Monday, December 4, 2023

የጋምቤላ የደን ምንጣሮና የማያባራው ውዝግብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአዲስ አበባ ከተማ 630 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን  ጎደሬ ወረዳ፣ ጉማሬ ቀበሌ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ይሁንታ ያላገኘ የሻይ ቅጠል ልማት ፕሮጀክት ይገኛል፡፡

መንግሥት ከክልሎች በውክልና የሚረከበውን የሰፋፊ እርሻ መሬቶች የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ይህንን መሬት እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ለቬርዳንታ ሐርቨስትስ ለተባለ የህንድ ኩባንያ ውል በመፈጸም አስረክቧል፡፡

ኩባንያው ለዚህ መሬት በአንድ ሔክታር በ111 ብር፣ በየዓመቱ የሚከፈል የሊዝ ገንዘብ 334,322 ብር፣ አጠቃላይ የመሬቱ የሊዝ ሒሳብ ደግሞ 16.7 ሚሊዮን ብር ሒሳብ በመክፈል መሬቱን ተረክቧል፡፡

ለዚህ ኩባንያ የተሰጠው የእርሻ መሬት አጠቃላይ የሊዝ ዘመን 50 ዓመት መሆኑን፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ በአቶ ተፈራ ደርበው የተፈረመው የሊዝ ውል ሰነድ ያስረዳል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ወደ መሬት ከወረደ ጀምሮ የአካባቢውን አርሶ አደሮችና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን ሲያስቆጣ የቆየ ነው፡፡ እንዲያውም በጥቅምት 2006 ዓ.ም. ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ፕሮጀክቱ ላይ የእሳት ቃጠሎ እንዲነሳ በመደረጉ፣ መንግሥት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ፕሮጀክቱን ከተፅዕኖ ለመጠበቅ የፌዴራል ፖሊስ ካምፕ አቋቁሞ ፕሮጀክቱን በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የአካባቢው ማኅበረሰብ ሳያምንበት በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገለት የሚካሄድ ፕሮጀክት ይህ የህንድ ሻይ ቅጠል ልማት ብቻ ሳይሆን እንደማይቀር አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቹ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስና የጋምቤላ ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ይህንን ፕሮጀክት በሚመለከት ደብዳቤ ጽፈው ነበር፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት የአካባቢው ነዋሪዎችን አቤቱታና የጉማሬ ቀበሌ አስተዳደር ቅሬታ መሠረት በማድረግ የካቲት 2003 ዓ.ም. ለሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ በምንም ምክንያት የደን መሬት ለእርሻ መሰጠት ስለሌለበት ደኑን ለማልማት በሚፈልጉ ሰዎች ወይም በሕዝብ ተሳትፎ እንዲለማ ጠይቀዋል፡፡

ከእነዚህ የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳደር አካላት በተጨማሪ፣ የዚህ ተፈጥሯዊ ደን ክልል ለሻይ ቅጠል ልማት መዋሉ ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ ያሉ የደን ባለሙያዎች መሬቱ  እንዳላሳመናቸው  የቀድሞው ፕሬዚዳንት ገልጸዋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ግርማ በተጨማሪም የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ በግልባጭ ደግሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በ2003 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች አልፎ አልፎ የሚስተዋለው ችግር ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለትና በሕግ አግባብ ካልተፈታ፣ በአካባቢው ላይ፣ በአካባቢው ኅብረተሰብና በአጠቃላይ የአገሪቱ ልማት ላይ የሚያስከትለው ጥፋት መጠነ ሰፊ ሆኖ፣ ሕዝብን ጉዳት ላይ የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

