Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየውጭ ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጥብቅ የሆነው ረቂቅ አዋጅ እንዲሻሻል ፓርላማውን ጠየቁ

የውጭ ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጥብቅ የሆነው ረቂቅ አዋጅ እንዲሻሻል ፓርላማውን ጠየቁ

ቀን:

በ2007 ዓ.ም. ሰኔ ወር ለፓርላማ የቀረበው የውጭ አገር ሥምሪትን ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ የቀረቡ ጥብቅና ምክንያታዊ አይደሉም ያሏቸው አንቀጾች እንዲሻሻሉላቸው፣ የሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ፓርላማውን ጠየቁ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በረቂቅ አዋጁ ላይ በጠራው የሕዝብ ውይይት ላይ የተገኙት የውጭ ሥራ ሥምሪት ኤጀንሲዎች፣ በማኅበራቸው አማካይነት ባለስምንት ገጽ የማሻሻያ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ካነሷቸው የማሻሻያ ጥያቄዎች መካከል ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 7 ላይ ለሁሉም ሥራ ፈላጊዎች የሚያስቀምጠውን የትምህርት ደረጃ ማሻሻያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል፡፡

‹‹የቤት ሠራተኝነት በነባራዊ ሁኔታና ተጨባጭ እውነታ ሲታይ የክህሎት፣ የቋንቋና የተግባር ልምድ የሚጠይቅና በትምህርት መታገዝ ከቻለ የበለጠ የሚጐለብት መሆኑ ታሳቢ ተደርጐ፣ ቀደም ሲል በውጭ ሥራ ሥምሪት ልምዱ የነበራቸውን ከግምት አስገብቶ፣ አዲስ የሚሄዱትንም አገር ውስጥ በቀጥታ ተግባራዊ ሥልጠና መስጠት በሚችሉ በግልም ሆነ በመንግሥታዊ አካላት ሥልጠና ወስዶ በሚሰጥ ማስረጃ ተዘዋውሮ በሕጋዊ መንገድ ሠርቶ መጠቀም እንዲችሉ የሚያመቻች እንጂ፣ ከሠርቶ መኖርና ከተንቀሳቅሶ መሥራት ሕገ መንግሥታዊ የሥራ ዋስትና ጋር የሚጋጭ የትምህርት ደረጃ ግዴታ አድርጐ ማስቀመጥ፣ ዜጐችን ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች አሳልፎ መስጠት ነው፣›› በማለት የትምህርት ደረጃ ግዴታው እንዲነሳና ሕጉ ክህሎቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ጠይቀዋል፡፡

በረቂቁ አንቀጽ 61 ላይ ስለዋስትና ገንዘብ የተቀመጠው 100 ሺሕ ዶላር ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ሲታይ የተጋነነ በመሆኑ፣ ወደ 50 ሺሕ ዶላር እንዲቀንስ ኤጀንሲዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የሥራ ሥምሪትና አገናኝ ኤጀንሲ ለመመሥረት በግል ከሆነ የአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል፣ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከሆነ አምስት ሚሊዮን ብር ተብሎ በረቂቁ የተጠቀሰው ተሻሽሎ በንግድ ሕጉ መሠረት እንዲሆን አቤት ብለዋል፡፡

በረቂቁ አንቀጽ 73 ላይ የማስረዳት ግዴታ የሚለው በወንጀልና በፍትሐ ብሔር አንፃር ተለይቶ ቢቀመጥ ተገቢ እንደሚሆን፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ኤጀንሲ በሌላ አገር ውስጥ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት የማስረዳት ግዴታ ሊጣልበት እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡

በሌላ በኩል በረቂቅ አዋጁ እንደ አዲስ ቢካተቱ ብለው ካነሷቸው ሐሳቦች መካከል፣ በሠራተኛ አያያዝ ረገድ ችግር በሚታይባቸው አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በሥራቸው የሚተዳደር ታዋቂ የሕግ አማካሪ እንዲቀጥሩ የሚያስችላቸው አንቀጽ እንዲካተት በዋነኝነት ጠይቀዋል፡፡

በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ከሰጡት የሕጉ አመንጪዎች መካከል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመጡት አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፣ የሕግ አማካሪ መቅጠር በአዋጅ እንዲካተት የቀረበው ሐሳብ ጥሩ ቢሆንም ሳይሞከር የቀረ ጉዳይ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዋናው መሠረታዊ ችግር ያለው እዚህ አገር ውስጥ በመሆኑ መሠራት ያለበት የአገር ውስጥ ችግሮችን መቅረፍ ላይ ነው ብለዋል፡፡

በትንሹ ስምንተኛ ክፍል የትምህርት ደረጃን በተመለከተ የመንግሥት አቋም ነው ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወደ ውጭ የሚላከው የሰው ኃይል እንጂ ሸቀጥ አይደለም በማለት፣ በሚሄዱበት አገር ተወዳዳሪ ሆነው የተሻለ ሊከፈላቸው ስለሚገባ መሠረታዊ ዕውቀት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

የካፒታልና የገንዘብ ዋስትናን በተመለከተ በረቂቁ የተካተተው ሆነ ተብሎ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ኤጀንሲዎችን ቁጥር ለመቀነስና ጥራት ያላቸው ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ400 በላይ ኤጀንሲዎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፣ ይህንን ያህል ቁጥር በዘርፉ በታወቁት እንደ ፊሊፒን ባሉ አገሮች እንኳን አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚቀርብለትን የውሳኔ ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ በቅርቡ አዋጁን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...