Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ ጉዳዮች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበዓለ ሲመታቸው ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር አብዛኛውን ሕዝብ አስደምሟል፡፡ በርካቶች ንግግራቸውን በየፊናቸው እየተቀባበሉ ሲያስጋቡት ታይተዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ደጋግመው አሰምተውታል፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾች በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶዎችና ንግግሮች ተጣበዋል፡፡

      በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ታዋቂ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም ይህንኑ ያጠናከረ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ንግግራቸው ተስፋን  የሚሰንቅ፣ አዲስ ጅማሮን የሚያመላክት ስለመሆኑ ከሕዝቡ እየተደመጠ ይገኛል፡፡

      ‹‹ሰውየው ያደረጉት ንግግር ሰውኛ ነው፤›› የሚለውን ዓይነት አስተያየት ጨምሮ በአገር ውስጥም በውጭ ያለውም፣ ብረት ያነገበው ተቃዋሚው ጎራም የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር መምጣት ብሎም የንግግራቸውን ተስፋ ሰጪነት እንደሚቀበለው ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ ‹‹ከአንድ የአገር መሪ የምንጠብቀው፣ ስናፍቀው የነበረ ኢትዮጵያዊነትን ያጎላ ‹ኢትዮጵያችን›፣ ‹ኢትዮጵያ› የሚሉ ቃላቶች ተደጋግመው የሰማንበት›› ያሉም አልታጡም፡፡ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን 35 ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ከ25 ጊዜ በላይ መጥቀሳቸውን በዚህ ዘመን መስማት እንዳስደሰታቸው የገለጹ አሉ፡፡

ስለእናታቸውና ባለቤታቸው የተናገሩትን በመጥቀስ ‹‹አስለቅሰውኛል›› ያለች አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አሁን የሕዝብ መሪ አገኘች፤›› በማለት ስሜቷን ተናግራለች፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም አንድ ሁለት ጊዜ ይቅርታ ሲጠይቁ ሰምቻለሁ፤›› ያለው ሌላ አስተያየት ሰጪ፣ ‹‹ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሰማሁት ይቅርታ ግን ተለይቶብኛል፤›› ብሏል፡፡

‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ስሰማ የታየኝ ትልቅ ተስፋ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉት የሕግ ባለሙያዋና የቀድሞ የእናት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ናቸው፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለአንድነትና በአጠቃላይ ሁሉንም ነገር የዳሰሰው ንግግራቸው አስደማሚ ነበር ይላሉ፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለፈውን ሳይሆን የወደፊቱን፣ ባለፈው ሳይሆን በመጪው ላይ ማተኮርን እንደሚሹ  ያሳዩበትን ንግግር ለሕዝብ እንዳሰሙ ወ/ሮ መዓዛ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም በእሳቸው ደረጃ የሴት ውለታን በሚያንፀባርቀው ንግግራቸው ውስጥ ለሴቶች የሰጡትን ክብር አወድሰውላቸዋል፡፡

      የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ተስፋፍቶ የወጪ ንግድ ሥራ ሲጀመር ከጥንስሱ አንስቶ ከነበሩና በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አንጋፋ የዘርፉ ተዋናዮች አንዱ የቀድሞው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ አበበ ይጠቀሳሉ፡፡ አቶ ፀጋዬ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ኢትዮጵያዊነት የጎላበት እንደነበር ጠቅሰው፣ አንድነትን ደጋግመው ማውሳታቸውም ልብ እንደሚሞላ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስለእኛና ስለኢትዮጵያ እንዲሁም ስለአካባቢው ሰላምና ብልፅግና የገለጹበት መንገድ ነገን በተስፋ እንድንመለከት ያደርጋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ኢትዮጵያውያንን ከሥጋት ካባ የገፈፈ ብቻም ሳይሆን፣ ሰላምን በማስፈን ልማት ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚጋብዝ፣ ድብርት ላይ የነበረውን ቢዝነስና ሌላውንም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃ ስለመሆኑም አቶ ፀጋዬ አክለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር አብዛኛውን ነገር ለመዳሰስ መሞከራቸውን ያስታወሱት አቶ ፀጋዬ፣ ‹‹ከአንድ የአገር መሪ የሚጠበቅ ንግግር ነበር፤›› ብለውላቸዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሕዝብ ለሰጣቸው ክብርና ዕውቅና እንደ ሥጦታ ያበረከቱት የሚደነቅ ንግግር፤›› በማለት ንግግራቸውን አወድሰውታል፡፡ ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለማቅናት ያደረጉትን ጥሪ ሁሉም ልብ ሊለው እንደሚገባም አቶ ሰለሞንም ሆኑ አቶ ፀጋዬ አስታውሰዋል፡፡

የኅብረት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር፣ የቀድሞው የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት የነበሩት ጉምቱው የመድን ዘርፍ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉም ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚገልጹት አላቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመትና ንግግር መደመማቸውን ጠቅሰው፣ ኢሕአዴግ እኝህን ሰው በመምረጥ ተዓምር ይሠራል ብለው በተስፋ መጠባበቃቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከምርጫው በፊትም ቢሆን ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የዶ/ር ዓብይ መመረጥ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ይጠበቅ እንደነበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ይናገራሉ፡፡ ኢሕአዴግ ወጣቱን ዓቢይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት  ሰይሞ ተዓምር ይሠራል በማለት ያስቀመጡት ትንቢያ እንደተሳካላቸውም ገልጸዋል፡፡

የዶ/ር ዓብይ መመረጥ ቀድሞም ይጠበቅ ነበር የሚሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ይህንን አባባላቸው ከራሳቸው በመነሳት ያብራራሉ፡፡ በግላቸው ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ እንደሚሆኑ በማመን ‹‹ፖስታ አዘጋጅቼና አሽጌ ምርጫ እስከማድረግ ደርሻለሁ፡፡ ይህንን ምርጫዬን የያዘውን ፖስታ በጓደኞቼ ፊት እከፍተዋለሁ ብዬ ነበር፡፡ ይህንኑም አድርጌያለሁ፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ዓብይ (ዶ/ር)  እንደሚረከቡ የራሳቸውን ምርጫ በማካሄድ ያደረጉትን ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን ዶ/ር ዓብይ ብቻ ሳይሆኑ ያሸነፉት ከእሳቸው ጋር ተወዳድረው ድምፅ ያላገኙትም እንዳሸነፉ ይቆጠራል፡፡ አንዳንድ መሪዎች ከእነሱ በኋላ የሚታወቁበትን ሁኔታ ይፈጥሩታል፡፡ አንዳንድ መሪዎች ደግሞ ሁኔታው ራሱ ይፈጥራቸዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በሁኔታዎች የተፈጠሩ ናቸው፤›› ብለዋቸዋል፡፡

