Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምውዝግብ ያጠላበት የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ

ውዝግብ ያጠላበት የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ

ቀን:

ፈረንሣይ ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቀውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ‹‹ኮፕ 21›› ከሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እያካሄደች ትገኛለች፡፡ የ150 አገሮች መሪዎችን ጨምሮ 189 የሚጠጉ አገሮች ተወካዮች በጉባዔው መክፈቻ የተገኙበትና ከ18 ዓመታት ወዲህ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ጤናማ ስምምነት ይደረስበታል ተብሎ የታሰበው ይኼው ጉባዔ፣ ከፓሪስ በስተሰሜን በምትገኘው ለቦርዤ እየተካሄደ ሲሆን፣ 20 ሺሕ ሰዎችም እየታደሙት ነው፡፡

በፓሪስ ከ15 ቀናት በፊት 130 ሰዎች በሞቱበትና ከ300 በላይ በቆሰሉበት የአሸባሪዎች ጥቃት ባጠላበት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ፣ የየአገሮቹ መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም  በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ቃል የገቡበትም ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ ቀደም የተገቡ ቃሎች በአግባቡ ተፈጻሚ አለመሆናቸው፣ በደሃና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም በበለፀጉት መካከል ውዝግብ ፈጥሯል፡፡ ከውዝግቡ ባለፈም በበረዶ ግግር በተከበቡ ደሴቶች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ለአደጋ ተጋልጠዋል፡፡ ደሴቶቹም ከዓይን ዕይታ የሚሰወሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንዴ የዓለም መሪዎች የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመቀልበስ እንዲረባረቡ ጠይቀው ይኼ ካልሆነ ግን ድርቅ፣ ረሃብ፣ ጅምላ ስደትና ጦርነት ዓለምን እንደሚንጣት አሳስበዋል፡፡ የአየር ንብረት ለውጡ ግጭት ሊያመጣ እንደሚችል፣ በተለይም ውኃን ለማግኘት በሚደረግ ጥረት የሚፈጠር ግጭት አሳባቢ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

የካርቦን ልቀትን መቀነስ በሚቻልበት አካሄድና የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ፣ በኪዮቶ ፕሮቶኮል የሠፈረውን ሁሉም አገሮች እንዲፈርሙት ለማስቻል ባለመው ጉባዔ፣ የሚተላለፉ ውሳኔዎች በየአገሮች በጎ ፈቃደኝነት ላይ መሠረት ያደረጉ፣ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ከአየር ንብረት ለውጡ የሚታደጉና ሁሉንም አገሮች በአንድ ማዕቀፍ የሚገዙ መሆን አለበትም ብለዋል፡፡

አገሮች የገቡት ቃል

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ2009 በኮፐንሃገን ሲካሄድ ጀምሮ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ቃል ይገባሉ፡፡ ሆኖም የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ በተሠራው ሥራ ይኼ ነው የተባለ ለውጥ አልታየም፡፡ የዘርፉ ተመራማሪዎችም የዓለም ሙቀት እየጨመረ የበረዶ ግግሮች እየቀለጡና ባህሮችም የውኃ መጠናቸው ከፍ እያለ፣ አገሮችም በጎርፍ እየተጠቁ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ከ180 የሚበልጡ አገሮች ችግሩን ለመቅረፍ ይበጀናል ያሉትን ሲዘረዝሩና ቃል ሲገቡም ከርመዋል፡፡ ተመራማሪዎች ደግሞ ቃል የገባችሁትን ፈጽሙ፣ አለበለዚያ ምድር በተጋረጠባት አደጋ ትጠፋለች ብለዋል፡፡

የሙቀት መጠኑ አሁን ካለበት በአማካይ ከሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ እንዳይጨምር ገደብ እንዲጣል የሚደረገው ስምምነትም ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አይፈታውም ብለዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ባለው የሙቀት መጠን ምድር ለድርቅና ለጎርፍ እየተጋለጠች መሆኑ ነው፡፡ በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ መክፈቻ ጉባዔ ህንድና ፈረንሣይ በቀጣዩቹ 15 ዓመታት የፀሐይ ሀብት ባላቸውና በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች፣ ከፀሐይ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል የአንድ ትሪሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ለማድረግ ማቀዳቸውን አሳውቀዋል፡፡

አሜሪካ፣ ቻይናና ህንድን ጨምሮ 20 አገሮች በታዳሽ ኃይል አቅርቦት ላይ እየተካሄዱ ላሉ ጥናቶች በጋራ የመደቡትን አሥር ቢሊዮን ዶላር፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ ለማሳደግ ቃል የገቡትም በዚሁ ጉባዔ ነው፡፡ ኖርዌይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ ደግሞ ለአየር ንብረት ለውጥ ትልቁን ድርሻ ይዟል ብለው ለሚያምኑት የደን ምንጠራን ለመታደግ፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አምስት ቢሊየን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡ ገንዘቡ የሚሰጠውም የደን ጭፍጨፋን በማስቀረት፣ የደን ሀብት በሚበለፅግበት ሁኔታ ላይ ለመሥራት ቁርጠኛ ለሆኑ አገሮች ነው፡፡ ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ ስዊድንና ስዊዘርላንድ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የካርቦን ልቀትን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥልቶችን ለመዘርጋት 500 ሚሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡ ስዊድን፣ ኒውዚላንድና ከ30 የሚበልጡ አገሮች ደግሞ በድንጋይ ከሰል ለሚመነጭ ኃይል የሚያደርጉትን ድጎማ እንደሚያቋርጡ ተናግረዋል፡፡

 የአየር ንብረት ለውጥን መታደግ የደሃ ወይስ የሀብታም አገሮች ኃላፊነት?

ፋይናንሻል ታይምስ እንደዘገበው፣ በጉባዔው ማብቂያም ቢሆን የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ በደሃና በሀብታም አገሮች መካከል ያለው ኃላፊነትን የመሸከም ልዩነት መፍትሔ ሳያገኝ ሊቋጭ ይችላል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቀዳሚውን ኃላፊነት ማን ሊወስድ ይገባል? የሚለውም ደሃና ሀብታም አገሮችን ሲያወዛግብ የቆየ ነው፡፡ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናረንድራ ሞዲ፣ ወደ ብልፅግና ጉዞ ለማቅናት በነበራቸው ጉዞ የድንጋይ ከሰል የተጠቀሙት የበለፀጉ አገሮች ትልቁን ሸክም መሸከም አለባቸው ይላሉ፡፡ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከልም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ መርከል እንደሚሉት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ የሚደረግ ስምምነት ሁሉ ፍትሐዊና የየአገሮችን ሁኔታ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው ከፍተኛ የጋዝ ልቀት በእኛ ባደጉ አገሮች የተፈጸመ ነው፡፡ በመሆኑም የበለፀጉ አገሮች በቀዳሚነት ችግሩን ሊጋፈጡ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ሆኖም ከበለፀጉ አገሮች አንዳንዶቹ በዓለም የተከሰተው የሙቀት መጨመር ቀድመው ያደጉ አገሮች በሚያደርጉት ጥረት ብቻ ሊስተካከል አይችልም ይላሉ፡፡ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ የሚገኝ አገሮች፣ ቻይናና ህንድን የመሳሰሉትም የጋዝ ልቀትን በመቀነስ በኩል ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦላንዴ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ሴሊሺየስ እንዳይበልጥ የሚገድበውን የኪዮቶ ፕሮቶኮል አገሮች እንዲስማሙበትና እንዲተገብሩት፣ የካርቦን ልቀት መጠናቸውን በየአምስት ዓመቱ እንዲቀንሱ የጠየቁ ሲሆን፣ ሳይንቲስቶች ደግሞ ሁለት ዲግሪ ሴሊሺየስ፣ አማካይ የሙቀት መጠን ጭማሪ ዓለምን ለከፋ ችግር ይዳርጋታል ብለዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የዓለም ሙቀት አንድ ዲግሪ ሴሊሺየስ ሊጠጋ ትንሽ ቀርቶታል፡፡ በዚህ ሙቀት መጠን ብቻ ዓለም ብዙ ፈተናዎችን እያየች ነው፡፡ የሙቀት መጠኑ ጭማሪ ከሁለት ዲግሪ ሴሊሺየሽ በታች መሆን አለበት፤›› ሲሉም በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአየር ንብረት ለውጥ ኤክስፐርት ፕሮፌሰር ክሪስ ፊልድ ተናግረዋል፡፡

