Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአመራር ለውጡ በስኬት እንዲታጀብ የድርሻን ማዋጣት ይገባል!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግሥት ከተመሠረተ ከ23 ዓመታት በኋላ፣ ሦስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰይመዋል፡፡ የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሞት፣ ሁለተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መልቀቂያ በማቅረብ ሲሰናበቱ፣ ሦስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ተተክተዋል፡፡ አገሪቱን ነውጥ ውስጥ በመክተት ቀውስ በፈጠረው የሦስት ዓመታት ያህል ተቃውሞ ምክንያት የመጡት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከፊታቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሕአዴግን በፈተነው የውስጥ ትግል በማለፍ በአብላጫ ድምፅ ተመርጠው ለሥልጣን ሲበቁ፣ የኢሕአዴግ አመራሮችና መላ አባላት የተሃድሷችን ትግል ውጤት ነው በማለት አብረዋቸው ሊሠለፉ ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን አጋጣሚ የራሱ ትግል ውጤት በማድረግ ለዘመኑ ትውልድ ምላሽ መስጠቱን ካልተጠቀመበት፣ የአገሪቱ ችግር በምንም ዓይነት ሁኔታ መፍትሔ አያገኝም፡፡ ምንም እንኳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከተለመደው የኢሕአዴግ ባህል ወጣ ያለና ሁሉንም አካታች ቢሆንም፣ ኢሕአዴግም እየተለወጠ ካለው ዘመን ጋር ራሱን ማስተካከል እንዳለበት ማሳያ መሆኑን በፍፁም መዘንጋት የለበትም፡፡ ነባሩ ባህል ከዚህ ትውልድ ፍላጎት ጋር አልተናበበምና፡፡

የአመራር ለውጡን ቅርፅ በማየት ይዘቱን በቶሎ መወሰን ባይቻልም፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት የተሰማው ከወትሮው ለየት ያለ ቃና ያለው ምልከታ ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ማነጋገር የቻለ ነው፡፡ ብዙዎችንም አግባብቷል፡፡ ለዓመታት ሲቀነቀን ከነበረው ብሔር ተኮር የማንነት ትርክት ውስጥ በመውጣት፣ ኢትዮጵያዊ የጋራ ምሥልን በስፋት ማውሳታቸው እንደ ትልቅ ዕርምጃ ተቆጥሯል፡፡ ይህ ዓይነቱ አቀራረብ በአገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደ ጅማሮ ከመታየቱም በላይ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የነበረውን መራጠርና መራራቅ ለመቅረፍ አዎንታዊ ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት በኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ልምድና ባህል መሠረት ትኩረት የማይሰጣቸው ቤተሰባዊና ሰዋዊ እሴቶችን በማውሳታቸው የብዙዎችን ልብ ነክተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በደም የተሳሰሩ፣ ከልዩነቶቻቸው ይልቅ በአንድነታቸው የሚደምቁ፣ በሕይወት ሲኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ኢትዮጵያ ይሆናሉ የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ብዙዎችን የኮረኮረ ነበር፡፡ ‹‹ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋሀደ ነው. . .›› ያሉት ደግሞ ቀልብ የሚስብ ነበር፡፡ ከቡድን መብቶች በተነፃፃሪ የግለሰብ መብቶችና ነፃነቶች በስፋት መነሳታቸው ይመጣል ተብሎ ለታሰበው ለውጥ ጥሩ መንደርደሪያ ነው፡፡ የሐሳብና የመደራጀት ነፃነት ፈተናዎች ውስጥ መግባት ምን ያህል ቀውስ እንደፈጠረ በሚታወቅባት አገር ውስጥ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አስተዳደራቸውን በርቱ ተበራቱ ማለት ተገቢ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያውያንን በጋራ አገራዊ ጉዳዮች በማግባባት ወደ አንድ መድረክ እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡበት መንገድ ልዩነትን የሚያከብር ጭምር በመሆኑ፣ ልዩነትን ይዞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠለፍ የግድ ይላል፡፡ የአገሪቱን ሥልጣን ተቀብለው ቢሮአቸውን በመረከብ ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ ለዓመታት የተከማቹ በርካታ ሥራዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ካቢኔያቸውን ከማደራጀት ጀምሮ ተቋማትን የማጠናከር ሥራም አለ፡፡ በዚህ መሀል አጠገባቸው ካሉ ጓዶቻቸው በተጨማሪ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ምክሮችና ማበረታቻዎች ይደርሱዋቸዋል፡፡ ካቢኔያቸውን ሲያደራጁ ከኮታ ይልቅ የትምህርት፣ የልምድና የብቃት ጉዳይን አንስቶ እሳቸውን ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ እሳቸውም ለትምህርት የሰጡት ልዩ ትኩረት አይዘነጋምና፡፡ እንደ ነገሩ የሆኑትን መንግሥታዊ ተቋማት በባለሙያዎች በማደራጀት ከዘመኑ ጋር እንዲመጣጠኑ ማድረግ እንደሚገባም መምከር ይገባል፡፡ በደካማ ተቋማት አገር መምራት አይቻልምና፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት በመባል የሚታወቁትን ነገር ግን እጅና እግራቸው መንቀሳቀስ ያቃታቸውን ፈትሾ ማስተካከልም ሌላው ሥራ ነው፡፡ በተለይ በምርጫ ቦርድ ላይ ለዓመታት የሚነሳው የገለልተኝነት ጥያቄ፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነትና የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ከአንገብጋቢዎቹ አገራዊ ችግሮች መካከል መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በሕግ ዋስትና የተሰጣቸው መሠረታዊ መብቶችም እንዲሁ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አገራዊ አንድነትና መግባባት ላይ ያተኮሩ በርካታ ቁም ነገሮች ተወስተዋል፡፡ ሥራቸውን በሙሉ ኃይል ሲጀምሩ ደግሞ በፖሊሲና በስትራቴጂ ማዕቀፎች ላይ ሊደረጉ ስለታሰቡ ለውጦች ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ ኢሕአዴግ በተለያዩ ጊዜያት አደረግኳቸው ባላቸው ተሃድሶዎች ለሕዝብ ቃል የገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ (2012 ዓ.ም.) ሥልጣን ላይ የሚቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ምርጫውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚረዱ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ጀምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን ሲያስፈጽሙ፣ ከድርጅታቸውና ከቅርብ ሰዎቻቸው በተጨማሪ የሕዝብ ድጋፍና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ቡድኖች ድጋፍ የግድ ይላል፡፡ ይህ ድጋፍ በኢትዮጵያ ምድር ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚመጥን ምኅዳር እንዲፈጠር ይረዳል፡፡ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ደግሞ ነገ የበለጠ የተሻለ እንዲሆን ይጠቅማል፡፡ በእልህና በቂም በቀል የተለወሰው የተለመደው የግትርነት ፖለቲካ ለአገርም ለሕዝብም የማይጠቅም መሆኑን በመገንዘብ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዳ ጠጠር መወርወር አገራቸውን የሚወዱ ዜጎች ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከቃል በላይ በተግባር ማግዘፍ ትልቁ ሥራ መሆን አለበት፡፡

