Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረገው ውይይት በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ይካሄዳል

በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚደረገው ውይይት በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ይካሄዳል

ቀን:

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚያደርጉት ውይይት በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ እንደሚካሄድ ታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ላይ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ከመጋቢት 26 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ውይይት ለማድረግ ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉት ውይይትም በተያዘለት ቀን እንደሚካሄድ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡  ኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሰየሟ አኳያ ውይይቱ ሊራዘም ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ቢደመጥም፣ ቀነ ቀጠሮው እንደማይራዘም ታውቋል፡፡

የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር አብደል አቲ ማክሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ለግብፅ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፣ ለወራት ያህል ተቋርጦ የነበረውን የሦስቱ አገሮች ውይይት በተያዘለት ቀነ ቀጠሮ ይካሄዳል ብለዋል፡፡ ‹‹ግብፅ የኢትዮጵያንና የሱዳንን የመልማት ጥረት አትቃወምም፡፡ ነገር ግን ውኃ ለግብፃውያን የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው፤›› ማለታቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል፡፡

ሦስቱ አገሮች በግድቡ አሞላልና አለቃቀቅ፣ እንዲሁም አካባቢያዊ ተፅዕኖን  በተመለከተ ጥናት ለማካሄድ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ቢታወቅም አጥኚው ኩባንያ ጥናት በሚያደርግባቸው የመነሻ ሐሳቦች ላይ ሦስቱ አገሮች በተለይም ኢትዮጵያና ግብፅ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በግብፅና በሱዳን በኩል ያለውን ሥጋት ለመቀነስ ስትልም ግድቡ ውኃ የሚይዝበትን ቀን እንዳሳወቀች መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የሦስቱም አገሮች የቴክኒክ ባለሙያዎች በካርቱም የሚያደርጉት ውይይትና የሚደርሱበት የውሳኔ ሐሳብ  እየተጠበቀ ነው፡፡

ግብፅ በዓባይ ወንዝ የሞትና የሽረት ወይም የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው እያለች ባለበት ጊዜ፣ ሦስቱ አገሮች የሚደርሱበት ስምምነት ተጠባቂ አድርጎታል፡፡

ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ አሞላልና አለቃቀቅ፣ እንዲሁም አካባቢያዊ ተፅዕኖን በተመለከተ ውይይት ሲያደርጉ እንደነበር መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ከወራት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ገጥሞ በነበረው ቀውስ ሳቢያ በሦስቱ አገሮች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውይይት እንዲራዘም ኢትዮጵያ መጠየቋን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ በዚህ ሳቢያም የሚደረገው ውይይት ለወራት እንዲራዘም ተደርጎ አሁን በሱዳን ሊካሄድ ተወስኗል፡፡

ውይይቱ ኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰየመችበት ጊዜ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የህዳሴ ግድቡ መላ የአገሪቱን ሕዝብ ያግባባ ፕሮጀክት እንደሆነ መጥቀሳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የግብፅ መንግሥት ከሚያንፀባርቀው የተለያየ አቋም አኳያ አሁንም ከግብፅ ትልቅ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡

ከአብዱልፈታህ አልሲሲ በፊት የነበሩት የግብፅ መሪዎች፣ ግድቡን በኃይል እናፈርሳለን የሚል አቋም ይዘው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ግን የአገሪቱ መንግሥት አቋም እየተለሳለሰ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ባላቸው የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ ግብፅ ኤርትራን በመጠቀም በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ ተፅዕኖ ልታደርስ ትችላለች የሚሉ አስተያየቶች ሲነገሩ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥሪ ማቅረባቸውና በአገሪቱ ያለውን የውስጥ ሁለንተናዊ ችግሮች በአንድነትና በመግባባት ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው፣ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥጋት እንዳይፈጠር የሚያደርግ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ አገር ውስጥ ያለውን ችግር መፍታት ከተቻለና ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለው የፖለቲካ ልዩነት ከጠበበ፣ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ላይ ሥጋት ሊኖር እንደማይችል ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...