Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጠያቂ ሲበዛ መላሹ ያደፍጣል!

ሰላም! ሰላም! ‹ብድር በምድር› ያለው ሰማይ ነው አሉ። ምነው ሲባል የማይከፈል ብድር፣ የማይታጨድ ዘር ሲፈጥረው በዚህ ዓለም ላይ የለም ብሎ። ነፍሱን ይማርና ጳውሎስ ኞኞ አንድ ጥያቄ አለኝ አለው። ማንን? ሰማዩን ነዋ። ሌላ ማን ሊጠየቅ ኖሯል? መልስ ያለው ሲኖር አይደል እንዴ ጥያቄ የሚጠየቀው? ምን አለ ሰማዩ? የኢትዮጵያ ብድር ዕውን እዚሁ በምድር የሚከፈል ነው እያልከኝ ነው? ሲለው፣  ሰማዩ ደግሞ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ሳቁን ለቀቀው። የሰማይም እኮ ሰማይ አለው። አናውቅም እንዳትሉ። እሺ የሰማዩን ቋንቋ ልተውና ምድር ለምድር ላውጋችሁ። ሰሞኑን መቼስ ዜና ሳትሰሙ አልቀራችሁም። የእስከ ዛሬው ግድ የለም ይሁን። አሁን ግን ቢያንስ ለኢቢሲ አዲስ አሠልጣኝ መቀጠሩን በተመለከተ ዜና መስማት ይኖርባችኋል። ይኼኔ አርሰን ቬንገር ለቀው አርሰናል አዲስ አሠልጣኝ ቀጥሮ ቢሆን ኖሮ አያመልጣችሁም ነበር። አሁን ግን ኢቢሲ አልጄዚራን በአሠልጣኝነት መቅጠሩን የማታውቁትን ማን ይቆጥራችኋል? ወይ አገርና ሰው? ወይ ስሜትና ፍቅር?

በቃ ግን እኛ ዘፈን ሲሆን ነው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ… የምንለው? የምር። ማነው እስኪ የሚወዳትን ሴት ወይ የምትወደውን ወንድ እስክታምር ጠብቆ ወይም እስኪፀዳ ታግሶ አቅፎ የሚስመው? ‹ከወደዱ ከነምናምኑ› አይደለም እንዴ ተረቱ? ተውት እሺ አሁን ይኼን ብቻ፡፡ በቀደም ዕለት ከማንጠግቦሽ ጋር ዜና እየሰማን የዓለም ባንክ በመጪው ዓመት የ4.9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ ሲሉ መስማት። ብድር ነው እንዳትሉ፣ የተባለው ድጋፍ ነው። ሲፈጥረን ድግሞ አብረን አልተወለድን። አብሮ የተዋለደ ለገንዘብ ሲል በሚከዳዳባትና በሚገዳደልባት በዚህች ዓለምና በዚህ ጊዜ፣ ድጋፍ ብሎ ዶላር ያውም በቢሊዮን እንዴት ይዋጥልኝ? ለአገሬ ባይሆን ኖሮ መቼም ዘንድሮ እሪታዬን ትሰሙት ነበር። ዋናው ግን የትም ፈጭተን መጋገራችን ነው። አይደለም እንዴ?

ይኼውላችሁ ሰሞኑን መኪኖችም እንደ ሰው ነዳጅ አጥሯቸው ሦስት አራት ሰዓት ተሠልፈው ሲውሉ ነበር። ነገራችን ሁሉ በሠልፍ ካላሸበረቀ አያምርባችሁም የተባለ መስለናል። “አሁንማ ተጠናክሮ በተያዘው የመራባት ባህላችን ሰበብ ገና ሆድ ውስጥ ሥጋ ሳይለብሱ ሠልፍ የጀመሩ ዜጎችም በሽ ናቸው፤” ሲለኝ ነበር ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። እውነቱን ሳይሆን ይቀራል? አያያዛችንም እኮ የሚመስለው ‘ገና ገና ገና፣ እንወልዳለን ገና!’ ነው። “እኔስ አንዳንዴ ሳስበው በሕዝብ ቁጥር ብዛት ኤርትራን የምናስመልስ የሚመስላቸው ሰዎች ሳይኖሩ አይቀሩም። አምላክ በስጦታ ለወላጆች ከሰጣቸው ሕፃናት ብሶት የወለዳቸው አልበዙም ትላለህ? እንዲያው እኮ!” የሚሉኝ ደግሞ ባሻዬ ናቸው።