አብዛኛው ሕዝቡ መሆን ያለበት ነገር ሆኗል ያሉት አቶ ኢየሱ ወርቅ፣ ከተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በተቃራው ድምፅ የሰጡም አሸናፊዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ያሸነፈው ሰው የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ድምፅ ካገኘ፣ አሸናፊው ሁሉም ነው፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጡበትን ሒደት አስታውሰው ከግሩም ንግግራቸው ባሻገር፣ አስገራሚ ሊሆን የሚችለው ግን በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ መፈጸም የሚችሉት ሥራና በመጪው አገር አቀፍ የፖለቲካ ምርጫ ሁሉንም ወገን ያሳተፈ ምርጫ እንዲካሄድ ሲያደርጉ ነው በማለት የወደፊቱን ወሳኝ ሥራ አስታውሰዋል፡፡ ለአቶ ኢየሱስ ወርቅ ትልቅ ተዓምር የሚሆንባቸው በመጪው ምርጫ የሚያዩት እውነታ እንደሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በርካታ ጉዳዮችን ከዳሰሰው የዶ/ር ዓብይ ንግግር ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የጠቀሷቸውን ነጥቦች፣ ሪፖርተር ያጋገራቸው የቢዝነሶች ሰዎች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቶሎ ሊተገብሯቸውና የሚገቡ ሥራዎች እንዳሉ አውስተዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈጽሟቸውና ጊዜ ወስደው ሊሠሯቸው ስለሚገቡ ጉዳዮችም ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ኢኮኖሚው ውስጥ ስለሚታዩ መልካም ጉዳዮች የመጥቀሳቸውን ያህል፣ የሚስተዋሉትን ችግሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥቀሳቸው አግባብ ነው በማለት አቶ ፀጋዬ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የአገሪቱ ኢኮኖሚ አድጓል፡፡ ትልቁ ችግር፣ መንግሥትም እንዳመነው ኢኮኖሚውን እየተፈታተነ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር  ነው፤›› የሚሉት አቶ ፀጋዬ፣ ይህ ማነቆ ከተፈታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እስካሁን ካለውም የተሻለ ውጤት እንደሚታይባቸው በመጥቀስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እያንዳንዱ የኢኮኖሚው ዘርፍ ውስጥ ያሉት ችግሮች ምን እንደሆኑ መዳሰስ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

የዚህች አገር መውደቅ ወይም ማደግ በወጪ ንግድ ላይ የተመሠረተና የውጭ ምንዛሪ ግኝት የተንጠለጠለ መሆኑን በማውሳትም፣ ለዚህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ሚና ያላቸው የቢዝነስ ዘርፎች በርካታ ችግሮች ስለሚታዩባቸው እነኚህን መፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡ አቶ ሰሎሞንም እንደ አቶ ፀጋዬ ሁሉ ለውጭ ምንዛሪ ችግር ተገቢው መላ ሊበጅ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ ድርጅቶች ያደረጉት ጥሪ፣ ለፖለቲካው ብቻም ሳይሆን፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ያግዛል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ሰሎሞን፣ ይህንን ሲያብራሩም በቅርቡ በውጭ ከሚገኙ ዜጎች ወደ አገር ቤት ገንዘብ እንዳይላክ እየተባለ ሲራገብ የነበረውን እንቅስቃሴ እንደሚሰብርና የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትም ከፍ ለማድረግ የሚረዳ ተስፋ ያለው ንግግር እንደሆነ በመጥቀስ ነበር፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እየሰፋ በመጣበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ሲወጡ ለችግሩ የሚኖረው የመፍትሔ አስተዋጽኦም እየተገለጸ ነው፡፡ በዘላቂነት የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ለመፍታት የወጪ ንግዱን መጠን ማሳደግ አንደኛው መንገድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ዘርፉ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ ገቢ እያስመዘገበች ቢሆንም፣ በአንፃሩ ግን 17 እና 18 ቢሊዮን ዶላር የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ በማስመዝገብ ከፍተኛ ወጪ እያወጣች ትገኛለች፡፡ ይህንን ያወሱት አቶ ሰሎሞን፣ የወጪ ንግዱን ማሳደግ ብቻም ሳይሆን፣ ከውጭ የሚገቡትን ሸቀጦች ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መርጦ ማስገባት በቀዳሚነት ሊሠሩ እንደሚገባቸው ያምናሉ፡፡ በዚህ ረገድ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቅባቸው ሥራ በርካታ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ላለው እጥረት መፍትሔ የሚሰጥና የማስተንፈሻ ሥራ መሥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ስለመሆኑ፣ ቀስ በቀስም ለችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ ወደሚሰጥ የአሠራር ሥልት ሊገቡ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ሥራ ጎን ለጎን መደረግ አለበት በማለት አቶ ሰሎሞን ያስቀመጡት ሐሳብ፣ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ጋብ ማድረግ እንደሚገባ የሚያሳስበው ነው፡፡ ‹‹መሠረተ ልማት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ዘጠኝ አሥር ቦታ ድስት ከመጣድ የተመረጡ መሠረተ ልማቶች ላይ በማተኮር አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ ይረዳል፤›› ብለዋል፡፡

ይህን ማደረጉ ጤናማ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲኖር አጋዥ ስለመሆኑም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የውጭ ምንዛሪው ኖሮም ሰላም ከሌለ ግን በተለይ ኮርፖሬት ቢዝነስ እንዳይኖር በማድረግ በወደፊቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚኖረው የሚያምኑት አቶ ሰሎሞን እንደ ስኳር፣ ቢራና ሲሚንቶ ያሉት ፋብሪካዎች፣ ልክ እንደ ፋይናንስ ተቋማት በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ ተዋቅረው እንዲሠሩ ማድረግም ጠቀሜታው እንደሚጎላ ያብራራሉ፡፡

 ከላይ ካነሷቸው ነጥቦች ባሻገር ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የትኩረት መድረክ እንዲሆን የጠቀሱት የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ የሚንቀሳቀስበት መንገድ አያስኬድም ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ይልቁንም ሰፊውን ሕዝብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ትላልቅ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በእሳቸው እምነት መደረግ ያለበት ብዙዎችን በአንድ ጊዜ የሚቀጥሩ በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የሚቋቋሙ ኩባንያዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን ሕግና አሠራር መዘርጋትም ለኢኮኖሚው ዕድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

አቶ ፀጋዬ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከንግግርነቱ ባሻገር ለውጦች ያመጣል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ኢኮኖሚውን ለማንቃት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱንም ለመቅረፍ መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የወጪ ንግዱን ሊያሻሽሉ የሚችሉ አምራቾችና ላኪዎች በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው የጠቀሱት አቶ ፀጋዬ፣ በየዘርፉ ያሉ የላኪዎችን ችግሮች ለመፍታት ሲቀርቡ የነበሩ ሐሳቦችና የመፍትሔ ዕርምጃዎች እንደሚፈለገው ባለመተግበራቸው አጥጋቢ ለውጥ አልመጣም ይላሉ፡፡ በመንግሥት የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦችን የጉዳዩ ባለቤት ከሆኑ ላኪዎች ጋር በመምከር ማፈላለጉና መተግበሩ ጠቃሚ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ ዶ/ር ዓብይ ለዚህ መሥራት ካለባቸው ይህንኑ ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋቸዋል፡፡

አምራቾች በጥሬ ዕቃና በግብዓት ዕጦት የሚፈለገውን ያህል በቂ ምርት ማምረት እንዳልቻሉ በማስታወስ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሳቢያ መድኃኒት ለማስገባት እንኳ ፈታኝ እየሆነ በመምጣቱ፣ የዶ/ር ዓብይ አመራር ፍትኃዊ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም የሚኖርበትን አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ለመቅረፍ መሠራት አለበት በማለት አቶ ፀጋዬ ከጠቀሷቸው ውስጥ ላኪዎችን በቅርብ መከታተልና ችግሮቻቸውን በእግር በእግር መፍታቱ አንዱ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለሕዝቡ ጥሪ የቀረበበትም ነው፡፡ ነጋዴው ጥሪው ከሚመለከታቸው ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የተዳከመውን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ከንግዱ ኅብረተሰብ ምን ይጠበቃል? ምን ሊደረግ ይገባል? ለሚለው አቶ ሰሎሞን  እንደሚገልጹት፣ ዋናው ነገር ነጋዴውን በአግባቡ ሊያሠራ የሚችል ፍትሐዊ አሠራር መዘርጋት ነው፡፡  እንደ አቶ ሰሎሞን ለነጋዴው የመጀመርያው ጉዳይ ነጋዴው ችግሩን የሚያደምጠው፣ ችግሩን የሚናገርበት ዕድል እንደልቡ ማግኘቱ ነው፡፡ እስካሁን ለነበረው እንቅስቃሴ መዳከም በነጋዴውና በመንግሥት መካከል እየከሰመ የመጣው መተማመን ነው ይላሉ፡፡  

