ ማሳለጫ ለአገሪቱ መንገዶች ዘመናዊነት ሲጠቀሱ ከማይዘነጋው መካከል ይመደባል፡፡ የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድም ከቅርብ ወዲህ የተጨመረውና አስደማሚው ዘመናዊ መንገድ ሆኗል፡፡ ሌሎችም የማሳለጫና በአንድ ጊዜ በሁለት አቅጣጫ በርካታ ተሽከርካሪ የሚያስተናግዱ የከተማ መንገዶች ተስፋፍተው ተዘርግተዋል፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁሉም ዓይነት መንገዶች ርዝመት ከ110 ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ ሆኗል፡፡ እሰየው ያሰኛል፡፡

ከመኪና መንገዶች በተጨማሪም ለከተማና ለአገር አቋራጭ የተገነቡ የባቡር ሐዲዶች ሌሎቹ የመንገድ ገጽታዎች ናቸው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱ እየተስፋፋ፣ ከመኪና አልፎ ባቡርን ሲያመጣ ግን ከሥጋት በላይ ሥጋትንም እየጨመረ እንደመጣ ልብ የተባለ አልመሰለም፡፡ እርግጥ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው አሠራሮች ተዘርግተዋል፡፡ የከተማው ባቡር መሐል ለመሐል በተነጠፈለት ሐዲድ፣ አጥሩን አስከብሮ ሲሻው በሜዳ፣ ሲሻው በድልድይ ሲለውም በዋሻ እያሳበረ ይጓዛል፡፡ በከተማው ባቡር ሳቢያ የተከሰተ አደጋ እስካሁን አልሰማንም፡፡ አላየንም፡፡ ወደፊትም እንዳናይ ምኞታችን ነው፡፡

ነገር ግን ባቡሩን ተጎራብተው የሚጓዙት፣ ግራና ቀኝ የሚግተለተሉት መኪኖች የደኅንነት ቀበኞች ሆነዋል፡፡ ለሰውም፣ ለራሳቸውም፣ ለአካባቢም ሰላም ሲነሱ የከረሙት ተሽከርካሪዎች፣ ባቡሩንም መፈታተን ጀምረዋል፡፡ አጥር ጥሰው፣ ሐዲድ ተረማምደው የባቡሩን መንገድ ሲያበላሹ እያየን ወቸ ጉድ ብለናል፡፡

ከመነሻውም አቤት ሲባልበት የነበረው ይህ የአደጋ ሥጋት የሚያቆም አልመሰለም፡፡ በየጊዜው አጥር ገጭተው፣ እየተምዘገዘጉ ባቡሩ ድንበር ላይ የሚጋደሙትን መኪኖች ያየ የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ባቡሩ እንኳ ባያደርስ መኪኖች እደረሱበት የከፋ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ ሕዝቡ ያደረበትን ሥጋት በተደጋጋሚ ሲያስተጋባ ሰንብቷል፡፡ በየማኅበራዊ ድረ ገጹም አሳስቧል፡፡ አደጋው ግን ቀጥሏል፡፡ የመንግሥት ዝምታ ግን አስገራሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሌላው ቢቀር ዕዳው ያልተከፈለና 475 ሚሊዮን ዶላር የወጣበት የከተማው ባቡር ትራንስፖርት፣ ወረቱና አዲስነቱ ገና ተነግሮ ሳያበቃ የአደጋ ሥጋት ቀለበት ውስጥ ወድቆ መታየቱ ከግርምት በላይ ይመስለኛል፡፡ በተሽከርካሪዎች ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ምንም ዓይነት ማምለጫ እንደሌለው ሲታይም አስደንጋጭም፣ አስፈሪም ያደርገዋል፡፡

በሌላው ዓለም የከተማ ባቡር፣ ከአውቶቡስ፣ ከፈጣን አውቶቡስ፣ ከተሽከርካሪዎችና ከእግረኞች ጋር መሳ ለመሳ ሲጓዝ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሕዝቡም ተሽከርካሪውም ስልጡን ነውና ይህ ነው የሚባል አስከፊ አደጋ በመኪኖች ምክንያት ሲደርስ አይደመጥም፡፡ አጥር ሳይኖራቸው አስፓልት መንገድ ላይ በተነጠፈላቸው ሐዲድ የሚጓዙት ባቡሮች ከመኪና የሚደርስባቸው ግጭትና አደጋ ስለመኖሩ ብዙም አንሰማም፡፡ በእኛ አገር ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ሁሌም የአደጋ ሥጋት እንዳንዣበበ ይታያል፡፡

ኮንቴይነር እንደጫኑ፣ በፍጥነት እንደጋለቡ፣ አጥር ጥሰው ሐዲድ ላይ የሚጋደሙ መኪኖችን እየተበራከቱ ከመጡ ማን ነው ግድ የሚለው ብለን ከመጠየቃችንም ባሻገር፣ ወደፊትስ ይህ ክስተት ቢያንስ እንዲቀንስ ለማድረግ የሚወሰደው ዕርምጃ ምን እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑ ይብሱን አስገራሚ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር አስቀድሞ አስቦ ቢቻል ከአደጋ ንክኪ ነጻ ማድረግ፣ ካልሆነም የሕዝቡ ንቃትና እንደባቡር ላለው ትራንስፖርት ያለው ቅብርብ እስኪዳብር ድረስ አደጋ የሚያስቀሩ፣ የሚቀንሱና ሲደርስም ያለጉዳት በቁጥጥር ሥር እንዲሆን የሚያስችሉ አሠራሮች ካልተዘረጉ፣ ዛሬ ብርቅና ድንቅ የሆነብን ባቡር ዓይናችን እያየ ሰው የሚማገድበት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

ሐዲዱን፣ የባቡሩን ፉርጎዎች፣ የኤሌክትሪክ መስመሩንና ሌላውን ለመዘርጋት ስንት መጠበብና መመራመር እንዳስፈለገ ሁሉ ለአደጋ መንስዔዎች እንዲህ ያለው ነገር ቸል መባሉ ከቶ ለምን ሲባል እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለምና ሕዝብም ለራሱ ሲል አደጋን የሚያስቀር ሥርዓትን ምርጫው ያድርግ፤ ይጠንቀቅ፡፡ መንግሥትም በሕዝብ ላብ፣ በሕዝብ ገንዘብ የሚገነባውን መሠረተ ልማት እንዲህ ካለው አላስፈላጊ ጥፋትና አደጋ ይታደግ፡፡

መሠረታዊ የአደጋ መከላከያ ሥርዓቶች በዘመናዊ መንገድ ለሕዝብ በሰፊው መዳረስ እንዲችሉ፣ ጥንቃቄ ባህል እንዲሆን፣ ጠንቃቃነት መሠልጠን መሆኑ የሁሉም ግንዛቤ እስኪሆን ድረስ ማስተማርና ማሳወቅ የመንግሥት ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም አደጋን ከነጭራሹ ማስቀረት አይቻለንምና አላስፈላጊ ጥፋትና ውድመት እንዳይከሰት እያንዳንዱ መንገደኛ፣ ተሳፋሪ፣ አሽከርካሪ የመንገድ ሥርዓቶችን በጥንቃቄ ያክብር፡፡ ያስተግብር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት