ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የዓለም ጤና ድርጅት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ያወጣውን ሪፖርት እንደሚያሳየው በየዕለቱ 3,000 የሚሆኑ ወጣቶች መከላከል በሚቻል ሕመምና አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ይህ ማለት በየዓመቱ 1.2 ሚሊዮን ታዳጊዎች በተገለጸው መልክ ለሕልፈት ይዳረጋሉ፡፡
በሪፖርቱ እንደተገለጸው ለምሳሌ እ.ኤ.አ. 2015 ላይ ከተጠቀሰው ቁጥር ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ሞት የተከሰተው በአፍሪካና በደቡብ እስያ በሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ነው፡፡ የታዳጊዎቹን ሕይወት እየቀጠፉ ነው ከተባሉ ነገሮች የታችኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን፣ የትራፊክ አደጋና ራስ ማጥፋት ናቸው፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች የሚከሰቱ ሞቶች በአብዛኛው በጥሩ የሕክምና አገልግሎት፣ በትምህርና ማኅበራዊ ድጋፍ መከላከል የሚቻሉ ናቸው፡፡ የአደንዛዥ ፅዕ ሱሰኛ የሆኑ የመከላከልና የእንክብካቤ አገልግሎት ማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ አገልግሎቱ ስለሌለ ወይም ስለመኖሩ መረጃ ስለሌላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጥሩ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲሁም አደገኛ ወሲባዊ ባህሪያት ታዳጊዎቹን ለተጠቀሰው አደጋ ያጋልጣሉ፡፡
‹‹ታዳጊዎች ለአሠርታት ከብሔራዊ የጤና ዕቅድ ውጭ ነበሩ፤›› ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት ረዳት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር ፍሊቪያ ቡስቴሪዮ ታዳጊዎች ላይ ያተኮረ የጤና ኢንቨስትመንት ማድረግ ከጤናው ባሻገር ለወጣቶች ውጤታማነትና ለማኅበረሰቡ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻልም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታዳጊዎችን ለሕልፈት እያደረጉ ነው ከተባሉት ነገሮች የመኪና አደጋ ቢወሰድ እ.ኤ.አ. 2015 ላይ 115,000 ታዳጊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ብዙዎቹ ተጎጂዎች ወንዶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የታችኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽንና ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ችግሮች ሴት ታዳጊዎችን በብዛት ለሕልፈት ይዳርጋል፡፡ ራስን ማጥፋት በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠ የታዳጊዎች የሕልፈት ምክንያት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 2015 ላይ 67,000 የታዳጊዎች የራስን ሕይወት ማጥፋት ተመዝግቧል፡፡
ታዳጊዎች አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ ኃላፊነቶች ይወድቁባቸዋል፡፡ ታናናሾችን የመንከባከብ ወይም ተቀጥሮ የመሥራት ሊሆን ይችላል በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ፣ ዕድሜያቸው ሳይደርስ ለማግባት፣ የወሲብ ንግድ ውስጥ ለመግባት ሊገደዱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ በተለያየ መልኩ ተጋላጭ ያደርጓቸዋል፡፡