Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉብኝትና የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ገመና

የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉብኝትና የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ገመና

ቀን:

በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ የስፖርት ዘርፎች የተዋቀሩ ከ20 በላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ይገኛሉ፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ የተቋቋሙበትን የስፖርት ዘርፍ የመምራት ብቃትና አቅም ሊኖራቸው ቀርቶ ለራሳቸው ህልውና እንኳ ጣር ውስጥ የሚገኙ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ ለስሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽን የሚል መጠሪያ ቢጎናፀፉም የሚገኙበት ሁኔታ ሲታይ ግን አገር አቀፍነት የማይገልጻቸው ከአንድ የመንደር ስፖርት ማኅበር ያነሰ አቅምና ይዘት ላይ እንደሚገኙ ማሳያዎችን መመልከት ይቻላል፡፡

በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የተዋቀረው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቀጣይ ሊከውናቸው ያሰበው ዕቅድ ዕውን ይሆን ዘንድ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የመስክ ጉብኝት አድርጓል፡፡ ሪፖርተር ከጉብኘቱ ለመረዳት እንደቻለው አብዛኞቹ በቁሳቁስለ፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኒክና በመሳሰሉት መመዘኛዎች ሲፈተሹ ለብሔራዊ ፌዴሬሽንነት እጅግ የሚበዛባቸው አነስተኛና ጥቃቅን የሚመስሉ ናቸው፡፡

በቅርቡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን የአመራርነት ድርሻ የተረከበው አዲሱ አመራር የመስክ ጉብኝት በዋናነት በኦሊምፒክ ኮሚቴው፣ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና መንግሥት መካከል የሦስትዮሽ ስምምነት በመፍጠር ስፖርቱ ከሚገኝበት አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሚገኙበት ወቅታዊ ሁኔታ ግን፣ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው በጉብኝቱ ወቅት ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሥራ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

እንደ ተናጋሪዎቹ ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት ሁለት ወይም ራሱን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ጨምሮ ሦስት ፌዴሬሽኖች ካልሆኑ በስተቀር ብዙዎቹ ሦስት በሦስት በሆነች ክፍል ውስጥ ሆነው ‹‹ብሔራዊ›› የሚለውን ስም ብቻ ይዘው ይገኛሉ፡፡ የቢሮ ጉዳይ በዋናነት ይጠቀስ እንጂ፣ በጀትና መሰል የቁሳቁስ እጥረት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ ህልውና ፈታኝ ሆኖ እንደሚገኝ ጭምር ተነግሯል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው እንደ ዕቅድ ሲቀርብ የነበረው ፌዴሬሽኖቹ አሁን ከሚገኙበት ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መላቀቅ ይችሉ ዘንድ የበጀትና የቁሳቁስ ድጋፍ ጥያቄ ዋናውና ብቸኛው እንደነበርም ተስተውሏል፡፡

ለብዙዎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ተመሳሳይ ጥያቄ መነሻው የችግሩ ስፋትና መጠን መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ነገር ግን ደግሞ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለዘለቄታዊ መዋቅራዊ ለውጥ በመፍትሔነት ለሚቀርበው ቢዝነስ ፕላን ከአንዳቸውም ሲቀርብ አለመደመጡ አግራሞትን መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በዕለቱ በነበረው የመስክ ጉብኘት ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የውድድር ተሳትፎን ለማስፋት የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ወይም የመንግሥት ድጎማ አስፈላጊ መሆኑ የተንፀባረቀበት ተሞክሮ እንደነበርም መመልከት ተችሏል፡፡

በጉብኘቱ ዕለት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስተቀር ሌሎቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ከኦሊምፒክ ኮሚቴው ጋር ተገናኝተው በወቅታዊ ክፍተቶቻቸውና በሚያስፈልጓቸው ድጋፍና ክትትል ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ የመስክ ጉብኝቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል የሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አመራሮች በተገኙበት ግማሽ ቀን የፈጀ ውይይት  ተደርጎም ነበር፡፡ በመድረኩ ለሁሉም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መዳከም ምክንያት ሆኖ ሲቀርብ የነበረው፣ ለዘርፉ ቅርበት የሌላቸው በዋናነትም የአመራርነቱ ሚና በቂ ጊዜ በሌላቸው የመንግሥት ኃለፊዎች መያዙ ለኦሊምፒክ ኮሚቴው ከቀረቡት ጥያቄዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

መድረኩን የመሩት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በመስክ ጉብኝቱ መግቢያ እንደተገለጸው፣ የመስክ ጉብኝቱም ሆነ ይህ ውይይት ያስፈለገበት ምክንያት በዋናነት የሦስትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር ለስፖርቱ የሚበጀውን የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመድረኩም አስፈላጊነት እንደነዚህ የመሰሉ የሐሳብ ልዩነቶች እንዲንፀባረቁና በግብዓትነት መወሰድ ያለባቸው እንዲወሰዱ መሆኑን ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹የሦስትዮሽ ግንኙነት›› ሲሉ ከኦሊምፒክ ኮሚቴው መዋቅራዊ አደረጃጀት ጭምር ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የመንግሥት አካሉን፣ ባለሀብቱንና ሙያተኞችን ያማከለ እንዲሆንና በዚህም የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በመድረኩም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ከበጀትና ድጋፍ አሰጣጥ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አቅም በፈቀደ መጠን ማገዝ እንዳለበት፣ ይህ ማለት ግን ፌዴሬሽኖች ገና ለገና ድጋፍ ይደረግልናል በማለት እጅና እግራቸውን አጣጥፈው መቀመጥ እንደሌለባቸው ጭምር ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እንደሚያስተዳድሩት የስፖርት ባህሪ አቅማቸውን ማጎልበት የሚችሉበትን ቢዝነስ ፕላን ማቀድና መንቀሳስ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ይህም ኦሊምፒክ ኮሚቴውም ሆነ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ዕቅዶቻቸውን የጋራ ለማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሚፈጥርላቸው ጭምር በመድረኩ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝም በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ለሚደረገው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የስፖርት ቤተሰቡ ዓላማና ግቡን በሚረዳበት መልኩ እንዲከናወን ዝግጅት ከወዲሁ መጀመር እንደሚገባ እንዲሁም ክልሎችም ሆኑ የከተማ አስተዳደሮች ውድድሩ ከዋንጫና ሜዳሊያ ባለፈ ትርጉም እንዲኖረው ማሰብና ለዚያም መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

እንደነዚህ የመሰሉ አገር አቀፍ ውድድሮች ሊያስገኙ ከሚችሏቸው ፋይዳዎች በዋናነት፣ አገሪቱን በዓለም የውድድር መድረኮች ሊወክሉ የሚችሉት አትሌቶችን ማፍራት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ መድረኩ በመጨረሻም ቶኪዮ ላይ ለሚደረገው የ2020 ኦሊምፒክ ከተወሰኑ የአትሌቲክሱ ተሳትፎ በተጨማሪ በውኃ ዋና፣ በብስክሌት፣ በቦክስ፣ በወርልድ ቴኳንዶ፣ በእግር ኳስና ያለ ማጣሪያ በቀጥታ ተሳትፎ በሚደረግባቸው እንደ ዒላማ ተኩስ በመሳሰሉት የአገሪቱን ተሳትፎና ተወዳዳሪነት ማስፋት እንደሚቻል ጭምር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ለዕቅዱ ተግባራዊነት ደግሞ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ያልዘመነውን የአሠራር ሥርዓት በአግባቡ መፈተሽና ማስተካከል እንደሚገባም ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሚያስተዳድሩት ተቋም በዚህ ረገድ ራሱን ለመፈተሽ መዘጋጀቱንና ይኼም ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚከታተል ማለትም በቴክኒካል፣ በአስተዳደር፣ በሕግና በሌሎችም ራሱን የቻለ ዲፓርትመንት እንደሚያቋቁም ጭምር አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...