Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ውሉ ያልተገኘው የቱሪዝም ልቃቂትና የቁጥቁጥ ውጤቶች

በልዑል ዘሩ

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አገራዊ ፋይዳ ስንዳስስ በመጣንበት ውልክፍክፍ መንገድ ከመዘነው ዋጋ የለውም፡፡ ወይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሪፖርቶች ወይም የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ስብሰባን ከተከታተልን የቁጥቁጥ ‹‹ውጤቶች›› ውጣውን ይቀራሉ፡፡

ከዚያ ይልቅ አገሪቱ ያሏት የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶችና ዕምቅ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶች ሚዛን ላይ ሊቀመጡ ግድ ይላል፡፡ እንደ አገር ባለፉት 25 ዓመታት በአንፃራዊነት የተገኘው ሰላምና የተዘመገበው ዕድገት (በተለይ የመሠረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦት፣ የሆቴሎችና የአስጎብኚ ድርጅቶች መጠንና ጥራት) ሊታይ ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈ የአገራችን ሕዝብ 100 ሚሊዮን መድረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ነባሩን እንግዳ ተቀባይነትና መንፈሳዊ ገጽታ ካስታወስነው የልብ ቁጭት ማጫሩ አይቀርም፡፡

በቱሪዝም መስክ ዓለም እየተጠቀመበት ካለው ትሪሊዮን ዶላር አንፃር በአገራችን ያለው ብጣቂ ፍሰት (በዓመት ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በታች) አያኩራራንም፡፡ በተለይ እንኳን ምሥራቁና ምዕራቡን ዓለም ይቅርና በአፍሪካ ያውም በጎረቤት የምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች (ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ. . .) ገቢ አንፃር ስንመዝነውም ገና ተራራውን የመውጣት ብርቱ ኃላፊነትና ትጋት ይጠብቀናል፡፡ በተለይ የመንግሥት ሸክሙ ደግሞ ከመርግ የከበደ ነው፡፡

የተቀናጀና የተመቻቸ የቱሪዝም አብዮት እንዴት?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹‹በተበጣጠሰ መንገድ›› ቱሪዝምን ለማሳደግ ከመዳከር በመውጣት፣ የአገሪቱ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ካለበት አዝጋሚ ጉዞ እንዲላቀቅ ጥረት ተጀምሯል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራው ‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት›› መቋቋሙ ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት እስካሁን የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን፣ በቅርቡ እንደተዘገበው ‹‹ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ›› (13th Months of Sunshine) የሚለውን የቱሪዝም መለያ (ብራንድ) ‹‹ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት›› (Ethiopia Land of Origins) በማለት ቀይሮታል፡፡ የአገሪቱ የቱሪዝም አባት የሚባሉትን አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር የዘርፉን አንቀሳቃሾች በተቀናጀ መንገድ ችግራቸውን (የመልካም አስተዳደር፣ የብድር፣ የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም የገጽታ ግንባታ) ለመቅረፍ የጀመራቸው ሥራዎች እንዳሉ ይደመጣል፡፡

ይሁንና አገሪቱ የብዝኃ ባህል፣ ልዩ ልዩ እምነቶች፣ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ከመሆን ባለፈ ከትልቁ የራስ ዳሸን ተራራ እስከ አፋር ዝቅተኛው ቦታ (ዳሎል) የታደለች ነች፡፡ በአየር ንብረት ክልልና በተፈጥሮ ሀብት ስብጥርም ከታደሉ ጥቂት የዓለም አገሮች አንዷ እንደሆነች ተገንዝቦ በተከታታይ ማስተዋወቅና ራስን መሸጥ፣ ቱሪዝምን በሁሉም መስክ ማበረታታት እየተቻለ አይደለም፡፡ አዳዲስ የባህልና ቱሪዝም ውጤቶች (Products) ይዞ ወደ ገበያ በመቅረብ ረገድም ውስንነት አለ፡፡

በተለይ እንደ አገር የዚህች አገር ዜጎች የቱሪዝም መስኩን ዕምቅ አቅሞች አሟጦ ለመጠቀም ያላቸው ተነሳሽነትና መቀናጀትም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እውነት ለመናገር ከተፈለገ የፖለቲካ እሰጥ አገባውን (ጥላቻና የቂም በቀል ሽኩቻው) ክፉኛ አጥሎባታል ለማለት ይቻላል፡፡ በሠለጠነው ዓለም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ‹‹የአገር ዲፕሎማት ናቸው›› የሚባሉበት መተማመኛ፣ በእኛ አገር የሚሠራ አይመስልም፡፡

ለአባባሉ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት በድህነትም ሆነ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የሚሰደዱ ሰዎች በውጭ አገር የሚደርስባቸው ምሬትና እንግልት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ‹‹ከአገር ውስጥ ይቅል በውጭ መማርና መሥራት ይሻለኛል›› ብሎ የሄደው፤ በትጥቅም ሆነ በፖለቲካ ትግል የተሸነፈው ወይም ያኮረፈው በሚሊዮን የሚቆጠር ኃይል የአገሩን ገጽታ ለማጠልሸት ወደ ኋላ የማይል መሆኑ ነው፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት የነበረን የድርቅና የጦርነት ምሥል ግድግዳው ላይ ሰቅሎ የቀረና የንግግሩ ማጣፈጫ የሚያደርግ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ አገርንና ፖለቲካን ነጣጥሎ ሳይመለከት ‹‹የኢሕአዴግ ኢትዮጵያ›› እያለ በወገኑ ላይ ጥላሸት የሚቀባ ስንቱ ነው?

ከዚህ አንፃር ሲታይ የትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱም ሆነ ራሱ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስለመቀናጀት ሲያስቡ ይህንንም ማየት አለባቸው፡፡ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት (ለእኔ ወደ ዕርቅ የቀረበ መደማመጥ ሊፈጠር ይገባል) ሳይኖር አንዱ በውስጥም በውጭም የአገር ገጽታ እያፈረሰ፣ ሌላው የቱሪዝም ቢሮዎች ‹‹ገነባን›› ቢል ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ እዚህ ላይ ዕውን የአገሪቱ አስጎብኝ ድርጅቶች (በተለይ አንዳንዶቹ)፣ ሆቴሎችና ተያያዥ አገልግሎት ሰጪዎች ለአገር ስምና ለገጽታ ተጨንቀው ነው እንግዳን የሚያስተናግዱት ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከቱሪዝም ብራንድ ጀምሮ በአገራዊ ቅርሶችና ታሪክ ላይ ያለን አረዳድና እምነት አገርን ያማከለና የተዋሀደ ነው (አንድ አስጎብኝ የአፄ ምኒልክ ሐውልት ለውጭ እንግዳ ሲያስረዳ የሰማሁት እስካሁን አግራሞትን ይጭርብኛል)፡፡

በመሠረቱ የራሷ ፊደል፣ ቋንቋና ዜማ ያላት አገር (በውስጥ ሁላችንም የምንኮራባቸው ሀብቶች ባይመስሉም)፣ ከአሥር የማያንሱ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶችን ታጥቀን፣ በዓደዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል፣ ቀዳሚነታችን በሰው ልጅ መገኛነት እየተወሳ፣ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለ የቱሪዝም ዓርማ ገንብተን፣ የአፍሪካ መዲና ሆነን. . . በዓመት አንድ ሚሊዮን ቱሪስት መሳበ አቃተን ሲባል የሚገኘው አንዱ ክፍተት፣ ይኼው የተቀናጀና የተዋሀደ አገራዊ ገጽታን የመገንባት ተነሳሽነት መጉደል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ በ2008 ዓ.ም. 910 ሺሕ የውጭ ቱሪስቶች ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ 3.4 ቢሊዮን ዶላር እንደገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡ ይህ አኃዝ በዘንድሮው አገራዊ ሁኔታ መሽቆልቆሉም ተገምቷል፡፡

ከዚህ እውነታ አንፃር የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም መንግሥታዊ መዋቅር፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ዜጋና  ምሁራንና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሊያሳልፍ የሚችል የቱሪዝም አብዮት መቀስቀስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከወዲሁ እርሾውን አጠናክሮ መጀመር ጎን ለጎን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብም ለመገንባት እንደሚያግዝ መገመት ይገባል፡፡

ያልተነካው የአገር ውስጥ ጎብኚ አቅም

እንደ የዓለም ጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት (WITC) መረጃ ቱሪዝም በአሁኑ ወቅት ለ300 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ ቱሪዝም በባህሪው ብዙ ሠራተኞችንና የሥራ ዕድሎች የሚፈጥር (Labor Intensive) በመሆኑ፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል፡፡ በዚሁ መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ. በ2020 የዓለም ጎብኚዎች ቁጥር ከ1.6 ቢሊዮን በላይ፣ ኢንቨስትመንቱና የገንዘብ ፍሰቱም ከ15 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል፡፡ ከዚህ ግዙፍ ሀብት ምን ያህል ሊገኝ ነው? ጥያቄው፡፡

በእርግጥ የቱሪዝም መስህብና የኢንዱስትሪው ገቢ ሲባል ከውጭ ወደ ውስጥ የሚወጣውን ጎብኚ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የአገር ውስጥ ጉብኝት ባህል ቢጠናከር በመስኩ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ተጨማሪ በቢሊዮን የሚገመት ሀብትም ሊገኝ ይችላል፡፡ የእርስ በርስ ትውውቁና አንድነቱም እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ አሁን የሚታየው ግን መንግሥት በፈየዳቸው ዓውደ ጥናቶችና ዓውደ ርዕዮች፣ እንዲሁም ፌስቲቫሎች (የብሔር ብሔረሰቦች ቀን፣ የከተሞች ቀንና የአርሶ አደሮች ቀን. . .) እና የፕሮጀክት ምርቃቶች ያለፈ ማኅበራዊ የጉብኝት ተነሳሽነት አልተጠናከረም፡፡ ምናልባት በአንዳንድ ሃይማኖት ተከታዮች እየተጠናከረ የመጣው መንፈሳዊ ጉዞ እንደ መልካም ጅምር ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡

ይህን ድፍረት የተሞላበት ትችት የምንሰነዝረው በፍጥነት እያደጉ ከመጡት ታዳጊ አገሮች አንፃር ያለንበትን ሁኔታ ለመመዘን ነው፡፡ በቀዳሚነት ቻይናን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹World Ometres›› የተባለ ድረ ገጽ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ቻይና በአገርህን እወቅ ክበባት በአሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ በማደራጀት በንግድ፣ በጉዞ፣ በጉብኝትና በገጽታ ግንባታ ሥራ ላይ አሰማርታለች፡፡ ምሁራኑም የአገር ገጽታ በመደገፍና ሙያዊ እገዛ በማድረግ ወደ ተጠቃሚነት ያሸጋግሯቸዋል፡፡ የአገር ውስጡ ጉበኝቱም መቶ ሚሊዮኖችን በማነቃነቅ እስከ 24 በመቶ የአገሪቱን የቱሪዝም ገቢ የሚሸፍን ሆኗል፡፡

130 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያላት ጃፓንም ‹‹ባህል፣ ተፈጥሮና ወዳጅነት›› በሚባል መሪ ሐሳብ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት የአገርህን ዕወቅ ባህል ገንብታለች፡፡ የአገሬው ሕዝብ አይደለም ድንቅ ቅርፅና ባህልን መጎብኘት ይቅርና ተራራ መውጣት፣ በረዶ መንሸራተትና በፍል ውኃ መታጠብ. . . የዕለት ተዕለት ሕይወቱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቅርስና ታሪክ በከፍተኛ እንክብካቤና አድናቆት ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ብቻ ሳይወሰን፣ የትም አገር የረገጠ ጃፓናዊ ‹‹አገሬን ጎብኙልኝ?›› ብሎ ሳይቀሰቅስ መመለስ ነውር አድርገውታል፡፡ ጃፓኖች የማስታወቂያና የገጽታ ግንባታ ሥራቸው ልምድ የሚቀሰምበት ነው፡፡

የህንድና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች (በተለይ አብዮትና ጦርነት ያልመታቸው) የአገር ውስጥ ቱሪዝም ብርታት እንተወውና የደቡብ አፍሪካን እንኳን ብንፈትሽ ‹‹ግሩም›› የሚባል ነው፡፡ ከ55 ሚሊዮን ከማይበልጠው የአገሪቱ ሕዝብ ውስጥ በየዓመቱ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ የአገር ውስጥ ጎብኝቶች (ያውም ቅርሳቸው በፓርክና በዱር እንስሳት ወይም በመናፈሻ ላይ ያተኮረ ነው) ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በዚህም በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ከዘርፉ ቢሊዮን ዶላሮችን ይሰበሰባሉ፡፡

እንግዲህ እነዚህን አብነቶች ማንሳታችን የአገራችን የአገር ውስጥ ጉብኝት አለመጠናከር ለማንሳት ቢሆንም፣ በቀጣይ ከዚህ ችግር መውጣት እንደሚያስፈልግ ለመጎትጎትም ነው፡፡ ‹‹ቱሪዝም የኢትዮጵያን ድንቁርናና ኋላ ቀርነት በግልጽ ለውጭ አገር ሰዎች ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ የለውም፤›› ከሚለው ወግ አጥባቂ መሳፍንትና ምሁራን አስተሳሰብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ዘርፍ የልቃቂቱን ውል ለመፈለግም ነው፡፡

እንዲያውም ለነገሩ ዓለም በመረጃ አንድ መንደር ሆና የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና የመሠረተ ልማት አመቺነቱ እያደገ፣ በዘርፉም ሆነ በሌሎች መስኮች ዩኒቨርሲቲዎች እየተስፋፉ. . . ለምን መፈላለግና ‹‹ልየው›› ማለት ራቀን? ምናልባት የሕዝቡ የገቢ አቅም ዝቅተኛ ነው ቢባል እንኳን ከነፍስ ወከፍ ገቢ ማደግም በላይ በቅንጦት የሚኖረውና ከፍተኛ  ገቢ ያለው አንዳንዱ የከተማ ነዋሪ ጋር እንኳን የመጎብኘት ባህል አላደገም (ከአዲስ አበባ ሶደሬና ላንጋኖ ለሽርሽር ከመሄድ የዘለለ አይደለም)፡፡

ከዚህ አንፃር ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች (በእነዚህ መስኮች እስከ 27 ሚሊዮን ሕዝብ እንደተሰማራ ይታወቃል) ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ከግል ኩባንያዎችና ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ማኅበራዊ ግንኙነቶች (ዕድር፣ ዕቁብና መንፈሳዊ ማኅበራት) ጭምር ጉዳዩን እንዲያስቡበት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የዘርፉ አንቀሳቃሾች (ባለሆቴሎች፣ ቱር ኤጀንቶችና አስጎብኚዎችም) በተቀናጀ መንገድ የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት አለባቸው፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ መውሰድም ያስፈልጋል፡፡

ማጠቃለያ

በኢትዮጵያ ‹‹የቱሪዝም ኢንዱስትሪው አላደገም›› የሚል ጭፍን ድምዳሜ የለኝም፡፡ በአገሪቱ መንግሥት የገጽታ ግንባታና ዲፕሎማሲም ይባል በነበሩን ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶችና ታሪኮች ምክንያት ቢያንስ መቶ ሺዎች የውጭ ሰዎች ጎብኝተውናል፡፡ አሁንም የእኔ መሞገቻ ግን ካሉን በርካታ ቅርሶችና ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲነፃፀር ጥቅሙ አይበቃንም ነው፡፡ በርካታ አሥር ሺዎች ወጣቶችና ሴቶችን በዘርፉ ልናሰማራበት ሲገባ ውሉ እንዳጠፋባት ልቃቂት እዚያም እዚህም ከመጎልጎል አልፈን፣ በውል እየተረተርነው አይደለም የሚል መከራከሪያ ላይ ነኝ፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ መፍትሔ፡-

  • ዓለም አቀፍ የቱሪዝምና የጉዞ ንግድ ትርዒትን ማሳደግ በቀዳሚነት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ይህን ዕድልም በውስን በጀት በውጤታማነት ለመጠቀም ቅድመ ዝግጅትና ብቃት ያለው የሰው ኃይል መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም በጀርመን በርሊንና በእንግሊዝ ለንደን በኋላም በቻይና ቤጂንግ ከተማ የተካሄዱ ተሳትፎዎች ነበሩ፡፡ ግን ምን ያህል ከፖለቲካ ትብት አውጥተን፣ በአቅምና ተወዳዳሪነት ተጠቀምንባቸው? ምንስ ትርፍ አገኘን?  የተማርነውስ? ብሎ በመፈተሽ በቀጣይ መጠናከር ይገባል፡፡
  • ማስተዋወቅና ራስን መሸጥ ላይ ዓለም አቀፍ ገበያን መቀላቀል ያስፈልጋል፡፡ ጎረቤቶቻችን እነ ኬንያና ኡጋንዳ ሳይቀሩ ሲኤንኤንና አልጄዚራን በመሰሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ጣቢያዎች ማስታወቂያ ይሠራሉ፡፡ ይህን አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንኳን ብዙም ሲገፉበት አይታይም፡፡ እርግጥ በጃፓንና በቅርቡ በአሜሪካ የተደረጉ የቢዝነስ መድረኮች የሚዲያ ሽፋንም አግኝተዋል፡፡ ግን በተጨባጭ ራሳችንን የምንሸጥበት ምቹ ሁኔታና ማበረታቻዎችን የምናስተዋውቅበት ሥልትን ማጠናከር ሥልጣኔ ነው፡፡
  • በውስጥ የሆቴልና አስጎብኝዎቻችን ደረጃና መጠንም ይበልጥ መሻሻል አለበት፡፡ በእርግጥ በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በርካታ ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ደረጃ ከወጣላቸው የመዲናችን ሆቴሎች ግን አራት ሆቴሎች ብቻ ባለ አምስት ኮከብ ሲሆኑ፣ 13 ባለ አራት፣ 25  ባለ ሦስት፣ 19 ባለ ሁለት ኮከብ ሲሆኑ፣ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ከዜሮ በታች ሆነዋል፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ ከእነ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኬንያ፣ ሞሪሺየስና ኡጋንዳ እንኳን ያነሰ ነው፡፡ ስለዚህ የመስኩ ዋነኛ ችግር የሆነውን ጥራትና ተወዳዳሪነት በተለይ በሰው ኃይልና አቅርቦት ረገድ ማረም ያስፈልጋል፡፡
  • የአገር ውስጥ ጉብኝትን የማጠናከሩ ጉዳይም ከላይ በተጠቀሰው መንገድ የብሔራዊ መግባባትና የአብሮነት እሴትንም ለመፍጠር በሚደረግበት ደረጃ  መጎልበት አለበት፡፡ እዚህ ላይ መንግሥትና ባለድርሻ አካላት አዲስ ዓይነት መላ ሊያበጁ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ክልሎች በዘርፉ የጀማመሯቸውን የተናጠል እንቅስቃሴዎች በማቀናጀት፣ ዘርፉ በምሁራንና በጥናት እንዲመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቱሪዝም ከፖለቲካ ልዩነትም በላይ አገራዊ አንድነትና ኅብረት እንደሚፈልግ ተረድቶ መነሳትም ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡

     ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles