Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በእነ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ...

የንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በእነ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ መሰከሩ

ቀን:

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና የሕግና የብድር ማገገሚያ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ከተመሠረተባቸው ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር በእስር ላይ በሚገኙት የኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ ላይ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው የምስክርነት ቃላቸውን ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ሰጡ፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሳሙኤል ታደሰ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት፣ አቶ ከተማ ከበደ ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር በተከሰሱበት የክስ መዝገብ ቁጥር 141352 ላይ ነው፡፡ በክስ መዝገቡ ሦስት ክሶች ተመሥርቶባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ክስ በ2001 ዓ.ም. አራጣ አበዳሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ተግባር በተጀመረበት ወቅት፣ በጥቆማ መልክ ከቀረቡ ዘጠኝ አራጣ አበዳሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ አቶ ከተማ ከበደ አራጣ አበዳሪ መሆናቸውን የሚገልጹ ማስረጃዎች የቀረቡ ቢሆንም፣ ሌሎቹ ተጣርቶባቸው ሲከሰሱ እሳቸው ግን አልተከሰሱም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አቶ ከተማ ከአቶ መላኩ ፈንታና ከአቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ጋር ሥውር የጥቅም ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ እንዳይከሰሱ አድርገዋቸዋል የሚል ክስ መሆኑን፣ አቶ ሳሙኤል መጀመሪያ ለዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው በቀረቡበት ወቅት ምስክርነት መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ለምስክርነት የተጠሩት፣ ከላይ ለተጠቀሰው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው ክስ ላይ ለመመስከር መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በጭብጡ ለማካተት ሲሞክር፣ የተጠርጣሪው ጠበቆች ‹‹በድጋሚ ሊቀርብ አይገባም›› በማለት ተቃውሞ ቢያነሱም፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹አልተቀበልነውም ወደ ሌላ ጭብጥ እለፉ›› በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ 23ኛ ክስ ላይ እንደጠቀሰው፣ አቶ ከተማ ከበደ አሜሪካ ከምትኖረው ትዕግሥት ከተማ ከምትባል ልጃቸው ውክልና በመውሰድ፣ ጌታነህ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ለነበሩት አቶ ዮሐንስ ጌታነህ 40 ሚሊዮን ብድር በመስጠት፣ ለባንኮችና ለፋይናንስ ተቋማት ብቻ የተፈቀደውን ሥራ፣ በሕገወጥ መንገድ መሥራታቸውን እንደሚያስረዱለት ጭብጥ አስይዟል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛ ጭብጥነት ያስያዘው ደግሞ አቶ ከተማ፣ አቶ ዮሐንስ ጌታነህ የተባሉትን ተበዳይ የገንዘብ ችግር መሠረት በማድረግ፣ ከተለያዩ ባንኮች በአቶ ከተማ፣ በልጃቸው ትዕግሥትና በኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም በተለያዩ ቼኮች ከተፈቀደው ወለድ በላይ 111,705,397 ብር አራጣ ማበደራቸውን ምስክሩ እንደሚያስረዱላቸው ገልጾ እንዳበቃ ምስከሩ መመስከራቸውን ጀመሩ፡፡

አቶ ሳሙኤል ተጠርጣሪው አራጣ ስለማበደራቸው ለፍርድ ቤቱ እንዲያስረዱለት ዓቃቤ ሕግ ጠይቋቸው ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ በ2001 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ነበሩ፡፡ የባለሥልጣኑ የሕግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት (በወቅቱ አቶ ገብረ ዋህድ ይመሩት የነበረው) በአራጣ አበዳሪዎች ላይ ማስረጃ አሰባስቦ ወደ ሕግ መቅረብ እንዳለባቸው፣ ከመንግሥት አቅጣጫ መሰጠቱን ዳይሬክቶሬቱ ጠቅሶ ማስረጃ እንዲያሰባስቡ እንዳዘዛቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ የነበሩት ምስክሩ ከፍርድ ቤት ማዘዣ ወስደው፣ ከቼክ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሠረተባቸው መዝገቦችን ዝርዝር ወደ መሥሪያ ቤታቸው መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ ያገኙት አቶ አየለ ደበላ (አይኤምኤፍ) አቶ ከበደ ተሰራ (ወርልድ ባንክ)፣ አቶ ገብረ ኪዳን በየነ (ሞሮኮ)፣ አቶ ኮነ ምሕረቱና አቶ አያሌው ተሰማ የሚሉ ፋይሎች ማግኘታቸውንም አክለዋል፡፡ በምርመራ እንዲጣራ በኃላፊዎች ትዕዛዝ ሲሰጥ ለአቶ ሳሙኤል የደረሳቸው የአቶ ከበደ ተሰራ ፋይል ሲሆን፣ ከፍርድ ቤት በወሰዱት ፋይል ውስጥ ከነበሩት ሰነዶች መካከል የተወሰኑት ስላልነበሩ፣ ሰነዱን የመረመረውን አካል ሲጠይቁ፣ ኃላፊዎቹ ‹‹ይኼ ይበቃል›› እንዳሏቸው ከመርማሪው መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀረበላቸው ሰነድ ብቻ ክስ ቢመሠርቱ እንደማያዋጣቸው በመረዳታቸው፣ በወቅቱ ምስክር ወደ ነበረ ግለሰብ ደውለው ሲያናግሩት ከከበደ ተሰራ ጋር በተያያዘ የኬኬ ድርጅት ባለቤት አብረው መከሰስ እንደነበረባቸው እንደነገራቸው፣ ለጌታነህ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ጌታነህ ሞት ምክንያት መሆናቸውን እንደጠቆማቸው ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፣ የአቶ ከተማ ጠበቆች ተቃውሞ አሰሙ፡፡

