Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊምስጢራዊ መስመሮች

  ምስጢራዊ መስመሮች

  ቀን:

  አስተናጋጁ ያመጣላቸውን ወተት አንዴ እንኳን ፉት አላሉትም፡፡ ከጎናቸው ተቀምጣ የነበረችን ወጣት መዳፍ ዓይኖቻቸውን ጥብብ አድርገው ይመለከታሉ፡፡ ስለተመለከቱት ነገርም ረዣዥም ጣቶቻቸውን እያወናጨፉ ያስረዷታል፡፡

  እንዲህ ሲያድጉ ለሚመለከት መጽሐፍ እያነበቡ ያሉ ሊመስለው፣ አልያም በትንሽ ስክሪን ፊልም እያዩ እንደሆነ ሊጠረጥር ይችላል እንጂ መዳፏን እንደ መጽሐፍ እያነበቡላት እንደሆነ አይገምትም፡፡ 

  የሰው ልጅ መዳፍ የተለያዩ ድርጊቶችን መፈጸሚያ ከመሆን ባሻገር ሌላ ልዩ ሚና አለው፡፡ በመዳፍ ላይ ያሉት ጉልህና ጥቃቅን መሥመሮች የአንዱ ከአንዱ የሚለያዩና የተለያዩ ቁም ነገር ያዘሉ ናቸው፡፡ መስመሮቹ ኃይልን፣ ማንነትን፣ ሥሜትን፣ ተሰጥኦን፣ በሕይወት ያጋጠሙና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን፣ ያሳያሉ፡፡ በሌላ በኩልም እነዚህ ምስጢራዊ መስመሮች ሰዎች ለነገሮች የሚሰጡትን ግምት፣ ለራሳቸው  የሚሰጡትን ዋጋ፤  የነፍስ ጥሪን፣ የሕይወትን ትርጉም የሚያንፀባርቅ ኅትመት ናቸው፡፡ መዳፍ መጽሐፍ ነው ይነበባልም ይባላል፡፡

  መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በመዳፍ ላይ ያሉ መስመሮች የልብ መሥመር፣ የአንጎል፣ የሕይወት ዕጣ ፈንታ፣ የጤና፣ የዕውቀትና፣ የፍቅር ህይወት፣ አንድ ሰው ሊኖሩት የሚችሉ የልጆች ብዛት፣ የጉዞና ሌሎችም የሰዎች አጠቃላይ ሕይወት ነፀብራቅ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ድርጊቶቻቸው፣ አላማና ፍላጎቶቻቸው ስለወንጀለኛነታቸው ሁሉ በመዳፎቻቸው ላይ ይከተባሉ፡፡ የእጅና የጣት ቅርፅ ቁመትና ይዘት ሳይቀር የሰዎችን ማንነት የማሳየት አቅም አላቸው፡፡ በመዳፍ ላይ የሚታዩ የተለዩ ምልክቶች ሳይቀሩ ትርጉም አላቸው፡፡

  የአንጎል መሥመር የሰዎችን ተሰጥኦ፣ ነገሮችን የመረዳት ፍጥነትና የመሳሰሉትን የአዕምሮን የማገናዘብ አቅም ያሳያል፡፡ የሕይወት መስመርም የሰዎችን የጤና ሁኔታ፣ ዕድሜ፣ የኑሮ ውጣ ውረድና የመሳሰሉትን ያንፀባርቃል፡፡

  የቀለበት ጣታቸው ከሌባ ጣታቸው የሚበልጥ ሰዎች መልከ መልካምና የተስተካከለ ተክለ ሰውነት አላቸው፡፡ እጅግ በጣም ተናዳጅና ለውሳኔ የፈጠኑ ቢሆኑም አደጋን ለመቀበል የማይፈሩ፣ ሌሎች በቀላሉ ሊያገኙዋቸው የማይችሉ ነገሮችን የማግኘት ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ፤ የሌባ ጣታቸው ከቀለበት ጣታቸው የሚበልጥ ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ የራስ መተማመን የሚታይባቸው፣ ነገር ግን ራስ ወዳድነትና ትዕቢት ቢጤ የሚያጠቃቸው፣ ብቻቸውን መሆን የሚያስደስታቸው፣ የፍቅር ግንኙነት ለመጀመር የሚፈሩ ዓይነት እንደሆኑ ይነገራል፡፡

  የተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ረጅም የልብ መስመር ያላቸው ሰዎች ምናባዊና በጓደኞቻቸው ላይ ጥገኛ የመሆን ባህሪ አላቸው፡፡ አጭር መስመር ያላቸው ደግሞ በማንኛቸውም ጉዳዮች ራሳቸውን የሚያስቀድሙ ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንዶች እንዲህ ከ ሀ እስከ ፐ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ በመዳፍ ላይ ተከትቦ ስለተቀመጡ መስመሮች በማጥናት መዳፍ የማንበብ ጥበብ ባለቤት መሆን እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ መዳፍ ለማንበብ መንፈሳዊ ተሰጥኦ ሊኖር እንደሚገባ፣ ካልሆነ ግን በንባቡ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እንደሚፈጠር በመግለፅ ይከራከራሉ፡፡

  ስለ መዳፍ ማንበብ (palm history) ጥበብ የተጻፉ የተለያዩ መጻሕፍት ማገላበጥ የጀመሩት ከዓመታት በፊት ነበር፡፡ በአንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ የላይብረሪ ባለሙያ ሆነው ስለሚሰሩ የሚፈልጉትን መጽሐፍ ለማግኘት አይቸገሩም፡፡ ወ/ሮ አስቴር ይልማ (ስማቸው ተቀይሯል) ባለትዳርና የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡

   ቀን ሥራ ውለው አመሻሽ ላይ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ስለ መዳፍ ማንበብ ጥበብ መሠረታዊ መረጃዎችን ከሚሰጡ መጻሕፍት መካከል አንዱን ይዋሳሉ፡፡ እራት ከተበላ በኋላ ባለቤታቸው ሲቀሩ፣ በመጽሐፉ የተቀመጡ የተለያዩ የመዳፍ ዓይነቶችን ከልጆቻቸው ጋር በማመሳሰል ማንበብ ይጀምራሉ፡፡

  መሥመሮቹን ተከትለው ስለ ልጆቻቸው ባህሪ፣ ዕጣ ፈንታ እያሉ ያነባሉ፡፡ በመካከል በአንደኛው ልጃቸው መዳፍ ላይ የተመለከቱት መሥመር አደጋ  አልያም መጥፎ ዕጣ ፈንታ የሚያመላክት ሲሆን ፈታቸውን አጥቁረው ‹‹ይኼ ከአንተ መዳፍ ጋር አይመሳሰልም፡፡ ተሳስቼ ነው›› በማለት ከሌላ የመዳፍ ዓይነት ጋር በግድም ቢሆን ለማመሳሰል እንደሚጥሩ ይናገራ፡፡

  መጽሐፉን ተከትለው የራሳቸውንና የልጆቻቸውን መዳፍ ቢያነቡም አምነው የሚቀበሉት ጥሩ ጥሩውን ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው ከሆነ ግን እንደተለመደው ከሌላ የመዳፍ ዓይነት ጋር ያመሳስላሉ፡፡  በመስመሩ ላይ ያሉትን ጥሩ ጥሩ ነገሮች እየመረጡ ያወሩላቸዋል፡፡ የሚመሳሰል ከጠፋ ደግሞ የተጻፈው ነገር ትክክል አለመሆኑን  በመግለጽ ልጆቻቸውን ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ ምን ዓይነት ጉድ ነው በሚል ፊታቸውን አጨፍግገው ያነበቡት ጉዳይ ከእውነታ የራቀ ስለመሆኑ ራሳቸውን ለማሳመን እየሞከሩ ወደ መኝታ ቤታቸው ይገባሉ፡፡

