Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልለአገር በቀል ትምህርት ቦታ መሰጠት እንዳለበት ተጠቆመ

ለአገር በቀል ትምህርት ቦታ መሰጠት እንዳለበት ተጠቆመ

ቀን:

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት  ለአገር በቀል ትምህርት ቦታ መሰጠት እንዳለበት ተጠቆመ፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖቶች ያሉ ዕድሜ ጠገብ አስተምሮቶች በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት ገሸሽ እንደተደረጉ፣ ነገር ግን ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር የሚጣጣሙበት መንገድ መፈለግ እንዳለበት የተጠቆመው ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በተደረገው ጉባዔ ላይ ነው፡፡

በአካዳሚው ‹‹የኢትዮጵያ ባህላዊ ትምህርት ምንነት፣ ባህሪያትና ለዘመናዊ ትምህርት ያለው አስተዋጽኦ›› በሚል በተዘጋጀው የአንድ ቀን ጉባዔ ላይ እንደተመለከተው፣ ቀደምቶቹ ባህላዊ ትምህርቶች በተለያየ ምክንያት እየተዳከሙ ከመምጣታቸው ባሻገር፣ በዘመናዊው ትምህርት ሒደት ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ በጉባዔው ስድስት ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ አገር በቀል ትምህርቶች በምን መንገድ በዘመናዊው ትምህርት ውስጥ መካተት ይችላሉ የሚለውን ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ጥናቶቹ በክርስትናና እስልምና ሃይማኖቶች ያሉ ትምህርቶች መነሻቸውን፣ አሰጣጣቸውንና በዘመናዊ ትምህርት ሊኖራቸው የሚችለውን ቦታም አሳይተዋል፡፡ ‹‹ጥንታዊው የኢትዮጵያውያን ትምህርት በሥነ ከዋክብት ጥናት፣ በአየር ትንበያና በዘመን አቆጣጠር›› በዶ/ር ሰሙ ምትኩ የቀረበ ጥናት ነው፡፡

ጥናቱ የዘመን አቆጣጠር፣ የሥነ ከዋክብት ጥናትና አየር ትንበያን የያዘው ጥንታዊው ትምህርት በዘመናዊ ትምህርት እንዳልተካተተ የሚያትትት ሲሆን፣ አጥኚውም ‹‹ትምህርቱ ታሪክ ለመሆን እየተቃረበ ነው፤›› ብለዋል፡፡ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት የዕውቀቱ ባለቤቶች ትምህርቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፉበት መንገድ ሳይመቻችላቸው እያለፉ በመሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በከዋክብት ጥናት እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ ያሉ ትምህርቶች ላይ ያተኮሩ ዘመናዊ ተቋሞች መነሻቸውን አገር በቀል ዕውቀት ማድረግ እንዳለባቸውና ባህላዊውን ትምህርት በማጥናት ማሳደግ እንደሚገባቸውም አጥኚው አሳስበዋል፡፡

‹‹አንድምታ የኢትዮጵያ ትርጓሜ መጻሕፍት ጥበብ ምንነት፣ ታሪክና አስተዋጽኦ ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፤›› የተሰኘ ጥናት ያቀረቡት ዶ/ር ዮሐንስ አድማሱ፣ አንድምታ (ግዕዝን ወደ አማርኛ የመተርጎም ስልት) ለዘመናዊ ትምህርት ያለውን አስተዋጽኦ አቅርበዋል፡፡

አንድምታ የአገሪቱን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና መልክዓ ምድር ለማጥናት አጋዥነቱ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ የአንድምታ የመማር ማስተማር መንገድም በዘመናዊው ትምህርት ሊተገበሩ የሚችሉ ጠቃሚ ሒደቶች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ እንደ አጥኚው ገለጻ፣ አብዛኛው ዕውቀት ያለው በቃል በመሆኑ በጽሑፍ ካልሰፈረ የመጥፋት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡

የጉባዔው ተካፋዮችም ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹አገር በቀል ትምህርት ሙዝየም ውስጥ የሚቀመጥ ሳይሆን በተግባር መዋል ያለበት ዕውቀት ነው፤›› ያሉ የጉባዔው ተካፋይ ነበሩ፡፡ ዘመናዊ ትምህርት የሚሰጥባቸው ተቋሞች አገር በቀል ትምህርቶች እንዲታወቁና ጥቅም ላይ እንዲወሉ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡

በአቶ ዘለዓለም መሠረት ‹‹ቅኔ ምንነቱና የትምህርት አሰጣጡ››፣ በዶ/ር ውቤ ካሳዬ ‹‹አገር በቀል ዕውቀት ለዕድገት ያለው ጠቀሜታ ከባህላዊ ዜማ ትምህርት (ዜማ ቤት) አኳያ ሲታይ›› እና በአቶ አብዱልመሊክ አቡበከር ‹‹ሐረርን እንደማጣቀሻ የወሰደ ባህላዊ እስላማዊ ትምህርት በኢትዮጵያ›› በተሰኙ ጥናቶችም ለአገር በቀል ትምህርት ትኩረት እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካውያን በአጠቃላይ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ዞር ብለን አላየናቸውም›› ያሉት ዶ/ር ውቤ ዘመናዊ ትምህርት ሀገር በቀል ዕውቀትን በትምህርት አሰጣጥ ዘዴ (ፔዳጐጂ) ማካተት እንደለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ በክርስትናና እስልምና ሥር ያሉ ትምህርቶች ላይ ያንዣበበው የመጥፋት አደጋ አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል ብለዋል፡፡ ትምህርቶቹ የሚሰጡባቸው ባህላዊ ትምህርት ቤቶች በገንዘብ ማጣት ይፈተናሉ፡፡ የተማሪዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ትምህርቶቹ ጠቀሜታ እንዳላቸው የሚገነዘቡ ሰዎችም ውስን ናቸው፡፡

ጃፓን፣ ቻይናና ሌሎችም በርካታ አገሮች ባህላዊ ትምህርቶቻቸውን ከዘመናዊው ጋር በማዳቀል እንደሚጠቀሙ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ባህሩ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የጐላ እንቅስቃሴ አልተደረገም፤ አገሪቱ ከአገር በቀል ትምህርቶች የምታገኘውን ጥቅምም እያገኘች አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አካዳሚው ለጥንታዊው የኢትዮጵያ ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ መድረክ ማዘጋጀቱ ውዳሴ ያተረፈለት ቢሆንም በአፍሪካ የመጀመርያው ፈላስፋ እንደሆነ የሚነገርለት የ17ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያዊው ዘርዐ ያዕቆብና ተማሪው ወልደ ሕይወት ሥራዎችና ኢትዮጵያ በፍልስፍናው ዘርፍ የነበራትን ቦታ የሚያሳይ ጥናት ለምን አልቀረበም? የሚል ጥያቄ ያነሱ ነበሩ፡፡ አስተባባሪዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ብቻ በመወሰናቸው በአገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት ያደረጉ፣ ባሁኑ ጊዜም እያደረጉ ያሉ ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም በዘርዐ ያዕቆብ ላይ የሠሩ እያሉ ለምን ለመጋበዝ አልሞከሩም የሚል አስተያየት በመድረኩ ላይ ያጡትን ዕድል በሻይ ሰዓት ያንፀባረቁም ነበሩ፡፡ ለዘመናዊ ትምህርት ከሚኖረው አስተዋጽኦ አኳያም የመነጋገሪያ ርእስ ሆኖ ሊቀርብ ይገባ ነበር፡፡ በመጀመርያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዘርዐ ያዕቆብ መቼ እንደነበር እንኳ በቅጡ ባለመመዝገቡ በመማሪያ መጻሕፍት ላይ ከንጉሡ የ15ኛው ክፍለ ዘመን ዘርዐ ያዕቆብ ጋር በመቀላቀል ሲዛባ ኖሯልም ብለዋል፡፡

ጉባኤው በአንድ ቀን ብቻ በመወሰኑ በቂ ውይይት ለማድረግ አለመመቸቱ የተጠቆመ ሲሆን፣ በተለይ ሐረርን እንደማጣቀሻ የወሰደ ባህላዊ እስላማዊ ትምህርት በኢትዮጵያ ያለውን ቦታ በተመለከተ የቀረበውን ጥናትና፣ በፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ የቀረበው የጥንታዊው የኢትዮጵያ ትምህርት ታሪክ የምርምር ጥያቄዎችን ተከትሎ የቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሳይሰጥባቸው ጉባኤው መበተኑም ቅሬታ አሳድሯል፡፡ ሌላው ጥያቄ የነበረው የእስልምና ባህላዊ ትምህርትን በተመለከተ የቀረበው ጥናት አንድ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ አዘጋጆቹ ከነበረው የዝግጅት ጊዜ አንፃር በመድረኩ የቀረበው እሱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከቀረቡት ወረቀቶች አራቱ ከጥናታቸው ጋር ግንኙነት ያላቸውና በውስጡም ያለፉ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፣ በሥነ ከዋክብት ጥናት፣ በአየር ትንበያና በዘመን አቆጣጠር ላይ ወረቀት ያቀረቡት እንደተናገሩት፣ ሁለቱ አቅራቢዎች የማቲማቲክስ ባለሙያ መሆናቸው [የባህላዊ] ትምህርቱ ባለሙያ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹የዚህ ባለሙያ አይደለሁም፤ አጥናና አቅርብ ስለተባልሁ ነው፤ አንዳንድ ነገሮችን አላውቅም ማለት አይደለም›› ማለታቸውን ያስተዋሉት አንድ የጉባኤው ተሳታፊ፣ አካዴሚው የባህላዊውን ትምህርት ዘርፍ ብዙ ባህርያትና አስተዋጽኦ በጥልቀት የሚፈትሹ ትንተናዎች በጉባኤው ይቀርባሉ ካለው ጋር እንዴት ሊታረቅ ይችላል? ብለዋል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...