ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ዳሰዋል፡፡ የንግግራቸው ሙሉ ቃል እንደሚተከለው ቀርቧል፡፡
የተከበሩ አፈ ጉባዔ
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ክቡራትና ክቡራን!
አገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቷ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከሁሉ አስቀድሜ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ለተከሰተው ፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍትሔ አካል ለመሆን፣ የአገር ክብርና ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ በአዲስ አመራር ሊጠበቅ ይችላል ብለው በማሰብ፣ ለአኅጉራችን ምሳሌ በሆነ መልኩ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ላሸጋገሩት ለክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፍ ያለ አክብሮቴን እገልጻለሁ፡፡ በተመሳሳይ የመንግሥታዊ ሥልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫወቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ሕዝባችን ስም ከልብ አመሠግናለሁ፡፡
ዕለቱ ለአገራችን ታሪካዊ ቀን ነው!
በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር ዕድሎችን አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል፡፡ አሁንም ይህ የሥልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ ዕድል ነው፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ማህፀነ ለምለም ናት፡፡ ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሁሌም የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች፡፡ ልጆቿም ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትሕ እንዲጠበቅ፣ ብልፅግና ያለ አድልኦ ለመላው ዜጎች ይዳረስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ. . . ይደክማሉ፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ ሆነው ስለአገር አንድነትና ሰላም፣ ስለፍትሕና እኩልነት እንዲሁም ስለብልፅግና ይጮሃሉ፣ ይሞግታሉ፣ ይሟገታሉ፡፡ ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት ዓበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው፡፡ ክስተቱ በአንድ በኩል በአገራችን ዘላቂ፣ የረተጋጋና ሁሉን አቀፍ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በሕዝብ ፍላጎት የሚገዛ፣ ሕዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑን ያመለክታል፡፡
ወቅቱ ከስህተታችን ተምረን አገራችንን የምንክስበት ወቅት ነው
መሪ ድርጅታችን ኢሕአዴግ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ አገራችንን ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት፣ በሁሉም መስክ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል፡፡ ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በሥጋት እየተመለከተው ያለ አገራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን፡፡ ያሳካናቸው በርካታ ድሎች እንዳሉ ሁሉ በፍጥነት መቀረፍ የሚገባቸው በርካታ ጉድለቶች እንዳሉም እናምናለን፡፡ ከስህተቶቻችን ተምረን ወደፊት በመራመድ ማተኮር ያለብን ጉዳይ የተሻለች አገር ለሁላችንም በመገንባቱ ላይ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር አገራችንን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገሩና አንድነቷን ጠብቃ የምትቆይበትን ሁኔታ በቀጣይነት እያረጋገጡ መሄዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ያስተማረን እውነታ በጊዜያዊ ችግሮች ተሸንፎ መውደቅን ሳይሆን፣ ፈተናዎችን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ ቀይሮ ድል መቀዳጀትን ነው፡፡
ትናንት አባቶቻችን በመተማ፣ በዓድዋና በማይጨውና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆዩዋት አገር አለችን፡፡ እኛ ዕድለኞች ነን፡፡ ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን፡፡ እኛ መነሻችንን እናውቃለን፡፡ በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ሕዝብ ነን፡፡ ኅብረታችንን ለዓለም ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ጠላቶቻችንን አንበርክኳል፡፡ ሉዓላዊነታችንን ጠብቆ ዛሬ ላይ ከማድረሱም በላይ፣ ለሌሎች ሕዝቦችም የነፃነት ትግል አርዓያ ሆኗል፡፡
ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋሀደ ነው
አማራው በካራማራ ለአገሩ ሉዓላዊነት ተሰውቶ የካራማራ አፈር ሆኖ ቀርቷል፡፡ ትግራዋይ በመተማ ከአገሬ በፊት አንገቴን ውሰዱ ብሎ የመተማ አፈር ሆኗል፡፡ ኦሮሞው በዓድዋ ተራሮች ላይ ስለአገሩ ደረቱን ሰጥቶ የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከዓድዋ አፈር ተቀላቅሏል፡፡ ሱማሌ፣ ሲዳማው፣ ቤንሻንጉሉ፣ ወላይታው፣ ጋምቤላው፣ ጉራጌው፣ አፋሩ፣ ስልጤው፣ ከምባታው፣ ሐዲያውና ሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በባድመ ከአገሬ በፊት እኔን ብለው እንደወደቁ ከባድመ አፈር ጋር ተዋህደዋል፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ አባት እንዳሉት እኛ ስንኖር ሰዎች፣ ስናልፍ አፈር፣ ስናልፍ አገር እንሆናለን፡፡ የየትኛውንም ኢትዮጵያዊ ክቡር ሥጋና ደም በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ አፈር ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያዊ እንሆናለን፡፡
ኢትዮጵያ የሁላችን አገር የሁላችን ቤት ናት
በአንድ አገር ውስጥ የሐሳብ ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ የሐሳብ ልዩነት እርግማን አይደለም፡፡ ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ መደማመጥና በመርህ ላይ ተመሥርተን መግባባት ስንችል የሐሳብ ልዩነት በረከት ይዞልን ይመጣል፡፡ በሐሳብ ፍጭት ውስጥ መፍትሔ ይገኛል፡፡ በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ፡፡ ስንደመር እንጠነክራለን፡፡ አንድነት የማይፈታው ችግር አይኖርም. . . አገር ይገነባል፡፡ የእኔ ሐሳብ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን እንኳን አገርን ሊያቆም ቤተሰብን ያፈርሳል፡፡ ያለችን አንድ ኢትዮጵያ ነች፣ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት በላይ አገራዊ አንድነት ይበልጣል፡፡ አንድነት ማለት ግን አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አንድነታችን ልዩነቶቻችንን ያቀፈ ብዝኃነታችንን በኅብረ ብሔራዊነት ያደመቀ መሆን አለበት፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲና ነፃነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም!
ዴሞክራሲ ለእኛ ባዕድ ሐሳብ አይደለም፡፡ በዓለም ውስጥ በብዙ ማኅበረሰቦችና አገሮች ዴሞክራሲ በማይታወቅበት ዘመን በገዳ ሥርዓታችን ተዳድረን ለዓለም ተምሳሌት ሆነን ኖረናል፡፡ አሁንም ዴሞራክሲን ማስፈን ከየትኛውም አገር በላይ ለእኛ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ዴሞክራሲ ያለነፃነት አይታሰብም፡፡ ነፃነት ከመንግሥት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታም አይደለም፡፡ ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንዱ ሰው የተፈጥሮ ፀጋ እንጂ፡፡ ነፃነትን በዚህ መልኩ ተረድቶ ዕውቅና የሰጠውን ሕገ መንግሥታችንን በአግባቡ መተግበር፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም ሐሳብን የመግለጽ፣ የመሰባሰብና የመደራጀት መብቶች በሕገ መንግሥታችን መሠረት ሊከበሩ ይገባል፡፡ የዜጎች በአገራቸው የአስተዳደር መዋቅር በዴሞክራሲያዊ አግባብ በየደረጃው የመሳተፍ መብትም ሙሉ በሙሉ ዕውን መሆን አለበት፡፡
ሁላችንም መገንዘብ ያለብን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መደማመጥን ይጠይቃል፡፡ ሕዝብ አገልጋዩን የመተቸት፣ የመምረጥ፣ የመጠየቅ ሙሉ መብት አለው፡፡ መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው፡፡ ምክንያቱም ገዥ መርሐችን የሕዝብ ሉዓላዊነት ነውና፡፡ በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የመጀመርያውም የመጨረሻውም መርሕ፣ በመደማመጥ የሐሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የጋራችን፣ የእኛ የሁላችን መሆኗን ተገንዝበን የሁሉም ድምፅ የሚሰማበት፣ ሁላችንንም የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመገንባቱን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
ዴሞራክሲ ሲገነባ መንግሥት የዜጎችን ሐሳብ በነፃነት የመግለጽ መብት ማክበር አለበት፡፡ ዴሞክራሲን ከዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴና ከመንግሥት መሪነት፣ ደጋፊነትና ሆደ ሰፊነት ውጪ ማዳበር አይቻልም፡፡ በመሆኑም መንግሥት የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል በፅናት ይሠራል፡፡ በተመሳሳይ ዜጎች ሐሳባቸውን ሲገልጹ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መሆን ይገባዋል፡፡ የራስን ዴሞክራሲያዊ መብት እየጠየቁ የሌላውን መብት መጋፋት እርስ በርሱ ይጣረሳል፣ ዴሞክራሲንም ያቀጭጫል፡፡ መንግሥት ሕግን ማክበር አለበት፣ ማስከበርም ግዴታው ነው፣ ታጋሽነትም ኃላፊነቱ ነው፡፡ የመንግሥት ታጋሽነት ሲጓደልም ዴሞክራሲ ይጎዳል፡፡ በሁለቱም አካሄድ የምንናፍቀው ዴሞክራሲ ሊመጣ አይችልም፡፡
በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ የሕግ የበላይነት መስፈን ይገባዋል፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን በምናደርገው ትግል መርሳት የሌለብን ቁም ነገር፣ ሕዝባችን የሚፈልገው የሕግ መኖርን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ መረጋገጥንም ጭምር ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ከፍትሕ የተፋታ ደረቅ ሕግ ሳይሆን በፍትሕ የተቃኘ፣ ለፍትሕ የቆመ የሕግ ሥርዓትን ነው፡፡ የሕዝብ ፍላጎት የሕግ አስከባሪ ተቋማት ገለልተኛና ለፍትሕ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ቀናዒ እንዲሆኑ ነው፡፡ ሕግ ሁላችንንም እኩል የሚዳኝ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ሕግ በተፈጥሮ ያለንን ሰብዓዊ ክብራችንን ያስጠብቅልናል፡፡ ይህን እውነታ በመረዳት በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲያብብ፣ ነፃነትና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት ዕውን እንዲሆን አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ በዘርፉ ያለውን ክፍተት እንሞላለን፡፡
ለሰላም መሠረቱ ፍትሕ ነው፡፡ ሰላም የግጭት አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ ሰላም በመግባባት ላይ የተመሠረተ ፅኑ አንድነታችን ነው፣ ሰላም መተማመናችን ነው፡፡ ሰላም በሁላችንም ፈቃድ ዛሬም የቀጠለ የአብሮነት ጉዟችን ነው፡፡ ሰላም አለመግባባትና ተቃርኖዎችን በሠለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችለን መንገድና ግባችን ነው፡፡
የተከበሩ አፈ ጉባዔ
ክቡራትና ክቡራን
ያለንበት ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ በቀውስ ውስጥ ያለበት፣ ብዙ የየራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ ያላቸው ኃይሎች የሚራኮቱበት፣ ውስብስብ መጠላለፍ በቀጣናው ያለበት ወቅት ነው፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረዥም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ያለንበት አካባቢ ነው፡፡ የውጭ ግንኙነታችንን በተመለከተ አገራችን የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት፣ የአፍሪካ ኅብረት መሥራችና መቀመጫ፣ የቀደምት ዓለም አቀፍ ተቋማት መሥራችና በዓለም አቀፍ፣ በአኅጉር አቀፍ፣ እንዲሁም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ጉልህና ገንቢ ሚና የምትጫወት አገር ናት፡፡ ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሠረተውን ፖሊሲያችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ከአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጋር በአጠቃላይና ከጎረቤቶቻችን ጋር በተለይ በችግርም በተድላም አብረን እንቆማለን፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለዓመታት ሰፍኖ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃም ከልብ እንፈልጋለን፡፡ የበኩላችንንም እንወጣለን፡፡ በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለጽኩ፣ የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የተከበሩ አፈ ጉባዔ
የተከራበችሁ የምክር ቤት አባላት
ክቡራትና ክቡራን
