Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ሮቦትን በኢትዮጵያ የማስረፅ ጉዞው

አቶ ሰናይ መኰንን የአይከን ኢትዮጵያ ሮቦቲክስ ኤዱኬሽን ኤንድ ኮምፒቲሽን ማዕከል መሥራች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2011 የተመሠረተው አይከን ኢትዮጵያ ታዳጊዎችን በዲዛይን ኢንጂነሪንግና ፕሮግራሚኒንግ የማብቃት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የማስቻል ሥራ ይሠራል፡፡ ድርጅቱ ለታጊዎቹ መሠረታዊ የሮቦቲክስ ጽንሰ ሐሳብና ሌሎች ወሳኝ ቀመሮችን ካስተማረ በኋላ እርስ በርስ እንዲወዳደሩ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ወጥተው በሌላው የዓለም ጫፍ ከሚገኙ አቻዎቻቸው እንዲወዳደሩ ያደርጋል፡፡ በተቋቋመበት በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ውድድር ይደረግ የነበረው እዚሁ አገር ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ተወዳድረው የሚያሸንፉ አሜሪካ ሄደው ዓለም አቀፉን የሕዋ ሳይንስ ምርምር ማዕከል እንዲጎበኙ ብቻ ነበር የሚታደሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት በትልልቅ ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድሮች ላይ እንደ አትሌቲክሱ አገራቸውን ወክለው እንዲሳተፉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከወራት በፊት ካናዳ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያኑ ታዳጊዎች የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ እንዲሁም በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎችን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን መሥራቹን አቶ ሰናይ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥ ይደረጉ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ውድድሮች እንዴት ነበሩ?

አቶ ሰናይ፡- በመጀመሪያ አካባቢ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ውድድሮች ብሔራዊ ውድድር በመሆናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያልቁ ነበሩ፡፡ አሸናፊ ልጆች አሜሪካ ሄደው ናሳን ይጎበኙ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ናሳን ከመጎብኘት ባሻገር ከግልም ከመንግሥትም ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎች የአገር ውስጥ ውድድሮችን አሸንፈው ሲመረጡ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በዚህ ብቃታቸውን ከመለካት ባለፈ አገራቸውን ያስጠራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አይከን ኢትዮጵያን ለመመሥረት የተነሱበት አጋጣሚ ምን ነበር? ሌሎች በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ እህት ድርጅቶችስ  አሉት? እንግሊዝ  ዞን የቋንቋ ትምህርት ቤት እንዳለዎት አውቃለሁ፡፡

አቶ ሰናይ፡- እንግሊዝ ዞን የቋንቋ ትምህርት ቤትን የከፈትኩት የቋንቋ አስተማሪ ስለነበርኩ ነው፡፡ ማስተማር የጀመርኩት ገና ኮሌጅ እያለሁ ነበር፡፡ በትርፍ ሰዓቴ እየወጣሁ አስተምር ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም. እንግሊሽ ዞን የሚባል የቋንቋ ትምህር ቤት ከፈትኩ፡፡ ትምህር ቤቱ እየሰፋ ሄዶ በአሁኑ ወቅት ስድስት ቅርንጫፎች ሊኖሩት ችለዋል፡፡ አይከን ኢትዮጵያ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡ አይከንን ለመክፈት የወሰንኩት ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያገናኝ ሌላ የተለየ ነገር ኖሮ አይደለም፡፡ በተለያዩ ሥራዎች ባህር ማዶ እመላለስ ነበር፡፡ በምመላለስበት ወቅት በየአገሩ ያሉ ሕፃናትና ታዳጊዎች በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚያደርጉትን ተሳትፎ፣ የሚሠሩትን የፈጠራ ሥራ እመለከት ነበር፡፡ ይኼም አገሬ እንዲመጣ እንድመኝ ያደርገኝ ነበር፡፡ በተግባር ተኮር የትምህርት ፖሊሲውን የሚደግፍ ሳይንስ ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ለምን አንጀምርም በሚል ነው አይከን ኢትዮጵያን የተመሠረተው፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች የተለያዩ የየራሳቸው ንግድ ፈቃድ ያላቸው የማይገናኙ ናቸው፡፡ ነገር ግን ባለብን የወርክሾፕ እጥረት ምክንያት ትምህርት በማይሰጥባቸው የሳምንቱ ቀናት የመማሪያ ክፍሎቹን በወርክሾፕነት እንጠቀማቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- አይከን ኢትዮጵያ ከተመሠረተ ከሰባት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ እነዚህ ጊዜያት ውስጥ ምን ያህል ተማሪዎችን ተቀብላችሁ ማብቃት ችላችኋል? ምን ያህል ጊዜስ ውድድር አደረጋቹ?