ችግር እየፈጠሩ ነው ካሏቸው ኩባንያዎችም ቬርዳንታ ሐርቨስትስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ለቀድሞው ግብርና ሚኒስቴር ለአሁኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ‹‹ቬርዳንታ ከመነሻው መሬቱን ሲረከብ ሻይ ቅጠል ለማልማት ቢሆንም፣ የእርሻ ሥራውን እያከናወነ የሚገኘው ከፍተኛ የሆነ ጥቅጥቅ ደን፣ ወንዞችና ጅረቶች በሚገኙበት ቀጣና በመሆኑ፣ ደን እየወደመና ጅረቶችም እየደረቁ የሚመጠቡት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፕሬዚዳንቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ በማቅረብ ከፍተኛ እሮሮ እያሰማ መሆኑን ገልጸው፣ ቬርዳንታ ከቆመለት ዓላማ በተቃራኒ ከሚያወድመው ደን ጣውላ በማውጣት ሲያጓጉዝ በተጨባጭ የተያዘ መሆኑን፣ ኩባንያው የዕፎይታ ጊዜ አለኝ በማለት የመሬት ግብር ለወረዳዎቹ በወቅቱና በአግባቡ ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡

ቬርዳንታ ሐርቨስትስ መሬቱን ከተረከበ ዓመታት ቢቆጠሩም ከሙከራ በዘለለ ለገበያ የቀረበ ምርት አለመኖሩን በመጥቀስ፣ መንግሥት የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ በጻፉት ደብዳቤ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የቀድሞው ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ፣ የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑት የሸካና የማጃንግ ብሔረሰቦች የሚያነሱት ጥያቄ ተመሳሳይ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ብቻ ሳይሆኑም በአካባቢው ላይ ጥናት ያካሄዱት ፓክት ኢትዮጵያና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ  ተመሳሳይ አቋም አላቸው፡፡

ለቬርዳንታ የተሰጠው መሬት በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ ጉማሬ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል፡፡ የጉማሬ ደን ከ1,800 እስከ 2,200 ሜትር ከፍታ ላይ ደልዳላ ቦታ ይዞ ከተራራው ወደታች ሲወርድ ቁልቁለታማ ሸለቆዎች በብዛት ያሉበት ነው፡፡ ከዚህ ተራራማና በጥቅጥቅ ተፈጥሯዊ ደን የተሸፈነ ምድር በርካታ ወንዞችና ወንዞችን የሚፈጥሩ ምንጮች ይነሳሉ፡፡ በአጠቃላይ 40 የሚደርሱ ምንጮችና ወንዞች ከአባቢው የሚነሱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሻይ፣ ጋጃ፣ ካጃዲ፣ ፋኒና ቢታሽ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከአካባቢው የሚነሱ የውኃ ምንጮች በኢትዮጵያ ከሚገኙ 12 ተፋሰሶች አንዱ የሆነው የባሮ አኮቦ ተፋሰስ አካል ናቸው፡፡ የጋምቤላ ክልል እስትንፋስ የሆነው ባሮ አኮቦ ወንዝ የነጭ ዓባይ ትልቅ ገባር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ለውኃ አካላቱ መሠረት የሆነው የአካባቢ ተፈጥሯዊ ደን በርካታ አገር በቀል ዛፎችን ያካተተ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቀረሮና ገተማ ዛፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የገተማ ዛፍ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ጨምሮ በርካታ ኢንቨስተሮችና የአካባቢው ንብ አናቢዎች ማር እንዲያመርቱ ምክንያት የሆነ ነው፡፡ የገተማ ዛፍ የተለየ ጥራት ያለው የማር ምርት ማስገኘት የሚችል መሆኑን የአካባቢው ማኅበረሰብ ይተርክለታል፡፡

ከማር ምርት በተጨማሪ ተፈጥሯዊው የጉማሬ ደን በርካታ ቅመማ ቅመሞች የሚገኝበት መሆኑም ይነገርለታል፡፡ ነገር ግን የህንዱ ኩባንያ ቬርዳንታ ሐርቨስትስ ያለ በቂ ጥናት ቦታውን መረከቡ የአካባቢውን ብዝኃ ሕይወት እየጎዳ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ጋትሉዋክ ለፌዴራል መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ቬርዳንታ ለሻይ ቅጠል ልማት እያወደመው የሚገኝ በመሆኑ ወንዞችና ጅረቶች እየደረቁ እየመጡ ነው፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ በፈረሙበት ውል ሰነድ ላይ ባይገለጽም፣ ዛፎቹን በመጨፍጨፍ ጣውላ በማውጣት እየከበረ መሆኑን፣ አይጠቅሙም ብሎ ያሰባቸውን ገተማን የመሳሰሉ ዛፎችን ደግሞ ሸለቆ ውስጥ እየቀበረ መሆኑ ይነገራል፡፡

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ1997 ዓ.ም. ተመሥርቶ በ1999 ዓ.ም. ነው ሥራ የጀመረው፡፡  ዩኒቨርሲቲው በቤንች ማጂ ዞን በ52 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቴፒ ከተማ ውስጥ ይገኛል፡፡ የዚህ ልጅ እግር ዩኒቨርሲቲ የወደፊት ራዕይ አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ በመሆኑ፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ዕድገት ማምጣት የሚቻሉ ሥራዎችን በሰፊው መሥራት ነው፡፡

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጀምር ቆጭቶ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የህንዱ ኩባንያ የሚያካሂደው ውድመት ከዩኒቨርሲቲው ራዕይ ብቻ ሳይሆን፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ አስተሳበብ ጋር በእጅጉ የሚጋጭ ነው፡፡

‹‹ፕሮጀክቱ ሥራው ሲጀመር ከአካባቢው ጋር የተጣመመ ልማት እንደሚያካሂድ ተገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን እያየን ያለነው ውድመት አስደንጋጭ ነው፤›› በማለት አቶ ጀምር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው እየተካሄደ ያለውን ውድመት እያጠና መሆኑንና መንግሥት አስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድ አቶ ጀምር ጠይቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባካሄደው ቅኝት በቤንች ማጂ ዞን፣ ሸካ፣ ማጃንግ፣ ኢሊባቦርና በእነዚህ አካባቢዎች የሚካሄደው የግብርና ልማት ቡና፣ ቅመማ ቅመምና ከጣውላ ውጪ የሆኑ ልማቶች መሆን እንዳለባቸው ግንዛቤ ተወስዷል፡፡

ነገር ግን በዚህ ቀጣና ውስጥ እየተካሄደ ያለው የቬርዳንታ ሐርቨስትስ ሻይ ልማት በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባው አቶ ጀምር ተናግረው፣ በተለይ ኩባንያው ከዚህ በፊት ካደረሰው ውድመት በተጨማሪ አሁንም ደን ጭፍጨፋ ውስጥ እየገባ መሆኑን አቶ ጀምር አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለቬርዳንታ ሐርቨስት 92 ሚሊዮን ብር ብድር አፅድቋል፡፡ ይህ ገንዘብ በአብዛኛው ለፋብሪካው ግንባታ የሚውል መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የፋብሪካው ግንባታ አለመጀመሩ ታውቋል፡፡

የኩባንያው ተቆጣጣሪ ሆኖ ለሁለት ዓመት የሠራውና አሁን መልቀቂያ ያስገባው ወጣት አዲሱ መከተ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በአካባቢው ዝናብ በብዛት የሚዘንብ በመሆኑ መንገድም ሆነ ፋብሪካው መገንባት አልተቻለም፡፡

እስካሁን ሻይ ቅጠል የተተከለበት 91 ሔክታር መሆኑን የሚናገረው ወጣት አዲሱ ኩባንያው በአብዛኛው ያተኮረው ደን ምንጣሮ ላይ ብቻ ነው በማለት ይናገራል፡፡ ፋብሪካ ለማቆም ቢሆን ከ150 ሔክታር በላይ የለማ ሻይ ቅጠል ያስፈልጋል በማለት አዲሱ ጨምሮ አስረድቷል፡፡

ኩባንያው እያካሄደ ያለው ሥራ መሬቱን ከተረከበት ጊዜ አንፃርም ቢሆን አነስተኛ መሆኑን አዲሱ ገልጾ፣ የኩባንያው የሠራተኛ አያያዝም አስከፊ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