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉት ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው፡፡ ሙስናን ፀረ ሙስና ተቋም በመመሥረት ብቻ መከላከል እንደማይቻል ተረድተን፣ ሁላችንም ኢትዮጵያችን አንዱ ሠርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር እንዳትሆን ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ በትህትና እጠይቃችኋለሁ፡፡
ትናንት የተፈጠረን ሀብት ከሌላው በመቀማት ሒሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም፡፡ ገበታው ሰፊ በሆነባት፣ ሁሉም ሠርቶ መበልፀግ በሚችልባት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት የለም፡፡ ይልቁንም ወቅቱ የፈጠረልንን ልዩ አጋጣሚና አገራዊ አቅማችንን አቀናጅተን የእጥረትና የዕጦት አስተሳሰብን በማስቀረት ለጋራ ብልፅግና እንትጋ፡፡ ታዋቂው የህንድ የነፃነት ንቅናቄ መሪ ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንደተናገረው አገር ለሁሉም የሚሆን በቂ ሀብት አላት፣ ሁሉም እንደ ልቡ የሚዘርፈው ሀብት ግን ሊኖራት አይችልም፡፡ አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትንና የተደራጀ ሙስናን መላው ሕዝባችንን በሚያሳትፍ ዕርምጃ ለመመከት ሌት ተቀን እንተጋለን፡፡
ክቡራትና ክቡራን
አገራችን ላለፉት ዓመታት ባስመዘገበችው ፈጣን ዕድገት የተነሳ በድህነት ቅነሳ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በሰው ኃይል ልማትና በመሳሰሉት ያገኘናቸው ስኬቶች ለሁሉም የሚታዩ ናቸው፡፡
ከዚህ አኳያ መንግሥት የዋጋ ንረትና የወጭ ምንዛሪ ዋጋን ለማረጋጋት፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤናማነት ለመጠበቅ፣ ለኢኮኖሚ የሚቀርበውን የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና አካታችነትን ለማስፋት፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እንዲሁም ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታት፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የሕዝቡን የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግ፣ እንዲሁም አስከፊ ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የፖሊሲና የትግበራ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡
በአንፃሩ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት የኢኮኖሚ ዕድገቱንና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ተከስተዋል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ የወጪ ንግድ በምንፈልገው መጠን አለማደጉ፣ ይኼን ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ በውጭ ዕዳ ጫናና በአገር ውስጥ ቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ናቸው፡፡ በግብርናው ዘርፍ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም ዘርፉን በተገቢው ሁኔታ በቴክኖሎጂ መደገፍ ባለመቻሉ፣ እንደ አገር ማግኘት የሚገባንን የኢኮኖሚ ትሩፋት ሳናገኝ ቆይተናል፡፡ እንደ ትልቅ አገርና ሕዝብ ከምናስበው የስኬት ጫፍ ላይ መድረስ የምንችለውና ችግሮቻችንን የምንፈታበትን ዋና ቁልፍ የምናገኘው በትምህርትና በትምህርት ብቻ እንደሆነ በማመን፣ መንግሥት ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም በተለይ የትምህርትን ጥራት ከማስጠበቅ አንፃር እጅግ ብዙ የቤት ሥራዎች ከፊታችን እንዳሉ በውል በመገንዘብ በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ የትምህርት መስፋፋት ይበል የሚያሰኝ የመንግሥታችን ስኬት ቢሆንም ይህ የትምህርት ሽፋን ዕድገት በጥራት እስካልተደገፈ ድረስ፣ ልፋት ጥረታችን ሁሉ የምንተጋለትን ውጤት ሊያመጣልን አይችልም፡፡ በመሆኑም ከመጀመርያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉትን የዕውቀት ዓለሞቻችንን በጥራት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ መንግሥት በፍፁም ቁርጠኝነት ይረባረባል፡፡ በተለይም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚወጡት ተማሪዎቻችን ከሚገበዩት ዕውቀት የሚነፃፀር ክህሎት እንዲኖራቸው ጥረት ይደረጋል፡፡ እንዚህንና ሌሎቹንም ችግሮቻችንን ለመቅረፍ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በመገምገምና አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን በመውሰድ፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል እንተጋለን፡፡
ውድ የአገራችን ወጣቶች!