አደራ እንደነገርኳችሁ አትንገሩዋቸው። እሳቸው አንዳንዴ በራሳቸው አዙረው ማየት የሚከብዳቸው ነገሮች አሉዋቸው። እስኪ አሁን ኑሮ እንደ እቶን በነደደበት ዘመን፣ ዓይንን በዓይን ከማየት ሌላ ምን መዝናኛ አለ? መዝናኛውስ ቢኖር ‘ቻፓው’ ከሌለ ምን ዋጋ አለው? አይደል እንዴ? አዎ! እና ወደ እኛና ወደ ሠልፋችን ስንመለስ አንዳንድ የወል ስሞቻችን ‘ሠልፈኞቹ’ ተብለው ቢቀየሩ እያልኩ እያውጠነጠንኩ ነው። ዘመኑ የውድድር ነው እየተባለ ራሳችንን በሙያችን (ሙያችን ሠልፍ መሆኑን ልብ ይሏል) ካላስተዋወቅን ተሠልፈን መቅረታችን ነዋ! ልብ አድርጉ!

 ታዲያ አንድ ወዳጄ ከጥግ እስከ ጥግ ጎዳናውን በነዳጅ ዕጦት ጭር ያደረጉትን መኪኖች እያየ፣ “ጉድ ነው! በሰው ሲገርመኝ ለካ ይኼ ሁሉ መኪናም በልቶ አዳሪ ነው?” አለኝ በዘይቤ። ሰው ነገር ነገር ካለው መመለሻ አጥሯልና ልሸሸው ሳስብ፣ “አንበርብር! ድሮ የተፈጥሮ ሀብቶች አላቂ ናቸው ብለው ሲያስተምሩን፣ ከማለቃቸው በፊት እኛን እንደሚጨርሱንና እንደሚያጨራርሱን ለምን አላስተማሩንም?” ብሎ  ጠየቀኝ። ሰው እርስ በእርሱና ከወዳጅ ከዘመዱ ጤንነቱንና ደኅንነቱን መጠያየቅ እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ የረባ ያረባውን እንደ ሰነፍ ተማሪ ሲጠይቅ የመዋሉ ሚስጥር ምን ይሆን እያልኩ ወደ ሥራዬ ተጣደፍኩ። ታዲያ መልስ የሌለው ጥያቄ ሳዳምጥ እኔም እንደ ገዢው ፓርቲ ብቻዬን ቆሜ ልቅር እንዴ? ምን አደረግኩዋችሁ!

ጨዋታን ጨዋታ ያጫውተዋል። እጄ ላይ ባለሁለት መኝታ ክፍል ኮንዶሚኒየም ቤት ስላለ እሱን የሚገዛ ደንበኛ ለማግኘት እታትራለሁ። እዚያ እደውላለሁ። እዚህ ሰው አስቁሜ አናግራለሁ። የማልሆነው ነገር የለም። ቤቱ የሚገኘው  ከሠፈሬ ቅርብ አካባቢ ስለነበር ምሳ ሰዓት ሲደርስ ወጪ ቁጠባ ቤቴ ሄጄ ልመገብ አስቤ አዘገምኩ። መቼም ውዷ ማንጠግቦሽ ቆቅ ናት ቤቱን አበባ አስመስላ፣ ቡና አቀራርባ ምሳ አዘጋጅታ ትጠብቀኝ ኖሯል። በነገራችን ላይ የኑሮዬን ቋጠሮ መንግሥት ብቻ ይፈታዋል ብላችሁ ለምታስቡ ላጤዎች የማስተላልፈው መልዕክት ቶሎ አግቡና ከመንግሥት አናት ላይ ውረዱ የሚል ነው። እንኳን ኑሮ ሥልጣንም ለብቻ ያንገፈግፋል። ይኼን የክፍል አለቃ ሆናችሁ የምታውቁ በደንብ ትረዱኛላችሁ! እና ምሳዬን እየሰለቀጥኩ ሳለሁ አንድ ወዳጄ ደውሎልኝ በአስቸኳይ ሊያገኘኝ እንደፈለገ አሳውቆኝ ቤት ና አልኩት።