‹‹ሕፃናቶች ስብስበህ አምጣ ደብተርና እስክርቢቶ እንሰጣለን ይሉኛል፡፡ ሰብስቤ ሳመጣ ሥራ ያሠሯቸዋል፤››  በማለት አዲሱ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ እንዳለና ለተቀጠረ ሠራተኛም ቢሆን የቀን ክፍያ ከአሥር ብር በታች እንደሆነ ይናገራል፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ኢንቨስትመንቱ ያለ አካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ እንዲካሄድ መደረጉ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ ያካሄደው ጥናት እንደሚጠቁመው፣ የሻይ ቅጠል ልማቱን የሚያከናውነው ድርጅት ምንጣሮውን እስከሚፈጽም ድረስ ምንም ዓይነት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አላደረገም፡፡ የአገሪቱ ሕግ እንደዚህ ዓይነት መጠነ ሰፊ የሆኑ ኢንቨስመንቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳያካሂዱ ምንም ዓይነት ሥራ መጀመር እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡

ነገር ግን ይኼን የማስፈጸም ሥልጣን ያለው የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የአካባቢ ነዋሪዎች ቅሬታ እስኪያቀርቡለት ድረስ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም፣ ቅሬታ ከቀረበለት በኋላ ለእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፏል፡፡

የአካባቢ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስቴር ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ በአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ ምንም ነገር ሳይል፣ ‹‹ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች አፍሪካን ወክላ በምትደራደርበት ወቅት፣ እንዲሁም ከእርሻው ይልቅ ከካርቦን ንግድ የምታገኘው ጥቅም የበለጠ ስለሆነ ደኑ የማይነካበት ሁኔታ እንዲመቻች፤›› በማለት ጠይቋል፡፡

በሁሉም የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ጣት የሚቀሰርበት የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ግን ለቬርዳንታ ሐርቨስትስ የተሰጠውን መሬት ‹ቁጥቋጦ› ብሎታል፡፡

ብዙዎች እንደሚስማሙትም ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ እንዳረጋገጠውም ቦታው ቁጥቋጦ ሳይሆን ደን ነው፡፡ የዓለም እርሻ ድርጅት ጥናት እንደሚያመለክተው ግማሽ ሔክታር የሚሸፍንና ቁመቱ አሥር ሜርት የሆኑ ዛፎች ያሉበት ቦታ ሁሉ ደን ነው፡፡

ነገር ግን በጉማሬ ያለው ከአምስት ሺሕ ሔክታር በላይ ስፋትና ቁመታቸው ከ35 ሜትር በላይ የሆኑ ዛፎች ጥቅጥቅ ብለው ይገኙ እንደነበር የአካባቢ ተሟጋቾች ጥናት ያመለክታል፡፡

ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ መታዘብ እንደቻለው ግዙፍ ዛፎች የወደቁ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ የሚገኙት አሁንም በመቆረጥ ላይ የሚገኙት ቁጥቋጦ ሳይሆኑ ግዙፍ ዛፎች ናቸው፡፡ እነዚህን ዛፎች ሊተኩ የማይችሉ በመሆናቸው መንግሥት ከፍተኛ የጥናት ቡድን በማዋቀር ጉዳዩን በሚገባ ሊያጤን እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ዘነበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤጀንሲው ኤክስፐርቶች በቦታው ተገኝተው ግምገማ አካሂደዋል፡፡

በግምገማው እስካሁን ድረስ 100 ሔክታር መሬት ላይ ሻይ ቅጠል ተተክሏል፡፡ 25 ሔክታር መሬት ላይ ደግሞ የሻይ ቅጠሉን ለማቀነባበር የሚያስችለው ፋብሪካ ኃይል የሚያገኘው ከእንጨት በመሆኑ ባህር ዛፍ አልምቷል፡፡ አቶ ዳንኤል እንዳሉት ግን በአጠቃላይ ሲታይ የኩባንያው የሥራ አፈጻጸም ደካማ ነው፡፡

የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ ስለሆነበት ምክንያት ቬርዳንታ የሰጠውን ማብራሪያ አቶ ዳንኤል ሲያስረዱ፣ የጋምቤላ ክልል ለፕሮጀክቱ የሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የባንክ ብድር አለመለቀቅ፣ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን በአፋጣኝ አለማግኘት፣ የመሬት አቀማመጡ ለሜካናይዜሽን የማይመች መሆኑ፣ የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ የመሬት ይገባኛል ማቅረቡና የፀጥታ ችግሮች እንደ ምክንያት አቅርቧል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ኤጀንሲው የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡ ከተሰጡት ድጋፎች መካከልም ኩባንያው ከቀረጥ ነፃ ማሽኖች እንዲያስገባ፣ የጋምቤላ ክልል የነዳጅ አቅርቦት እንዲያሻሽልና የጉልበት ሠራተኞችንም የሚያገኝበት መንገድ እንዲመቻች እየተደረገ መሆኑን አቶ ዳንኤል አስረድተዋል፡፡

ከአካባቢው ማኅበረሰብና መዋቅሮች እንዲሁም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የሚቀርቡ የማሻሻያ ሐሳቦች ካሉ ለማስተናገድ የሚቻልበት አግባብ መኖሩን አቶ ዳንኤል ገልጸው፣ ቀደም ሲል ይህ ቦታ ለኩባንያው ሊሰጥ የቻለው አካባቢው ቁጥቋጦ ነው የሚል ጥናት በመቅረቡ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሳይኖር መሥሪያ ቤታቸው ቦታውን እንደማይሰጥ አቶ ዳንኤል የተናገሩ ቢሆንም፣ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ጥናት ግን የደን ምንጣሮ ከተካሄደ በኋላ ጥናቱ እንደተካሄደ ያመለክታል፡፡

ይህ ኩባንያ በአጠቃላይ ያለው የሥራ አፈጻጸም ደካማ ነው ቢባልም 148 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ደን መመንጠሩና አሁንም በመመንጠር ላይ ስለሚገኝ፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ ይህንን ድርጊት አምርሮ እየተቃወመው ነው፡፡

የአካባቢው ማኅበረሰብ ለዚህ ፕሮጀክት ያለው ጥላቻ ከፍተኛ ቢሆንም፣ መንግሥት ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ይጠይቃል፡፡ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ባካሄደው ምንጣሮ የጀመረው ፕሮጀክት መልክ ሳይዝ፣ በድጋሚ ወደ ምንጣሮ መግባቱ ዳግም አለመግባባት እየፈጠረ መሆኑንም ያመለክታል፡፡

የጋምቤላ ክልል ዓቃቤ ሕግ ቬርዳንታ ሐርቨስትስ ደን በመጨፍጨፍ ወንጀል ፈጽሟል በማለት ክስ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ጉዳዩን የመረመረው የማጃንግ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድርጊቱ የተፈጸመው ኩባንያው በተረከበው መሬት ላይ በመሆኑ፣ የክልሉ የደን ልማትና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 65/1999 ጋር የሚጣረስ ባለመሆኑ ጥቅምት 7 ቀን 2006 ዓ.ም. ኩባንያውን ነፃ አድርጎታል፡፡ ድርጊቱ ሕገወጥ እንደሆነና ደኑ በመንግሥት ወይም በግለሰብ ባለቤትነት መያዝ እንዳለበት የክልሉ ሕግ ይደነግጋል፡፡

ቬርዳንት ሐርቨስትስ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ በቅርቡ ኩባንያው ከ250 በላይ ሕፃናትን በማሠራት የጉልበት ብዝበዛ ፈጽሟል በሚል የቀረበው ዘገባ የቁጥር ስህተት እንዳለው ቢያመለክትም፣ ድርጊቱን ላለመፈጸሙ የጋምቤላ ክልል የሕፃናትና የሴቶች ጉዳይ ቢሮ የመስክ ጉብኝት ጭምር አረጋግጦ እንደነበር ገልጿል፡፡ በዚህም ሦስት ዕድሜያቸው ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት የሚሆኑ ሕፃናት መገኘታቸውን ቢያምንም፣ ከ250 በላይ ሕፃናት ተቀጥረው ይሠራሉ መባሉን ግን አስተባብሏል፡፡ በሪፖርተር የመስክ ምልከታ ግን አሁንም ለሥራ ያልደረሱ ሕፃናት በሥራ ላይ እንደሚገኙ ነው፡፡

 

 

 

  

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -