Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ሌብነት የለመደ በአንድ ሳምንት ውስጥ ቴሌቪዥን ላይ ወጥተን ስለጮህን እጁን ይሰበስባል ማለት አይደለም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሐሙስ ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ዘካሪያስ ስንታየሁና አሥራት ስዩም ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ቆይታ አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ዓይነት ቆይታ ከግል የኅትመት ሚዲያ ጋር ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸውም ወቅታዊ በሆኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በቅርቡ ከተከሰተው ድርቅ አንስቶ ስለመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ እንዲሁም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ልዩ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

  • ፡- ከኤልኒኖ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ድርቅ መከሰቱ ይታወቃል፡፡ እስካሁን ድረስ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 8.2 ሚሊዮን መድረሱን መንግሥት አስታውቆ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች የተረጂዎቹ ቁጥር 15 ሚሊዮን እንደሚደርስ እየተናገሩ ነው፡፡ በተጓዳኝ ደግሞ ከለጋሾች የሚጠበቀው ዕርዳታ በተጠበቀው መጠን እየተገኘ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ መንግሥት ጉዳዩን እንዴት ለመወጣት አስቧል? የሚታጠፉ የመንግሥት ፕሮጀክቶች አሉ ብለዋል፡፡ የትኞቹ ናቸው? የአገሪቱ የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ምን ይመስላል? በተለይ ከዚህ ድርቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ተጎጂዎች ዕርዳታው በአግባቡ እየደረሳቸው አለመሆኑን ነው፡፡ እኛም በቦታ ላይ ተገኝተን ይህን መታዘብ ችለናል፡፡ ስለዚህ በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን የመርዳቱ ሒደት ቅንጅት የጎደለው ነው ይባላል? እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- ቅድሚያ በዚህ ጠቃሚ በሆነ አገራዊ ጉዳይ ላይ ጥያቄ በመነሳቱ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የኢልኒኖ ክስተት እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እንደ አገር የምትቆጣጠረው ክስተት አይደለም፡፡ ክስተቱ የተፈጠረው ያደጉ አገሮች ኃላፊነት በጐደለው መንገድ የግሪን ሃውስ ጋዝ በአየሩ ውስጥ በማሠራጨታቸው ምክንያት ነው፡፡ ይህ ለዘመናት የተጠራቀመ ችግር ነው፡፡ ኤልኒኖ የተፈጠረው በአየር ንብረት መዛባት ነው፡፡ መነሻውም ውቅያኖሶቹ በሚሞቁበት ጊዜ በተለምዶ ሊዘንብ የነበረው ዝናብ እንዳይዘንብ የሚያደርግና ከዚያ የሚነሳው ግፊት ባለመኖሩ ምክንያት የተፈጠረ ነው፡፡ ይሄ ሳይንሳዊ ሁኔታ መፈጠሩ ከአቅማችን ወይም ከቁጥጥራችን ውጪ ነው፡፡ በእኛ በኩል ማድረግ የሚቻለው ነገር እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያ በተለያዩ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ስታከማች የመጣችውን ጉልበትና አቅም ተጠቅመንና በተጨማሪም ሌላ ድጋፍ በማድረግ ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይቀየርና ሕፃናት፣ አጥቢና እርጉዝ እናቶች እንዳይጐዱ ማድረግ ነው፡፡ በተቻለ መጠንም እንስሳት እንዳይጐዱ ማድረግ ነው፡፡ በእኛ ኃላፊነት ላይ የወደቀው ይህ የመከላከል ሥራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት ይሄ ክስተት መኖሩ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ሥራ ሲሠራ ነበር የቆየው፤ ማንንም አልጠበቀም፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነ እናምናለን፡፡ እስከዛሬም ድረስ በአገራችን ሕዝቦች ላይ በሕፃናት፣ በእናቶችም ሆነ በመላው ኅብረተሰብ ላይ የሞትና የረሃብ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡

  እስከዛሬም ድረስ የተሳካ ሥራ ሠርተናል ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ ጉዳይ በጣም ስሱ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የዕርዳታ እህል ባይደረስ ኖሮ፣ ይሄ ሕዝብ ለሳምንት እንኳን ያህል መቆየት እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የዕርዳታ እህል እየደረሳቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ስፋት ድርቅ ተከስቶ አያውቅም፡፡ ይሄ ድርቅ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከሰተው ድርቅ ሰፋ ያለ ነው፡፡ የሸፈነው አካባቢም በጣም ሰፊ ነው፤ ስለዚህ ጉዳዩ የቁጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ማንም የማይቆጣጠረው ሰፊ አካባቢ በድርቁ ተጠቅቷል፡፡

  በአብዛኛው በምሥራቁ የአገራችን ክፍልና በደቡብም ሰፊ ክልል በድርቁ ተጠቅቷል፡፡ ስለዚህ ቁጥሩ ምን ይሁን ምን በሒደት የሚወሰን ነው፡፡ አሥራ አምስት ሚሊዮንም ሊሆን ይችላል፤ ሃያ ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ብዙ ትኩረት የምንሰጠው ቁጥሩ ላይ አይደለም፡፡ ዋናው ግን እኛ እያደረግን ያለነው እያንዳንዱ ቤተሰብ ምን ደረጃ ላይ ነው? የሚለው ላይ ነው፡፡ ስለዚህ የአገራችን ዕድገት አንዱ ውጤት ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራማችን፣ የግብርና ሙያተኞችና በየቀበሌው ያሉ ሙያተኞቻችንም የአርሶ አደር አመራሮችም በየቤቱ የመለየት አቅም ነበራቸው፡፡ በመሆኑም ችግሩ በየአካባቢው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሲጨምርም ጨመረ ብለን እንነግራለን፡፡ ምንም የሚደበቅ ነገር የለውም፡፡ አንዳንዶች መንግሥት ቁጥር ቀንሶ እናያለን ብለው በጣም ጓጉተዋል፡፡ እኛ ቁጥር የምንቀንስበት ምክንያት የለም፡፡ ዋናው የተጐዳው ሰው ምን ያህል ነው? እስካሁን ድረስ በተሠራው ጥናት መሠረት 8.2 ሚሊዮን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በቅርቡ ደግሞ የመኸር ግምገማ ተካሂዷል፡፡ ውጤቱ ሲመጣ 12 ሚሊዮን ወይም 10 ሚሊዮን ወይም 15 ሚሊዮን ሊሆን ይችላል፡፡ የትኛውም ቁጥር ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር በድርቁ የተጐዳው የኅብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ ምን ያህል ነው የሚለውን ማወቅና፣ ለእሱም ዝግጁ መሆን ነው ከእኛ የሚጠበቀው፡፡ በመሆኑም የግምገማውን ውጤት በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ግምገማ መንግሥት ብቻውን የሠራው ሳይሆን፣ መልቲ ኤጀንሲ ቲም የሚባልና ከተለያዩ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር አንድ ላይ በመሆን የሚከናወን ነው፡፡

  እኛ ግን አስቀድመን ይሄ ግምገማ ከመሠራቱ በፊት መጥፎ ሁኔታ ቢፈጠር፣ ምን ያህል ቁጥር ሊኖር ይችላል በሚል ተዘጋጅተናል፡፡ መጀመሪያዎቹ አካባቢ ከውጭ ያስገባነው ወደ 250 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል ነበር፡፡ አሁን ግን ተጨማሪ 650 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እህል እንደገና አዘናል፡፡ ይህን ያደረግንበት ዋናው ምክንያት ግመታው ወይም ወደፊት ሊከሰት ይችላል ተብሎ በባለሙያዎች የተጠናው ጥናተ የሚያሳየው ቁጥሩ እየጨመረ ሊሄድ ስለሚችል፣ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል በሚል ነው፡፡ ወዳጆቻችን ቢደግፉን ደስ ይለናል፡፡ ባይደግፉንም ግን መንግሥት የመጀመሪያ ኃላፊነት የተጣለበት እንደመሆኑ መጠን፣ ዜጐቹ ምንም ዓይነት ረሃብ ሳይከሰትባቸው ይህንን ሒደት ማለፍ አለብን የሚል ጽኑ አቋም ይዘን እየሠራን እንገኛለን፡፡

  ሀብት ከየት ነው የምታገኙት መጠባበቂያ በጀት የተያዘው አንድ ቢሊዮን ብር ብቻ ነው ለተባለው፣ በመጀመሪያ ደረጃ ተጨማሪ በጀት በዓመቱ አጋማሽ አካባቢ ሁሌም እናውጃለን፡፡ በቅርቡ ለዚህ አደጋ ሊሆን የሚችል መጠባበቂያ በጀት በሕዝብ በተወካዮች ምክር ቤት አቅርበን ስለምናሳውጅ፣ ይሄ ጉዳይ ብዙ የሚያሳስብ አይሆንም፡፡ ፕሮጀክቶች እናጥፋለን ስንልም ዋና ዋና ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማለታችን አይደለም፡፡ አገራችንን ዋና ዋና ሜጋ ፕሮጀክቶችን የምትሠራው በመንግሥት በጀት አይደለም፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚሠሩት በብድር ገንዘብ ነው፤ ከዓለም አቀፍ ብድር ወይም ከአገር ውስጥ ብድር፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችን የሚያከናውኑ ተቋማት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የሚታጠፍ ፕሮጀክት አይኖርም፡፡