የኢትዮጵያ የታላቅነት ክብር የሚመለሰው በገዛ ልጆቿ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር እንደ መሆኗ መጠን በውስጥ ጉዳይዋ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ የመላ ኢትዮጵያውያን የማይገሰስ መብት ነው፡፡ ምዕራባውያንም ሆኑ ሌሎች በውስጥ ጉዳያችን ገብተው እንዲፈተፍቱ መፍቀድ አይገባም፡፡ ለዚህ ደግሞ መከፋፈል ሳይሆን የጋራ አቋም ሊኖር የግድ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እነሱን እስካገለገለ ድረስ አስፈላጊ ነው ብለው ያመኑበትን ሁሉ በማድረግ፣ አምባገነን ተላላኪያቸውን ሁሉ ሥልጣን ላይ ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ፍላጎታቸው በኢትዮጵያ ምድር ተቀባይነት ማግኘት የለበትም፡፡ የኢትዮጵያ ልጆችም የእነሱ ተላላኪ መሆን የለባቸውም፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ደግሞ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር ሳይሆኑ ከዳር እስከ ዳር የሚሳተፉበት ምኅዳር መኖር አለበት፡፡ ብልሹ አሠራሮች መወገድ አለባቸው፡፡ የሕዝብና የአገር ፀር የሆነው ሙስና (ሌብነት) በጠንካራና በአስተማማኝ ዕርምጃ መምከን አለበት፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በምልዓት እንዲከበሩ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ቀና ሐሳብ ተግባራዊነት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና አስተዳደራቸውን በአገር ፍቅር ስሜት መደገፍ ይገባል፡፡

አስተዋዩና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የተደሰተውን ያህል፣ ድጋፍ ከመስጠት ወደ ኋላ እንደማይል በተለያዩ መንገዶች ስሜቱን እየገለጸ ነው፡፡ ይህ የማስተዋል ፀጋ ባለቤት የሆነ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖር የተከበረ ሕዝብ ይህንን ስሜቱን የገለጸው፣ ሁሌም እንደምንለው ከአገሩ በላይ ምንም የሚያስቀድመው ነገር ስለሌለ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ተምሳሌታዊ ሕዝብ በመምራት ተዓምር መሥራት እንደሚቻል ጥርጥር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በንግግራቸው ለማመልከት የፈለጉት ይህንን ነው፡፡ አሁን ትልቁ ነገር ያጋጠሙ ችግሮችን በሰከነ መንገድ መፍታት እንደሚቻል የጋራ መግባባት መፍጠር ነው፡፡ በተለይ በፖለቲካው ውስጥ ያሉ ኃይሎች ለዓመታት ያባከኑትን የሰው ኃይል፣ ጊዜና ኃይል ብቻ ሳይሆን መልካም አጋጣሚዎች በመገንዘብ ለወቅቱ የሚመጥን ቁመና ላይ ቢገኙ ይመረጣል፡፡ የዓመታት ችግሮች የሚቀረፉትና ወደተሻለ ጊዜ መሸጋገር የሚቻለው በቀና መንፈስ የለውጥ ኃይል ሆኖ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም ጣጣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለአስተዳደራቸው አስረክቦ ‹ሥራህ ያውጣህ› ማለት ለአገር አይጠቅምም፡፡ ዛሬ አመሥግኖ ነገ ለመውቀስ የተለመደው ሸለብታ ውስጥ መግባትም ፋይዳ የለውም፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር ዴሞክራሲያዊት አገር ዕውን መሆን የምትችለው ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡ የሚያምርባቸውም በኅብረት ሲቆሙ ነው፡፡ የአመራር ለውጡ በስኬት እንዲታጀብ የድርሻን ማዋጣት ይገባል! ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም የሥራ ጊዜ እንመኛለን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከ700 ሺሕ በላይ የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ 716,624 የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ የአዲስ አበባ...

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ተስፋ የተጣለባቸው የንግድ ማዕከላት

ፆም ሲገባ ዋጋቸው ከሚጨምሩ የምግብ ፍጆታዎች ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ ...

የወጣቶችን ፈጠራ የሚያስቃኘው የስታርት አፕ ዓውደ ርዕይ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ...

በግጭት ለተጎዱ ልጆች 80 ሺሕ መጻሕፍት ማሠራጨት መጀመሩን ኢትዮጵያ ሪድስ አስታወቀ

በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት ከትምህርት ቤት ለተስተጓጐሉ፣ በሥነ ልቦናና በሌሎች...

የም እና መስህቦቿ

በቱባ ሀገሬ የም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ በ239...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...