Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የምትደራደረው ባድመ ከተመለሰላት ብቻ እንደሆነ አስታወቀች

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የምትደራደረው ባድመ ከተመለሰላት ብቻ እንደሆነ አስታወቀች

ቀን:

ኤርትራ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላትን የፖለቲካ ልዩነት በማጥበብ ልትደራደር የምትችለው፣ ባድመ ከተመለሰላት ብቻ እንደሆነ አስታወቀች፡፡

የኤርትራ መንግሥት ይህን ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰየሙ በኋላ፣ ባደረጉት ንግግር ለኤርትራ መንግሥት ላቀረቡት ጥሪ በሰጠው ምላሽ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗን፣ የኤርትራ መንግሥትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ላቀረበችው ጥሪ በጎ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ለተለያዩ  ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ልትደራደር የምትችለው ባድመ ከተመለሰላት ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሰላም ሁለቱን አገሮች ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ዓለም አቀፍ ሕጉን ባልተከተለ መንገድ ባድመን በኃይል ይዛለች፤›› ብለዋል፡፡

የድርድር ኳሱም በኢትዮጵያ እጅ እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የኤርትራን ሉዓላዊነት በማክበር በኃይል የያዘችውን የኤርትራ ግዛት ባድመን ጨምሮ መልቀቅ አለባት፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም. በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት አድርገው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በጦርነቱ ሳቢያም ከሁለቱም ወገኖች የ70 ሺሕ ዜጎች ሕይወት እንደጠፋ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሁለት አሥርት ያህል አሳልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለመጀመርያ ጊዜ በትረ ሥልጣን ሲይዙ ባደረጉት ንግግር፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት መንግሥታቸው ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን ቢናገሩም፣ የታሰበው ድርድር እልህ አስጨራሽና በሰጥቶ መቀበል መርህ ካልሆነ ሊፈታ እንደማይችል የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራዊያን የተሰማቸውን ለሪፖርተር አጋርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተወካይ አቶ ይስሐቅ ዮሴፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራን በተመለከተ የጠቆሙትን ሐሳብ አድንቀው፣ ‹‹ከዚህ በፊት የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ለምናደርገው ጥረት የበለጠ ያበረታታናል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ይስሐቅ ቀደም ሲል የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎችም ጥረታቸውን ሲያበረታቱ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት በይፋ ለኤርትራ መንግሥት ጥሪ ማቅረብ በራሱ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥና የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአዲሱ የኢትዮጵያ አመራር ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ሊሆኑ እንደሚችል እጠብቃለሁ፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ይህን የኢትዮጵያ ጥረት ለማሳካትም አዲሱ አመራር ለሁለቱ አገሮች ወዳጅ የሆኑ አካላትን በማነጋገር የሽምግልና ሥራ እንዲያከናውኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኤርትራዊያን ተወካዮችን በማነጋገር ውጤታማ ሊሆን እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ከኤርትራ ከመጡ ዘጠኝ ዓመት እንደሞላቸው የሚናገሩት አቶ አሸናፊ ተክላይ በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው፣ ‹‹ይህ ቀድሞውንም ቢሆን ከእሳቸው የሚጠበቅ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በኤርትራ መንግሥት በሚታዩ በርካታ ችግሮች ሳቢያ ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይቻል ጠቁመው፣ ‹‹ከወትሮው አሁን የተለየ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ፕሮጀክት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ያለውና ሴሌብሪቲ ኢቨንስትስ የተሰኘው አገር በቀል ተቋም ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ገብረ ሊባኖስ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር ድርጅታቸው ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በኤርትራ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ንግግር ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ሆኖ ነው ያገኘነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለኤርትራ መንግሥት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ተአማኒ ያደረገና ያስደሰተ ንግግር ነው፡፡ ትልቅ የምሥራች ነው ይዘውልን የመጡት፤›› ብለዋል፡፡

ድርጅታቸው ይህንን ችግር ለመፍታትና የሁለቱ አገሮች ሕዝቦችም በመንግሥታቱ ላይ ጫና በማሳደር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት አመራር ይዞት የመጣው ሐሳብ ድርጅታቸው ስኬታማ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ተቋማቸው ተቋርጦ የነበረውን የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማስቀጠልና በመንግሥታቱ መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተለያዩ ሕዝባዊ ውይይቶች ማካሄዱንም አክለዋል፡፡

ለስድስት ዓመታት ያህል በጠቅላይ ሚኒስትርነት የቆዩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኤርትራ ድረስ ሄጄ ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ ሲሉ ቢደመጡም፣ በእሳቸውና ከእሳቸው ቀደም ብለው በነበሩት በአቶ መለስ ዜናዊ የሁለቱ አገሮች የፖለቲካ ልዩነት ሳይፈታ ቆይቷል፡፡ በአቶ ኃይለ ማርያም የሥልጣን ዘመንም ኢትዮጵያ ኤርትራን በተመለከተ የምትከተለውን ፖሊሲ ልትቀይር እንዳሰበች በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ነበር፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...