  እንዲህ ያሉ መጻሕፍትን ለዓመታት ያነበቡ ቢሆንም፣ ራሳቸውን ችለው መዳፍ ማንበብ እንደማይችሉ ይናገራሉ፡፡ መዳፍ ለማንበብ መጽሐፍ መያዝ ግድ ይላቸዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ አንዳንድ መስመሮችን ለመለየትና ትክክለኛውን ፍቺ ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡

  መዳፍ የማንበብ ጥበብ ሳይንሳዊ መሠረት እንዳለው የተለያዩ መላምቶችን በመደርደር የሚከራከሩ አሉ፡፡ ይሁንና የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች ለአስተያየት ክፍት የሆኑና ምሉዕነት የጎደላቸው የሚባሉ አይነት ናቸው፡፡ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መሠረት የለውም ብሎ ለመደምደምም አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡

   ሰዎች በማመንና ባለማመን መሃከል ሆነው አንድም ዕጣ ፈንታቸውን ለማወቅ አንድም ስለ መዳፍ ምስጢር የሚባሉት ነገሮች ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መዳፋቸውን ያስነብባሉ፡፡ አንዳንዶች ራሳቸው ብቻ የሚያውቁት ምስጢራቸው እስኪነገራቸው አንባቢውን በጥርጣሬ ይመለከቱታል፡፡ ድንገት ምስጢራቸው ሲነገራቸው እንደ መደንገጥ ብለው በተለይ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን በተመለከተ ብዙ እንዲነገራቸው መወትወት ይጀምራሉ፡፡  

  የ25 ዓመቱ ብሩክ ታመነ የኮሌጅ ተማሪ ሳለ በአንድ አጋጣሚ መዳፉን አስነብቦ እንደሚያውቅ ይናገራል፡፡ መዳፉን ያነበበለት ወጣትም እንደሱ የኮሌጅ ተማሪ የነበረ፣ የብዙዎችን መዳፍ በማንበብ የታወቀ ነበር፡፡ መዳፋቸውን ያነበበላቸው ተማሪዎች አብዛኛዎቹ የነገራቸው ነገሮች ትክክል እንደሆኑ ሲያወሩ የብሩክ ጆሮ ገብቷል፡፡ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን መዳፉን ለማስነበብ ወደ ልጁ ሄዱ፡፡

  ‹‹እጄን ዓይቶ ‹አባትህ ሞቷል፡፡ በኪስህ ይዘኸው የነበረውን የአባትህ ፎቶም ጥለኸዋል፡፡ ኪስህ ውስጥ የለም› አለኝ፡፡ ከዚያም በጣም ደነገጥኩኝ፤›› የሚለው ብሩክ ይህ እንደተነገረው ትኩረቱን ሰብስቦ መዳፍ አንባቢውን መከታተል እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡

  ቀጥሎም ወደ ውጭ አገር እንደሚሄድ፣ ሀብታም እንደሚሆን ነግሮታል፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ግን ትክ ብሎ ይመለከትና እንደመደንገጥ ብሎ ሳይነግረው ያልፍ እንደነበር፣ ምን እንዳየ ደጋግሞ ቢጠይቀውም መልስ ሳይሰጠው አረሳስቶ እንዳለፈው ያስታውሳል፡፡ አብዛኛዎቹ የነገረውን ነገር ስለ እሱ ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቆ ያጠናቀረው ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡ አንዳንዶቹን ደግሞ ለራሱ ብቻ የሚያውቃቸው በመሆናቸው የነገረው ነገር ሁሉ በትክክል ከመዳፉ ያነበበው ሊሆን እንደሚችል ይገምታል፡፡

  ‹‹ማንም በምንና መቼ እንደሚሞት ቢያውቅ ደስ ይለዋል፤›› የሚለው ብሩክ፣ መቼ እንደሚሞት ጠይቆ ነበር፡፡ ይሁንና ለጥያቄው የተሰጠው ምላሽ ሁሌም እንደሚያስጨንቀው ይናገራል፡፡ በወቅቱ ዕድሜው አጭር እንደሆነ፣ በአርባ ዓመቱ እንደሚሞት ተነግሮታል፡፡ ይኼ እውነት እንዳይሆን ሥጋት አለው፡፡ ‹‹አርባ ልደርስ 15 ዓመታት ነው የቀሩኝ፡፡ ወደዛ በተጠጋሁ ቁጥር እፈራለሁ፤›› በማለት በመዳፉ ላይ የተመዘገበው የሞት ዕጣ ፈንታው መቃረቡን ባሰበ ቁጥር እንደሚያስጨንቀው ይናገራል፡፡

  መዳፉ ሲነበብ አንባቢውም ሆነ አስነባቢው በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ በማኅበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው የትዳር፣ የስኬት፣ የዕድሜ፣ የልጅ፣ ውጭ አገር የመሄድና አለመሄድ ጉዳዮች ቅድሚያ ይተነተናሉ፡፡

  ‹‹ሁሉም የአካል ክፍላችን የተሠራው በምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያታዊ የሆነ ትንተና መስጠት ስላልተቻለ የመዳፍ ምስጢር ምንም አይደለም ብሎ ማለፍ ተገቢ አይደለም፤›› የምትለው ወ/ት ሕይወት አሠፋ ነች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት መዳፏን ያነበቡላት ሰዎች በሕይወቷ ሊያጋጥማት የሚችሉ ነገሮችን እንዲሁም ባህሪዋን ጭምር ነግረዋታል፡፡ የትዳር ሕይወቷ አጭር እንደሚሆን፣ ብዙ ልጆች እንደምትወልድ፣ ውጭ አገር እንደማትሄድ ነግረዋታል፡፡ እስካሁን እነዚህን ማህበረሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለማድረግ ሙከራ ባለማድረጓ የተነገሩዋት ትክክል መሆን አለመሆናቸውን መመሥከር እንደማትችል ትናገራለች፡፡ ይሁንና ባህሪዋን በተመለከተ የተነገሯት ከሞላ ጎደል ትክክል መሆኑን እርግጠኛ ነች፡፡   

  የግትርነትና ወላዋይነት ባህሪ እንደሚታይባት፣ ራሷን ከማኅበረሰቡ ገንጥሎ የማየት ነገር እንዳለባት እንዲሁም ሰዎች የነገሯትን ሁሉ እውነት ነው ብሎ የመቀበል ፀባይ እንዳላት ነግረዋታል፡፡ እሷም ትክክለኛ መገለጫዎቿ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ አንዳንድ ጥርጣሬ የሚያጭሩ ነገሮችን በተመለከተም ‹‹ብዙ ጊዜ የሚናገሩት ጥቅል ስለሚሆን ሙሉ ለሙሉ ትክክል ነው ብሎ ለመውሰድ ለአንዳንዶች አስቸጋሪ ሊሆን ችላል፤›› ትላለች፡፡

  በሌላ በኩል ደግሞ ወደፊት ዕጣ ፈንታችሁ ከአንድ ነገር ጋር የተቆራኘ ነው የተባሉና በትክክል ሆኖ ያገኙትም አሉ፡፡ የ35 ዓመቱ አቶ ሠይፉ ከበደ ልጅ ሳሉ ነበር መዳፋቸውን ያነበበ አንድ ሰው በትምህርት ስኬታማ እንደሚሆኑ የነገራቸው፡፡

  ‹‹አክስቴ ሱቅ ነበራት፡፡ ሁሌም ከትምህርት ቤት ስመለስ ወደ ሱቅ እሄዳለሁ፡፡ አንድ ቀን አንድ ሰውዬ እጄን ዓይቶ ሱቅ አትጠብቅ በትምህርትህ ትልቅ ደረጃ ትደርሳለህ አለኝ፡፡ ልጅ ስለነበርኩ ብዙም ቦታ አልሰጠሁትም፤›› የሚሉት አቶ ሠይፉ፣ በትምህርታቸው ከክፍል አንደኛ የሚወጡ ተማሪ እንደነበሩ፣ ከኮሌጅ የተመረቁትም በከፍተኛ ነጥብ እንደሆነና በአሁኑ ወቅት በአንድ መሥሪያ ቤት በጥሩ ደመወዝ በኃላፊነት ቦታ ላይ እንደሚሠሩ፣ ይህም ስኬታቸው ከመዳፋቸው የተነበበበትን አጋጣሚ እንደሚያስታውሳቸው ይናገራሉ፡፡

  መዳፍ ለማንበብ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ማንነት ቁልፍ መሆኑን የሚናጉሩት አቶ ዙሮሜል ተገኘ ናቸው፡፡ የ33 ዓመቱ አቶ ዙሮሜል፣ መዳፍ ማንበብ የጀመሩት ገና በልጅነታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕልም ለማየት ትምህርት ቤት መግባት ወይም የተለየ ዝግጅት ማድረግ አያስፈልግም፡፡ በፈጣሪ ላይ ያለን እምነት ጥልቅ ከሆነ ክስተቶችን አስቀድሞ የማወቅ ዕድል ይኖራል፡፡ ከሰባት ዓመቴ ጀምሮ የማያቸው ህልሞች በትክክል የሚፈጸሙ ነበሩ፡፡ ቤተሰቦቼም ህልሜን ይፈሩት ነበር፤›› በማለት፣ አንድ ሰው መዳፍ ለማንበብ ጠንካራ እምነት ሊኖረው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ የተለያዩ የአስትሮሎጂና የፓልሚስትሪ መጽሐፍትን ማንበባቸው ደግሞ በሥነ ከዋክብትና በመዳፍ ማንበብ ረገድ ያላቸውን ዕውቀት አዳብሮታል፡፡

  እሳቸው እንደሚሉት፣ በመዳፍ ማንበብ (ፓልሚስትሪ) ዙሪያ እስካሁን ብዙ አልተፃፈም፡፡ አንድ መሥመር  ብቻ ቁጥር ሥፍር የሌለው ፍቺ አለው፡፡ የመዳፍ ምስጢር ጠቅላላ የሰውን ማንነት እንደ መስታወት አውጥቶ የሚያሳይ ነው፡፡ እስካሁን በመዳፍ ዙሪያ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ አምስት የመዳፍ ዓይነቶች ብቻ እንዳሉ ነው፡፡ ‹‹ እኔ ተጨማሪ ሰባት የመዳፍ ዓይነቶች እንዳሉና እነሱን የሚተነትን ያልታተመ መጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ፤›› ይላሉ፡፡

  ‹‹መዳፋችን መዝገብ ነው፤›› የሚሉት አቶ ዙሮሜል፣ ሰዎች ክፉም ሆነ ደግ ለማድረግ ሲያስቡ ከእነ ውጤቱ በእጃቸው መዳፍ ላይ እንደሚጻፍ ይናገራሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አንድ ሰው የባህሪና የአስተሳሰብ ለውጥ ሲያመጣ በመዳፉ ላይ ያሉ መስመሮች ይቀያየራሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ የሌባ፣ የአጭበርባሪ ሰዎች የአንጎል መስመራቸው ከጫፉ ቀና ይላል፡፡ ባህሪያቸው ሲቀየር ግን የአንጎል መስመር ወደ ነበረበት ይመለሳል፤›› ብለዋል፡፡

  አቶ ዙሮሜል፣ በርካታ ደንበኞ አሏቸው፡፡ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የሥነ ልቦና አማካሪዎች ጋዜጠኞች ሳይቀሩ ችግር ሲያጋጥማቸው እንዴት ነው ነገሩ ለማለት አቶ ዙሮሜል ጋር ጎራ እንደሚሉ ይናገራሉ፡፡ ዜጎችን እያጭበረበሩ እንደሆነ ለመንገርና እንዴት እንደሚያነቡ ለማወቅ የሚያናግሯቸውም አሉ፡፡            

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...