አቶ ሰናይ፡- እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ የተለያዩ የሮቦቲክስ ውድድሮችን አካሂደናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያውን ውድድር ያካሄድነው በዩኒቲ ኮሌጅ፣ የሁለተኛ ሦስተኛ ዙር ውድድር ደግሞ በቀበሌ 19 አዳራሽ ነበር፡፡ በወቅቱ ከ1,500 ተማሪዎች በላይ ነበር የተሳተፉት፡፡ የሒሳብ፣ ሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ ላይ ያተኮሩ የጽሑፍ ፈተናዎች ሁሉ ነበሩ፡፡ ቀጥሎ በነበሩ ውድድሮችም የተሳታፊ ተማሪዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር ፈተናዎች ላይ ብዙ ተማሪዎች ይወድቃሉ፡፡ መጨረሻ ላይ የሚወዳደሩ ተማሪዎች ወደ ሦስት መቶና አራት መቶ ተማሪ ብቻ ይሆናሉ፡፡ ከዚያ ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል በነጥብ ብልጫ ያሳዩ የተወሰኑ ተመርጠው ለዓለም አቀፍ ውድድር ዝግጅት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዴት መካፈል እንደምንችል አናውቅም ነበር፡፡ ግንኙነታችንም ከህንድ ጋር ብቻ ነበር፡፡ ህንድ አገር ድረስ እየሄድን እንወዳደር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በአሜሪካ ናሳ የሚያዘጋጀው የሮቦቲክስ ውድድር እንዳለ ሰማን፡፡ የዚህ አካል ለመሆን ፈልገንም ተመዘገብን፡፡ ናሳ ስፖንሰር አድርጎ በሚዘጋጁ እንደ ቴክስ ኦሊምፒክ ያሉ ውድድሮች ላይ ጋበዙን፡፡ በመጀመሪያው ዙር እኔ ብቻ ነበርኩ የሄድኩት፡፡ ፕሮግራሙ በጣም ትልቅ ነው፡፡ ወደ 24,000 ተማሪዎች የሚሳተፉበት ትልቅ የውድድር መድረክ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዙር የኢትዮጵያን ተወዳዳሪዎች ይዤ ሄድኩኝ፡፡ ከአፍሪካ የተሳተፍነው እኛ ብቻ ነበር፡፡ የግብፅ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩበትም እዚያው አሜሪካ የሚኖሩ ግብፃውያን ነበሩ የተሳተፉት፡፡ ከአፍሪካ የመጀመሪያ አገር መሆናችን አስደስቶናል፡፡ ከዚያ ሁሉ አገሮች መካከል አንዲት የአፍሪካ አገር ተጠርታ ስትወጣ ማየት ደስ ይላል፡፡ ከዚያም በቬክስ የሮቦቲክስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ቻልን፡፡ ይኼንን ስናደርግ አገር አቀፍ ውድድሮችን ከህንድ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ለሦስትና አራት ጊዜያት ያህል አዘጋጅተን ነበር፡፡ ነገር ግን እ.ኤ.አ. ከ2016 በኋላ በአሜሪካ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ በየዓመቱ ለመሳተፍ ተስማምተን እየተሳተፍን እንገኛለን፡፡ በፊት የተለያዩ ለሮቦቲክስ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከውጭ እያስመጣን እዚህ ነበር የምንወዳደረው፡፡ አሁን ግን ከውጭ አስመጥተን እዚህ ሠርተን እዚያ እንወዳደራለን፡፡ በቬክስ ኦሊምፒክ ላይ ሦስት ጊዜ ተሳትፈናል፡፡ በአንድ ጉዞ እስከ 40 ተማሪ እንደወስዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ካናዳ ተካሂዶ በነበረው የሮቦቲክስ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ እስቲ ስለ ውድድሩ አጠቃላይ ሁኔታ አብራሩልን?

