Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተቃዋሚ ፓርቲዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደ ተግባር እንዲቀየር አሳሰቡ

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደ ተግባር እንዲቀየር አሳሰቡ

ቀን:

ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ መሐላ የፈጸሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማው ያደረጉት ንግግር ይዘት፣ በአብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ዘንድ ተስፋን የጫረ እንደሆነና ወደ ተግባር እዲቀየርም ጠየቁ፡፡

ለግማሽ ሰዓት ያህል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያማከለ ንግግር እንዳደረጉ ብዙዎች ተስማምተውበታል፡፡

በዚህም መሠረት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በጣም ጥሩ ነው በማለት ያወደሱ ሲሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ ያደረጉት ንግግር ነገሮችን በዝርዝር ለማስረዳት የሞከረ ነው፤›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የጠቃቀሷቸው ነገሮች መኢአድ ላለፉት 27 ዓመታት ሲናገራቸውና ተግባራዊ እንዲሆኑ ሲታገልላቸው የነበሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ላለፉት 27 ዓመታት ለኢትዮጵያ የሚበጃት አንድነት ነው፣ ኢትዮጵያዊነት ነው በማለት ለማስረዳት ጥረት ስናደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን ያኔ ምንም ሰሚ አልነበረም፡፡ እንዲያውም እነዚህን ሐሳቦች ስናቀርብ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች እየተባልን ብዙ ስም ይወጣልን ነበር፡፡ አሁን ግን እርሳቸው እኛ ለዓመታት ስንናገር የነበረውን ተመሳሳይ የሆነ ነገር ነው የተናገሩት፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከልብ መሥራት የሚፈልጉ ከሆነ ቃላት ብቻ ሳይሆን ተግባር ያስፈልጋል፡፡ የተናገሩትን በከፊል ማሟላት ቢችሉ እንኳን ለአገራችን ተስፋ ይሆናሉ፡፡ ያንን ማሟላት ካልቻሉ ግን ችግሩ ይቀጥላል፣ እርሳቸውም በችግር ውስጥ ይኖራሉ፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ማሳሰቢያ አስተላልፈዋል፡፡

ንግግሩ እስካሁን ከቀረቡ ንግግሮች በተለየ ሁኔታ የቀረበ ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ናቸው፡፡

‹‹የሕዝቡን ስሜት ሊያነቃቃ የሚችልና ካሁን ቀደም ያላየነው ዓይነት አነቃቂ ንግግር ነው፡፡ ምንም እንኳን የመሥራቱ ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ንግግሩ በውስጡ እውነት የሚመስል ነገር ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ነው፤›› በማለት የተሰማቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት መጀመርያ በድርጅታቸው ውስጥም ከፍተኛ ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ትዕግሥቱ፣ ‹‹የነበረውን ችግር ለመፍታት እንደ መሪ ዘይት ሆው እስከሠሩ ድረስ ሁሉም ይስተካከላል፡፡ ምክንያቱም መጀመርያ የራሳቸውን ሰዎች ማለስለስ አለባቸው፡፡ የተናገሩትን ለማስፈጸም በራሳቸው ድርጅት ውስጥ አለስላሽ ሆነው መቅረብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተናገሩት መንገድ ግማሹን ቢሠሩ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ይችላሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ዕውቀት ላይ የተመሠረተ የመግባባት ሥራ መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በንግግራቸው እንዳደመጥነውና የኋላ ታሪካቸው እንደተነገረን ይኼን ከማድረግ የሚሳናቸው አይደሉም፤›› በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በኢሕአዴግ ታሪክ ውስጥ ተጠቅሰው የማያውቁ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ የሞቱ ዜጎችን ይቅርታ መጠየቅ፣ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የተደረገው ጥሪ የንግግሩ አካል መሆኑ ንግግሩን ጥሩ አድርጎታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጥሩና ተስፋ ሰጪ ናቸው፣ አፈጻጸማቸውን በተግባር የምናየው ከሆነ…›› በማለት አስተያየቸውን የሰጡት ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ተስፋ ሰጪ ናቸው ቢሉም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተቋማትን ማደራጀት አለመካተቱ ጎደሎ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይኼ ሁሉ ሰው የሞተው ሰው ለመቀየር ሳይሆን ሥርዓት ለመቀየር ነው፡፡ ሥርዓቱን የሚቀይረው ደግሞ በራሱ እግር ቆሞ በራሱ ሳንባ የሚተነፍስ ተቋም ሲኖር ነው፤›› በማለት የተቋማቱን ግንባታና ዳግም አወቃቀር የንግግሩ አካል መሆን ነበረበት በማለት ሞግተዋል፡፡

‹‹ዋናው ነገር ግን ከተናገሩት በላይ በተግባር ብዙ ይጠበቃል፡፡ ፈጣን፣ ቆራጥና በግልጽ የሚታዩ ዕርምጃዎች ይጠበቃሉ፡፡ በንግግር ደረጃ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢሕአዴግ ዘመን ሰምቶ የማያውቀው ንግግር ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

በተመሳሳይ ንግግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ገላጭ በመሆኑ ረገድ ብዙም እንከን የሚወጣለት እንዳልሆነ፣ ነገር ግን መነሳት የነበረባቸው ግን ያልተካተቱ ነገሮች እንዳሉ በመጠቆም አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡

‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የማንሳት ነገር፣ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን ለሕግ ማቅረቡ ጉዳይ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረ የወሰን ግጭት የተፈናቀሉ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ወደቀዬአቸው የመመለስ ጉዳይ በሰፊው በንግግሩ ውስጥ መካተት ነበረበት፤›› በማለት ጎደለ ያሉትን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

‹‹ከዚህ አንፃር እንዲህ ዓይነት ቁም ነገሮችን ያልያዘ ንግግር ነው፡፡ ነገር ግን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍላጎት የላቸውም፣ መልካም አያስቡም የሚል ፍርድ እየሰጠሁ አይደለም፡፡ ግን ንግግሩ በፖሊሲ መታጀብ አለበት፡፡ እርሳቸው ደግሞ የተቀመጡት የኢሕአዴግን ፖሊሲ ለማስፈጸም ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ተግባር ሲገባ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አጀንዳ ሁልጊዜ ቅድሚያ ይይዛል፡፡ ይኼን ሁሉ አገናዝቦ ማየት ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ የዋህ አንሁን፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...