Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መሥራቴን ሰው ያያል ብዬ አስቤ አላውቅም››

ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር፣ የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር

ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ ረዥም ዓመታት በዳኝነት አገልግለዋል፡፡ ጠበቃም ነበሩ፡፡ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሲቋቋም ደግሞ በማኅበሩ ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ የማኅበሩ የቦርድ አባል የነበሩት ወይዘሮ ማሪያ በወቅቱ የማኅበሩ የሕግ ቢሮዎች እንዲከፈቱም ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የሕግ ምክር አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማኅበሩ ይሄዱ የነበሩ ሴቶችና ሕፃናት ማረፊያን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ያጋጥሟቸው ስለነበር ጥቃት የደረሰባቸውና የምክር አገልግሎት የሚሰጣቸው ሴቶችና ሕፃናት ያርፉበት ዘንድ ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የቀድሞውን ጾታዊ ጥቃት ተከላካይ ማኅበር የአሁኑን የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር እ.ኤ.አ. 2003 አቋቁመዋል፡፡ ወደሥራ የገቡት ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በማኀበሩ ምስረታ ግንባር ቀደም የነበሩት ወይዘሮ ማሪያ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በየዓመቱ በአሶሴሽን ኦፍ ውሜን ኢን ቢዝነስ (AWiB) የሚያዘጋጀው ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በማኅበሩ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ ምሕረት አስቻለው የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት ከወይዘሮ ማሪያ ሙኒር ጋር አጭር ቆጥታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ዋና ዋና እንቅስቃሴዎች ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ሦስት ነገሮች ላይ እናተኩራለን፡፡ ዋናው ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የሚያገግሙበትና የሚለወጡበት መጠለያ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ እነዚህ ሴቶች አካላዊም ሥነልቦናዊም ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ተስፋ የቆረጡ ራሳቸውንም ማጥፋት የሚያስቡ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ከክፍለ አገር መጥተው አዲስ አበባ ላይ ከዘመድ ተጠግተው የሚኖሩ የቤት ሠራተኞችም ናቸው፡፡ እንደ ምግብና ሕክምና ያሉ አገልግሎቶች በመጠለያው ይሰጣል፡፡ እየቆየን እንደተገነዘብነው ደግሞ እነዚህ ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች ይህ ነው የሚባል ገቢ የሌላቸውና በኢኮኖሚ ጥገኛ የሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሴቶች የሙያ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረግ ጀመርን፡፡ በዚህም ጥሩ ውጤት አይተናል፡፡ ሌላው መጠለያዎቻችን በሚገኙባቸው አካባቢዎች አደጋዎች ሲደርሱ ለምሳሌ በአንድ አጋጣሚ አዳማ ላይ ጎርፍ በደረሰበት አጋጣሚ፣ ብዙ ሕፃናትና ሴቶች ዕርዳታ በፈለጉበት ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ በተመለሱበት ጊዜም ተንቀሳቅሰናል፡፡ ጾታዊ ጥቃትን መከላከል ላይም እንሠራለን፡፡ ይህን የምናደርገው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ አተኩረን ግንዛቤ በመፍጠርና አቅም በመገንባት ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በምንሠራባቸው ስድስት ትምህርት ቤቶች ሴቶችንም ወንዶችንም ተማሪዎች ስለ ሥነተዋልዶ ጤና፣ የአቻ ግፊት እንዲሁም የሕይወት ክህሎት ግንዛቤ እናስጨብጣለን፣ መምህራንን እንዴት የምክር አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ችግሮችንም እንዴት መመልከት እንዳለባቸው እናሰለጥናለን፡፡ በሌላ በኩል ወላጆች፣ መምህራንና ተማሪዎች አንድ ላይ የሚነጋገሩባቸውን መድረኮች እናመቻቻለን፡፡ ለተማሪዎች ዩኒፎርምና ሌሎችንም ዕርዳታዎች እናደርጋለን፡፡ የምንሠራባቸው ትምህርት ቤቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ለማኅበረሰብ መሪዎች ግንዛቤ እናስጨብጣለን፡፡ ምክንያቱም ጥቃቶች ሲደርሱ የመሸፋፈንና ሪፖርት እንዳይደረጉ የማድረግ ነገር ስላለ እንዴት ለፖሊስ ማመልከት እንዳለባቸው መረጃ እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለሌሎች አካላት ሥልጠና ትሰጣላችሁ?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ጥቃት የደረሰባቸው፣ ጥቃት የደረሰባቸውን የሚያገኙ ሰዎችም የሚሄዱት ወደ ፖሊስና ሴቶች ጉዳይ በመሆኑ ለእነዚህ አካላትም ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ሥልጠናው ፖሊሶችን የኮሚኒቲ ፖሊሶችንም ያካትታል፡፡ ይህንን የምናደርገው በአሥሩም ክፍለ ከተሞች ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጠለያው ላገገሙ ሴቶች የምትሰጧቸው የሙያ ሥልጠናዎች ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ማሪያ፡- የምግብ ዝግጅት፣ የእጅ ሥራ፣ የፀጉርና የሞግዚትነት ሥልጠናም እንሰጣለን፡፡ የምንሰጣቸው ሥልጠናዎች እንደ ሴቶቹ ሁኔታ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ እኛ መጠለያ ውስጥ ያሉ ሴቶች አንዳንዶቹ ፖሊስ ባደራ ያስቀመጣቸው በመሆናቸው ከመጠለያው ቅጥር መውጣት አይችሉም፡፡ እነዚህ ሴቶች የፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሌላ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ እነሱም ሊጠፉ ይችላሉ በሚል ሥጋት ነው እንዳይወጡ የሚደረገው፡፡ ሌሎቹ ግን ከጊቢ ወጥተው የቀርከሀ፣ ሥጋጃ፣ ቆዳ ሥራ ሥልጠናዎች ይወስዳሉ፡፡ በአንድ ወቅት ከግንባታ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሥራዎች ሥልጠና መስጠትንም ሞክረነው ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- መጠለያውን የሚለቅቁ ሴቶች እንዴት ነው የሚሰናበቱት?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ሙያ ሠልጠነው ሲወጡ ባዶ እጃቸውን አይወጡም፡፡ ብዙዎቹ ዘመድ የሌላቸው የክፍለ አገርም ልጆች ናቸው፡፡ እዚህ (አዲስ አበባ) እንሠራለን ለሚሉ ለሥራ የሚያስፈልጓቸውን ዕቃዎች እንገዛለን፡፡ ገንዘብ በእጅ አንሰጥም፡፡ የሦስት ወር የቤት ኪራይም እንከፍላለን፡፡ ልጅ ከወላጆቹ ቤት ሲወጣ ባዶ እጁን እንደማይወጣው ሁሉ ለተወሰነ ጊዜ የሚሆናቸውን እህል እናዘጋጅላቸዋለን፡፡ ጤናቸው ለሚፈቅድ ደግሞ ራሳቸውን ዳግም ከጥቃት ይከላከሉ ዘንድ የቴኳንዶ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ይህን የቴኳንዶ ሥልጠና አዲስ አበባም አዳማም ላይ እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የቴኳንዶ ሥልጠናውን ወስደዋል?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ሠራተኞችም ሥልጠናውን ይወስዳሉ፡፡ እኔም ሠልጥኜ ቢጫ ቀበቶ ላይ ደርሻለሁኝ፡፡ አሁን እየወፈርን ስለሆነ መቀጠል ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህ የሆነው ሠራተኞቻችን ጥቃት የደረሰባቸውን ይዘው ሲሄዱ ወይም ገፍቶ በመጠለያው ጥቃት ለመፈጸም ቢሞከር ለመከላከል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ የዓመታት እንቅስቃሴ ሊጠቀሱ የሚችሉ ስኬቶች የትኞቹ ናቸው?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ሕይወት ጨልሞባት ተስፋ የቆረጠችና ወደ ሞት እየሄደች ያለች ሴት ሕይወት ተቀይሮ መመልከት ትልቅ ነገር ነው ለኔ፡፡ በመደፈር የወለዷቸውን ልጆች አፍነው ለመግደል ሙከራ ያደረጉ ሴቶች በሥነ ልቦና ተረጋግተው ሕይወታቸውን ለማስተካከል ሲሞክሩ ማየት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ከባድ ሁኔታ ውስጥ ከነበሩ አንዷ አሁን በመጠለያው የፀጉር ሥራ አሠልጣኝ ስትሆን ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገብታ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተመረቀችም ወጣት አለች፡፡ አሁንም በዩኚቨርሲቲ ትምህርት እየተከታተለች ያለች ልጅ አለችን፡፡ ለእነዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየወሩ ገንዘብ እንልካለን ትምህርት ሲዘጋም እንደ ቤት ለዕረፍት እኛ ጋር ይመጣሉ፡፡ መጠለያው ምንም እንኳ ጊዜያዊ ቢሆንም በትምህርታቸው ጎበዝ የሆኑትን ልጆች እንደ ልዩ ኬዝ ነው የምናየው፡፡ እነዚህ ነገሮች ትልቅ ስኬቶቻችን ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አስቸጋሪ ሁኔታዎችስ?