አቶ ሰናይ፡- በፈረንጆቹ ያለፈው ዓመት ካናዳ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የሮቦቲክስ ውድድር ላይ የኔ ልጆች አንደኛ ነበር የወጡት፡፡ ውድድሩን ያሸነፉት በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ምድብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ፣ በፕሮግራሚንግ ነበር የተወዳደሩት፡፡ በውድድሩ ከ16 አገሮች የተወጣጡ በርካታ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ከዚያ እንደተመለስን የቻይና ውድድር ነበር፡፡ በዚህ ውድድር ላይ 24 ተማሪዎችን ነበር የወሰድነው፡፡ በዚህኛው ውድድር 44 አገሮች ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ አገሮች የተውጣጡ በጣም ብዙ ተማሪዎች ነበሩ የተሳተፉት፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የኛ ተወዳዳሪዎች በቡድን ተቀናጅቶ በመሥራት ሜዳሊያና ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን ዘጠኝ ውድድሮች አድርገናል፡፡ አሥረኛውን ዙር ውድድር ደግሞ በቅርቡ በአሜሪካ ይካሄዳል፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ ግብዓቶችን ለማግኘት የምታደርጉት ጥረት ምን ያህል አድካሚ ነው? ከዚህ ሲያልፍም የትምህርት ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚቸገሩ ተማሪዎችን ጉዳይ እንዴት ታደርጋላችሁ?

አቶ ሰናይ፡- የተለያዩ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ስናስገባ ጉምሩክ ላይ ግብር እንድንከፍል ይደረጋል፡፡ የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ ትብብር እንዲያደርጉልን በደብዳቤ ጠይቀናል፡፡ ነገር ግን ፈጣን ምላሽ ስለማናገኝና ለውድድሮች የሚኖረንን ጊዜ በመመለስ እንዳንጨርስ ስንል ሌላ አማራጭ እንጠቀማለን፡፡ ሰዎች ሮቦቲክስ ሲባል ለሀብታሞች የተተወ የቅንጦት ነገር ነው የሚመስላቸው፡፡ አሜሪካ፣ ካናዳ ለመወዳደር የሚያስፈልጉ ሮቦቶችን አልያም ሌሎች መሠረታዊ ግብዓቶችን ከታክስ ነፃ አልያም አነስተኛ ታክስ ከፍለን ወደ አገር ለማስገባት ጥያቄ ስናቀርብ የሚቀበለን የለም፡፡ ብዙዎች የሮቦቲክስ ጉዳይ በራሱ አዲስ ይሆንባቸዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና ለማግኘት አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ስንሄድ ዘርፉ አዲስ ስለሆነ በምን ስታንዳርድ ፈትሸን ነው ዕውቅና የምንሰጣችሁ ተባልን፡፡ ከዚያ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በቴክኖሎጂና ሒሳብ ዘርፍ ዕውቅና ይሰጠን ብለን ጠይቀን ነው ያገኘነው፡፡ የሮቦቲክስ ጥቅም ተረድቶ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ማድረና ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ወይም በቅናሽ ለማስገባት ስለማንችል ብዙ ገንዘብ እንከፍላለን፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ የሊቲየም ባትሪ ያላቸው ድሮኖችን ፕሮግራም አድርገን ለመወዳደር ተነስተን ነበር፡፡ ነገር ግን የሊቲየም ባትሪ ዋጋው በጣም ውድ ነው፡፡ ከዚያ ሲያልፍም ዕቃውን አሽጎ በአውሮፕላን ጭኖ ከመላክ ጀምሮ የተለየ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ልንከፍል የምንችለውን ታክስ ስናሰላው ከሚገዛበት ዋጋ ዕጥፍ ድርብ ሆነ፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ሲያጋጥሙን ረከስ ያለ ነገር ለመፈለግ አልያም መጀመርያ በመረጥነው ዘርፍ ላለመወዳደር እንወስናለን፡፡

ሪፖርተር፡- በውጭ አገሮች በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ ስታደርጉ ወጪያችሁን የምትጋሩት እንዴት ነው? ስፖንሰር የሚያደርጋችሁስ አካል አለ?

አቶ ሰናይ፡- የቅንጦትና የሀብታም ነገር ስለሚመስላቸው ብዙዎች እኛን ስፖንሰር ማድረግ አይፈልጉም፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት አንድን ድርጅት አሜሪካ ሄደው በሮቦቲክስ የሚወዳደሩ ተማሪዎቻችንን ስፖንሰር አድርግልን ብለን ጠየቅን፡፡ ስንት የታመሙ ከባድ የሕክምና ችግር ያለባቸው እያሉ አሜሪካ ሄደው ለሚወዳደሩ ልጆች ስፖንሰር ማድረግ ይከብደናል ብለው መለሱን ኃላፊው፡፡ ይኼ የብዙዎቹ ኩባንያዎች ምላሽ ነው፡፡ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ነገር ግን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ልጆች ሲያጋጥሙን የትራንስፖርት፣ የሆቴል፣ ምግብና ሌሎችም ወጪያቸውን የሚችልላቸውን አካል ስፖንሰር ፈልጉ እንላለን፡፡ እኛም እናፈላልጋለን፡፡ ነገር ግን ካልተገኘ ወጪውን የሚችለው ወላጅ ራሱ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን ጉዞው ይቀርበታል ማለት ነወ፡፡ በውድድሩ ብቁ ሆነው በዚህ ምክንያት ብቻ የሚቀሩ ልጆች አሉ፡፡ እኛ ደግሞ እናወዳድራለን እንጂ ሌሎች ወጪዎችን የመሸፈን አቅም የለንም፡፡ ልጆቻችንን ከዓለም የሮቦቲክስ ውድድር ከመቅረት የሚያድን ሳይንስ አፍቃሪ ባለሀብት ማግኘት ያስፈልገናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሮቦቲክስ ዕድገት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች የሚኖረው ፋይዳ ምን ያህል ነው?

አቶ ሰናይ፡- ያደጉት አገሮች አብዛኛውን ሥራቸውን በሮቦቲክስ ተጠቅመው ነው የሚሠሩት፡፡ በሰው ልጅ ጉልበት ሊሠሩ የማይችሉ አድካሚና ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልጉ ውስብስብ ሥራዎች በኤአይ (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ነው የሚሠሩት፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች አብዛኞቹ በሰዎች የሚሠሩ ሥራዎች በኤአይ እየተሠሩ በመሆናቸው የሰው ልጅ ሥራ እንዳይፈታ ትልቅ ሥጋት እስከ መሆን ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ ምን ያህል ተጠቀምንባቸው የሚለው ነገር ነው እንጂ ብዙ ሥራዎች በኤአይ እየተሠሩ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ከፋዩን ሥራ ኤቲኤም ማሽን እየሠራው ነው፡፡ ካለንበት ሳንንቀሳቀስ ገንዘብ በስልካችን መላክና መቀበል እንችላለን፡፡ የመስኩ ዕድገትና ርቀት ኑሮን ያቃልላል፡፡ በኢትዮጵያ ባሉት ችግሮች ወደኋላ ቀረ እንጂ ብዙ ቢሠራበት የልማት መሠረት መሆን የሚችል ነው፡፡ ያሉት ችግሮች እንዳሉ ቢሆንም ሮቦቲክስ የማይቀር ነገር ነው፡፡ መግባት ካለብን አሁን ነው፣ ልጆቻችንን ኢንጂነሪንግ፣ ዲዛይን ኮዲንግ ማስተማር ያለብን አሁን ነው፡፡ ይኼንን ማድረግም መጪው የሥራ ዓለም ላይ መግባት የሚችሉ የሚመጥኑ ትውልድ ቀረፅን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከስንት ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎችን ትቀበላላችሁ? በተማሪዎቻችሁ ላይ የምታዩት ችግር ምንድነው ይላሉ?

አቶ ሰናይ፡- ከስድስት ዓመት ጀምሮ ያሉ ልጆችን እንቀበላለን፡፡ አልጀመርነውም እንጂ የሁለትና የአራት ዓመት ልጆችን የምንቀበልበት ፕሮግራምም አለ፡፡ ተማሪዎች በጽንሰ ሐሳብ የሚያውቋቸውን ትምህርቶች በተግባር አለማየታቸው የሚፈጥረው ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተግባር ትምህርት ሊሰጥ ይገባል፡፡ እኛ የምንቀበላቸው ልጆች የተግባር ትምህርት ነው የምንሰጣቸው፡፡ ተግባር ተኮር የትምህርት ፖሊሲው ጥሩ ቢሆንም፣ ምን ያህል ተተግብሯል የሚለው ግን የሁሉም ጥያቄ ነው፡፡ የቃሉን ትምህርት አልያም ቲዎሪን በተግባር መማራቸው ነገሮችን ይበልጥ ቀላል ያደርጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...