እንደመጣ “ምንድነው?” ብዬ ያጣደፈውን ጉዳይ ስጠይቀው፣ “ዕቁብ መጣል ልንጀምር ስለሆነ ከእኛ ጋር መጣል ጀምር ብዬ ነው፤”  አለኝ። የዘንድሮ ወጣት የኑሮን ብልኃትና አያያዙን አላውቅበት ብሎ ሲንገታገት እንደሚያበሽቀው ሁሉ፣ ሲያውቅበት ደግሞ እንዴት አንጀት እንደሚያርስ አልነግራችሁም። “ጥሩ ነዋ ለመሆኑ ስንት ነው?” ማለት። “በሳምንት አሥር ሺሕ ነው!” ሲለኝ ጉሮሮዬ ላይ ቆሞ አልወርድ ያለውን እህል ለመግፋት ሁለት ሊትር ውኃ (ያውም በሌለ ውኃ) ጨረስኩ። “እንኳን እኔ ይኼን ያህል ገንዘብ በሳምንት የመጣል አቅም ሊኖረኝ የሚጥል የቅርብ ወዳጅም አላውቅም። ይገርማችኋል ጭራሽ እኛ ሠፈር ተርፎት ዕቁብ መጣል ይቅርና እንቁላል የምትጥል ዶሮም አናውቅም። ከተረጋጋሁ በኋላ፣ “ለመሆኑ ሠርቼ ነው ዘርፌ ነው በሳምንት አሥር ሺሕ ብር የምጥለው?” ስለው ቅር ብሎት ተነስቶ ሄደ። አይገርማችሁም? አገርህን እወቅ ይሉኛል ሠፈሬን በቅጡ ሳላውቅ። ኧረ እንዴት ያለ የብልፅግና ዘመን ሆኗል ግን!

ያልኳችሁን ቤት አሻሽጬ እንደጨረስኩ ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ ስልኬን እጎረጉር ያዝኩ። የሚከራይ መጋዘን ፈልግልኝ ላለኝ ደንበኛዬ መጋዘን ፍለጋና ስነካካት ሳለሁ ስልኬ ድንገት እጄ ላይ ጠርታ አስደነጠችኝ። የባሻዬ ልጅ ኖሯል። ሳነሳው፣ “ምነው አንበርብር ምነው?” ብሎ ወቀሳ ጀመረ። ምን እንደሆነና ምን እንደሰማ ስጠይቀው፣ “በሳምንት አሥር ሺሕ ብር መጣል አልችልም’ ብለህ ከምትመልሳቸው ‘ቆይ እስኪ አስቤበት ምናምን’ ብለህ አትሸኛቸውም? ስምህን እኮ አጠፉት…” አለኝ። ከስም እስከ ሥጋ መግደፍ መገዳደፍ፣ ማጥፋት መጠፋፋት ያደግንበት ነውና አልገረመኝም። ግን የተባልኩትን ለመስማት፣ “ምን ብለው?” ስለው፣ “አናውቀውም ወይ? እያለው የሌለው መስሎ የሚያሞኘውን ያሞኝ እንጂ እኛን አያሞኝም። እንኳን ይኼን የመንግሥት ሌባ የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን…” መባሌን ነገረኝ። ‹ሲነግሩህ ውለው ሳትሰማ ግባ…› አለ የዘመኔ ዘፋኝ። ሲያስችል እኮ ነው!

