መንግሥት በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ትሆናለች በማለት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግሥታት የንግድና የልማት ጉባዔ ገለጸ፡፡
ተቋሙ የዘንድሮውን ያላደጉ አገሮች ዓመታዊ ሪፖርት፣ ‹‹ትራንስፎርሚንግ ሩራል ኢኮኖሚስ›› በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ የአፍሪካ ዲቪዥን፣ ያላደጉ አገሮችና የልዩ ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ዶ/ር ታፈረ ተስፋቸው እንዳሳሰቡት በመካከለኛ ገቢ ደረጃ የሚገኙ በርካታ አገሮች የሚገኙበት ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ከመሆኑም ባሻገር ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ሲገባ የሚታጡ አገራዊ ጥቅሞችም ታሳቢ ሊደረጉ ይገባል፡፡
እንደ ዶ/ር ተስፋቸው ማብራሪያ አገሮች ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ሲያድጉ ከዚህ ቀደም በዝቅተኛ ዕድገት ደረጃ ላይ በሚገኙበት ወቅት ያገኙ የነበረውን ጥቅም ያጣሉ፡፡ ኢኮኖሚያቸው ያላደገ በመሆኑ ሳቢያ ከሚያገኟቸው ጠቀሜታዎች መካከል ከታሪፍና ከኮታ ነጻ ልዩ የገበያ ዕድል፣ ልዩ የአካባቢ ተፅዕኖ ድጋፍ፣ ልዩ ዕርዳታዎችና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ በሚገቡበት ጊዜ እንዲህ ያሉትን ድጋፎችና ነጻ የገበያ ዕድሎችን የሚያጡ በመሆኑ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ዶ/ር ታፈረ አሳስበዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ያላደጉ አገሮች ወደ መካከኛ ገቢ ተርታ በሚገቡበት ወቅት የሚጋረጥባቸው ፈተናንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሚድል ኢንካም ትራፕ›› እየተባለ የሚጠራው (መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች የሚወድቁበት መወጥመድ ሊባል ይችላል) ዋናው መሰናክል ነው፡፡ ይህ ችግር ኢትዮጵያን ሊያጋጥማት እንደሚችል ዶ/ር ተስፋቸው አስታውሰዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በመካከለኛ ገቢ ደረጃ የሚፈረጁ አገሮች የሚወድቁበት ወጥመድ ንድፈ ሐሳባዊ ትንታኔ ሲሆን፣ ይህም አንድ አገር ለኢኮኖሚያዊ ልማቱ ሲያገኝ ከነበረው ድጋፍና ማበረታቻ አኳያ ገቢው በመጨመሩ ቢያድግም፣ የተወሰነ እርከን ላይ ከደረሰ በኋላ ግን ከዚያ በላይ ማደግ ተስኖት የሚቀርበትን ሒደት የሚያመላክት አገላለጽ ‹‹ሚድል ኢንካም ትራፕ›› ይባላል፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ ያደጉ አገሮች በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ከሚቸገሩባቸው ምክንያቶች መካከልም የሠራተኞች የደመወዝ መጠን እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተያያዥነት እንደሚኖረው መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ የማያበቃው ተፅዕኖ ወደ መካከለኛው ተርታ የመጡትን አገሮች ካደጉትና ከበለጸጉት አገሮች ጋር መወዳደር እንዳይችሉ የሚያደረግበት ደረጃ ላይ ስለሚያደርሳቸውም ተጎጂነታቸውን እንደሚያባብሰው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
እንዲህ ያሉ ተፅዕኖችን ለመሸሽ ብቻም ሳይሆን ከዓለም ነጻ ገበያ ያላቸውን ተጠቃሚነትና የሚያገኟቸውን ልዩ ድጋፎች ላለማጣት አገሮች ካላደጉ አገሮች ተርታ መውጣት ባይፈልጉም ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ የመጡ አገሮች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ ዶ/ር ታፈረ አስታውቀዋል፡፡
በአንፃሩ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመሆን ቆርጣ መነሳቷን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ባሻገር በዚህ ደረጃ መሰለፍ ከተረጂነት መላቀቅ መሆኑን የመንግሥት ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ እንደ ዶ/ር ታፈረ ማብራሪያ፣ ወደ መካከለኛው ገቢ ተርታ ለመግባትም ሆነ ከዚህ ምድብ ወደ ታች ለመውረድ ሦስት መሠረታዊ መሥፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ የአገሮች ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ፣ ሰብዓዊ ሀብቶችና ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነቶች ታሳቢ ይደረጋሉ፡፡
በመሆኑም አንድ አገር ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማደግ የነፍስ ወከፍ ብሔራዊ ገቢው 1,242 ዶላር መድረስ አለበት፡፡ ከመካከለኛ ገቢ ወደ ዝቅተኛ ገቢ ለመውረድ የሚያበቃው የነፍስ ወከፍ ገቢ መጠን ደግሞ 1,035 መሆኑን የተቋሙ ትንታኔ ይጠቁማል፡፡ በሁለተኛው መሥፈረት ሥር የሚገኙት ሰብዓዊ ሀብቶች ተብለው የሚጠቀሱት ሲሆኑ፣ ከአጠቃላዩ ሕዝብ ውስጥ የተመጣጠነና የሥነ ምግብ ይዘቱ የተሟላ ምግብ የሚያገኘው ሕዝብ ቁጥር ሬሾ፣ የሕፃናት ሞት መጠን፣ ጥቅል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቅበላና ጥመርታ መጠን እንዲሁም የጎልማሶች የትምህርት ደረጃ ይጠቀሳሉ፡፡ በሦስተኛ መሥፈርትነት የተቀመጡት ኢኮኖሚያዊ ተጋላጭነትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህም ያልተረጋጋ የግብርና ምርት፣ ያልተረጋጋ የወጪ ንግድና ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ይዘት ያላቸው ችግሮች ወደ መካከለኛ ገቢ ተርታ ለማደግም ሆነ ከዚያ ክልል ለመውረድ የሚያበቁ ናቸው፡፡ ከሦስቱ መሥፈርቶች ሁለቱን በአግባቡ በአወንታዊነት የሚያሟሉ አገሮች ወደ መካከለኛ ገቢ ማደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሦስቱ ሁለቱን የማሳካት አፋፍ ላይ እንደምትገኝ ዶ/ር ታፈረ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ 48 አገሮች ባላደጉት ተርታ ተመድበው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 34ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ቢሆኑም እ.ኤ.አ. በ1978 ከአፍሪካ ያላደጉ አገሮች ተብለው የተመደቡ አገሮች ስድስት ብቻ እንደነበሩና በጠቅላላው በዓለም የነበሩት አገሮችም 25 ብቻ እንደነበሩ ምሁሩ አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና ከአሥር ዓመት በፊት በቱርክ የመከሩት ያደጉና በማደግ ላይ የሚገኙ አገሮች፣ ከ48 ያላደጉ አገሮች ውስጥ ግማሹ እ.ኤ.አ. በ2020 ወደ መካከለኛ ገቢ ተርታ እንዲገቡ ለማድረግ ድጋፍና እግዛ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው እንደነበርም ዶ/ር ታፈረ አስታውሰዋል፡፡