  ከመንግሥት በጀት የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ከምንላቸው የተወሰኑ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከመንገድ ፕሮጀክት የተወሰነውን ልናጥፍ እንችላለን፡፡ ሁኔታውን አይተን ማለት ነው፡፡ መጠባበቂያችን ምናልባት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ልናገኝ እንደምንችል ወይም ደግሞ ተጨማሪ በጀት ልናገኝ እንደምንችል እያየን ነው ያለነው፡፡ ከገቢ ትንበያው እንዲሁም ደግሞ ከሌሎች ምንጮች ይህንን ገንዘብ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ይሄ በቂ ካልሆነ በሒደት የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ በእኔ እምነት ግን የፕሮጀክቶች መታጠፍ ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ዋናው ግን ምንም ይሁን ምን ፕሮጀክት ብናጥፍ እንኳን ሕዝባችን አይራብም የሚለውን መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡      

  ሪፖርተር፡- ይህ ድርቅ ባለበት ወቅት ሰሞኑን ብአዴን 35ኛ ዓመቱን በተለያዩ ዝግጅት ሲያከብር ነበር፡፡ ለዚህም ዝግጅት በርካታ ገንዘብ ወጥቷል ተብሎ ይገመታል፡፡ አሁንም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለማክበር በዝግጅት ላይ ናችሁ፡፡ እንደሚታወሰው በንጉሡ ጊዜ በተከሰተው ድርቅ ንጉሡ ለልደታቸው ኬክ ያወጡት ወጪ ከፍተኛ ነበር ብለው ተተችተዋል፡፡ በተመሳሳይም ደርግ በአገሪቷ ውስጥ ድርቅ እያለ ለአብዮቱ 10ኛው ዓመት በዓል ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱ አስተችቶታል፡፡ መንግሥቶት ለእነዚህ በዓላት ያወጣውን ወጪ ከቀድሞው መንግሥታት በድርቅ ጊዜ ካወጡት ወጪ ጋ ተመሳሳይነት አለው በማለት የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ከሞራል አኳያም ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህ ምላሾት ምንድነው?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- በመጀመሪያ ደረጃ በዓሎቻችን እንደ ማንኛውም ሥራ አንድ የሥራ አካል ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በዓሎቻችን የፈንጠዝያና የዳንስ በዓላት አይደሉም፡፡ እንደምታውቁት ትልቁ የዚህ አገር ሀብት የሕዝብ አዕምሮ፣ የሕዝብ አስተሳሰብ፣ የሕዝብ አመለካከት መቅረጽ ነው፡፡ አመለካከቱና ተነሳሽነቱ ካለ ተራራ መናድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን የልደት በዓላት አይደሉም፡፡ የድሮ መንግሥታት የልደት በዓሎቻቸውን ነበር ሲያካሂዱ የነበሩት፤ የግለሰብ በዓሎች ነበሩ፡፡ ይሄ ግን የሕዝብ በዓል ነው፡፡ ይህን በዓል ስናከብብር ሕዝቡ የበለጠ ለልማት እንዲነሳሳ፣ የበለጠ ወደፊት እንዲገሰግስ፣ የበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር፣ የበለጠ ግንኙነቱን እንዲያሰፋ የሚያደርግ ነው፡፡ በአንድ በኩል በዓሎቻችን ሥራ ናቸው፡፡ አንድ ትልቅ ሥራ፣ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርባቸው ናቸው፡፡ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ሥራ አይደለም ተብሎ ከተወሰደ ይሄ ስህተት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አገሪቷ ያጣችው ነገር ቢኖር ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ዙሪያ ነው፡፡ የጋራ አስተሳሰብ በመያዝ ዙሪያ ያለ ጉድለት ነው፡፡ እናንተም የሚዲያ ተቋማት የምትለፉት የእናንተም ሥራ ላይሆን ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ አዕምሮ ነው የምትቀርጹት፡፡ የሕዝብ አዕምሮ መቅረጽ ሥራ አይደለም ከተባለ ትክክል አይደለም፡፡

  ሁለተኛው ለእነዚህ በዓላት የወጣው ወጪ ምንድን ነው? ለእነዚህ በዓላት ሕዝቡ እንደማንኛውም ጊዜ ከቤቱ መጥቶ በዓሉን ተካፍሎ ይሄዳል እንጂ እኛ ውስኪ አንራጭም፡፡ ቢበዛ ውኃ ነው የምንጠጣው፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን በጣም በትንሹ ወጪ የሚወጣባቸው ናቸው፡፡ ከድሮ ሥርዓቶች ጋር ሊወዳደር አይችልም፡፡ በዓሎቻችን የሕዝብ በዓላት ናቸው፡፡ እኛ ገንዘብ አናወጣም፤ ሕዝቡ ነው ከየቤቱ ወጥቶ ስብሰባ የምናካሂደው፡፡ ስብሰባ ለማካሄድ ወጪ አናወጣም፡፡ የብአዴን 35ኛ በዓል በየከተሞቹ ስብሰባ በማካሄድ ነው የተደረገው፡፡ በዚህ ስብሰባ ቢበዛ ሰው ትንሽ ውኃ ጠጥቶ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ ይሄን ያህል ወጪ አልወጣም፡፡

  በዓሎቻችን ወጪያቸው እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ሕዝቡ ራሱ የሚሳተፍበት እንጂ በመንግሥትም ሆነ በድርጅት ወጪ እየወጣ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የብአዴን አባሎች በሒደትም የኢሕአዴግ አባላት በሙሉ ከኪሳቸው አውጥተው ለዚህ ድርቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህ አኳያ ብአዴን 30 ሚሊዮን ብር ከአባላቱ መዋጮ አውጥቶ ለድርቅ ሰጥቷል፡፡ ማሳየት የፈለገው ምንድን ነው አባላት የበለጠ ያወጣሉ እንጂ ተጨማሪ ወጪ እያወጡ አይደለም፤ ለድርቅ የበለጠ እያዋጣን ነው የሚለውን ለሕዝቡ እያሳወቀ ነው፡፡

  የብሔር ብሔረሰቦችንም ቀን ስናከብር እኛ የምንጠቀምበት ያንን አካባቢ በተለይም ታዳጊ ክልሎች በሚሆኑበት ጊዜ ክልሎቹ ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅመው፣ ሌሎችም ደግፈዋቸው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እንዲገነቡ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሁኑን የጋምቤላን በዓል ብንወስድ የጋምቤላ ከተማ ውኃ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን የጋምቤላ ከተማ ውኃ ሙሉ በሙሉ ጥሩ የውኃ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ፕሮግራም ቀርጸን ተግባራዊ አድርገናል፡፡ የጋምቤላ ከተማ መንገዶች ብዙ አስፋልቶች አልነበሩም፤ ይህን በዓል መሠረት አድርገን አስፋልት መንገድ ሠርተናል፡፡ የጋምቤላ ስታዲዮምም በጣም ደካማ ነበር፤ በመሆኑም በዓሉን መሠረት አድርገን ጥሩ ስታዲዮም እንዲገነባ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን ዘላቂ ልማትንና የኅብረተሰብ የጋራ መግባቢያ መፍጠሪያ ናቸው፡፡ እነዚህ በዓሎች ብሔሮች፣ ብሔር ብሐረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው ባህላቸውን የሚለዋወጡበትና አንድነታቸውን የሚያጐለብቱባቸው ናቸው፡፡ ለእኛ የጋራ ኢኮኖሚያዊ፣ የጋራ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ መፍጠር ትልቅ ስለሆነ ነው በዓሉ የሚከበረው፡፡ ስለዚህ ትርጉሙም ትልቅ ነው፤ ወጪው ግን ትንሽ ነው፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን ከድርቅ ጋር ማገናኘት አያስፈልግም፡፡

  • ፡- በቅርቡ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በእርሶ መሪነት ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የተካሄደ ስብሰባ ተላልፎ ነበር፡፡ በስብሰባው ላይም የመልካም አስተዳደር ችግር አንገብጋቢ መሆኑ ተወስቷል፡፡ ምንም እንኳን በቲቪ በተላለፈው ፕሮግራም በርካቶች ቢደሰቱም፣ ችግሩ አሁን ድረስ በመኖሩ ውይይቱ ድራማ ነው እያሉ ይገኛሉ፡፡ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ስላለው የመልካም አስተዳደር ችግር ከእርስዎ መንግሥት ሕዝቡ ምን ይጠብቅ? የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ላይ በተለይ መሬት፣ ፍትሕ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ሎጂስቲክስ ከፍተኛ ችግር የሚታይባቸው ነው፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ላይ በታች ባሉ አስፈጻሚዎች ማን አለብኝነት ሰፋኗል፡፡ በተለይ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሚመረምራቸው ጉዳዮች አነስተኞች ናቸው፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት እያካሄደችው ባሉት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች እየተመረመሩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚፈጸሙ ሙስናዎችን ለመዋጋት ምን ዓይነት ስትራቴጂ ነድፋችኋል?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- በመጀመሪያ ደረጃ የመልካም አስተዳደር ችግር ጉዳይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ይስተካከላል ብሎ የሚያምን አካል ካለ፣ ይህ አስተሳሰብ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም የመልካም አስተዳደር ችግርን የመቅረፍ ጉዳይ በተከታታይ በሚከናወን ሥራ የሚቀረፍ እንጂ ባለፈው አንድ ወር አካባቢ የተደረገውን ስብሰባ መሠረት አድርጐ ችግሩ ተጠራርጐ ይጠፋል የሚል አስተሳሰብ ካለ፣ በመጀመሪያ በአስተሳሰብ መግባባት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ጉዳይ በሒደት እየተገነባ የሚሄድና አፈታቱም ቢሆን ኅብረተሰቡ ራሱ ተሳትፎበትና ባለቤት ሆኖበት የሚፈታ ጉዳይ እንጂ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለተሰበሰቡ ብቻ የሚፈታ አድርጐ መወሰድ የለበትም፡፡ እዚህ ጋ ሁለቱንም አመዛዝኖ ማየት ያስፈልጋል፡፡ በእኔ ንግግር ውስጥ የነበረው መንግሥት ቁርጠኛ መሆን አለበት፡፡ ኅብረተሰቡ ደግሞ ሙሉ አቅሙን በዚህ ጉዳይ ላይ ማሳረፍ አለበት፤ የመፍትሔው አካል መሆን አለበት፤ ይሄም በሌለበት ሁኔታ ሊከናወን አይችልም በሚል በግልጽ ተነጋግረናል፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ የመጀመሪያው የመንግሥት ቁረጠኝነት መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይሄ ድራማ አይደለም የመንግሥት ቁርጠኝነት ለሕዝቡ ማረጋገጥና ግልጽ ማድረግ ድራማ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሁለት መልኩ ነው የምንተቸው ማለት ነው፡፡ ግልጽ አድርገን የመንግሥትን አቋም ለመግለጽ ስንሞክር ድራማ ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ዝግ ናችሁ ይባላል፡፡ መሆን ያለበት እውነተኛ መሆን ነው የሚያስፈልገው፡፡ መጀመሪያ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ ማወቅና ማመን፤ ከዚያ በኋላ ለምን ችግሩ ተፈጠረ እንዲሁም ችግሩ ምንድን ነው ብሎ መንስዔውን መረዳትና ወደ መፍትሔው መሄድ ያስፈልጋል፡፡ እዚያ ላይ መታገልና መፍትሔውን ማምጣት ነው፡፡ ችግሩ በአንድ ሳምንት ውስጥ በስብከት የሚወገድ አይደለም፡፡ ሌብነት የለመደ በአንድ ሳምንት ውስጥ ቴሌቪዥን ላይ ወጥተን ስለጮህን እጁን ይሰበስባል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ሒደት ነው፤ ሒደቱንም ጠንካራ ሒደት አድርገን መቀጠል ነው ያለብን፡፡

  በመንግሥት በኩል ያላንዳች ጥርጥር ቁርጠኝነቱ አለ፡፡ ይህንን ቁርጠኝነት ከሕዝቡ ውስጥ ካለው ቁርጠኝነትና ተሳትፎ ጋር አመጋግቦ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በጥናት ላይ የተመሠረተ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ መግባባት ፈጥሯል፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ መግባባት መፍጠር ማለት ለእኔ የመፍትሔው 50 በመቶ ተሠራ ማለት ነው፡፡ ችግሮቹ ካልታወቁና መግባባት ላይ ካልተደረሰ መፍትሔው አይገኝም፡፡ የችግሩንም መንስዔ በእያንዳንዱ ዙሪያ ላይ ለይተናል፡፡

  ይህ ችግር በጥቅል ውይይት የሚፈታ ሳይሆን በእያንዳንዱ መንስዔ ተለይቷል፡፡ መንግሥትም መፍትሔ ያለውን አስቀምጧል፤ ይሄ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ ሕዝቡም የመፍትሔው አካል መሆን አለበት፡፡ በጥረት እበለጽጋለሁ የሚል አመለካከት በኅብረተሰቡ ውስጥ በሌለበት ሁኔታ፣ ምንድን ነው የሚፈጠረው የሚለው ጉዳይ መታየት አለበት፡፡ ይሄ ኅብረተሰባዊ ችግር ነው፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲባል ሕዝቡ በአስተሳሰቡ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? አሁን አብዛኛው ሰው የያዘው አስተሳሰብ በውድድር የሚያምን ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳት አለብን፡፡ አቋራጭ ቢገኝ ሁሉም ሰው ለመውሰድ ዝግጁ ነው የሚል ጥያቄ አንስተን መወያየት አለብን፤ መልሱንም መመለስ አለብን፡፡ ይሄ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት ባልተቀየረበት ሁኔታ መንግሥት የፈለገውን ያህል ቢጮህ፣ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ሕዝቡም የሚዲያ አካላትም መረዳት ያለባችሁ ይሄ አመራር ከኅብረተሰቡ የወጣ አመራር እንጂ ከሰማይ ዱብ ያለ አመራር አይደለም፡፡ የፈለቀው ከሕዝቡ ውስጥ ነው፤ በሕዝቡ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ ይዞ ነው የመጣው፡፡ ሕዝቡ ሙስና አያስፈልግም የሚል አመለካከት ሲኖረው፣ እዚህም ያለው አመራር ቀጥ ለጥ ብሎ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ብልሹ አሠራሮችን እያየ ምን አገባኝ ብሎ ዝም የሚል ከሆነ፣ እዚህ ያለው ይፋፋል፡፡ በአመራር ደረጃ የሚታየው ወይም በሲቪል ሰርቪሱ የሚታየው የስርቆት አመለካከት እየፋፋ ይሄዳል፡፡ ትግሉ አስተሳሰብ መቅረጽንም ጭምር የሚጠይቅ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

  ሜጋ ፕሮጀክቶችን አስመልክቶም፣ ፕሮጀክቱ ትልቅ ስለሆነ ወይም ትንሽ ስለሆነ አይደለም ሌብነት የሚከሰተው እንዲያውም ትልልቆቹ ፕሮጀክቶች ሁሉም ሰው ዓይን የጣለባቸው በመሆናቸው፣ የዓለም ባንክም ሆኑ ሌሎቹም እንዳጠኑት በእነሱ ዙሪያ ያለ ከፍተኛ ሙስና ይሄን ያህል የሚያሳስብ አይደለም፡፡ እዚህ አገር ላይ የሚያሳስበው መካከለኛውና አነስተኛ ሙስና ነው፡፡ ከፍተኛ ሙስና የለም ባይባልም፣ ይሄን ያህል የሚያሳስብ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ሙስና አለ የሚባል ከሆነ፣ ይህን ከማጣራት ወደኋላ አንልም፡፡ አሁን ሰውን እያስመረረ ያለው አገልግሎት ለማግኘት የሚሰጠው ጉቦ ነው፡፡     

  • ፡- ኢሕአዴግና አጋሮቹ በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ 100 በመቶ ቢያሸንፉም፣ ከምርጫውም በፊት ሆነ በኋላ የመልካም አስተዳደር ችግር ተባብሷል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ መቀመጫ አሽንፋችሁ እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ተቃርኖ ይፈጥራል፡፡ እስቲ ይኼን ነገር ያስታርቁት? ይህ ሁናቴ በዚሁ ይቀጥላል ብለው ያስባሉ? ሕዝቡ ከማላውቀው መላዕክት የማውቀው ሰይጣን ይሻለኛል በሚለው ብሂሉ የሚቀጥል ይመስልዎታል?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- የመልካም አስተዳደር ችግርን ከፋፍለን ማየት አለብን፡፡ ችግሩ በገጠርና በከተማ የተለያየ ነው፡፡ ትኩረታችንን እያደረግን ያለነው ዋናው ከከተማ መሬት ጋር በተያያዘ ነው፤ የገጠር መሬት እዚያም እዚህም ትንሽ ችግሮች እንዳሉበት እናውቃለን፡፡ ነገር ግን መሠረታዊ የሆነና ሕዝቡን የሚያበሳጭ ችግር አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው የከተማ መሬት ጉዳይ ወሳኝ ነው የምንለው፡፡ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋና ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ያለው፣ የከተማ መሬት ነው፡፡ ለዚህም ነው በዚህ ዙሪያ እናሻሽል ብለን ዘመናዊ አሠራር የጀመርነው፡፡

  በሁለተኛ ደረጃ ከማይታወቀው መላዕክት የሚታወቀው ሰይጣን ይሻላል ተብሏል የተባለው፣ እስከዛሬ ድረስ ኅብረተሰቡ ውስጥ ኢሕአዴግ የሚታወቅ ሰይጣን ተብሎ የሚፈረጅ ነው ብዬ በግሌ አላምንም፡፡ ምክያቱም ኢሕአዴግ ጉድለቱም ይታወቃል፤ ጥንካሬውም ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ ሳይመርጠን ሲቀር ጉድለታችንን አውቆ ነው፡፡ ሲመረጠንም ደግሞ ጥንካሬዎቻችንን አውቆ ነው፡፡ ስለዚህ በቅርቡም ከሕዝቡ ጋር በተደጋጋሚ ተወያይተናል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ማለት በሕዝቡ ውስጥ ኢሕአዴግ የሠራቸው ጥሩ የሚባሉ ሥራዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዓለም የመሰከረው ጥሩ ሥራዎች አሉት፡፡ ስለዚህ ከአንድ ደረጃ ተነስተን ወደ ጨለማ መሄድ የለብንም፡፡ ችግሩ አለ ሲባል በሚዛን ነው ማየት ያለብን፡፡ ለምሳሌ በትምህርት ዙሪያ ኢሕአዴግ በጣም ጥሩ ሥራ ሠርቷል፤ በዓለም ደረጃም የተመሰገነ ሥራ ሠርተናል፡፡ ግን እዚያው ላይ የትምህርት ጥራ አሳሳቢ ነው፤ ይህንንም ማስተካከል አለብን፡፡ ይሄን ለሕዝብ በግልጽ ተናግረን ነው የተመረጥነው፡፡ በተመሳሳይ በጤና ጉዳይ በተለይ በገጠሩ፣ አሁን ደግሞ በከተማ ጥሩ ሥራ ሠርተናል፡፡ ዓለም የመሰከረው ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንዲያውም ለአፍሪካ ምሳሌ ሆና የወጣችበት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ደርምሰን አይደለም የመልካም አስተዳደር ችግራችንን የምንቀርፈው፡፡ ያለበለዚያ ጨለማ ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ ሞራል ነው የምናጣው፡፡ ችግር የመፍታት አቅማችንም ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ሁሉንም በልኩ አስቀምጠን ነው መሄድ ያለብን ማለት ነው፡፡ ይሄ በልክ ማስቀመጥ ጥቅሙ ምንድን ነው፣ ማጋነን ሳይኖርበት ሲቀመጥ፣ ይሄ ጥሩ ነገር የጐደለውን ነገር ለመሙላት እንደ መስፈንጠሪያ ይሆናል፡፡

  ጥሩ ነገር ከሌለህና የምትረግጠው ከሌለ ግን መስፈንጠር አትችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ማለት በሁሉም መስክ ችግር አለ ማለት አይደለም፡፡ እኔ በግሌ የማምነው ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ መንግሥት የሠራቸው በርካታ ጥሩ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን እኛ በባህሪያችን ጥሩ ነገሮቹ ላይ ሳይሆን ማተኮር ያለብን ጉድለቶቻችን ላይ ነው፡፡ እነዚህ ጥሩ ጥሩ ነገሮቻችን ላይ ብዙ ሙገሳ ከበዛ፣ ጉድለቶቻችን ዝቅ ብለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ዝቅ ብለው ሲታዩ ደግሞ ይገድሉናል፡፡ በሒደት እየገዘፉ ይሄዱና የማይመለስ ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ጥሩ ነገሮቻችንን እዚያው አስቀምጠን ጉድለቶቻችን ላይ አተኩረን መጮህ አለብን፡፡

  በእነዚህ ላይ አጉልተን መወያየት አለብን፤ ችግሩን መፍታት አለብን የሚል አቅጣጫ የተያዘው ከዚሁ ተነሥቶ ነው፡፡ ስለሜጋ ፕሮጀክቶቻችን ማውራት ይቻላል፤ ስለጥሩ ነገራችን ማውራት ይቻላል፡፡ ይሄን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዋናው ቁልፍ ችግራችን የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፤ እሱን ለመፍታት መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ለሚቀጥለው ጊዜ ሕዝቡ ማንን ይመርጣል የሚለው ጉዳይ፣ እሱ የሕዝብ ፋንታ ነው፡፡ ዋናው ነገር አገሪቱ ወደፊት እንደትሄድ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ለምርጫ ብለን አይደለም አሁን የምንሠራው፡፡ ምክንያቱም ብንመረጥም ባንመረጥም፣ በተመረጥንበት በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ድኅነትን በሚፈለገው ደረጃ ወደታች ማውረድ አለብን፡፡ ሕዝባችን የተሻለ ኑሮ መኖር መጀመር አለበት፡፡ ዋናው የእኛ ጭንቀት የሕዝቡን ሕይወት የመቀየር ጉዳይ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጠናቋል፤ ተገምግሟል፡፡ ግምገማውን በተመለከተ ጥቅል ዕቅዱ ምን ያህል ግቡን መቷል የሚለው ሐሳብ ላይ የእርስዎ መንግሥት ውስጥ ግማሹ ሙሉ ለሙሉ ዕቅዱ ግቡን መቷል ይላሉ፡፡ ግማሾቹ ደግሞ ይሄ ዕቅድ እንደ መማሪያ ጊዜ ከመወሰድ ባለፈ የስኬት ፋይዳ የለውም የሚል አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡ እርስዎ የቱ ጋር ነው ያሉት?  ይኸው ዕቅድ የመዘጋጃ ዓመቱ አንድና ሁለት ዓመት ከመፍጀቱ አንፃር ይሄ ዕቅድ ቢያንስ ሁለት ዓመት ሊሰጠው ይገባል የሚሉ አሉ፡፡ ይሄ ነገር ታይቷል ወይ? በዕቅዱ የተቀጡ ግቦች ዓመታቶቹ እየተቃረቡ ሲመጡ እንደማይሳኩ እየታወቁ ለምን ዕቅዱ መከለስ አቃታችሁ?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- ዕቅዳችንና አፈጻጸማችን ተገምግሟል፡፡ ሲገመገምም በየዘርፉ ያሉ ጥንካሬዎችንና ጉድለቶችን በግልጽ ለማስቀመጥ ሞክረናል፡፡ ጥቅል ነገር ማየት የሚቻለው በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ነው፡፡ ስለዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ውጤቶች ምንድን ናቸው ብለህ ነው የምታየው፡፡ በእያንዳንዱ ዘርፍ ሊገለጹ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ግልጽ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ግምገማ የሚያካሂዱ ሰዎች ካሉ ምናልባት የግንዛቤ ችግር ስላለባቸው ነው፡፡ በማክሮ ደረጃ ዕቅዱን ስንገመግመው አንደኛው የማክሮ ውጤት የሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት ነው፡፡ ይህ ዕድገት በአማካይ 10.1 በመቶ ነው፤ የትኛውም አገር ይሄንን አልፈጸመም፡፡ የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ምንም እንኳን ቁጥሩን ትንሽ ዝቅ ቢያደርጉም፣ በዓለም ላይ በፍጥነት ያደገች አገር መሆኗ መስክረዋል፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አጠቃላይ ማክሮ ወደ ውስጡ በሚገባበት ጊዜ ግን ግብርናን እናሳድጋለን ባልንበት ስምንት በመቶ አልተሳካም፡፡ 6.6 በመቶ ነው የሆነው፡፡ ከግብርናም ይህ የተከሰተው በሰብል ላይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በእንስሳት፣ በአትክልት፣ በፍራፍሬና በሌሎች ቅመማ ቅመምና ቡና የመሳሰሉት ላይ ያደግነው ዕድገት ግን ወደታች ስቦናል፡፡ በማክሮ ደረጃ የዕድገት ፍጥነቱ ግብርና ስምንት በመቶ ባልነው ደረጃ ብናመጣ ኖሮ የተባለውን 11 በመቶ ልናሳካ እንችል ነበር፡፡

  በኢንዱስትሪም ደረጃ ወደ 10.1 በመቶ እንድንመጣ ካደረጉን ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ በፍጥነት ያድጋል ባልነው መሠረት አድጓል፡፡ በአማካይ 20 በመቶ ያድጋል ብለን 20 በመቶ አድጓል፡፡ ውስጡ ሲፈተሽ ግን ኢንዱስትሪ ውስጥ ኮንስትራክሽን አለ፤ ማኑፋክቸሪንግ አለ፤ ኤሌክትሪክ አለ፤ ማዕድን አለ፡፡ ወደ ማዕድን ስትመጣ ከዜሮ በታች ነው ያደገው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ላይም በ13 በመቶ ነው ያደግነው፤ ሆኖም ማደግ ያሰብነው 18 በመቶ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት በራሱ ከፋፍለህ ስታይ፣ ከፍተኛ ወይም ትልልቅ የሚባሉት ኢንዱስትሪዎች አድገዋል፡፡ ነገር ግን ትልቅ ድርሻ ሊይዙ ይችሉ የነበሩት አነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው ደረጃ አላደጉም፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋና የዕድገት ምንጭ ሆኖ ያገለገለን ኮንስትራክሽን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም በዓይን የሚታይ ነው፤ ኮንስትራክሽን ካሰብነው በላይ ነው ያደገው፡፡ ድምር ውጤቱን በተመለከተ አሁንም ጉድለት አለብን ብለናል፡፡ ከማክሮ አኳያ የሚታየው ሌላው የዋጋ ግሽበት ነው የዋጋ ግሽበት ዕቅዳችንን በምንጀምርበት ሁለት ዓመታት ወቅት ሰማይ ደርሶ ነበር፡፡ ይኼንን ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በአንድ አኃዝ እንዲቆይ አድርገናል፡፡ ስለዚህ የተሳካ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ሥራ ተሠርቷል ማለት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በየጊዜው ብቅ ስለሚል እንዳይወጣ መሥራት መጀመር አለብን፡፡

  አጠቃላይ ኢኮኖሚው ሲገመገም ሌላው የሚታየው የውጭ ምንዛሪ መረጋጋት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ መረጋጋት ላይ ትልቅ ሚና የሚጫወተው ኤክስፖርት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ከየትኛውም ዘርፍ ያነሰ ውጤት ያመጣንበት ነው፡፡ ኤክስፖርት ላይ ደግሞ እያንዳንዱ ለምን ሆነ የሚለውን ለይተናል፡፡ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኤክስፖርት ከጨርቃ ጨርቅ አንድ ቢሊዮን ዶላር፣ ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች ግማሽ ቢሊዮን ዶላርና የመሳሰሉ እናገኛለን ብለን ያልናቸውን በአብዛኛው በሚፈለገው ደረጃ አላገኘንም፡፡ ስለዚህ ችግሮቻችን ይታወቃሉ፤ ተለይተዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ለሚቀጥለው ውጤታማ ሥራ ለመሥራት መነሻ ይሆኑናል ማለት ነው፡፡ ግምገማው ይሄ በሚታይበት ጊዜ የተሳኩ አሉ፤ ደግሞ ያልተሳካ አሉ፡፡ የዕድገት ፍጥነቱን በምታይበት ጊዜ ተሳክቷል ማለት ትችላለህ፡፡ የትኛውም አገር ያልሞከረው ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ዕቅዱን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ነው ያልነው፣ ትራንስፎርሜሽኑን በምታይበት ጊዜ በግብርናው ውስጥ ትራንስፎርሜሽን  ያካሄዱ ዘርፎች አሉ፡፡ ነገር ግን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የፈለግነውን ያህል ትራንስፎርሜሽን አላደረግንም፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ በኢኮኖሚ መዋቅራዊ ትራንስፎርሜሽን በሚባለው ትንሽ ነው ፈቅ ያለው እንጂ የሚፈለገውን ያህል ደረጃ ላይ አልደረሰም ብለን ከፋፍለን ገምግመናል፡፡ በጥቅሉ በሚታይበት ጊዜ ኢኮኖሚያችን በእጥፍ አድጓል፡፡ አንድ አገር በአምስት ዓመት ውስጥ ኢኮኖሚውን አጥፏል ማለት ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በታሪክ ብዙ አገሮች ይሄን አላደረጉም፡፡

  የዕቅድ ክለሳን በተመለከተ ለምሳሌ እኛ ያደረግነው አንድ ነገር ቢኖር የተከለሱ ቦታዎች አሉ፤ ያልተከለሱ ቦታዎች አሉ፡፡ ክለሳ የሚደረገው መሃል ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ መሃል ላይ ጉባዔ አካሂዶ ነበር፡፡ በጉባዔው ላይ ባደረገው ውይይት አንዳንድ መስኮች ላይ ክለሳ አካሂዷል፡፡ ለምሳሌ ቁጠባችን ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው የተሳካ ሥራ የተሠራበት ነው፡፡ ቁጠባችን የኢኮኖሚ 15 በመቶ ይሆናል ብለን አስቀምጠን ነበር፡፡  ስለዚህ በጉባዔው ወቅት 16 በመቶ መድረሳችንን ስናይ ዕቅዱን 20 በመቶ እንዲሆን አድርገን ከልሰናል፡፡ ኤክስፖርታችንም በተመሳሳይ መንገድ ወደ አሥር ቢሊዮን ዶላር ነበር ያስቀመጥነው፣ አየንና አምስት ቢሊዮን ዶላር አድርገን አስቀምጠናል፡፡ አምስት ቢሊዮኑንም አላሳካንም እንጂ ከልሰናል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ዘርፎች ላይ ክለሳ አድርገናል፡፡ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ዓመታዊ ስለሚሆኑ፣ እዚያው ላይ እንግፋ ብለን የሄድንባቸው አሉ፡፡ ስለዚህ የመሃል ጊዜ ወይንም የሁለት ዓመት ተኩል ክለሳ አካሂደን ስለነበር፣ ክለሳዎች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

  ሪፖርተር፡- ይህ ዕቅድ የግሉን ዘርፍ ያላሳተፈ ነበር ይባላል፡፡ ዕቅዱ በመንግሥት ታቅዶ፣ በመንግሥት ተተግብሮ፣ በመንግሥት የተገመገመ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እዚህ ላይ ምን ይላሉ? ሁለተኛው ዕቅድስ የግሉን ዘርፍ በማሳተፉ ረገድ ምን የተለየ ነገር ይዞ መጥቷል?    

  አቶ ኃይለማርያም፡- ይህ ዕቅድ በሚነደፍበት ጊዜ የግል ዘርፉ ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ የግል ዘርፉ ተወካዮች በየዘርፋቸው አጠቃላይ ንግድ ምክር ቤቱም ሆነ የዘርፍ ማኅበራት ተወካዮቻቸው ተሳትፈዋል፡፡ እንግዲህ ሁሉንም የግል ዘርፍ አንድ መድረክ ላይ አምጥቶ ማሳተፍ አይቻልም፡፡ ተወካዮቻቸውም እነሱን ይወክላሉ ተብለው ነው፡፡ የተሳተፉት፡፡ ምናልባት ይሄ ችግር የሚከሰተው በተወካዮቹ ያለማመን ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም ተወካዮቹ ሲሳተፉ ተወካዮቹ ላይ ካላመነ እኔ አልተሳተፍኩም ይላል ማለት ነው፡፡ ዋናው ነገር ተወካዮቹ ሲመጡ የግሉን ዘርፍ ፍላጐት ይዘው መምጣት አለባቸው ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ ከዚህ አኳያ የዘርፍና የንግድ ማኅበራት ተወካዮች በዚህ ዕቅድ ዝግጅት ውስጥ ተሳተፈዋል፡፡ ከዚያም አልፈን ዋና ዋና የግሉ ዘርፍ ተዋንያን የሆኑትን ጭምር ለብቻቸው ለማወያየትና ከእነሱም ግብዓት ለማግኘት ተሞክሯል፡፡ እኔ ራሴ በዚህ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ አምስት ጊዜ ከግሉ ዘርፍ ጋር በትላልቅ መድረኮች ተወያይተናል፡፡ ስለዚህ ለብቻችን ያደረግነው ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በጉባዔያችን ጭምር የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ጭምር አድርገናል፡፡

  የፓርቲ ጉባዔ ነው የግል ባለሀብቱ ላይሳተፍ ይችላል፡፡ ግን ሐሳባቸውን ለመውሰድ ስለፈለግን በዚያ ገብተው በቡድን ውይይት ጭምር ተሳትፈው ሐሳባቸውን ያቀረቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ በማሳተፍ ዙሪያ የኢሕአዴግና የኢሕአዴግ መንግሥት ያነሰ ሥራ ሠርቷል ብዬ አላምንም፡፡ የትም አፍሪካ አገር እንደዚህ አይደረግም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የግል ዘርፉ በሚፈለገው መጠን የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሆኗል ወይ ነው ጥያቄው፡፡ በስብሰባ ተሳትፈዋል ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ሆኖም ግን የእኛ የግል ዘርፍ ዕድሜው ገና አሥራ አምስት ዓመቱ ነው፡፡ ይህ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በፍላጐት ብቻ ዘርፉ ሊያድግ አይችልም፡፡ ዘርፉ ለማደግ የተወሰነ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ በተለይ አገራዊ ባለሀብቱ ለማደግ የተወሰነ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ አገራዊ ባለሀብቱ ወደ ሥራ ሲገባ ዘሎ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ውስጥ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ከበድ ይላል፡፡ ዕውቀት ይጠይቃል፤ ክህሎት ይጠይቃል፤ የማስተዳደር አቅም ይጠይቃል፤ ቴክኖሎጂ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ገና ጀማሪ ለሆነ የግል ዘርፍ ምቹ አይደሉም፡፡ የትም አገር የግል ዘርፉ ሲጀምር በንግድና በአገልግሎት ነው፡፡ የእኛ የግል ዘርፍ 99 በመቶ በንግድና በአገልግሎት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ይህ ሃቅ ነው፤ የሚካድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው ሴክተሩ፣ ገና ሕፃን ነው የሚባለው፡፡ ይህ ታዳጊ የግል ዘርፍ ደረጃ በደረጃ ከበድ ወደሚሉና ዘላቂ ወደሆኑ የልማት ዘርፎች እየገባ መሄድ አለበት፡፡ በዚህ ቀለል ባለ ወይም ንግድና አገልግሎት ዘርፎች የግል ዘርፉ መቆየት ያለበት ምክንያት  ልማታዊ በሆኑ መንገድና ፈጥኖ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዳይሄድ ገትሮ የሚይዝና ፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግር በመኖሩ ነው፡፡

  የፖለቲካ ኢኮኖሚ ችግር ስንል ለምሳሌ መሬት አቅርቦት ላይ ያለ ብልሹ አሠራር፣ ማለትም ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር የተያያዘ ነገር ተወዳዳሪ አያደርገውም፡፡ ስለዚህ በአቋራጭ ከመሬት የሚገኘውን ጥቅም ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ለማግኘት የሚሯሯጡበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ግን ፖለቲካ ኢኮኖሚው ተቀይሮ የመሬት ጉዳይ ግልጽ ሆኖ እያንዳንዷ መሬት ታውቃ፣ በውድድር ላይ የተመሠረቱ የመሬት ሥርዓት በሚኖርበት ጊዜ ጥቂቶች የሚሻሙበት ሳይሆን ተወዳዳሪዎች ብቻ ያንን የሚቀበሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ይሄ ስላልተፈጠረ በአቋራጭ ለመውሰድ የመፈለግ አዝማሚያ ፍላጐት እየጐለበተ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የግሉ ዘርፍ እንዳይጐለብትና እንዳያድግ ይህ የራሱ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

  ሌላው አገራችን የማትታማበት ዘርፍ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው፡፡ አዲስ አበባ ሁላችንም እንደምንለው የኮንስትራክሽን ሳይት ነው የምትመስለው፡፡ ምክንያቱም እዚያም እዚህም የሚበቅል ሕንፃ ነው የሚታየው፡፡ ከሳምንት በኋላ ሳትወጣ ቆይተህ ወደ ከተማ ብትወጣ፣ መዓት ሕንፃ በቅሎ ታገኛለህ፡፡ ይኼ የሚበቅልበት ዋናው ምክንያት ምንድን ነው ከተባለ፣ በአንድ በኩል ኢኮኖሚው ላይ ጥሩ ነው፤ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ እንዳያድግ ደግሞ ራሱ ማነቆ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ይሄን ፈጥነህ ከገነባህና ካከራየህ ብዙ ገንዘብ ትገኛለህ፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ ለፍተህ ለፍተህ የምታገኘው ገቢና ሕንፃ አሠርተህ የምታገኘው ገቢ የተለያየ ነው፡፡ ስለዚህ ፖሊሲያችን ይሄንን በቀላሉ የሚከበርባቸውን ዘርፎች ጠንከር የሚያደርግ፣ ዘላቂ የሆነውን የኢንዱስትሪ ልማታችንን የሚደግፈውን ደግሞ ላላ የሚያደርግና እዚያ ውስጥ ሰዎች እንዲገቡ የሚያደርግ ድጋፍ ይጠይቃል፡፡ ይሄ ድጋፍ በመንግሥት በኩል የተሰጠበት አግባብ በሚታይበት ጊዜ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ፣ የእኛ የግል ባለሀብት ወደ እሴት ፈጣሪ ዘርፎች የመግባት ሁኔታው አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ የዕቅድ ዝግጅት አይደለም ችግሩ፣ ጥቂት ባለሀብቶች ብቻ ናቸው በዕቅዱ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የገቡት፡፡ እነዚህ ደፋር ባለሀብቶች ቁጥራቸው ትንሽ ነው፡፡ አሁን ግን በግልጽ ተወያይተንና በጋራ መልምለን፣ ችግራቸውን አውቀንና ቀርፈን በስፋት እንዲገቡ ማድረግ አለብን፡፡ ምክንያቱም አገራችንን በውጭ ባለሀብቶች ላይ የተንጠለጠለች ከሆነ አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ የአገራችን የኢንዱስትሪ መማርና ማደግ የሚወሰነው በአገራችን ባለሀብቶች ነው፡፡ የውይይት ማነስ ሳይሆን የፖለቲካል ኢኮኖሚው ችግር ነው ተብሎ ነው መወሰድ ያለበት፡፡       

  • ፡- ለአሥራ አምስት ዓመታት ያህል ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት “No war, no peace” የሚል ነው፡፡ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ሞኒተሪንግ ግሩፕ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ በየመን ለሚያደርጉት ጦርነት የአሰብ ወደብ ለ30 ዓመታት ተከራይተውታል፡፡ ከዚያም ባለፈ የኤርትራ ወታደሮች በየመን እየተዋጉ ሲሆን፣ የጦር መሣሪያም ወደ ኤርትራ እየገባ መሆኑን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የማይቀር አደጋ (Imminent danger) አይደለም ወይ? ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በጉዳዩ ላይ ምን ዓይነት ውይይት እያደረጋችሁ ነው? ሁለቱ አገሮች የተመድን ማዕቀብ የሚጥስ ነገር አልፈጸሙም? ከእነሱስ ጋር ውይይት አድርጋችኋል? በቅርቡ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያደረጉት ጉዞ ይህን ይመለከታልን?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት በተመለከተ በተደጋጋሚ ለሕዝብ ስንገልጽ እንደመጣነው፣ ይህ ግንኙነት ቶሎ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገባ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በአስመራ ያለው መንግሥት ሁልጊዜ የተለመደ ግትር አቋም አለው፡፡ ከዚህ ግትር አቋሙ የተነሳ እስካሁን ድረስ ብዙ ለውጥ ሳይመጣ ቆይቷል፡፡ በእኛ በኩል ለውጡ እንዲመጣ ሁሌም መግፋት አለብን ብለን ውሳኔ ወስደናል፡፡ የአስመራ መንግሥት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ብሎ የሚሠራቸው የታቀዱ ሥራዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ተነስቶ አልሸባብን ሲደግፍ ነበር፡፡ ይሄን በዓለም መንግሥታትም አቤት ብለን፣ ጉዳዩ ታውቆ ማዕቀብ የተጣለበት መንግሥት ነው፡፡ ማዕቀቡ እስካሁን ድረስ አልተነሳም፡፡ በቅርቡ የሞኒተሪንግ ግሩፑ እንዳላችሁት ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡ እንዲቅጥል ብሏል፡፡ ይሄ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ አሁንም የሚቀጥል ከሆነ፣ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንወስዳለን ብለናል፡፡ በተደጋጋሚም ተመጣጣኝ ዕርምጃ ወስደን አደብ አስገዝተናል፡፡ ከዚያ በላይ ግን ለመሄድ አንችልም፡፡ የዓለም ሕጉ የሚለው ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ አክባሪዎችና ሰላም ፈላጊዎች መሆናችንን ጭምር ያስመሰከርንበትና እያስመሰከርን የምንቀጥል ይሆናል፡፡

  በቅርቡ እኛ የምናውቀው ሁለቱ አገሮች በተለይ ደግሞ ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ አሰብን ተጠቅማ የመን ላይ ያላቸውን ስትራትጂያዊ ጉዳይ ለማስታገስ አውሮፕላናቸው የመን ላይ የኦፕሬሽን ሥራ እንደሚሠራ ይታወቃል፡፡ ይሄን ጉዳይ ነግረናቸዋል፡፡ ከሚመለከታቸው አካላትም ጋር በግልጽ ተወያይተናል፡፡ የኤርትራን መንግሥት ደግፈው ያልገቡ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ዋናው ዓላማቸው የመን ላይ ያለውን ስትራቴጂያዊ ጉዳያቸውን እዚያ ሆነው አውሮፕላን እየላኩ ለመደብደብ እንዲመቻቸው ነው፡፡ በቀይ ባህር በኩልም የሚደረገው ጉዞና ምልልስን በተመለከተ የቀይ ባህር ስምምነት አላቸው፡፡

  ዋናው ጉዳይ በኢትዮጵያ ፀጥታና ደኅንነትን በተመለከተ ምን ተፅዕኖ ያመጣል የሚለው ነው፡፡ በዚህ ላይ ከሁለቱም አገሮች ጋር ግልጽ ውይይት አድርገናል፡፡ እኛ የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነት፣ ዕድገትና ልማት የሚያደናቅፍ አምስት ሳንቲም አንሠራም ብለዋል፡፡ ይሄ ታክቲክ የመን ላይ ላለን ኦፕሬሽን ቦታው ስለሚመቸን ብቻ ያደረግነው ነው ብለዋል፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህን ኦፕሬሽን ቶሎ ፈጽመን ከዚያ አካባቢ ለመውጣት ዝግጁ ነን ብለው ነግረውናል፡፡ ነገር ግን እኛ አስጠንቅቀናቸዋል፡፡ እኛ በዚህ አካባቢ በምታደርጉት እንቅስቃሴ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር ንክኪ ካለው አብሮ የራሳችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ስንል በምንወስደው ዕርምጃ ብትጐዱ እኛ ተጠያቂዎች አይደለንም፡፡ ምክንያቱም እኛ አስቀድመን ይሄን ጉዳይ ከእናንተ ጋር አልተመካከርንም፤ እኛንም አላማከራችሁንም፡፡ ፍላጐታችሁ ይገባናል፡፡ ነገር ግን እኛ ልዑላዊ አገር እንደመሆናችን መጠን የኤርትራ መንግሥት የተለየ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ከሆነ፣ ለዚያ እንቅስቃሴ አፀፋ ስንወስድ የእናንተ ፍላጐት ቢጐዳ፣ የእኛ ችግር እንዳይደለ እንድትረዱ ብለናል፡፡ ይሄን እንረዳለን ብለዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሁለቱ አገሮች ኦፕሬሽናቸውን ጨርሰው በጊዜ የሚወጡ ከሆነ ወደቡን ለምን ለ30 ዓመታት መከራየት አስፈለጋቸው?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- እኛ እንደዚህ ዓይነት መረጃ የለንም ብለዋል፡፡ የተፈራረምነውም ግልጽ የሆነ 30 ዓመት፣ 40 ዓመት የለንም ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እኛም በተጨባጭ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ አንዳንድ ሶሻል ሚዲያ ላይ ሲያወራ እንሰማለን፡፡ ግን በተጨባጭ ከመንግሥታት ያወቅነውና የተፈራረሙት ስምምነት የለም፡፡ ከዚሁ ተነስቶ እኛ ምንም የምንለው ነገር የለም፡፡ ለራሳችን በቂ መረጃ ሳይኖረን በስሚ ስሚ ብቻ አገሮች አይጠየቁም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን መርጠናል፡፡

  ሪፖርተር፡- አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የት ነው ያሉት? በምን ሁኔታስ ላይ ይገኛሉ?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- እስር ቤት ነው ያለው፤ እንደማንኛውም እስረኛ እስር ቤት ነው ያለው፡፡   

  ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠይቀው እስር ቤቱ እኔ ጋር የሉም ብሎ ነበር?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- ፍርድ ቤቱማ እስር ቤት አይቆጣጠርም፤ ማረሚያ ቤት ነው እስር ቤት የሚቆጣጠረው፤ ማረሚያ ቤቱን ሊጠይቁ ይችሉ ነበር፡፡    

  • ፡- የቤቶች ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ባለፈው ዓመት በ10ኛው ዙር መጋቢት ላይ ዕጣ የወጣላቸው ዕድለኞች እስካሁን ቤታቸውን መረከብ አይችሉም፡፡ ቤቶች ኤጀንሲ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሠራ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የ40/60 ቤቶች ፕሮጀክቶች መጠቀስ ይችላል፡፡ እሱ ላይ ምን እየተሠራ ነው? በተጨማሪም ሕዝቡ ለቤቶች የሚያዋጣውን ገንዘብ መንግሥት ለሌሎች ፕሮጀክቶች እያዋለው ይገኛል የሚል ሥጋት አለ፡፡ ለዚህ ምላሽዎት ምንድነው? የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በዚሁ ዘርፍ ውስጥ እንዴት ሊሳተፉ ይችላሉ? ችግሩስ የፖሊሲ ነው ወይስ የማስፈጸም? መፍትሔውስ?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ ቤቶቹ በተቻለ መጠን አነስተኛ ወጪ ያላቸው ሆነው መካከለኛና አነስተኛ አቅም ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ገብተው የሚኖሩባቸው ቤቶች እንዲሆኑ ነው ፕሮግራሙ የተቀረፀው፡፡ ከዚህም በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በርካታ ሥራ የሚፈጥሩና ብዙ መሐንዲሶችና የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከሞላ ጐደል በሁሉም መስኮች በያዝናቸው ፕሮግራሞች የተሳካ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ማሳያው ምንድን ነው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኮንትራክተሮች ፈጥረናል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮንሰልታንት ፈጥረናል፡፡ ከዛም በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ላይ የተሰማሩ በር የሚሠሩ፣ ብሎኬት የሚሠሩ እንዲሁም ሌሎች የግንባታ ሥራዎች የሚሠሩ በርካታ ኩባንያዎች ፈጥረናል፡፡ በአጠቃላይ ጥሩ እየሄደ ነው ያለው የሚል እምነት አለን፡፡ ከዛ ባሻገር ግን ዜጐች ከአገሪቱ ሀብት መቋደስ ዕድል አግኝተዋል፡፡ የመሬት ዋጋ ላይ አምስት ሳንቲም ሳይጨመርላቸው ኮንዶሚኒየሙ የተሠራበትን ዋጋ ብቻ እየከፈሉ የቤት ባለቤት መሆን ችለዋል፡፡ ስለዚህ ፕሮግራሙ ሁለንተናዊ ጥቅምን ያገናዘበ ነው፡፡