በሉ እንሰነባበት። ተፍ ተፍ ብዬ ኮሚሽኔን ተቀበልኩና እግረ መንገዴን ባሻዬን ሰላም ለማለት ወደቤታቸው ጎራ አልኩ። ባሻዬ ሬዲዮን እያዳመጡ ነው። ጋዜጠኛው ስለትራኮማ በሽታ ያወራል። ሰልችቷቸው ሬዲዮናቸውን ሊወረውሩት ሲቃጡ እኔ መድረስ። “እስኪ እንካ አንበርብር ይኼን ሬዲዮ ለአንድ ሳምንት ቤትህ ወስደህ አኑረው፤” አሉኝ። “እንዴ ባሻዬ እርስዎም ብለው ብለው እንደ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የቤት ዕቃዎችዎን ያለማስጠንቀቂያ ማባረርና ማገድ ጀመሩ?” ስላቸው፣ “ተወኝ የእሱን ሰውዬ ነገር አታንሳብኝ። ብለህ ብለህ ደግሞ እኔን ከእሱ ጋር ታመሳስለኝ? አንዱ ትራኮማ እኮ እሱ ነው፤” አሉኝ። “አቤት ባሻዬ? ደግሞ ምንድነው እሱ?” አልኳቸው አልገባ ብሎኝ ። “ትራኮማ አታውቅምና ነው? ይኼ ዓይን የሚጋርደው በሽታ። ደግሞ እኮ አድፍጦ ሳይታወቅበት ነው የሚያጨልምብህ። እኔ ይኼውልህ የዘንድሮ ትራኮማ በዓይነቱ፣ በምርቱ በይዘቱ ዘርፈ ብዙ ነው። አሁን አሁን የሰው ትራኮማም መጥቷል፤” ሲሉኝ ደንገጥ አልኩ።

“አልገባኝም?” ባሻዬ ብዬ አጠገባቸው ወንበር ስቤ ተቀመጥኩ። “አንድያውን! አሁን አንተ ነህ ነገር የማይገባህ? ይልቅ አንበርብር እንዲያው ምን አባታችን ብናደርግ ይሻለናል? ለገዛ ጥቅሙና ዝናው በሰው ቁስል እንጨት እየሰደደ፣ ከመሠረታዊ አመክኗዊ ጽንሰ ሐሳብ ይልቅ ለስሜትና ለተራ የሥጋ ፍላጎቶች የቀረቡ አባባልና ግጥሞች ይዞ ባልዋለበት እየዋለ፣ ባልተጠመቀበት እየሰገደ ሕዝበ አዳምን ዓይኑን የሚያጥበረብረው ግብዝ መድረሻ አሳጣን እኮ አንበርብር? በዚያ የዘራነውን እንዳይበቅል የበቀለልንን እንዳናይ ቢሮክራሲው፣ ሙስናው፣ የፍትሕና መልካም አስተዳደር ትራኮማ አውሮናል። ደግሞ በዚህ በግለሰብ ንቃተ ህሊና ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብ ንቃት እንዳይመጣ፣ ለገዛ ጥቀማቸውና የሰብዕና ግንባታቸው ያልሆኑትን መስለው የሚያወጫብሩን ትራኮማዎች አሉ። እኮ እንዴት ነው ዓይናችን የሚበራው?” ሲሉ፣ “እሱ ጥሩ ጥያቄ  ነው፤” ብዬ ቢራዬን ልቸልስ ትቻቸው ሄድኩ። ጥያቄ ሲበዛ ሌላ ምን ሊታየኝ ኖሯል? ጠያቂ ዚበዛ መላሹ ያደፍጣል አይደል እንዴ የሚባለው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት