– ከእስያ ኢንቨስትመንትና መሠረተ ልማት ባንክ የ45 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ ገዝታለች
– የአፍሪካ አገሮች ባንኩን ለመቀላቀል ፈራ ተባ እያሉ ነው
በቻይና ጠንሳሽነት በቅርቡ የተመሠረተው የእስያ የመሠረተ ልማትና የኢንቨስትመንት ባንክ፣ ዓምና በጥር ወር፣ በቻይና አማካይነት በይፋ ከመመሥረት አልፎ አባል አገሮችን መቀበል መጀመሩን ካበሰ ወዲህ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሦስተኛዋ አገር በመሆን አባልነቱን ተቀላቅላለች፡፡
ባንኩ ከወራት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ የእስያ የመሠረተ ልማትና የኢንቨስትመንት ባንክን ለመቀላቀል ያቀረበችውን ጥያቄ ባንኩ ተቀብሎ፣ ይሁንና የሚጠበቅባትን የሰነድና ዝቅተኛውን የገንዘብ መጠን እስክታዋጣ በተጠባባቂ አባልነት መዝገብ እንዳሰፈራት ይፋ ያደረገው በየካቲት ወር ነበር፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በእስያ ቀጣና ውጭ የሚገኙና እንደ አፍጋኒስታን፣ ፊጂ፣ ሆንግ ኮንግ ቻይና፣ ቲሞርን አካቶ 13 ተጠባባቂ አገሮችን እንደመዘገበ አሳውቆ ነበር፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቋሚ አባልነት የተመዘገቡ አገሮች ብዛት 77 መድረሱን ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡
በመሆኑም በ100 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ከተመሠረተው ከእስያው ባንክ፣ ኢትዮጵያ የገዛችው የአክሲዮን ድርሻ የ45 ሚሊዮን ዶላር መጠን እንዳለው ከባንኩ መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም በባንኩ የ2900 ድምፅ ወይም የ0.0498 በመቶ ድርሻ መያዟን ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡ በአንፃሩ ግብፅ የገዛችው የአክሲዮን ድርሻ መጠን 650 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ0.7 በመቶ ድርሻ ከባንኩ ገዝታለች፡፡
ባንኩ ከመመሥረቱ ቀደም ብሎ ማለትም ከሦስት ዓመታት በፊት ቻይና የእስያ ኢንቨስትመንትና መሠረተ ልማት ባንክ የሚባል ዓለም አቀፍ ባንክ እንደምትመሠርት ካስታወቀችበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሀ አገሮች አማራጭ የፋናንስ ምንጭ ለማግኘት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆንላቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ በተለይም ቱርክ ከሁለት ዓመት በፊት ባስተናገደቻቸው የቡድን 20 አባል አገሮች ስብሰባዎች ወቅት፣ የባንኩ የምሥረታ ጉዳይ ሲያነታርክ፣ ፖለቲካዊ አንድምታም ሲያሰጠው ቆይቷል፡፡
በወቅቱ ከሚሰጡ ሙያዊ ትንታኔዎች መካከል አሁንም ሚዛን የሚደፋው፣የባንኩ መመሥረት የዓለም ከፍተኛ ወቀሳ ለሚቀርብበት የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ተፎካካሪ ይሆናል፣ ለደሀ አገሮች ብድር በአነስተኛ ወለድ ያቀርባል የሚለው ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በቱርኳ ሪዞርት ከተማ በተካሄደ የምሁራን ጉባዔ (ቲንክ ታንክ ግሩፕ) ወቅት ተሳትፈው ከነበሩት መካከል ራሄል ካሁን (ዶ/ር) አንዷ ነበሩ፡፡
[በ400 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚንሠራፋ ባለአምስት ኮከብ ሪዞርት ሆቴል ሊገነባ ነው]
ምሁሯ አፍሪካ አንባውንድ የተሰኘ ተቋም መሥራችና ኤክሲኪዩቲቭ ዳሬክተር ናቸው፡፡ በስብሰባው ወቅት የዚህን ባንክ መሥረታ ጨምሮ አምስቱ የብሪክስ አገሮች ማለትም ብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ፣ ቻይና እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱት የብሪክስ ባንክና አዲሱ የእስያ የኢንቨስትመንትና የመሠረተ ልማት ባንክ ለአፍሪካ አገሮች በተለይ ትልቅ ተስፋዎች መሆናቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ እንደውም አፍሪካውያን ላሉባቸው የብድር አቅርቦት ችግሮች ትልቅ መፍትሔ የሚሰጡ ተቋማት እየተመሠረቱ በመሆናቸው ነቅተው እንዲሳተፉ መምከራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ እነዚህ የታዳጊ አገሮች ባንኮች ከሚያቅርቡት ወጪ ቆጣቢና አነስተኛ ወለድ ከሚጠየቅባቸው ብድሮች ባሻገር፣ የዓለም ባንክም የሆነ አይኤምኤፍ የሚያደርጉትን የፖሊሲ ጫና ገደብ ለማስያዝ እንደሚያግዙም ምሁሯ አስታውቀው ነበር፡፡
ይሁንና እስካሁን በአባልት የተመዘገቡ የአፍሪካ አገሮች ሁለት ብቻ መሆናቸው ግርምት ማጫሩ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ ሙሉ አባል በሆኑበት በእስያው የኢንቨስትመንትና የመሠረተ ልማት ባንክ ውስጥ በታሳቢ ወይም በተጠባባቂ አባልነት የተያዙትም ቢሆኑ እስካሁን ሁለት አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ፡፡
ይህ በመሆኑም አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ዓይነ አፋር የሆኑበት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል ትንታኔ የሚሰጡ ምሁራን አልታዩም፡፡ ምንም እንኳ እስካሁን የባንኩ አባል አገሮች ብዛት 77 ቢደርስም፣ አሁንም በርካታ አገሮችን ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ያስታወቀ በመሆኑ የአፍሪካ አገሮች ሊቀላቀሉት እንደሚችሉ መላምቶች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ከአፍሪካውያኑ ባሻገር ከባንኩ ጥንስስ ጀምሮ ተቃውሞ ሲያሰሙ ከነበሩ አገሮች መካከል አሜሪካና ጃፓንም እስካሁን አባል ለመሆን አልፈቀዱም፡፡ ቀድሞውንም በአሜሪካ የተመራው የምዕራቡ ዓለም ካምፕ ቻይና ያመጣችውን ጥያቄ ክፉኛ ሲተቸው ቢቆይም ባንኩን ዕውን ከማድረግ አላገዳትም፡፡ እንደውም የባንኩን አንድ አራተኛ በላይ ድርሻ በመያዝ፣ በ30 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል ዋና ባለድርሻ ሆና፣ ሌሎችም እንደ እንግሊዝና አውስታራሊያ ያሉት የቡድን 20 አገሮችን አሳምና የባንኩ መሥራች አባል አድርጋቸዋለች፡፡
ቻይና የመሠረተችው የመሠረተ ልማት ባንክ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት በማግኘት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን እንዲሆን ካበቁት ምክንያቶች ውስጥ የሚጠቀሰው፣ አይኤምኤፍ መዋቅራዊ ለውጥ ያምጣ፣ ሪፎርም ይደረግበት የሚለውን ግፊት አሜሪካ ችላ በማለት በገንዘብ ድርጅቱም ሆነ በዓለም ባንክ ላይ የሚነሱ ትችቶችን ወደ ጎን ማለቷ እነዚህን ተቋማት የሚገዳደር፣ ለብድር ጥያቄዎች የፖሊሲ ግዴታዎችን የማያስቀምጥ ተቋም እንዲፈጠር ሰበብ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
ሰሞኑን በቻይና በተካሄደ ስብሰባም የእስያ ኢንቨስትመንትና መሠረተ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሚስተር ጂን ሊኩን፣ የባንኩ ገዥዎች ቦርድ የአትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ በመቀበል ሙሉ የአባልነት መብት እንደሰጣት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገልጸውላቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ባንኩ የኢትዮጵያን አባልነት መቀበሉ እንዳስደሰታቸው አስታውቀው፣ በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ባንኩ ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በእስያና ፓስፊክ ቀጣናዎች ውስጥ ለሚገኙ አገሮች የመሠረተ ልማት ሥራዎችና የኢንቨስትመንት መስኮች ድጋፍ እንደሚሰጥ የሚጠበቀው ይህ ባንክ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት ለህንድ የመጀመሪያውን የ160 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቁንም ይፋ አድርጓል፡፡