  የቤቶቹን የሥራ ፍጥነት በተመለከተ እንግዲህ ይሄ የሚወሰነው በአገራችን ባሉ የኩባንያዎች ጥራትና ፍጥነት ላይ ነው፡፡ በሁሉም መስኮች የአቅም ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይሄም ዘርፍ ከዚያ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚሀ የተነሳ ባሰብነው ጊዜ የማይጠናቀቁበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡

  አንዱ ለምሳሌ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጉዳይ ነው በቶሎ መግባትና መስተካከል ያለበት፡፡ ይሄ እንግዲህ ከአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሥርዓት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ እነዚሁ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ እያንዳንዱ ሳይት ላይ አንድ ትልቅ የክልል ከተማ የሚያክል ሕዝብ የሚገባበት ነው፡፡ ለምሳሌ 30 ሺሕ የያዘች አንድ ሳይት ላይ በአንድ ቤት ውስጥ አምስት አምስት ሰው አለ ብትል፣ 150 ሺሕ ሰው አለ ማለት ነው፡፡ 150 ሺሕ ሕዝብ ያለው ከተማ እኛ አገር ውስጥ የትልልቅ የክልል ከተሞች ካልሆኑ በስተቀር ትንንሽ ከተሞች 150 ሺሕ ሕዝብ የላቸውም፡፡ ስለዚህ በእያንዳንዱ ቢያንስ ስድስት ሰብስቴሽን ይጠይቃል፡፡ ይሄን ሰብስቴሽን ገንብተህ እስከምትሄድ ድረስ ባለው ፍጥነት የገንዘብም አቅም የመሳሰሉት አሉ፡፡ ለምሳሌ ሰብስቴሽን መገንባት ብር ብቻ ቢሆን አይቸግርም፡፡ ምክንያቱም የሚቆጠበው ገንዘብ በብር ነው፡፡ ነገር ግን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ቅድም እንደነገርኳችሁ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዳልደረሰ ይታወቃል፡፡

  ስለዚህ ሰብስቴሽኑን እንሥራ ስንል ወይ ወደ ብድር መሄድ አለብን፡፡ ወይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ በበቂ ሁኔታ ሊኖረን ይገባል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የሰብስቴሽን ግንባታ ዘግይቷል፡፡ ሌላው የግንባታው የሲቪል ሥራ አልቆ እያለ የኤሌክትሪክ ማገናኘት ሥራ ዘግይቷል፡፡ ይሄ ከፍላጐት ማጣት የተነሳ ሳይሆን ከአቅም ውስንነት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በዓመት የምናወጣው ወጪና የተቆጠበው በሚታይበት ጊዜ ሰማይና ምድር ነው፡፡ ለምሳሌ አምና አሥር ቢሊዮን ብር ነው ያወጣነው፤ ዘንድሮም አሥር ቢሊዮን ብር ነው የተያዘው፡፡ የተቆጠበው ግን በሚታይበት ጊዜ ከ10 እስከ 12 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ስለዚህ 20 ቢሊዮን ብር እያወጣን 12 ቢሊዮን ብር ነው የተቆጠበው፡፡ ስለዚህ የእኛ ገንዘብ ለሌላ ውሏል የሚባለው፣ የሌላ ፕሮጀክት ወደ እኛ መጥቷል ቢባል ነው ትክክለኛ የሚሆነው፡፡ ነገር ግን በባንክ እንቅስቃሴ ወቅት የሚከፈልበትና የማይከፈለበት ወቅት ላይ ገንዘብ ይሯሯጣል፡፡ ገንዘብ ዝም ብሎ ቁጭ አይልም፤ ይዘዋወራል፡፡ የቁጠባ ዓላማውም ባንክ ውስጥ ገንዘብ እንዲዘዋወር ማድረግ ነው፡፡

  ዋናው ነገር በአቅም ማነስ በተለይም የኤሌክትሪክ ሥራ ላይ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ይሄንን በሚቀጥሉት ጊዜያት እንዴት አድርገን ማስተካከል አለብን የሚለውን ጉዳይ ተወያይተናል፡፡ በተለይ ኮንዶሚኒየም ቤት ጣራው ለፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፓናሎች ለማስቀመጥ ምቹ ስለሆነ የቤቶቹን ኃይል በዚህ አማካኝነት ማስገባት ይቻላል፡፡ ከዚያም ውጪ ከቤቶቹ የሚወጣው ቆሻሻ በራሱ ኃይል መሆን ይችላል፡፡ ሁለቱ በጋራ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግራችንን ይቀርፋሉ በሚል እየሠራን ነው፡፡

  ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ሰብስቴሽን ባለባቸው ቦታዎች ያጋጠመን ችግር አለ፡፡ ከአየር ንብረቱ መዛባት ጋር ተያይዞ ብዙ ቦታዎች ላይ ያሉ ግድቦቻችን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል፡፡ ስለዚህ ኃይል በሌለበት ኃይል ቢገጠም ከተማውን በሙሉ ነው የሚረብሸን፡፡ ስለዚህ ሰው ባልገባበት ኃይል ከምንሰጥ ሰው ባለበት ራሱ እየተቆራረጠ ስለሆነ፣ ሰው ያልገባበት ቢቆይ ይሻላል የሚል ውሳኔ ወስደናል፡፡ የአየር መዛባቱ እስኪስተካከልና ግድቦቻችንም ውኃ እስከሚይዙ ድረስ ያንን ነገር መታገስ ነበረብን፡፡ ይሄን ደግሞ በሚዲያም ገልጸናል፡፡ ምክንያቱም ይሄ እኛ የፈጠርነው ችግር አይደለም፡፡ የድርቅ ችግር ነው፡፡ ብዙዎቹ ግድቦቻችን ለምሳሌ አዋሽ ወንዝ ላይ ያለው የቆቃ ግድብ በጣም ብዙ ችግር ውስጥ ገብቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ የአዋሽ ወንዝ ፍሰቱ ጭምር ሊጠፋ የደረሰበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ በተመሳሳይ መልካ ዋከና ቆሟል ማለት ይቻላል፡፡ ተከዜም አሥር ሜጋ ዋት ብቻ ነው የሚያመነጨው፤ እየደረቀ ነው፡፡ ስለዚህ ድርቁ ራሱ በፈጠረው የውኃ ችግር የኤሌክትሪክ እጥረት አጋጥሟል፡፡ ስለዚህ ቤቶቹ ቢያልቁም ኤሌክትሪክ በዚህ ምክንያት መግጠም አልተቻለም፡፡ ይህ ሁሉ ሲደማመር የሚፈለገው ጊዜ ላይ አልመጣም፤ ግን ደግሞ መንግሥት የሚችለውን ሁሉ አድርጐ በሚቀጥለው ጊዜያት ችግሮቹ እየተቀረፉ ይሄዳሉ የሚሉ እምነት ይዘናል፡፡

  የ40/60 ቤት ግንባታ በተመለከተ ከዚህ በፊትም ዕጣ አልወጣበትም፡፡ ስለዚህ እዚህ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኩባንያ እንዳይሳተፉ የሚከለክል ሕግ የለም፤ ፖሊሲም የለም፡፡ ለምሳሌ ፀሐይ ሪል ስቴት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ፖሊሲ ቢከለክል ኖሮ እሱን ይከለክል ነበር፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የውጭ ኩባንያን ፖሊሲ ስለከለከለ ሳይሆን፣ የውጭ ኩባንያ ሥራውን የሚሠራው በብር ሆኖ መጨረሻ ላይ ሲወጣ ግን በዶላር ይዞ ስለሚወጣ፣ በብር ሠርቶ በዶላር ይዞ ለመውጣት የሚያስችል የተጠራቀመ ዶላር የለንም፡፡ የውጭ ኩባንያን ዝም ብለህ ቤት ውስጥ ግባ ማለት ለማኑፋክቸሪንግ ልንሰጥ የነበረችውን ዶላር ለእሱ አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ በዚሁ ደግሞ የአገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት እንጐዳለን ማለት ነው፤ ከዚህ አኳያ ያዝ የምናደርግበት አካሄድ አለ፡፡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ግን ምንም የሚከለክል ነገር የለም፡፡ ብዙዎቹም እየሠሩ ነው ያሉት፡፡ የሚሠሩት ግን ለአነስተኛና ለመካከለኛ ገቢ ላላቸው ሳይሆን፣ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍል ነው እስካሁን እየሠሩ ያሉት፡፡ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ገቢ ላላቸው ሳይሆን፣ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍል ነው የሚሠሩት፡፡ ለአነስተኛ መሥራት ከፈለጉ ዛሬውኑ በሩን ለመክፈት ዝግጁ ነን፡፡  እኛ አሁን ከምንሠራቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች ውስጥ ግማሹን የግል ኩባንያዎች ቢወስዱ፣ በሩ ክፍት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በአገሪቷ ከፍተኛ የዶላር እጥረት አለ፡፡ ባንኮች አካባቢም ሕገወጥ የሆነ አሠራር አለ ይባላል፡፡ በዚሁ ሁኔታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ስንሞክር ይህ ችግር እክል አልሆነብንም?     

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- የዶላር እጥረት በታዳጊ ኢኮኖሚ ውስጥ ሁሉም አገር አልፈውበታል፡፡ ቻይና በዚህ ዓይነት አልፋለች፤ ኮርያ በዚህ ዓይነት አልፋለች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ እጥረት እንደሚያጋጥም ይታወቃል፡፡ እስከሚያልፍ ያለፋል ግን የሚያልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ አንደኛው ሩብ ዓመት ላይ ኤክስፖርት ዘግይቶ ስለሚጀመር እጥረት አጋጥሞናል፣ ሁለተኛው ሩብ ላይ ግን እጥረት የለንም፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ያቀረበ ሰው መውሰድ ይችላል፡፡ ይህ እጥረት የሚቀጥል አይደለም፡፡ ሁልጊዜም የመጀመሪያዎች ሩብ ዓመት ላይ በየዓመቱ ያጋጥመናል፡፡ ከዚያ በኋላ የኤክስፖርት ገቢውና የሌሎች የኢንቨስትመንት ገቢ እንዲሁም ሬሚታንስ በሚገባበት ጊዜ እየቀለለ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ አሁን ብዙ ሥጋት አይደለም ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡       

  • ፡- የተቀናጀ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በመንግሥት መዋቅር ውስጥና በሕዝብ መንግሥት መካከል ከፍተኛ ቁርሾ ፈጥሮ ነበር፡፡ ባለሙያዎቹ ሥራቸውን ሠርተው ጨርሰው ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ ስለሚያስፈልገው የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ነጥብ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለባትን ጥቅም በሕግ ይደነገጋል ተብሎ በሕገ መንግሥቱ ቢቀመጥም፣ እስካሁን ይህ ተግራባዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ የችግሩም ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህ ማስተር ፕላኑን በተመለከተ ምን ላይ ደርሳችኋል? ተግባራዊ ይሆናል አይሆንም? ሌላው አዲስ አበባ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበችው የምትተዳደረው ከተማዋን በማያውቁ ግለሰቦች ስለሆነ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከተማዋ የምትተዳደረው ከተለያዩ ፓርቲዎች በመጡ ሰዎች ነው፡፡ ይህም የከተማዋ ችግር እንዳይቀረፍ አድርጐታል ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- አዲስ አበባን የሚያስተዳድሩ ወጣት ባለሙያዎችን በተለይም በወረዳ ደረጃ ያሉት በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከአራት እስከ አምስት ሺሕ ይሆናሉ፡፡ ሁሉም እዚህ የተማሩና ከአዲስ አበባ የመጡ ናቸው፡፡ የተወሰነ ከሌላ ቦታ የገባ ሊኖር ይችላል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው ግን፡፡ አዲስ አበባ ምን ያህል ነው መኖር ያለበት የሚለውን ግን መመለስ አለብን፡፡ እኔም አዲስ አበባ ላይ ነዋሪ አይደለሁም፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባን ማስተዳደር አትችልም ልባል ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ አይመስለኝም ጥያቄው፡፡ ሕዝቡን የሚያውቁ ወጣት ልጆች ተመድበዋል፡፡ በክፍለ ከተማም በተመሳሳይ መንገድ ብዙ የአዲስ አበባ ልጆች ተመድበዋል፡፡ ዋናው ኃላፊዎቹ የከተማ የማስተዳደር ልምድና ክህሎት የሌላቸው ነው ቢባሉ ያስማማናል፡፡ አዲስ አበባም ተወለደ፣ ክፍለ አገርም ተወለደ የከተማ ሥራና የገጠር ሥራ ይለያያል፡፡ ከገጠር ሥራ ልምድ አንስተህ ከተማ ልታስተዳድር ትችላለህ ማለት አይቻልም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ስለኖረ የከተማ አስተዳዳርም ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን የገጠር አመራሮችን አምጥተን አዲስ አበባ ላይ የከተማ አመራር ስናደርግ፣ የከተማ ስትራቴጂን የገጠር ስትራቴጂ የተለያየ ነው፡፡ በደንብ ሠልጥነው ክህሎት ይዘው የከተማ አመራር ዕውቀት ይዘው፣ የከተማ አመራር ደግሞ የትምህርት ብልጽግናም ስለሚጠይቅ፣ በዚያ መሄድ አለብን ተብሎ ነው የተገመገመው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ላይ በወረዳ ደረጃ ቢያንስ ዲግሪ ሊኖረው ይገባል፡፡ ስለዚህ ከዲግሪ በታች ያሉ አመራሮቻችን ወደ ትምህርት አስገብተናል፡፡ በቅርቡም ለከተማ አመራሮች ከፍተኛ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ዋናው ቁርጠኝነቱ ነው፡፡ እሱ ካለ ማንበብና ማወቅ ይቻላል፡፡ ከኅብረተሰቡም መልመድ ይቻላል፡፡

  የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ገና ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ኅብረተሰቡ ቅሬታ እያቀረበ ነው የሚባለው፣ ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ ሳይደረግ ምንድን ነው ቅሬታው? ተግባራዊ ሲሆን የሚነካ ሰው፣ ቅሬታውን ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ማስተር ፕላኑ እኮ ገና አልፀደቀም፡፡ በሙያተኞች ተጠንቶ ሕዝቡም ተወያይቷል፡፡ ማስተር ፕላን በተፈጥሮው ከሕዝብ ጋር መወያየት ይጠይቃል፡፡ ዝም ብለህ ስዕል ሠርተህ ይህን ላደርግ ነው ብለህ የምትሄደው አይደለም፡፡ ገና ሲጀመር ጀምሮ እያንዳንዱ ነገር ላይ ከታች ጀምሮ ሕዝብ ተወያይቷል ነው በወረቀት ላይ የሚያርፈው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እየተወያየበት የመጣ ማስተር ፕላን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ይህ ማስተር ፕላን አዲስ አበባ ላይ ተግባራዊ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከኦሮሚያ ጋር የሚያያይዘው ጉዳይ ይሄ ማስተር ፕላን በሚተገበርበት ጊዜ እንዲያውም አዲስ አበባ ያሰበው ነገር ቢኖር በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ተነጥለው የሚቀሩ ከሆነ፣ ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሲሠራ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች የማስተር ፕላኑ አካል ሆነው ቢሠሩ ከአዲስ አበባ ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ይሄ ማለት አዲስ አበባ በአዲስ አበባ፣ የኦሮሚያ ከተሞች በኦሮሚያ እየተዳደሩ ማለት ነው፡፡

  እዚህ ላይ ሁለት የተሳሳቱ ነገሮች ነው የሚራመዱት፡፡ አንደኛው ወገን በስህተት ሕዝብ ለማነሳሳት ሲፈልግ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ ነው ብሎ ይቀሰቅሳል፡፡ ይህ በጭራሽ ያልታሰበና ሊሆንም የማይችል ነው፡፡ አዲስ አበባ የራሷ ድንበር አላት፡፡ ከድንበሩ አንድ ኢንች ወደ ኦሮሚያ አትገባም፡፡ አሁን የታሰበው ማስተር ፕላኑ በጋራ ቢሠራና የጋራ ተጠቃሚነት ይኖራል በሚል ነው፡፡ ለምሳሌ የባቡር መሠረተ ልማት ሲዘረጋ አዲስ አበባ ወስዶ ጫፍ ላይ ቢያቆም፣ ኦሮሚያ ከተማ ውስጥ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከዚህ ባቡር የሚጠቀሙት ዕድል ዝግ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ማስተር ፕላን እስከ ኦሮሚያ ከተሞች ድረስ ቢሄድ የባቡር መስመሩ በዚያ ቢለይ፣ የአዲስ አበባ የውስጥ መስመር እስከ ኦሮሚያ ከተሞች ድረስ ቢዘልቅ፣ በኦሮሚያ ያለው ኅብረተሰብ ከአዲስ አበባ ጋር በንግድም ለመተሳሰር ይጠቅመዋል፡፡ ኤሌክትሪክና ውኃ ሲዘረጋም በተመሳሳይ መንገድ ማለት ነው፡፡

  አዲስ አበባ እያደገች የኦሮሚያ ከተሞች እየቆረቆዙ ከሄዱ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘውን ጥቅም ታጣለች ማለት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዕድገት ለኦሮሚያ ከተሞች ጥቅም ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ አንድምታ የሌለውና አዲስ አበባ ዙሪያ ላይ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ምንም ዓይነት ጥቅም የሚያጡበት ሳይሆን፣ ጥቅም የሚያገኙበትና ተያይዞ የማደግ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር አንዱ የአንዱን የመውሰድ ጉዳይ እንዳይደለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

  ሪፖርተር፡- መንግሥት በገቢ ግብር ላይ ማሻሻያ እየሠራ ነው፡፡ በተለይ ዕድገት እያሳየ ያለው የግብርና ዘርፍ ለግብር ሥርዓት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ምንም እንኳን የፓርቲዎ መሠረት ገበሬው ቢሆንም፣ በግብር ሥርዓቱ ላይ ፍትሐዊነትን ከማምጣት አንፃር በግብር ሥርዓቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማምጣት ያስባሉ ወይ?

  አቶ ኃይለ ማርያም፡- በሚቀጥለው አምስት ዓመት የታሰበ ነገር የለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

  ዘካሪያስ ስንታየሁና አሥራት ስዩም

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...