Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመንግሥት ቁርጠኛ አለመሆን የመረጃ ነፃነት ሕጉ ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጓል ተባለ

የመንግሥት ቁርጠኛ አለመሆን የመረጃ ነፃነት ሕጉ ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጓል ተባለ

ቀን:

‹‹ቁርጠኛ ካልሆነ ሕጉን ማዘግየት ይችል ነበር›› አቶ ጌታቸው ረዳ

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ጋር በመተባበር በሒልተን ሆቴል ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ባዘጋጀው የፓናል ውይይት፣ ባለድርሻ አካላት የመረጃ ነፃነት ሕጉ ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ያልዋለው መንግሥት ቁርጠኛ ስላልሆነ ነው አሉ፡፡ መንግሥት ግን ቁርጠኛ በመሆኑ በርካታ ሥራዎች ቢሠሩም አፈጻጸም ላይ ችግር እንዳለ አምኗል፡፡

የኢብኮ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ገብረ መድኅን ሕጉ ቢኖርም፣ ለተለያዩ የሚዲያ ተቋማት መረጃ በአግባቡ የማይሰጡ የመንግሥት አካላት እየበዙ እንደመጡ አመልክተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሚዲያ ተቋማት ሥራቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንደተቸገሩም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው፣ ተቋማቸው ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ቢያከናውንም አሁንም ለመረጃ ክፍት የሆኑ የመንግሥት አካላት የመኖራቸውን ያህል ዝግ ቢሮዎች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም የሚስጥራዊ መረጃ፣ የክፍያ ተመንና የሰነድ አመራር ሕግ እንዲወጣ አለመደረጉ ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ ኤንድ ኮሚዩኒኬሽንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ ሕጉ በጣም ጥሩ የሚባል ቢሆንም በተግባር ግን እንዳልተፈጸመ አመልክተዋል፡፡

በሕግ ደረጃ ሚዲያውን ብቻ የሚመለከተውን የፕሬስ ነፃነት ሁሉንም ዜጋ ከሚመለከተው የመረጃ ነፃነት ሕግ ጋር ቀላቅሎ ማውጣት ስህተት በመሆኑ ሊለያይ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

መንግሥት ቁርጠኛ ቢሆን ኖሮ ሕጉ ከወጣበት ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን መጠበቅ ባልተገባ ነበር ብለዋል፡፡ መረጃ መስጠት አሁንም እንደ ውለታ የሚወሰድ በመሆኑ መንግሥት በጉዳዩ ላይ በቂ ሥራ እንዳልሠራ የሚያሳይ ነው ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹በመንግሥት እጅ ያለ መረጃ የሕዝብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ መረጃ የማግኘት ነፃነት ከሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ጋር መያያዙም ትልቅ ችግር እንደፈጠረ ጠቁመዋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ቢሮዎች ኃላፊዎች የአቅም ውስንነት እንደሚስተዋልባቸውና የአመዳደብ ሥርዓቱም ችግር ያለው እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ከአወቃቀርና ከሥነ ሥርዓት አኳያም መረጃ የማግኘት ነፃነት በብዙ ውጣ ውረዶች የሚያልፍ መሆኑ ሌላ ችግር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያን የወከሉት አቶ ዘሪሁን ተሾመ በተመሳሳይ ሕጉ የአፈጻጸም ችግር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ስምንት ዓመት ተዘጋጅቶ የሕጉን አፈጻጸም የት እንዳደረሰውም ጠይቀዋል፡፡ በመረጃ እጦት የሐሜት ሚዲያ እየተበራከተ ነው ብለዋል፡፡    

የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን መኮንን በበኩላቸው፣ የመረጃ ነፃነት ሕጉ ችግር ላይ ነው ብለዋል፡፡ ጋዜጠኛው አሁንም ከሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊዎች ደጅ እየጠና መረጃ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡ የምርመራ ጋዜጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ የመረጃ አፈትላኪዎች ጥበቃ ሕግ እንዲወጣም ጥሪ አድርገዋል፡፡

በዕለቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ዘለቀና ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የጥናት ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ላይ ያለው የግንዛቤ ውስንነት ትልቅ ተግዳሮት እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ዶ/ር ደረጀ የመረጃ አደረጃጀት ሥርዓት አለመኖር፣ በአዋጁ ላይ በቂ ግንዛቤ የሌለ መሆኑ፣ የሚስጥረኝነት ባህል፣ ወጥ አሠራር አለመኖር፣ ጥቅል ይዘት ያላቸውና ያልተብራሩ የክልከላ ምክንያቶች መኖራቸውና አጋላጭ የሆኑ መረጃዎችን የማግኘት ችግር ሕጉ ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ዶ/ር ነገሪ መንግሥት ከስኬት መረጃዎች ውጪ ያሉትን የሚያገል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የመረጃ ነፃነት ሕጉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመሆኑ፣ በአገሪቱ ያለው የምርመራ ጋዜጠኝነት ደረጃ ደካማ እንዲሆን፣ ጋዜጠኞች በፍርኃት ውስጥ ሆነው ራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ ለማድረግ መገደዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ መንግሥት ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ አይደለም የሚለውን ሐሳብ ተቃውመዋል፡፡ መንግሥት ሕጉን ያወጣው ጠቀሜታውን ተገንዝቦ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ቁርጠኝነቱ ከሌለ አዋጁን ማዘግየት ይቻል ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የተቋማት አመራሮች የሕዝቡ ግንኙነት ኃላፊዎችን ጨምሮ የመረጃ ነፃነት ሕጉ አተገባበር ላይ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ አናሳ መሆኑን ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ላይ በአገሪቱ የተንሰራፋው የሚስጥራዊነት ባህልና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የተቋማቸውን መልካም ገጽታ ብቻ የመንከባከብ አዝማሚያ ለትግበራው ተግዳሮት እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡ የእነዚህ ችግሮች ስፋትና ጥልቀት ሊያከራክር እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡

የሕግ ማዕቀፎች አለመሟላታቸው ችግር መፍጠሩ በእንባ ጠባቂ ተቋም፣ በአጥኚዎቹና በባለድርሻ አካላት ስለቀረበው ቅሬታ ሲናገሩም ሕጎቹ አለመውጣታቸው የፈጠረው ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እስካለ ድረስ አሁን ያለው ሕግ ለችግሮቹ መፈጠር ምክንያት እንደማይሆን አስገንዝበዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ሕጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ውይይት ተደርጎ እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሕጎቹን ለማውጣት መንግሥት የቁርጠኝነት ችግር የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን ተሾመ፣ ‹‹ቁርጠኝን የሚገመገመውና የሚለካበት መሥፈርት ምንድነው? ገምጋሚውስ ማነው? መንግሥት ነው? ፓርቲው ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ መረጃ የማግኘት ነፃነት የመንግሥት ዋነኛ አጀንዳ ለሆነው የመልካም አስተዳደር መሥፈን ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ለሕጉ አፈጻጸም ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...