ወ/ሮ ማሪያ፡- እኔ ፈተናን ተጋፍጦ በማለፍ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ሁሉም ነገር ያልፋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር አላውቅም፡፡ አንድ በር ቢዘጋ በሌላ እሄዳለሁኝ ቢሆንም ግን በዚህ ሥራ ትልቅ ፈተና የሆነብን የራሳችን የሆነ ቤት አለመኖር ነው፡፡ በመጠለያው ያለው ዕቃ በጣም ብዙ ነው ቤት ልቀቁ ሲባል ይህን ዕቃ ማጓጓዝ ፈተና ነው፡፡ ሌላ ቤት ለመከራየት ሲባል ቤቱ የሚፈለግበትን ዓላማ ስንነግራቸው ብዙዎቹ ለማከራየት ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ ቁልፍ ከሰጡን በኋላ ሐሳባቸውን የቀየሩም አሉ፡፡ የግድ ቤቱን ለምን እንደምንፈልገው መናገር አለብን፡፡ አንዳንዴ ግን የሚኖረውን ሰው ቁጥር ለመቀነስ ሁሉ እንገደዳለን፡፡ መጀመሪያ ላይ ለማከራየት አቅማምተው መጠለያውን ስናስመርቅ ጠርተናቸው የምንሠራውን ሲረዱ ያደነቁም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ችግር የራሳችን የሆነ ቋሚ መጠለያ ስለሌለን ነው፡፡ በእርግጥ ለኪራይ የሚወጣውም ገንዘብ ብዙ ሴቶች ሊረዱ የሚችሉበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዘንድሮው የAWiB ውሜን ኦፍ ኤክሰለንስ በአሸናፊነት መርጠዋል፡፡ ዕውቅናውን እንዴት ተቀበሉት?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ሥራ ሥሠራ መሥራት ያለብኝን ማከናወን እንጂ መሥራቴን ሰው ያያል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ሌላው የሚሠራውን ሰው ያያል እንዴ ነው ያልኩት በመጨረሻ ምክንያቱም መሥራቴን ብቻ ነበር የማውቀው፡፡ ማን እንደጠቆመኝም አላውቅም፡፡ መጀመሪያ ሰባት ውስጥ ገባሁኝ ከዚያ አንደኛ ስሆን ተደሰትኩኝ፡፡ የተደሰትኩት ለራሴ ብቻ ሳይሆን ይህ የብዙ ሰዎች ዕርዳታና ድጋፍ ያለበት በመሆኑ ነው፡፡ ቤተሰብን ጨምሮ፡፡ ስለዚህ ይህ የዚህ ሁሉ ዋጋ ነው፡፡ ሁለት ወንዶች ልጆች ናቸው ያሉኝ የእነሱን ጊዜ ሁሉ ሥራ ላይ ነው የማውለው፡፡ እነሱም በተለያየ መንገድ ያግዙኛል፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ ስንወጣ ሁሉ አብረው ይወጣሉ፡፡ በአጠቃላይ ብቻዬን ያደረኩት ነገር የለም፡፡ ግን ሁልጊዜ ጎልቶ የሚታየውና መጨረሻ ላይ ዋጋ የሚሰጠው ለመሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በማኅበሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ቁጥር በአጠቃላይ ስንት ይሆናል፡፡

ወ/ሮ ማሪያ፡- በየጊዜው ይለያያል፡፡ አዳማ ላይ በሚገኘው መጠለያ ብቻ ሰማንያ የሚሆኑ አሉ፡፡ በአዲስ አበባው ከመቶ ሃያ አንሶ አያውቅም፡፡ ይህ በትምህርት ቤቶች ላይ የምንሰጠውን አገልግሎት ሳይጨምር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአጭር ጊዜ ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?

ወ/ሮ ማሪያ፡- ብዙ ጊዜ ከፖሊስና ከሴቶች ጉዳይ ሲደወልልን ሞልቷል ቦታ የለንም የሚል መልስ መስጠት ልብ የሚነካ ነገር ነው፡፡ አሁንም ቢሮዎችን ሌሊት በፍራሽ መኝታ ቤት እያደረግናቸው ነው፡፡ ልንቀበላቸው ያልቻልነው ሴቶች የደረሱ እርጉዞች፣ በደረሰባቸው ጥቃት ክፉኛ በሥነ ልቦና የተጎዱ ናቸው፡፡ የሚደውሉልን አካላት እነዚህን ሴቶች የት እንደሚያስጠጓቸው ይጨነቃሉ፡፡ ስለዚህ የመጠለያውን አቅም ከፍ የማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ ሌላው አዳማ ላይ 24 ሰዓት አገለግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ አለን፡፡ የራሳችን ቋሚ ቦታ ቢኖረን ይህንን ክሊኒክ የማስፋት ፍላጎት አለን፡፡ ሌሎችም አሉ እነዚህ ግን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች