Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊማየት የተቸገሩ ተማሪዎችን ለመታደግ

ማየት የተቸገሩ ተማሪዎችን ለመታደግ

ቀን:

ተማሪዎች በተለይም ታችኞቹ ክፍሎች ላይ የሚገኙት በክፍል ውስጥ መምህር ሲያስተምር ጥቁር ሰሌዳው ላይ የተጻፈው አይታየንም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ አንዳንዶች ከፊት አስቀምጡን አይታየንም ቢሉም የሚሰማቸው ያጣሉ፡፡ አንዳንዱም ተማሪ ከረብሻ ወይም ትምህርት ካለመፈለግ ተቆጥሮበት የሚቀጣበት ጊዜ አለ፡፡ መምህራንም ሆኑ ወላጆች ልጆች ከቅርብ ወይም ከርቀት ከፊት ለፊታቸው ያለው ነገር እንደማይታያቸው ሲነግሯቸው ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ችላ ይሏቸዋል፡፡ ይህ ግን አግባብ እንዳልሆነና ልጆቹን ወደ ዓይን ሕክምና መውሰድ እንደሚገባ የዓይን ሐኪሞች ይመክራሉ፡፡

የስምንት ዓመቷ ታዳጊ አሰለፈች ደረጀ በዓባይ የመንግሥት መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ በትምህርት አቀባበሏ ጎበዞች ከሚባሉት ተርታ የምትሰለፍ ብትሆንም ጥቁር ሠሌዳ ላይ ከሚጻፉት መካከል አብዛኞቹ ፊደሎች አይታያትም፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ጥቁር ሠሌዳ ጠጋ ብላ መጻፍ ወይም የክፍል ጓደኞቿን ደብተር እየተዋሰች መገልበጥ ግድ እንደሆነባት ትናገራለች፡፡

አሰለፈችን ያገኘናት ወደ 50 ከሚጠጉ የዕድሜ እኩዮቿ ጋር ሆና በትምህርት ቤታቸው ቅጽር ግቢ ግንቦት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የዓይን ምርመራ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡ አሰለፈች እንደምትለው፣ ጥቁር ሠሌዳ ላይ የተጻፈውን መምህሯ አልፎ አልፎ እያነበቡላት የምትጽፍበት ጊዜ አለ፡፡ አንዳንዴም ጓደኞቿን ታስቸግራለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህም የክፍል ጓደኞቿንና መምህሯን ክፉኛ ያሰለቸች እየመሰላት ትረበሻለች፡፡ ሆኖም ይህን ችግሯን ለወላጆቿ አልነገረችም፡፡

በትምህርት ቤቷ በተካሄደው ቅድመ ምርመራ እሷን ጨምሮ 30 ታዳጊ ሕፃናት የእይታ ችግራቸው በመነጽር የሚስተካከል ሆኖ የተገኘ ሲሆን፣ የቀሩት 20 ሕፃናት ደግሞ በመነጽር ሊስተካከል የማይችልና ውስብስብ ችግር ያለበት ነበር፡፡ ለመነጽር ፈላጊዎች መነጽር ሲሰጣቸው፣ ሃያዎቹ ሕፃናት ግን ከወላጆቻቸው ጋር ወደ ክሊኒክ በመሄድ ሕክምና እንደሚያገኙ ሰምተናል፡፡

የቅድመ ምርመራውን ጨምሮ የመነጽሮቹን አቅርቦትና ሕክምናውን በነፃ የሚያከናውነው ሳሚ ቪዥን ልዩ የዓይን የግል ክሊኒክ ነው፡፡ የክሊኒኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ አያሌው እንደገለጹት፣ ክሊኒኩ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙና የእይታ ችግር ላለባቸው ታዳጊ ሕፃናት ሕክምናና የመነጽር አቅርቦት በነፃ ለማከናወን አቅዶ ወደ ሥራ ከገባ ዘጠኝ ወራት አስቆጥሯል፡፡ ይህን የሚያከናውነውም ኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ ከተባለው ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በመቀናጀት ነው፡፡

የክሊኒኩ ኦፕቶሜትሪስት አቶ ቃለአብ ገነነ፣ እስካሁን ባደረጉት ሕክምና (እኛ በተገኘንበት ቀን የተመረመሩትን ሳይጨምር) በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በሚገኙና በስምንት የመንግሥት መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የእይታ ችግር ላለባቸው 200 ታዳጊ ሕፃናት የመነጽር አቅርቦት፣ ለ300 ታዳጊ ሕፃናት የሕክምና ዕርዳታ በነፃ እንዳበረከቱ ተናግረዋል፡፡ ይህ ዓይነቱም እንቅስቃሴ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ በሌሎች የመንግሥት መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይቀጥላል፡፡

ልጆች የማየት ችሎታቸው ትክክል ይሁን አይሁን ቀድሞ ማረጋገጥ ልጆችን ሊድኑ ወይም ሊታገዙ ከሚችሉ የዓይን ሕመሞች መታደግ የሚያስችል ቢሆንም፣ ይህ እምብዛም ሲተገበር አይታይም፡፡

የዓይን ሐኪም (ስፔሻል ኦፕቶሞሎጂስት) ዶ/ር ወንዱ ዓለማየሁ ‹‹ልጆች ትምህርት ቤት ከመግባታቸው በፊትም ሆነ እየተማሩ ዓይናቸው በትክክል ማየት አለማየቱን መከታተል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት የእይታ መቀነስ ችግሮች ዋነኛው በመነጽር የሚስተካከል መሆኑንም ዶ/ር ወንዱ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ከ150 ያላነሱ የዓይን ሐኪሞች እንደሚገኙ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህም አንድ የዓይን ሐኪም ለ67,000 የዓይን በሽተኞች ማለት ነው፡፡ በ1998 ዓ.ም. በተከናወነ አገራዊ ጥናት እስከ 4,000,000 የሚጠጉ ዜጎች ለዓይነ ስውርነትና ለከባድ የዓይን እይታ መቀነስ ችግር ተዳርገዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 80 ከመቶ ያህሉ የበሽታው መንስኤ መከላከል ወይም ማዳን ከሚቻል በሽታ ነው፡፡ ለዚህም የዓይን ቅድመ ምርመራ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...