የጠበቆቹ ተቃውሞ ምስክሩ እየተናገሩ ያሉት ቀደም ብሎ በተነሳ ጭብጥ ላይ ምስክርነት የተሰጠበትና ብይን ያረፈበት በመሆኑና በጅምላ እየተጠየቁ መሆኑን ጠቅሰው፣ መልስ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው ያስረዱ ቢሆንም፣ ሥጋት መሆኑን እንደተረዳው ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ከጭብጡ ሲወጡ ተቃውሞ ማንሳት ተገቢ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ከሰጠው ብይን ጋር እንደማይገናኝ ገልጾ ምስክሩ እንዲቀጥሉ አዘዘ፡፡

ምስክሩ ቀጥለው እንዳብራሩት፣ ተጨማሪ ማስረጃ ሲያፈላልጉ በቼክ ምክንያት የአቶ ዮሐንስ ወንድም፣ አጥናፉ ዮሐንስ የሚባሉ ግለሰብ መታሰራቸውን በማወቃቸው፣ ማረሚያ ቤት ሄደው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ አጥናፉም ሲፈቱ ሲያነጋግሯቸው፣ አቶ ከተማ ከበደ አራጣ ማበደራቸውን የሚያስረዳ የብድር ውል ሰነድ እንደሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ ውሉም አቶ ከተማ የወ/ሪት ትዕግሥት ወኪል ሆነው 40 ሚሊዮን ብር ለአቶ ዮሐንስ እንዳበደሯቸው ይገልጻል፡፡ 20 ሚሊዮን ብር እንደከፈሉና 20 ሚሊዮን ብር መተማመኛ ሰነድ ለአቶ ከተማ መስጠታቸውን እንዳረጋገጡ ምስክሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ከተማ በመቀጠል የ25 ሚሊዮን ብር ክስ በአቶ ዮሐንስ ላይ ክስ እንዲመሠርቱባቸው፣ አምስት ሚሊዮን ብር ወለድ መሆኑንና በተለያዩ ቼኮች የባንክ ሥራ በመተካት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ለኬኬ ድርጅት መከፈሉን ማረጋገጣቸውንም አቶ ሳሙኤል መስክረው ጨርሰዋል፡፡

የአቶ ከተማ ከበደ ጠበቆች ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ አቶ ተስፋዬ ዘውዴና አቶ የሺጥላ አሰፋ፣ ለኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የተለያዩ መስቀልኛ ጥያቄዎችን አቅርበውላቸዋል፡፡

ምስክሩ አቶ ሳሙኤል የብድር ኮንትራት በአቶ ከተማና በአቶ ዮሐንስ መካከል ሲደረግ ስለመኖራቸው ተጠይቀው ‹‹አልነበርኩም›› ብለዋል፡፡ አራጣ ስለመሆኑ እንዴት እንዳወቁ ሲጠየቁ ከተበዳሪው የሰሙ መሆኑንና የዮሐንስ ወንድም አጥናፉ እንደነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ለአቶ ከተማ ውክልና ሰጥታለት ከተባለችው ወ/ሪት ትዕግሥት አራጣ ስለመሆኑ ስለመስማታቸው ሲጠየቁ፣ አቶ ሳሙኤል የሰሙትና ያረጋገጡት ከሦስተኛ ወገንና ሰነዶችን ከመተንተን ተነስተው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰነዶችን የመተርጎምና ትንታኔ የመስጠት ሥልጣን የፍርድ ቤት መሆኑን ጠበቆቹ አስረድተው፣ ምስክሩ ሥልጣን እንዳላቸው ሲጠይቋቸው ምላሽ ሳይሰጡ አልፈውታል፡፡ የብድር ውሉ አራጣ ስለመሆኑ የተጠቀሰ ነገር እንዳለ ማየታቸውን ሲጠየቁ እንደማይናገሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ ሳይከፍሉ በቀሩት 20 ሚሊዮን ብር ላይ የተጨመረው አምስት ሚሊዮን ብር ወለድ መሆኑ በሰነዱ የተጠቀሰ ነገር ስለመኖሩ ተጠይቀው፣ እንደማይገልጽና ‹‹ወለድ›› እንደማይል አስረድተዋል፡፡

ከምን ተነስተው ምስክሩ ወለድ እንደሚሉ እንዲያስረዱ የተጠየቁት አቶ ሳሙኤል፣ አቶ ዮሐንስ 40 ሚሊዮን ብር ተበድረው 20 ሚሊዮን ብር ከከፈሉ በኋላ፣ የ25 ሚሊዮን ብር ክስ በአቶ ዮሐንስ ላይ ከቀረበ፣ አምስት ሚሊዮን ብሩ ወለድ ነው በሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ከተማ የመሠረቱትን የክስ ውሳኔ ስለማየታቸው ተጠይቀው፣ አቶ ሳሙኤል ‹‹አላየሁም›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በአራጣ አበዳሪዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ የሰጠው ለእሳቸው ስለመሆኑ የተጠየቁት ምስክሩ፣ ‹‹ለአለቆቻችን ነው የተሰጠው፤›› ብለዋል፡፡ ወደ ምስክሮች ቢሮ መሄድ ለምን እንዳስፈለጋቸው ተጠይቀው፣ አለቆቻቸው አዘዋቸው መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሳሙኤል አራጣ መሆኑን ሌላው ያረጋገጡበት መንገድ፣ የአቶ ከተማ ልጅ በወቅቱ ከ25 ዓመታት እንደማይበልጣትና በዚያ ዕድሜዋ 40 ሚሊዮን ብር ሊኖራት እንደማይችል እንዴት ግምት ሊወስዱ እንደቻሉ ጠበቆቹ ሲጠይቋቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ 40 ሚሊዮን ብር በዚያ ዕድሜ ሊኖራት አይችልም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአቶ ከተማ ጠበቆች ሌላው ያነሱት ጥያቄ አቶ ከተማ ሰጧቸው የተባሉት ቼኮች እንዴት አራጣ መሆኑን እንደሚያረጋግጡ እንዲገልጹላቸው ምስክሩ ሲጠየቁ፣ ‹‹አያረጋግጡም›› ብለዋል፡፡ በኬኬና በጌታነህ ትሬዲንግ መካከል የንግድ ግንኙነት መኖሩን ስለማወቃቸው ተጠይቀው እንደሚያውቁ፣ ሁሉም ሰነዶችና ማስረጃዎች ከአቶ ዮሐንስ ወንድም ከአቶ አጥናፍ መገኘታቸውንና ለፍርድ ቤትም ያቀረቡት ያንኑ ሰነድ ስለመሆኑ ተጠይቀው ‹‹አዎ›› በማለት አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ከተማን በሚመለከት ከፍርድ ቤት ሰነድ ስለማግኘታቸው የተጠየቁት ምስክሩ ‹‹አላገኘንም›› ብለዋል፡፡ አቶ ከተማ አቶ አጥናፉን የከሰሱት በአራጣ ስለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ነግሯቸው ከሆነ ሲጠየቁ እንዳልነገራቸው ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በማጣሪያ ጥያቄው ኬኬ ድርጅት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰጠው በቼክ ስለመሆኑ እንዲያረጋግጡለት ምስክሩን ጠይቋቸው፣ በቼክ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በምርመራ ስለማረጋገጣቸው ሲጠይቋቸው ‹‹ምስክሩ ነግረውን ነው፤›› ብለዋል፡፡ አምስት ሚሊዮን ብር አራጣ ስለመሆኑ ሲጠየቁ ‹‹ወለድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አምስት ሚሊዮን ብሩ ከ40 ሚሊዮን ብሩ ጋር ስላለው ግንኙነት ማጣራታቸውን ምስክሩ ሲጠየቁ፣ ‹‹ለማጣራት በጉዞ ላይ እያለን ክሱ ተቋረጠ፤›› ብለዋል፡፡ ማጣራት የጀመሩት ፍትሕ ሚኒስቴር ውክልና ከሰጣቸው በኋላ ወይም በፊት ስለመሆኑ ተጠይቀው፣ ውክልና ከመስጠቱ በፊት መሆኑን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ ውክልናውም ‹‹እነ አቶ አየለ ደበላንና ሌሎችም›› ስለሚል እንጂ አቶ ከተማ ከበደ እንዳልተጠቀሱ ገልጸዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...