Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየተጋነነ የቤት ኪራይና መዘዙ

የተጋነነ የቤት ኪራይና መዘዙ

ቀን:

የዚህ ጽሑፍ መነሻ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በቤት ኪራይ ምክንያት ጎዳና ከመውጣት እባካችሁ አድኑኝ የሚል የምስኪን ተከራዮች ተማጽኖን በተደጋጋሚ ለመስማት ነው፡፡ ተከራዮች ሲጠየቁ ባልተጠበቀ ጊዜና መጠን አከራዮች ድንገት ኪራይ ስለሚጨምሩባቸው ምንም እንኳ የገቢያቸውን አብላጫውን ለቤት ኪራይ ቢያውሉም ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለከፍተኛ የኑሮ ጭንቀት ተዳርገዋል፡፡ አከራዮቹ ሲያሻቸው ምክንያት እየፈጠሩ እንዲወጡ ስለሚያደርጓቸው፣ የሚከራይ ቤት ለመፈለግ ሲንከራተቱ እንደሚኖሩ በምሬት ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይ በአዲስ አበባና በአገሪቱ ዋና ከተሞች ችግሩ እየተባበሰ በመሄድ ላይ በመሆኑ፣ አስቸኳይና ተገቢ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ችግሩ እየተስፋፋ መሄዱን ከቀጠለም ማኅበራዊ ቀውስ ለሚያመጡ መሠረታዊ ምክንያቶች ነዳጅ በመሆን ቀውስ እንዳያስከተል ትኩረት ያሻዋል፡፡

የተጋነነ የኪራይ ዋጋው አደጋው

የቤት ኪራይ ዋጋ እንደማንኛውም ሸቀጥ በነፃ ገበያ መርኅ መሠረት በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ መወሰኑ ተገቢ ነው፡፡ የሰው ልጅ ራሱን ለማኖር በውድድር የሚያደርገው ጥረት የዕድገትና ልማት መሠረት ቢሆንም፣ አሁን ያለው የቤት ኪራይ ዋጋ ግን ምንም ምርታማነትና ምርት ሳይጨምሩ አእምሯዊና አካዊ ጥረትና እሴት ሳይጨምሩ በጽንፍ ራስ ወዳድነት ተመሥርተው፣ በደላላ እየተመሩ በአቋራጭ ሀብት የማግበስበስ ድርጊት ነው፡፡ ተግባሩ እኔ ብቻ በሚል ማኅበራዊ እሴትን መረዳዳትን፣ መተሳሰብንና በሥራ ትጋት፣ በላብና በጥረት ደክሞ ማግኘትንን ያፋለሱ የኪራይ ሰብሳቢነት ግልጽ ማሳያ ነው፡፡

- Advertisement -

የተጋነነ የቤት ኪራ በቤት አልባ ዜጎች ሁሉ ላይ በሚያሳድረው ከፍተኛ ተፅዕኖ ምክንያት ለኑሮ ውድነቱ መባባስ በተለይም ወደ ሥራ ዓለም በሚገቡ ወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡ ወጣቶቹ ከሚገኙት ገቢ አብላጫውን ለቤት ኪራይ እንዲከፍሉ ስለሚገደዱ፣ ሠርተው ለመኖር ባለመቻላቸው ለጭንቀት ተዳርገዋል፡፡ ሥራ መሥራታቸው ከሥራ ፈትነት ጋር አኳያ ምንም ልዩነት አላገኙበትም፡፡ በመሆኑም በኑሮ ጭንቀት ስለሚወጠሩ ተስፋ መቁረጥ ይታይባቸዋል፡፡ በአገርና በወገን ያማርራሉ፡፡ በሥራ ታግሎ የመኖር መርኅ መሠረት ተመርተው ከመሥራት ይልቅ ራሳቸውን ለሙስና እና ለጉቦ ያመቻቻሉ፡፡ ግድየለሽነት፣ ዋልጌነት፣ ምንቸገረኝነት ያሳያሉ፡፡ ለአገርና ለወገን ከመቆርቆር ይልቅ ተገቢ ምክንያት በሌለው አቅጣጫ እየተመሩ ራሳቸውንና አገራቸውን በሚጎዳ አመለካከት ይመራሉ፡፡ አገራቸውንና ወገናቸውን በመጥላት ወደ ማያውቁት አገርና ሕዝብ ለመሰደድ ያዘጋጃሉ፡፡ ስለሆነም የተጋነነ የቤት ኪራይ ጦሱ ከባድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የተጋነነ የሚጠይቁ አከራዮች

ቤት ሠርቶ ማከራየት በአንጻራዊነት ቀላልና ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ በመሆኑ፣ በዚህ ዘርፍ መሥራት ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ገንዘብ ያላቸው ዜጎች ለኪራይ የሚውል ቤት ለማግኘት በመረባረብ ላይ ናቸው፡፡ ነጋዴዎች፣ ባለሥልጣናት ዴያስፖራዎች፣ መሬትና ቤት በመሻማት አስተማማኝና ዘላቂ ገቢ የሚያገኙበትን ዘዴ እያስፋ ነው፡፡ ቤት ለማግኘት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን ያስፋፋሉ፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ በድጎማ፣ በዕጣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ወደ ሀብታሞቹ አከራዮች  በመተላለፍ ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም በሙስና እና  በጉቦ እንዲሁም ታክስ በማጭበርበር የተገኘ ገቢ በቤትና በቦታ ግዢ ላይ እንዲውል እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይህም የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ይበልጥ ያበረታታል፡፡ ሠርቶ በጥረት መኖርን ገንቢ የኑሮ መርኅ ከማድረግ ይልቅ ዋልጌነት፣ ስንፍና፣ ሙሰኝነትን እና ብልሹ አስተዳደርን ያስፋፋል፡፡ ይህ አዝማሚያ ትኩረት አግኝቶ በቁጥጥር ካልተገታ፣ ኅብረተሰቡን በማናጋት በቀላሉ ወደ ማይፈታ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያመራ ይችላል፡፡ ይህንን ከፈረሱ አገሮችና ከተደላደለ ኑሯቸው ተፈናቅለው ለሰቆቃ ከተዳረጉ አገሮችና ሕዝቦች በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የተጋነነ የቤት ኪራይ ከራስ ወዳድነትና ከደላላ አመራር ተላቆ በነፃ ገበያ፣ በውድድር፣ በፍላጎትና በአቅርቦት ተጣጥሞ እንዲመራ ብርቱ ትኩረትና ጥረትን ይጠይቃል፡፡

የተጋነነ የቤት ኪራይን የመቆጣጠሪያ ስልቶች

  1. የጋራ መኖሪያ ቤቶች የኪራይ መወሰን፡- የጋራ ቤቶች በመንግሥት ወጪ ተገንብተው ለቤት አልባ ዜጎች በዕጣ በድጎማ የተላለፉ ናቸው፡፡ በሕዝብ ሀብት የተገነባውን ንብረት ጥቂቶች ሕዝብን እንዲበዘብዙበት መፍቀድ ትክክል አይሆንም፡፡ ኢ-ፍትሐዊ ስለሆነም የኮንዶሞንየም ቤት ኪራይ ዋጋ መወሰን አለበት፡፡ ዋጋው ለባንክ ብድር ከሚከፍለው እጥፍ ሆኖ ግሽበቱን የሚያካክስ ጭማሪ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ አቶ መልካሙ የተባሉ ሰው በዕጣ ለደረሳቸው መኖሪያ ቤት ለባንክ ብድር ብር በየወሩ 1,000 ብር ቢከፍሉ፣ ቤት የሚያከራዩበት ዋጋ በምንም መልኩ ከ2,500 ብር መብለጥ የለበትም፡፡
  2. መንግሥት አቅም በፈደቀ መጠን ቤት ሠርቶ ወጪውን በረዥም ጊዜ በሚከፈል ሒሳብ ቤት ማከራየት አለበት፡፡ ይህም እንደ እህል ሁሉ የዋጋ ንረቱንም የሚጋጋ ዕርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ትክክለኛ ቤት አልባዎችን በመለየት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲደረግ ያግዛል፡፡ ራስ ወዳድነት የተጠናወታቸው ስግብግቦችን ያግዳል፡፡ በሒደት ተከራዮች በቁጠባ አማካይነት የቤቱ ባለቤት እንዲሆኑ ማበረታታትም ይገባል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት በዕጣ የደረሳቸው መነሻ ክፍያ ለመፈፀም ስለሚቸገሩ፣ መንግሥት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲሰፍን የሚያስችሉ አሠራሮችንም ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡
  3. የግል ቤት አከራዮችን ማበረታታት፡- ነፃ መሬት በመስጠት፣ የቤት ኪራይ ግብር በመቀነስ ቤት ሠርተው እንዲያከራዩ፣ የባንክ ብድር እንድያገኙ በማበረታታትና በመደገፍ የቤት አቅርቦትን ማሳደግ እንዲቻል የግል ቤት አከራዮችንም ታሳቢ ያደረገ ዕርምጃ መታሰብ አለበት፡፡
  4. የአከራዮችን ማንነት መፈተሽ፡- በሥራና በጥረት በተገኘ ሀብት ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጥ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ በሙስና እና በጉቦ በተገኘ ሀብት ያፈሩት ንብረት መሆኑ ከተረጋገጠ እስከ መውረስ የሚያደርስ ዕርምጃ መውሰድ፣ ይህም መጪው ትውልድ በሥራ እንድያምን፣ ራሱን ለሥራ እንድያነሳሳ፣ ለውድድርና ለፈጠራ እንዲተጋ፣ በሥራና በሥራ ብቻ እንዲያምን ስለሚያደርግ እንዲህ ያለውን እምነት ለማስረጽ በተግባር የተረጋገጠ አሠራር ሲፈጠር ዜጋው ሁሉ ለሥራ ይተጋል፡፡ ስንፍናን ይጠየፋል፡፡ ተፈጥሮዓዊ ቁመና መኖር ትክክለኛ የትግል ስልት በመሆኑ፣ ምንም እሴት ሳይጨምሩ በአቋራጭ ሀብት ለማግነት መሞከር ተፈጥሮዓዊ ባለመሆኑ መጨረሻው ውድቀት መሆኑን አምኖ ራሱን ለሥራ ጥረት  ያዘጋጃል፡፡
  5. የተጋነነ የቤት ኪራይ እንዳይኖር መቆጣጠር፡- መንግሥት እንደ ነዳጅ፣ ዘይት፣ ስኳር ባሉት መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ቁጥጥርና አልፎ አልፎም ድጎማ ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዋና ዋና የአገሪቱ ከተሞች የቤት ኪራይ ውድነት የነዳጁ ጭማሪ ከሚያሳድረው ጫና ጋር ተዳምሮ የሚያደርሰው ጉዳት እየባሰ ነው፡፡ የበርካታ ዜጎች የዕለት ተዕለት ጭንቀት እየሆነ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት ካለበት ውስብስብ አገራዊ ችግሮች አኳያ ትኩረት ሰጥቶት በተግባር የሚውል አስቸኳይ የቤት ኪራይ ዋጋ መቆጣጠሪያ መመሪያ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡

ማጠቃለያ

        የተጋነነ የቤት ኪራይ ውድነት በከተማ የሚኖሩ በርካታ ተከራዮች ላይ የኑሮ ጭነቀት ፈጥሯል፡፡ በተለይ ወደ  ሥራው ዓለም የሚቀላቀሉ ወጣቶች ላይ አስጨናቂነቱ የከፋ ነው፡፡ ከገቢያቸው ብዙውን ለቤት ኪራ ከፍለው በቀረው ለመኖር አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ለሙስናና ለጉቦ ማመቻቸት ተገቢ እንዲሆነ ያስባሉ፡፡ ብዙዎችም በኑሮ ተስፋ በመቁረጥ አገርና ወገንን በመጥላት ስደትን ይመርጣሉ፡፡ በመሆኑም ችግሩ አሳሳቢ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ሊገኝለት የሚችል ችግር ነው፡፡ ችግሩን ለመከላከል ለመቀነስና ለመፍታት የሚደረገው ትግል መስዋዕትነት ቢጠይቅም፣ የችግሩ አሳሳቢነት ከታመነበት ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ አሁን የምንከፍለው መስዋዕትነት ከሌሎች ችግሮች ጋር ተዳምሮ ከሚያደርሰው ጉዳት አኳያ ታይቶ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ለቆመ መንግሥት  መፍትሔ መፈለግ በአንፃራዊ መልኩ ቀላል ነው፡፡

(ዳዲ ገብረ ሐዋርያ፤ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...