Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አንድ ነን!

‹‹እኔ ግን ሕዝቡን ሁሉ እንደዚህ አንድ ያደረጉበት ምትሃታዊ ኃይል ምን እንደሆነ እስካሁን አልተገለጠልኝም፤›› እያለ ወያላው ወሬውን ቀጠለ፡፡ እኔ መሀል ላይ ነው የተቀላቀልኳቸው፡፡ ማለትም አራት ኪሎ ላይ፡፡ ከስድስት ኪሎ ድረስ ይዘውት የመጡት ወሬ እንደሆነ ጠርጥሬያሁ፡፡ ጉዟችን ደግሞ ወደ ሜክሲኮ ነው፡፡ ሾፌሩ በበኩሉ፣ ‹‹መቼም ከላይ ካልተሰጠ በቀር እንደዚህ አገርን አንድ ማድረግ የሚችል መሪ በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ አያለሁ ብዬ ገምቼም አላውቅም ነበር፤›› አለው፡፡ በዚህ መሀል እንደኔው አራት ኪሎ ተንጋግተው ታክሲ ውስጥ ከገቡት ሰዎች አንዱ፣ ‹‹የአራት ሰው ሒሳብ ስንት ነው?›› በማለት ጠየቀው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ዘመኑ የመደመር ነው፣ እንኳን ይህችንና ሌላም እደምራለሁ፤›› የሚል እንግዳ የሆነ መልስ መለሰ፡፡

ይኼን ጊዜ ሒሳቡን የጠየቀው ሰውዬ ሁኔታውን በደንብ ለማጣራት ፈልጎ፣ ‹‹እሺ የአንድ ሰው ሒሳብ ስንት ነው?›› በማለት ጥያቄውን አስተካከለለት፡፡ የሰውዬው ጥያቄ ምናልባት ‘አንተ መደመር ካልቻልክ በነጠላ ዋጋውን ንገረኝና ደምሬ ልንገርህ’ የሚል ይመስላል፡፡ ወያላውም የሰውዬው አዝማሚያ ገብቶት፣ ‹‹እንዲያው እግዜሩ ያሳያችሁ በዚህ ዘመን ቢጠፋኝ ቢጠፋኝ መደመር ይጥፋኝ?›› በማለት ሁላችንንም ጠየቀን፡፡ ወያላው ተሳፋሪው የጠየቀውን የአንድ ሰው ሒሳብ ስንት ነው የሚለውን ችላ በማለት፣ የአራቱን ሰዎች ሒሳብ ደምሮ ነገረው፡፡

የአንድ ሰው ሒሳብ ጠይቆ የአራት ሰው የተነገረው ተሳፋሪ ቆጣ አለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወያላው የአንድ ሰው ሒሳብ የነገረው መስሎት የታክሲ ታሪፍ ባለማወቁ ሊያጭረበብረው እንደፈለገ ነበር የጠረጠረው፡፡ ዳሩ ግን ወያላው በመደመር ሳይጦዝ አይቀርም፡፡ ወያላው ቀጠለ፣ ‹‹እንኳንስ እዚህች ታክሲ ውስጥ የታደሙትን የ12 ሰዎች ድምር ይቅርና የመቶ ሚሊዮኑን የኢትዮጵያን ሕዝብ ድምር አውቃለሁ፤›› በማለት ተፈላሰፈ፡፡ ሾፌሩ ትንሽ ደስ ያለው አይመስልም፣ ‹‹አሁን ፍልስፍናውን ተውና የአሥራ ሁለት ሰው ድምር ብቻ እንድትሠራ ነው የተጠየቅከው፤›› ሲለው፣ ሌላ ነገሩ ግራ የገባው ተሳፋሪ፣ ‹‹ደግሞ የመቶ ሚሊዮን ድምር አውቃለሁ የምትለው የምን ቅዠት ነው? መቶ ሚሊዮን… መቶ ሚሊዮን ነው…›› በማለት የተቃውሞ ድምፁን አሰማ፡፡

ዛሬ ታክሲ ውስጥ ነግሳ የዋለው ወያላ አሁንም እያብራራ ነው፡፡ ‹‹ምን መሰለህ ለብዙ ዘመናት መቶ ሚሊዮን ሆነን ኖረን ነበር፡፡ ብዛታችን ኃይለኛ ያደርገን መስሎን ለካ ብዛት ከንቱ ነው፤›› በማለት ትንሽም ቢሆን እያሰበ ስላለው ነገር ፍንጭ ሰጠ፡፡ እኛም ብንሆን ፍንጫችንን እንደያዝን የወሬውን መጨረሻ ለመስማት ቋመጥን፡፡ በዚህ መሀል አንድ ወጣት ወሬያችንን ተቀላቀለ፣ ‹‹አይገርማችሁም?›› በማለት ወሬውን ቀጠለ፡፡ ‹‹አይገርማችሁም?›› አባባሉን ላጤነው ከዚህ በፊት በደንብ ለሚያውቃቸው ሰዎች ሐሳቡን እየገለጸ ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ‹‹አይገርማችሁም? እኔም ከረዳቱ ሐሳብ ጋር መደመር እፈልጋለሁ፤›› በማለት ሲቀጥል አንድ የተቃውሞ ድምፅ አስተናገደ፡፡ አንድ መቃወም የሚወድ የሚመስል ዓይነት ሰው ነው፣ ‹‹መጀመርያ ወያላው ምን ለማለት እንደፈለገ ሙሉ ሐሳቡን አድምጥ፡፡ ከዚያ ከፈለግክ መደመር አሊያም መደረብም ትችላለህ፡፡ ዝም ብሎ ሆ ብሎ መከተል ያለፈበት ዘመን ነው፤›› በማለት ትንሽ ውጥረት ቢጤ ታክሲው ውስጥ ፈጠረ፡፡