ኢትዮጵያ የእናንተ ነች፣ መጪው ዘመን ከሁሉ በላይ የእናንተ ነው፡፡ አሁንም አገሪቱን በመገንባት ግንባር ቀደም ሆናችሁ መሳተፍ ይኖርባችኋል፡፡ የወጣቱ ጥያቄ የኢኮኖሚና የእኩል ተጠቃሚነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከማሳደግ አንፃር ክፍተቶች ነበሩ፡፡
አገራችን ጥሩ የሚባል ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እያስመዘገበች እንደሆነ ቢታወቅም ዕድገቱ በቅርፅና በይዘት ተለዋዋጭ የሆነውን የወጣቱን ትውልድ ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ የሚያረካ አልነበረም፡፡ ይህም ሕዝባችንን ለብሶት እንደዳረገው እንገነዘባለን፡፡ ያለወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አገር የትም ልትደርስ እንደማትችልም እንረዳለን፡፡ ኢትዮጵያ ለወጣቶቿ ተስፋ የምትሰጥ እንጂ፣ ተስፋ የምታስቆርጥ አገር እንዳትሆን የምንችለውን ሁሉ እንደምናደርግ ቃል እገባለሁ፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያት ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን ወጣት ባለሀብቶች በብዛት እንዲፈጠሩ እንሠራለን፡፡ ለዚህ እንቅፋትና መሰናክል የሚሆኑ አመለካከቶችና የተንዛዙ አድሏዊ የሆኑ አሠራሮችን አስወግደን ፍትሐዊ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዲኖረን መንግሥት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ መርሳት የሌለብን ሀቅ ግን ለራሱም ሆነ ለአገሩ በሥራውና በጥረቱ ሀብት የሚፈጥረው ወጣቱ ራሱ መሆኑን ነው፡፡
ውድ የኢትዮጵያ ሴቶች
በብዙ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያን ገንብታችሁ፣ ታሪክ ሠርታችሁ፣ ትውልድ ቀርፃችሁ ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ በትግላችሁም የተሻለች አገር እንድትኖረን ብዙ መስዋዕትነት ከፍላችኋል፡፡ ትግላችሁ የፍትሕ ትግል ነው፣ ትግላችሁ ክቡር ትግል ነው፣ ትግላችሁ ትግላችን ነው፡፡ መንግሥት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና በአገራችን ሁለንተናዊ የዕድገት ግስጋሴ ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ አሁንም ከሠራነው ይልቅ ያልሠራናቸው ሥራዎች እጅግ እንደሚበዙ እናምናለን፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የአገራችን ሴቶች ተፈጥሮና ኑሮ የሰጧችሁን በረከቶች ተጠቅማችሁ ለአገራችን ዕድገትና ብልፅግና፣ እንዲሁም ለፖለቲካችንም ስምረት አዎንታዊ ሚና እንደምትጫወቱ ተስፋዬ የላቀ ነው፡፡
አገራዊ ማንነታችን ያለ እናንተ ያለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምንም ነው፡፡ አገሪቷን የገነቡ፣ ያገለገሉ፣ ያቆሙ ሴቶችን ዕውቅና በመንፈግ አገራዊ ትንሳዔን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ መንግሥታችን ለሴቶች መብትና እኩልነት የሚቆመው፣ ለሴቶቻችን ውለታ ለመዋል ሳይሆን ለሁላችንም ብለን ነው፡፡ ግማሽ አካሉን የረሳ አገር ሙሉ የአገር ሥዕል ይኖረው ዘንድ ከቶ እንደማይችልና ወደፊትም እንደማይራመድ መንግሥት በውል ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም መንግሥታችን ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍጥነትና የትግበራ ስኬት በላቀ መልኩ ለሴቶች ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ይሠራል፡፡
የተከበሩ አፈ ጉባዔ
የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
የተከበራችሁ የአገራችን ሕዝቦች
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች
ክቡራትና ክቡራን
ችግሮቻችንን በርካታና ፋታ የማይሰጡ ናቸው
የዳበረ የዴሞክራሲ ባህል አለመኖር፣ ሥር የሰደደ ድህነት፣ የተደራጀ የሙስናና ብልሹ አሠራር መስፋፋት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ተደማምረው ሰፊና ውስብስብ ፈተና ደቅነውብናል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወገኖቻችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለመፈናቀል፣ ለሕይወትና ንብረት መጥፋት ተዳርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዜጎች በአገራቸው ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት መብታቸው መከበር አለበት፡፡ በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዲያበቃና ዳግም እንዳይፈጠር መሥራት ይኖርብናል፡፡
ችግሮቻችንን ተለያይተን ቀርቶ ተባብረንና ተዋደንም ለመፍታት ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡ በመሆኑም የባከነውን ጊዜ በማካካስ ወደፊት መጓዝ እንችል ዘንድ በአዲስ መንፈስ መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡ ሁሉም ችግሮቻችን በአንዲት ጀንበር ሊፈቱ አይችሉም፡፡ ነገር ግን የጀመርነውን የተሻለች አገር የመገንባት ሒደት ማፋጠን እንችላለን፡፡ የተሻለች አገር መገንባት የሚያስችል ጠንካራ ተነሳሽነት አለ፡፡ ጠንካራ አገር ለመገንባት ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ እንደ ተለያየ አገር ዜጋ በባዕድነትና ባይተዋርነት ሳይሆን፣ ሁላችንም እንደ ባለቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ሲሆን ስንወድቅም፣ ስንነሳም በጋራ ይሆናል፡፡
በቀሪው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ዓመታት ቀሪ የልማት መርሐ ግብሮቻችንን በፈጠነ ጊዜ ለማሳካት ጥረት ይደረጋል፡፡ ከመደበኛው የሥራ ሰዓታችን በሚሻገር ጊዜ፣ ከፍ ባለ ፍጥነትና ተነሳሽነት በመሥራት በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የደረሰብንን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት ለማካካስ አገራዊ ንቅናቄ እንድናደርግ ከአደራ ጭምር መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
የተከበሩ አፈ ጉባዔ
የተከራበችሁ የምክር ቤት አባላት
ክቡራትና ክቡራን
በውጭ አገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሥራም ሆነ ለትምህርት በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ተሸክሟት ይዞራል፡፡ ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሁላችሁም በታታሪነታችሁ፣ በልቀታችሁና የትም በሚከተላችሁ የአገራችሁ የጨዋነት ባህሪ የኢትዮጵያና የእሴቶቿ እንደራሴዎች ናችሁ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለፀጉ አገሮች ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለአገራችሁ ቁጭት ሳይሰማችሁ አይቀርም፡፡ ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ፡፡ እንደ አገር ያለንን ሀብት አሟጠን ለመቀጠም የምናደርገው ጥረት በቂ ሳይሆን ሲቀር መቆጨታችሁ አይቀርም፡፡ መቆጨትም አለባችሁ፡፡ ይኼንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ አገር አለችንና ዕውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ አገራችሁ መመለስና አገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን፡፡ በውጭ አገሮች ኑሯችሁን ላደረጋችሁትም ቢሆን በማንኛውም መልኩ በአገራችሁ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንድትሆኑና አገራችንን በሁሉም መልክ ለመቀየር ለምታደርጉት አስተዋጽኦ መንግሥት ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል፡፡
ውድ የልማት አጋሮቻችን
እስከ ዛሬ ባደረግነው የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ከጎናችን የቆማችሁ የልማት አጋሮቻችን የአገራችን ጥብቅ ወዳጆች እንደሆናችሁ እንገነዘባለን፡፡ የአገራችንን ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት እንደ ወትሮ ሁሉ ከጎናችን እንደምትቆሙ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
መጪው ጊዜ በኢትዮጵያ የፍቅርና የይቅርታ ጊዜ ነው
አገራችን ፍትሕ፣ ነፃነትና ሰላም የሰፈኑባት፣ ዜጎቿ በሰብዓዊነት የሚተሳሰቡባት፣ በእህትና ወንድማማችነት የተሳሰሩባት እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ህልማችን ዕውን የሚሆነው ከእንቅልፋችን ነቅተን ስንሠራ ነው፡፡ መመኘታችን መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ምኞታችን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መሥራት፣ መትጋትና መታገል ይጠበቅብናል፡፡ በመጀመርያ ሥራችን ልናደርገው የሚገባንና ትግላችን ማተኮር ያለበት ራሳችን ላይ ነው፡፡ አመለካከታችንን ከጥላቻ፣ ከቂም በቀል ስሜትና ከዘረኝነት ማፅዳት ይኖርብናል፡፡ በብሔር፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አመለካከትና በሃይማኖት፣ ወዘተ. ያሉንን ልዩነቶች እንደ በረከትነታቸው በፍቅር ማስተናገድ ከልዩነቶቹ የሚነሳ አለመግባባት ቢኖር እንኳ ከፍትሕ እንጂ ከበደል ጋር ባለመተባበር ሞራላዊ ዕይታዎቻችንን ልናስተካክል ይገባል፡፡ ፍትሕ ዋናው መርሐችን፣ ለሰው ልጆች ሁሉ ፍቅርና ክብር የሞራል መልህቃችን ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ሠርተን የማናገባድደው፣ ሁሌም ልፋት፣ ሁሌም ትግል፣ የሚጠይቅ የዕድሜ ዘመን ሁሉ የቤት ሥራ ነው፡፡
አገራችን በአሁኑ ወቅት ለደረሰችበት ምዕራፍ በርካታ ትውልዶች መስዋዕት ሆነዋል፡፡ አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ዕውን እንዲሆንም አዕላፎች ተሰውተዋል፡፡ ታዳጊውን ዴሞክራሲያችንን ለማዳበር ግን ተጨማሪ የሕይወትም ሆነ የአካል መስዋዕትነት አያስፈልገንም፡፡ ባለፉት ዓመታት እንደ መንግሥትም እንደ ዜጎችም ከዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበር ጋር ተያይዞ በታዩብን እጥረቶች በዜጎቻችን ሕይወትና በግልም በጋራም ንብረቶቻችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህንን ሁላችንም ማስቀረት እንችልና ይገባንም ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎችና ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቦርቁ ሕይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች፣ ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ቀውስ ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ እንዲሁም ሰላም ለማስከበርና ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲንቀሳቀሱ ሕይወታቸውን ላጡ የፀጥታ ኃይሎች አባላት፣ ለከፈሉት መስዋዕትነት ያለኝን አድናቆትና አከብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት በማበጀት ሕዝባችንን እንደምንክስም ጭምር በዚሁ አጋጣሚ ቃል እገባለሁ፡፡
በአገር ውስጥም ሆነ በስደስት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምዕራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ አገራዊ ምዕራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
ክቡራን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎች የምናይበት መነጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ እንደ መጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግሥት በኩል ፅኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ፣ ስለሰላምና ፍትሕ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና አገራዊ ፍቅር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
የአገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ በሁሉም ደረጃ የምትገኙ የአገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ በገጠርም ሆነ በከተማ የምትገኙ የተለያየ ሙያ ባለቤቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ሙስሊሞች፣ ክርስቲያኖች፣ ዋቄፈታዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ሃይማኖቶችን የምትከተሉ ወገኖች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የምትገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁላችንም የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንረባረብ! አገራችንን ከድህነት አዘቀት ውስጥ ለማውጣት እንትጋ! ዘረኝነትና መከፋፈለን ከአገራችን እናጥፋ! የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!
የዛሬው ዕለት በአኩሪ ኢትዮጵያዊ ወኔ የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ሰባተኛ ዓመት ነው፡፡ በዚህ ግድብ ግንባታ የታየው አንድነትና መሰባሰብ የአገራችንን ችግሮች በሙሉ መቅረፍና መሻገር እንደምንችል ያረጋገጠልን በመሆኑ፣ ይህንኑ መንፈስ ይዘን ከግድቡ መጠናቀቅ ባሻገር የአገራችንን ብልፅግና እስከምናረጋግጥበት ከፍታ ድረስ እንድንዘልቅ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በመጨረሻም በዚህ ወቅት አገሬንና ሕዝቤን ለማገልገል ይህን ከባድ ኃላፊነት ስቀበል አመሠግናቸው ዘንድ የሚገቡኝን አካሎች እንዳመሠግን ትፈቅዱልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ በመጀመርያ ለዚህ ኃላፊነት የመረጡኝና እምነት የጣሉብኝ ድርጅቴ ኢሕአዴግንና የአገሬን ሕዝብ በተለየ አክብሮትና ፍቅር አመሠግናለሁ፡፡
ሁለተኛ የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ እንዲህ ከፊታችሁ እንደምቆም የምታውቅና ይህንን ሩቅ፣ ጥልቅና ረቂቅ ራዕይ በውስጤ የተከለች፣ ያሳደገችና ለፍሬ ያበቃች አንዲት ኢትዮጵያዊ እናት እንዳመሠግን በትህትና እጠይቃለሁ. . . ይቺ ሴት እምዬ ናት፡፡ እናቴ ከሌሎቹ ቅን የዋህና ጎበዝ ኢትዮጵያውያን እንደ አንዶቹ የምትቆጠር ናትና ቁሳዊ ሀብት ብቻ ሳይሆን ዓለማዊ ዕውቀትም የላትም፡፡ በእናቴ ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያ እናቶች ዋጋና ምሥጋና እንደ መስጠት በመቁጠር ዛሬ በሕይወት ካገጠቤ ባትኖርም ውዷ እናቴ ምሥጋናዬ ከአፀደ ነፍስ ይደርሳት ዘንድ በብዙ ክብር ላመሠግናት እወዳለሁ፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እናቶቼ በልጆቻቸው የነገ ራዕይ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በመገንዘብ፣ ነገ ለሚያጭዱት መልካም ፍሬ ዛሬ ላይ የሚዘሩት ዘር ዋና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ለሚከፍሉት መስዋዕትነት ያለኝን በምንም የማይተካ አድናቆት ምሥጋናና ክብር በብዙ ፍቅር ሳቀርብ፣ በቀጣይም ልጆቻችን የዚህ አገር ህዳሴ እንዲረጋገጥ ዋና ተዋንያን መሆን እንዲችሉ እናታዊ አይተኬ ሚናችሁን እንድትወጡ አደራ ለማለት ጭምር ነው፡፡
ሦስተኛ የሚስቶች ስኬት ሁለት – ሦስት ነው፡፡ ሁለት ሲሆን አንዱ የራሳቸው ሌላው የባላቸው፡፡ ሦስት ሲሆን ደግሞ የልጆቻቸውም ይጨመርበታል፡፡ አንዳንዴ የድል ስኬታቸው ከዚህም ይሻገራል፡፡ የእናቴን ራዕይ ተረክባ በብዙው የደገፈችኝና የእናቴ ምትክ የሆነችልኝ ውዷ ባለቤቴ ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከእነዚህ ሚስቶች ተርታ ትመደባለችና እጅግ አድርጌ ላመሠግናት እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻም ከትግል ጓዶቼና በዝለት ጊዜ ብርታት፣ በድካም ጊዜ ኃይል ከሆኑኝ የቅርብ የሩቅ ወዳጆች ውጪ ዛሬ እኔ ከፊታችሁ መቆም ባልቻልኩ ነበር፡፡ ለሁላችሁም ከልብ የመነጨ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልፅጋ ለዘለዓለም ትኑር!›› ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ! አመሠግናለሁ!