Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የእንስሳት ማቆያ

በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የእንስሳት ማቆያ

ቀን:

ሰው መሆን ሌላ ነው

ቀን – ደምን

ደም – ቀለምን

ቀለም – ደግሞ – ስምን

       ሲጠራ – ሲመራ

ሰው መሆን ገረመኝ

እማ – ያገባችን

       ቀን ሽቶኝ – ለመጣሁ

ቀን ትቶኝ – ልሔደው

ተልኬ በመጣሁ

ነፋስ እገዛ ብዬ

ቀን – ደምን

ደም – ቀለምን

ቀለም ደግሞ ስምን

ሲገዛ – አ – የሁ፡፡

ቁራ ልሁን – እርግብ

የቱ ይሻለኛል … ?

      ገበያው ጎተተኝ – ያልመጣሁበቱ

አደራው ከበደኝ – የታመንኩበቱ፡፡

እርግብ – ልሁን – ቁራ

የቱ ይሻለኛል … ?

      ሰው መሆን – ሲያስጠላ

      ሰው መሆን – ሲያስፈራ

      ዕርግብ ልሁን ቁራ … ?

  • አዳነ ድልነሳው ጨለማን ሰበራ፣ 1997

************************

መግባባት

ለየትኛውም ዓይነት ስኬታማ ግንኙነት መግባባት ቁልፍ ነገር እንደሆነ እናውቃን፡፡ ሁሉም ስኬታማ ጥምረቶች የተመሠረቱት በመልካም መግባባት ላይ ነው፡፡ ለፍቅር ግንኙነቶች ውድቀት ዋናው መንስኤ የመግባባት ችግር ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ወንዶች ስለፍቅር ግንኙነቶች ከሴት ጓደኛቸው ጋር ማውራትን አይወዱም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ውይይት ያለውን ጠቀሜታ አጥተውት አይደለም፡፡ ባለሥራው ወንድ የሥራ ገበታው ላይ ከሚያገኛቸው ባልደረቦቹ ጋር ያለው ተግባቢነት አመርቂ ሆኖ ሳለ ከፍቅር አጋሩ ጋር ሸካራ ግንኙነት ሲኖረው ግራ ያጋባል፡፡

አለመግባባት የፍቅር ግንኙነታችሁን ማገር ለሚያፈርሱ ግብዓቶች የመሠረት ድንጋይ ይሆናል፡፡ ይህ ችግር በሁሉም ጥቃቅን ሕይወታችሁ ላይ ሊስተዋል ይችላል፡፡ በምግብ ቤት አሊያም በመለስተኛ ሆቴል ውስጥ እራት ለማዘዝ ረጅም ጊዜ ይወስድባችኋል፡፡ እነዚህን ያለመግባባት ችግሮች በቶሎ መፍታት ካልቻላችሁ ሥር ይሰደዳሉ፡፡ ለብርቱ ጥል የሚጋብዟችሁ ጥቃቅን ሰበቦች ይሆናሉ፡፡ አንዴ ጥል ከጀመሪችሁ ደግሞ ባልሸነፍ ባይነት ራሳችሁን ከተጠያቂነትና ከስህተተኝነት ለማዳን ትከራከራላችሁ፡፡ ያለፉ ጥቃቃን ችግሮቹን እያነሳሽ የቃላት ዝናብ ታዘንቢበታለሽ፡፡ እሱም ተመሳሳዩን ያደርጋል፡፡ አንዴም ቢሆን አስባችሁት የማግተውቁት ነገር ሁሉ እየተነሳ ሁለታችሁንም ለብስጭት ይዳርጋል፡፡ ባለሥራ ወንዶች ራሳቸውን ለመከላከልና ከተጠያቂነት ለማዳን የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም፡፡

  • ናኦሚ፣ የወንዶች ገመና፣ 2000

************************

በሠርጉ ቀን የታሰረ ሙሽራ

ጉዳዩ የተፈፀመው በኬንያ ነው፡፡ ሙሽራው ቻርለስ ማኖአ ከሙሽሪት ካሮ ጋር የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በቤተክርስቲያን እፈፀሙ ነበር፡፡ ታዳሚዎችም የሠርጉን ሥነ ሥርዓት እየተከታተሉ ነው፡፡ ድንገት የስምንት ወር ሕፃን የታቀፈች እናት ከቤተክርስቲያኑ ተገኝታ ‹‹ማኖአ ባሌ ነው›› ስትል በጠበጠች፡፡

የኬንያው ስታንዳርድ እንደዘገበው፣ የሠርጉ ታዳሚዎች ሕፃን ልጇን ታቅፋ ‹‹ልጁም ከባሌ ማኖአ የወለድኩት ነው›› እያለች የምትናገረውን እናት መደብደብ ጀመሩ፡፡ ሠርጉ መበጥበጡን ተከትሎ ከስፍራው የደረሰው ፖሊስ፣ ማኖአን ከሠርግ ድግሱ ነጥሎ ወደ እስር ቤት ወስዶታል፡፡

ሊዲያ አቺንግ የተባለችው ሚስቱ ባነሳችው የ‹‹ባሌ›› ነው ጥያቄ መሠረት የቤተክርስቲያኑ ፓስተር የሙሽሮቹን አንድነት ሰርዘውታል፡፡

‹‹ሠርጉ ቢቀጥልም እንኳን ማኖአ ባሌ ነው፡፡ የልጄም አባት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ጥሎን ጠፍቷል፡፡ ሊያገባ ነው የሚል ወሬ ሰምቼ ነው የመጣሁት›› ስትል አቺንግ ተናግራለች፡፡

ማኖአ በዜግነቱ ኡጋንዳዊ ሲሆን፣ ኬንያ የገባውም በሕገወጥ መንገድ ነው፡፡ በኬንያ ተደብቆ እንደነበር፣ በኡጋንዳ መንግሥትም በመፈለግ ላይ እንዳለ ዘገባው ያሳያል፡፡

**********************

ኦንላየን ሕፃን ለመሸጥ የሞከረችው ሴት ወንጀለኛ ተባለች

በደቡብ አፍሪካ የ20 ዓመቷ እናት ሕፃን ልጇን ኦንላየን በ346 ዶላር ለመሸጥ በመሞከሯ ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ወንጀለኛ እንዳላት ኒውስ ትዌንቲፎር ዘግቧል፡፡ ወንጀለኛ የተባለችው እናትም ‹‹ያደረግኩት ነገር ስህተትና ሕገወጥ መሆኑን አምናለሁኝ የምከራከርበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለኝም›› ብላለች፡፡ ፖሊስ እንዳስታወቀው ወንጀለኛዋ የተያዘችው ሕፃኑን በኢንተርኔት ገበያ መሸጧ በመጠቆሙ ከአንድ ወር በፊት ነው፡፡ ይህን ያደረገችው እናት ለጊዜው በዋስ ብትለቀቅም በቤት ውስጥ የቁም እስረኛ እንድትሆን መወሰኑን ዘገባው ያመለክታል፡፡

************************

በንቅሳት መመሳሰል ለ16 ዓመታት የታሰረው ሰው በመጨረሻ ተለቀቀ

የ46 ዓመቱ ሉዊስ ሎሬንዞ ቪርጋስ እ.ኤ.አ. በ1995 እስር ቤት የገባው ሦስት ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል ገድሏልም ተብሎ በመታመኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ቪርጋስ ለእስር የተዳረገው እውነትም ገዳዩ እሱ በመሆኑ ሳይሆን በ20 ዓመታት ውስጥ 39 ሴቶችን ከደፈረ ሰው ጋር ተመሳሳይ ንቅሳት ስላለው ነበር፡፡

በመጨረሻ ነፃ ሊወጣ የቻለው በተደጋጋሚ ጉዳዩ ተጣርቶ ይለቀቅ የሚል ተደጋጋሚ ዘመቻ በመካሔዱና የዲኤንኤ ምርመራ በመደረጉ እንደሆነ የዘኢንዲፔንደንት ዘገባ ያመለክታል፡፡

ትክክለኛው ወንጀለኛ በኤፍቢአይ እየተፈለገ ሲሆን፣ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በሙሉ ማለት ይቻላል ከግራ ዓይኑ ሥር የእንባ ዘለላ የሚመስል ንቅሳት እንዳለው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ መርማሪዎች ንቅሳት ተብሎ የተገለጸው ምናልባትም ጠባሳ ሳይሆን እንደማይቀር ጠርጥረዋል፡፡

ሚስተር ቪርጋስ ከዚህ ወንጀል በመጨረሻ ነፃ መውጣት ቢችልም የስደተኝነት ያልተቋጨ ጉዳይ ስላለው በእስር ቤት ሊቆይ የግድ ሆኗል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...