ሰውዬውም የዋዛ አልነበረም፡፡ ‹‹ምንም አለ ምን ከዚህ በኋላ ያለን ብቸኛው አማራጭ እንደምንደመር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ሐሳቡን ጨረሰው አልጨረሰውም እሱ ሐሳብ ላይ እንዴት እንደመር ነው እንጂ የማስበው፣ ሌላ ከመደመር የሚያዘገየኝን አንድም ነገር ለአንዲትም አፍታ ማሰብ አልፈልግም፤›› በማለት ፅኑ የአቋም መግለጫውን አስረዳ፡፡ ይኼኔ ወያላው መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹አሁንም ቢሆን የመቶ ሚሊዮን ድምር ውጤት እስካሁን ድረስ ጠፍቶበት የነበረው የአገሬ ሕዝብ፣ አሁን በጥቂቱም ቢሆን ተገልጦለታል፤›› ሲል ሾፌሩ ተቀበለውና፣ ‹‹ነገርን ማወሳሰብ ማንንም አልጠቀመም፡፡ ሐሳብህን ግልጽ አድርግልንና ወይ እንደመር…›› በበማለት ፈገግ አሰኘን፡፡ ከመደመር ውጪ ምንም ዓይነት አማራጭ የለም ለማለት የፈለገ ይመስላል፡፡

በዚህ መሀል አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው መናገር ጀመሩ፣ ‹‹እንግዲህ የኢትዮጵያ እንባ የሚታበስበት ዘመን ደረሰ ማለት ነው፤›› በማለት አፋቸውን አሟሹ፡፡ ብዙ የሚሉት እንዳላቸው ከፊታቸው ላይ ማንበብ ይቻላል፡፡ እኛም ፊት አልነሳናቸውም እንዲቀጥሉ ጆሮ ሰጠናቸው፡፡ ‹‹ብዙም የተለየ ሐሳብ ኖሮኝ ሳይሆን ወንድሜ ባለው ላይ ትንሽ ለመጨመር ብዬ ነው፡፡ በቅንፍ ውስጥ ለመደመር ብላችሁ ያዙልኝ፤›› በማለት አስፈገጉን፡፡ ሰሞኑን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመደመር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ይኸው ሁሉም ሰው ልብ ውስጥ ሰርፆ ገብቶ፣ ‹‹መደመር›› የምትለው የሒሳብ ሥሌት የትም ቦታ መግባት ችላለች፡፡ ሒሳብ ዝር ከማይልባቸው የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ሳይቀር ‹‹መደመር›› በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለች ትገኛለች፡፡

ሰውዬው ማብራራታቸውን ቀጥለዋል፣ ‹‹እንደ ጤፍ ለተቀላቀለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመደመር ውጪ ምንም ዓይነት አማራጭ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ ቢሆን እየተጠማ የነበረው ተራራ የሚያህል ዳቦ የሚጋግርለት መሪ ሳይሆን፣ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አንድነትን ከፍ አድርጎ የሚያውለበልብለት መሪ ነበር…›› እያሉ ሰፊ የአየር ሰዓት ወስደው ማብራራት ጀመሩ፡፡ ማንም ሰው ሊቃወማቸው የደፈረ አልነበረም፡፡ አዛውንቱ ቀጠሉ፣ ‹‹አያችሁልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ሲፈልግ እንደኖረ? ሰላም ወዳድ ሕዝብ እኮ ነው፡፡ ሰላሙም የሚረጋገጥበትን መንገድ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ እስከ ዛሬም የተሄደበትን መንገድ ሲቃወም የቆየው ውጤቱን ከሩቁ ተመልክቶት እኮ ነው፡፡ መቼም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በነፍስ ወከፍ ለማንም የሰጡት ገንዘብ ወይም የሥራ ዕድል የለም፡፡ ሆኖም ግን ለአንድነት፣ ለፍቅር፣ ለሰላምና ለእርቅ ያላቸው ፅኑ አቋም ገና ከመጀመርያው ቀን በሕዝብ ዘንድ ያጎናፀፋቸውን ተቀባይነት መመልከት ችለናል፡፡ ምክያቱም ለዘመናት ሕዝባችን ሲጠማ የነበረውን ነገር ስለሆነ ይዘውልን የመጡት፣ ገና ንግግራቸውን ሲያደምጥ ከንግግራቸው ቀዝቃዛ ምንጭ ጠጥቶ በመርካቱ ግማሹ በጭብጨባ፣ በእንባና በደስታ ነው የተቀበላቸው፤›› እያሉ ደስታ የተቀላቀለበትን ረዥም ማብራሪያቸውን አቀረቡልን፡፡