አማካይ የሙቀት መጠን ጭማሪ ከሁለት ዲግሪ ሴሊሺየስ እንዳያልፍ የሚጣለውን ገደብ በፓሪስ ጉባዔ የተሳተፉ አገሮችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲስማሙበት እንዲተገብሩትም ነው ኦላንዴ ያሳሰቡት፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦቦማ ደግሞ፣ ‹‹የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ የመጀመርያ ትውልድ ነን፡፡ የመጨረሻ መሆንም አለብን፤›› ሲሉ ኃያላን አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹አገሮች የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የረዥም ጊዜ ዕቅድ መንደፍ ይገባቸዋል፡፡ አሜሪካም ይኼንን ለማድረግ ቃል ትገባለች፡፡ ሌሎች አገሮችም የሙቀት መጠኑን ለመቀነስ መረባረብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ሲነሳ ለነበረው የካርቦን ልቀት መጠን መቀነስ፣ አገሮች ከዚህ ቀደም ሲያንገራግሩ ከርመዋል፡፡ በፓሪሱ ጉባዔ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ኦባማ እንደሚሉት ይህ አሁን አክትሟል፡፡ አሜሪካ በዓለም የትልቁ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት፡፡ ወደ አየር በምትለቀው የካርቦን መጠን ደግሞ ሁለተኛ አገር ነች፡፡ አሜሪካ በሙቀት መጨመር ምክንያት ለተፈጠሩ ችግሮች ዋና ሚና አላት፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለመቀልበስ ኃላፊነት ትወስዳለች፡፡ በበለፀጉት አገሮች የካርቦን ልቀት ምክንያት በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ፣ ደሃና በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ተጎጂ ሆነዋል ሲሉ በማደግ ላይ ያሉና ደሃ አገሮች የበለፀጉትን ይኮንናሉ፡፡ ለዚህም የበለፀጉት አገሮች ለአረንጓዴ ልማት ገንዘባቸውን ማፍሰስ አለባቸው ይላሉ፡፡

ያደጉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ በየዓመቱ ለመስጠት ቃል የገቡትን አንድ ቢሊየን ዶላር ተፈጻሚ ማድረግ አለባቸው ሲሉም ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች መሪዎች ደግሞ የበለፀጉ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ከፍተኛ ገንዘብ ካልመደቡ፣ ቃል የገቡትንም ካልፈጸሙ፣ የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ሴሊሺየስ እንዳይበልጥ የሚገድበውን የኪዮቶ ፕሮቶኮል እንደማይፈርሙ መግለጻቸውን ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል፡፡ በፓሪሱ ጉባዔ በሁሉም አገሮች ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን የሁለት ዲግሪ ሴሊሺየስ ገደብ አስመልክቶ በሀብታምና በደሃ አገሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብም ጀርመን፣ ኖርዌይና እንግሊዝ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ለሚሠሩ ሥራዎች እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ በየዓመቱ አንድ ቢሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ አቀንቃኞች ሠልፍ

 እ.ኤ.አ. ከ2009 በኮፐንሃገን ከተጀመረው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አንስቶ፣ በየዓመቱ በሚካሄዱ ጉባዔዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አቀንቃኞች ተቃውሞ ያነሳሉ፡፡ የአሁኑ ጉባዔ በፈረንሣይ ፓሪስ ከመጀመሩ አንድ ቀን አስቀድሞም አቀንቃኞቹ ሰላማዊ ሠልፍ አድርገዋል፡፡ 4,500 የሚጠጉ አቀንቃኞች የዓለም መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀልበስ እንዲተጉ እጅ ለእጅ በመያያዝ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ ሆኖም የፈረንሣይ መንግሥት ከ15 ቀናት በፊት በአሸባሪዎች ከደረሰበት ጥቃት ጋር በተያያዘ፣ ማንኛውንም ሰለማዊ ሠልፍ አግዷል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ አስታከው ሁከት ፈጥረዋል የተባሉ 208 ሠልፈኞች ታስረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ

የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም የሚገኙ አገሮችን በሙሉ ይጎዳል፡፡ ድርቅ፣ በሽታ፣ ረሃብና ጎርፍ የተፅዕኖው መገለጫዎች ናቸው፡፡ በዓለም ከሚገኙ 2.3 ቢሊዮን ሕፃናት 700 ሚሊዮን ያህሉ የችግሩ ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡ ፕሬስ ቲቪ ዩኒሴፍን ጠቅሶ እንደ ዘገበው፣ 530 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በተለይም በእስያ የሚኖሩ ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ተጋልጠዋል፡፡ 160 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጨማሪ ሕፃናት ደግሞ በተለይም በአፍሪካ ድርቅን ተከትሎ ለሚመጣ ረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ገዳይ በሽታዎችም ችግሩን አሳባቢ አድርገውታል፡፡ ወባ፣ የሳንባ ምች፣ ተቅማጥና በተመጣጣነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ በሽታዎች ሁሉ የአየር ንብረት ለውጡ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...