‹‹መንግሥት የሶሻሊስት አመለካከት አለው፤›› የሚሉት አቶ ሰሎሞን፣ በዚህ ሳቢያም መሥራት የሚገባውን ያህል መሥራት አልቻለም ይላሉ፡፡ ከዚህ በኋላም ኢኮኖሚው የበለጠ እንዲራመድ ከተፈለገ፣ የንግዱ ኅብረተሰብ ማነቆዎችን ማጥራት እንደሚገባ ያሰምሩበታል፡፡ የንግዱ ኅብረተሰብ ዋናው ጥያቄ ፍትሐዊ አሠራር ይኑር የሚል እንደሆነ በመጥቀስ፣ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር በማስረጽ ነጋዴውን የመፍትሔው አካል ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ ተሟልቶ በነፃነት የሚሠራበት ዕድል ከተፈጠረ፣ ከእስካሁኑ የበለጠ እንቅስቃሴ ይኖራል፤›› ይላሉ፡፡

 የግሉን ዘርፍ ሳይዙና ወይም ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥሩ የግሉን ዘርፍ እንደ ትልቅ አጋር እንመለከተዋለን ማለቱ ብቻውን ውጤት አያመጣም ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ከሙስና የፀዳ አሠራር ሲጨመርበትም የተደረገው ጥሪ በአግባቡ ተግባር ላይ የሚውልበት ዕድል እንደሚኖር ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው እስካሁን የነበረው የኢኮኖሚው ጉዞ በሙሉ መጥፎ እንደማይባል፣ ተዓማኒነት ያለው ዕድገት ይታይበት እንደነበር አውስተው፣ ሆኖም በቁጥር የሚገለጸው ዕድገት አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በተጠቃሚነት እንዳላሳተፈ ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር አንዱ ምክንያት ሥራ አጥነትና በነገ ሕይወት ውስጥ ተስፋ ማጣት ያመጣው ችግር ስለሆነ፣ ይህን ለማቃለል የግል ዘርፉ ሚና በሚገባ መታየት አለበት ብለዋል፡፡

‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲኖር ካሰበ ከቢዝነስ መውጣት አለበት፡፡ ዛሬ ትላልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች በፓርቲው መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ተቋሞች የሚገኙ በመሆናቸው የግሉን ዘርፍ እየጎዳው ነው፡፡ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ሊሠራ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡  እንዲህ ያለው አካሄድ የግሉን ዘርፍ እየጎዳው ስለመሆኑ የተለያዩ ነጥቦችን በማጣቀስ የገለጹት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹ሌላው ቀርቶ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ፈቃድ የመለሱ ነጋዴዎች ቁጥር ብዙ ሆኑ መገኘቱ የግል ዘርፉ ላይ ያለውን ጫና ያሳያል፤›› በማለት ሙግታቸውን አጠናክዋል፡፡

ስለዚህም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥት ከተቆጣጣሪነት አስተሳሰቡ ወጥቶ ወደ የልማት ደጋፊነት ሚና መግባት አለበት ይላሉ፡፡ የኢኮኖሚው እንቅፋቶች ተለይተው መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

አቶ ፀጋዬ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት ሊፈታ የሚችል አሠራር መዘርጋት አለባቸው ይላሉ፡፡ እየታየ ያለው ችግር በርካታ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ ዕጦት ሥራቸውን እያቆሙና ነገ ሠራተኛ ወደ መበተን ሊገቡ የሚችሉበትን አዝማሚያ እየጠቆመ ነው ያሉት አቶ ፀጋዬ፣ ‹‹ይህ በመንግሥት ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ ስለዚህ የአጭር ጊዜ መፍትሔው በብድር ጭምር መጥቶ የተወሰነ ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የወጪ ንግዱ የሚያድግበት መንገድ መመቻቸት ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እንዲህ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሰባትና ስምንት ወራት ወረፋ የሚጠብቁ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ስለሚቻል፣ በዚህ ረገድ ተደራራቢ ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ እያደር ለኢኮኖሚው ቀውስ ሊሆን የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር መፍታት ተገቢ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተስፋፋውን ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሥራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ይበልጥ ቢያስፋፉት፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማስቀጠል የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥራላቸዋል ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ የአገሪቱን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የተደረገውን ጥረትና የተሠራውን ሥራ በመጠቀም የውጭ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡ በአጠቃላይ አላላውስ ያሉ አሠራሮችን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡም አጋዥና ተዋናይ እንዲሆን በማድረግ ለውጥ ይመጣል ብለው ያምናሉ፡፡

ዕውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በንግግራቸው እንደገለጹት ኢኮኖሚው ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፀጋዬ፣ ‹‹መፍትሔ የሚያመጡ፣ ለዚህም ዝግጁ የሆኑ ሰው ይመስሉኛል፤›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይ ወጣትና ጠንካራ በመሆናቸው ብዙ ነገር ሊቀይሩ ይችላሉ ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ በበኩላቸው፣ ለውጡን ለማምጣት ብዙ ሊሠሩና ሊተጉ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ገለጻ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ማነቆዎች ማድረቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚጠብቃቸው ኃላፊነት ውስጥ ይመደባል፡፡ ‹‹የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት እዚህ የደረሱት ከ20 ዓመታት በፊት እንዲሠሩ በመፈቀዱ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ማነቆዎች ስለነበሩባቸው መድረስ የሚገባቸውን ያህል ደረጃ ሊደርሱ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እዚህ አካባቢ ያለው ጉዳይ መፈተሽ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ዜጎችን የሚያነጋግርና የመደመጥ ዕድል የሚሰጥ አገልግሎት ሰጪ መፈጠር እንዳለበት ያስረዱት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ የተባሉ ሐሳቦችን እንኳ ለመቀበል የማይፈልግ አገልግሎት ሰጪ ላይ ዕርምት ካልተደረገ ግን ነገሮችን ማስተካከል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢኮኖሚ ጉዳዮችም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ እንዲያመጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ተስፋም ተጥሎባቸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም የፖሊሲ ለውጥ እንደሚኖር እምነት ያደረባቸው አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚኖሩም ያምናሉ፡፡ ‹‹ዶ/ር ዓብይ አንድ ሰው ናቸው፡፡ ሆኖም ተሸናፊም አሸናፊም ሳይባል ሁሉም ለለውጥ እንዲነሱ በማድረግ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ውጭ ያሉትም እንዲገቡ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን ነው ትንግርት ሊፈጠር የሚችለው፡፡››

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከድርጅታቸውና ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን መወጣት  ይጠብቃቸዋል ያሉት ወ/ሮ መዓዛ፣ በመሆኑም አገሪቱ የሚያስፈልትን ሥራዎች በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ይሠራሉ ብለው ያምናሉ፡፡ በግላቸው ግን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለው የሚያምኑት ከሰብዓዊ መብቶች ጋር ለተያያዙ ችግሮች መፍትሔ መስጠቱን ነው፡፡

መጪዎቹ ሁለት ዓመታት እንደ ሽግግር ጊዜያት እንደሚቆጠሩ በማስታወስ፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገትም ሆነ ለሌሎች ችግሮች መፍቻ የሚሆኑ አዳዲስ ፖሊሲዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚቀርፁ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ቃል የገቡባቸውን ሁሉ ለመተግበር የሚችሉበት ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ግን ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች