Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሕገወጥ ማስታወቂያዎች ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ ነው

በሕገወጥ ማስታወቂያዎች ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ ነው

ቀን:

የምግብና ምግብ ነክ ነገሮች ማስታወቂያ መሥፈርት ሳያሟሉ የሚሠሩ አሳሳችና ፈር የለቀቁ ማስታወቂያዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድ መሆኑ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ ከእውነታው ውጪ ግነት የበዛባቸው ሐሰተኛና ማኅበረሰቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የመምራት ይዘት ያላቸው ማስታወቂያዎች ዕገዳ ከመጣል ባለፈ ሕጋዊ መፍትሔ እንደሚሻ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ ይህ የተገለጸው ባለሥልጣኑ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በጤና ቁጥጥር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው የሦስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው፡፡

የማስታወቂያ አዋጁ ከወጣ አንድ ዓመት እንደሞላው፤ ከፀደቀ ጀምሮም ባለድርሻ አካላት በአዋጁ መሠረት እንዲሠሩ የማስገንዘብ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የገለጹት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የማስታወቂያ ክትትልና ድጋፍ ቡድን አስተባባሪው አቶ እሱባለው ሸዋወልድ ‹‹እስካሁን በቂ ግንዛቤ መፍጠር ችለናል፡፡ ከሕግ ውጪ የሆኑ ማስታወቂያዎች ሲያጋጥሙንም አስተካክለው እንዲሠሩ ስናስተምር ቆይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ሕግ ፊት እናቀርባቸዋለን፤›› ብለዋል፡፡ የሕገወጥ ማስታወቂያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ይህም በምግብና መጠጥ ነክ ማስታወቂያዎች ላይ እንደሚያይል አክለዋል፡፡

በጉዳዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የዋና ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐሪ ብርሃነ እንዳሉት በጤና ተቋማት፣ በምግብና መጠጥ ነክ ማስታወቂያዎች ላይ የሚታዩት ችግሮች አሳሳቢና አፋጣኝ መፍትሔ ይሻሉ፡፡ ‹‹ከፍተኛ ክሊኒክ የሚል ለክሊኒኮች የተሰጠ ደረጃ በሌለበት ከፍተኛ ክሊኒክ የሚሉ ማስታወቂያዎች ያጋጥማሉ፡፡ በተጨማሪም አገልግሎት መስጠት የማይችሉ መሣሪያዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ የሚያስነግሩ ሕዝቡን የሚያሳስቱ ማስታወቂያዎች ይስተዋላሉ፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም የ24 ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ ከሌላው ጤና ተቋማት የላቀ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች እንዳሏቸው በማስታወቂያ በማስነገር ታካሚው ተገቢውን ሕክምና እንዳያገኝ እንቅፋት የሚሆኑ ማስታወቂያዎች በርካታ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጠጥና ምግብ ነክ ማስታወቂያዎች ላይም እንዲሁ ተመሳሳይ ችግር እንደሚስተዋል ‹‹ከፍተኛ ጨው፣ ስብና የስኳር መጠን ያላቸውን ምግብና የአልኮል መጠጦች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያበረታቱ ማስታወቂያዎች በማስነገር ለጤና ጎጂ የሆኑ ነገሮችን በማኅበረሰቡ እንዲዘወተሩ የሚገፋፉ ማስታወቂያዎች በዝተዋል፤›› ያሉት አቶ መሐሪ መሰል ማስታወቂያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ እንደመጣና አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያሻቸው ገልጸዋል፡፡

ከመገናኛ ብዙኃን ውጪ የሚተዋወቁ በኔትወርክ ማርኬቲንግ የሚሸጡ መድኃኒቶች የሚተዋወቁበት መንገድም ለማኅበረሰቡ ጤና ሥጋት መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡ አቶ ብርሃን ፍቅሩ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የምግብ ሕግ ዝግጅት ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ተጨማሪ ምግብ (Supplement) ተብለው የሚሸጡ ምርቶች ማስታወቂያ ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

‹‹ስለተጨማሪ ምግቦች ጥቅም የሚያስተዋውቁ ብቁ ባለሙያዎች የሉም፡፡ የሚተዋወቀውም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ሲሆን፣ ከአንድ ተጨማሪ የምግብ ዓይነት ሁሉንም ዓይነት ማዕድን እንደሚገኝ፣ በማንኛውም መጠን ቢወሰዱ ችግር እንደማይፈጥሩ አድርገው ያስተዋውቃሉ፤›› የሚሉት አቶ ብርሃን ከመጠን በላይ ሲወሰድ ለተለያዩ የውስጥ ደዌዎች እንደሚያጋልጥ በዘርፉ የሚሠሩ ማስታወቂያዎችም ሊጤኑ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እስካሁን የተሰጠው የማስተማሪያ ጊዜ ገደብ በቂ መሆኑን የገለጹት አቶ እሱባለው ከዚህ በኋላ በሚያጋጥሙ መሰል የማስታወቂያ ስህተቶችን ወደ ሕግ በመውሰድ ማስታወቂያ ከመሥራት እስከ ገንዘብ ቅጣት የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣል፤ ማስታወቂያ አስነጋሪውም የማስታወቂያ ተቋማትም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ የሚገኙ ሕገ ወጥ መድኃኒቶችን መቆጣጠር የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት በዚህ ዓመት እንደሚዘረጋ የባለሥልጣኑ ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደመቀ ገልጸዋል፡፡ ሥርዓቱ ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ጋር በመተባበር የሚዘረጋ ሲሆን፣ ሕገ ወጥ መድኃኒቶችን በስልክ መልዕክት አማካይነት አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ የሚያስችል መሆኑን አክለዋል፡፡ በመድኃኒቶች ጀርባ የሚዘጋጅን የሚስጥር ቁጥር ፍቆ በስልክ በመሙላትና ለባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መልዕክት በመላክ መድኃኒቶች በሕጋዊ አልያም በሕገወጥ መንገድ የገቡ መሆናቸው የሚለይበት የስልክ ቴክኖሎጂው ሕገወጥ የመድኃት ዝውውርን በመቆጣጠር ረገድ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

‹‹ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ይታወቃሉ፡፡ የት እንደተሰራጩ ጭምር ተመዝግቦ ይያዛል፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ የተላከው መልዕክት ወደ ሥርዓቱ እንደገባ የመድኃኒቱን ሕጋዊነትና ሕገወጥነት የሚለይ የጽሑፍ መልዕክት ለደንበኛው እንደሚደርስ ጠቁመዋል፡፡

መድኃኒቱ ሕገወጥ ሆኖ ከተገኘም መልዕክቱ የተላከበትን አካባቢ በጉግል ማፕ በመድረስ አስፈላጊው ዕርምጃ እንደሚወሰድበት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የሚዘረጋው ይህ ሥርዓት በሌሎች አገሮች ተሞክሮ አበረታች ውጤት አስገኝቷል፡፡ በአገር ውስጥም በገበያው ላይ ከሌላው በተለየ ተፈላጊነት ባላቸው መድኃኒቶች ላይ እንደ ሕፃናትና የእናቶች መድኃኒት ላይ የሚሞከር ሲሆን፣ በቀጣይ በሁሉም የመድኃኒት ዓይነቶች እንዲሁም በመዋቢያ ዕቃዎችም ሆኑ ምግብና መጠጥ ነክ ነገሮች ላይ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው አቶ የሁሉ ገልጸዋል፡፡

በአዳማ ከተማ ለሦስት ቀናት በተካሄደው ሥልጠና የትምባሆ ቁጥጥርና ፀረ ተህዋሲያን መድኃኒት መላመድም የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

       

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...