‹‹እንደ እውነቱ ከሆነ ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ለቆ ለሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ የሰጠ ያህል ነበር ሕዝቡ ዘንድ የነበረው ስሜት…›› በማለት አአንድ ፀጥ ብላ ወሬውን ስታደምጥ የነበረች ወጣት ተናገረች፡፡ ‹‹በእርግጥም…›› አለች ቀጥላ፣ ‹‹በእርግጥም ገዥው ፓርቲ እያሳየ ያለው መታደስ ይበል የሚያሰኘው ነው፡፡ ኢሕአዴግ አከተመለት፣ የዘመናት ግስጋሴው እየተገባደደ ያለ ይመስላል ተብሎ በሚገመትበት ወቅት አፈር ልሶ እንደ አዲስ በማቆጥቆጡ የሚገርም ጥልቅ ተሃድሶ ነው፡፡ መቼም የዘመናቱን ጥልቅ ተሃድሶ ሀ ብሎ ጀመረ ማለት ይቻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመምረጥ ያደረገውን ታላቅ ውሳኔ በቀጣይም በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ አጠናክሮ ሊገፋበት ይገባል፡፡ እስከ ታች ድረስ ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት ለተቀመጡበት ቦታ የማይመጥኑ ሰዎችን በመሸኘት፣ የተጀመው ጥልቅ ተሃድሶ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፤›› አለች፡፡

አይገርምም ይህንን ሁሉ ሰፊ ማብራሪያ ስትሰጥ ማንም ሊቃወማት የፈለገ እንኳን አልነበረም፡፡ ለበርካታ ደቂቃዎች ግላዊ ማብራሪያዋን ስታቀርብ ሁሉም ሰው በአክብሮት ነበር ያደመጣት፡፡ የሐሳብ ልዩነት ስለተፈጠረ ብቻ ድንጋይ መወራወር ድሮ ቀረ የሚሉ ይመስሉ ነበር የታክሲው ታዳሚዎች፡፡ ያንተ ሐሳብ ከእኔ ሐሳብ ስለተለየ መደባደብ ድሮ ቀረ፡፡ አንድ ዓይነት ለምን አልሆንም ብለን አስከፊ የሆነ ግጭት ውስጥ መግባት ድሮ ቀረ፡፡ በምትኩ የፈለግከውን ዓይነት የማሰብ ነፃነት አለህ፣ እኔንም አትንካኝ፡፡ በአንድነታችን እንቀላቀል፣ በልዩነታችን ደግሞ እንከባበር የሚል አስተሳሰብ የሰረፀ ይመስላል፡፡

ውይ ሞት ይርሳኝ ከአራት ኪሎ የጀመረው መንገዳችን በቤተ መንግሥት በኩል ሲያልፍ ሁሉም ሰው ማለት እደፍራለሁ አንገቱን እያንቀሳቀሰ ወደ ቤተ መንግሥቱ ግቢ አጮልቆ ይመለከት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ግቢ ውስጥ ምናልባት ጎርደድ ጎርደድ ሲሉ ባያቸው ብሎ ሳያስብ አልቀረም ያሰኛል፡፡ የሆነ ሰው፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚጠብቃቸው ፌዴራል ፖሊስ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምር እንጂ፤›› ያለው አስፈግጎኛል፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ በጉዞ መነሻዬ ላይ ወያላው ላላት ነገር አሁንም ድረስ መልስ አላገኘሁላትም ነበር፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር ይባርከውና ወያላው መልሱን ሰጠኝ፡፡ ‹‹የመቶ ሚሊዮን ድምር ውጤቱ ታውቋል፣ እርሱም አንድ ነው፡፡ በዚህ በኋላ በመቶ ሚሊዮንነታችን እንድንታወቅ አያስፈልገንም፣ ይልቁንም በአንድነታችንና በአንድነታችን ብቻ፡፡ ከዚህ በኋላ መቶ ሚሊዮን ሳይሆን አንድ ነን፡፡ ይኼ ነው የመደመር ውጤት፤›› አለ፡፡ በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደሰረፀ ተረዳሁ፡፡ ይህንን የሰማው ጎልማሳ፣ ‹‹የባቤልም ሕዝቦች እኮ ኑ አንድ ላይ ሆነን ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ ብለው በተነሱ ጊዜ ነበር እግዜሩ ከሰማይ ተመልክቷቸው እነዚህ ሰዎች አንድ ሆነዋል፣ ያሰቡትንም ነገር ከማሳካት የሚያግዳቸው ነገር የለም ብሎ ነበር፤›› አለ፡፡ ‹‹እነሆ ለዘመናት ቋንቋችንን የደበላለቀው ጋንጩር ተወግቶልናል፡፡ ከዚህ በኋላ መቶ ሚሊዮኖች ሳንሆን አንድ ነን፣ ስማችን ኢትዮጵያዊ፤›› የሚል ድምፅም ይሰማ ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት