በተጠረጠሩባቸው ሁለት የተለያዩ ወንጀሎች ዋስትና ከተፈቀደላቸው በኋላ በነፍስ ግድያ ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት መምህር ግርማ ወንድሙ ላይ፣ ፖሊስ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደለት፡፡
በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ የሠራውን የምርመራ ሒደት እንዲያስረዳ ጠይቆት እንደገለጸው፣ መምህር ግርማ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አጥር ሥር ያካሂዱት በነበረው የማጥመቅ ተግባር አንዲት ሴት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሴትየዋ የአድዋ ነዋሪ በመሆናቸው የቀብር ሥርዓታቸውም የተፈጸመው በአድዋ በመሆኑ፣ የአስከሬን የምርመራ ውጤት ለማምጣትና ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ የ14 ቀናት ጊዜ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የፖሊስን ጥያቄ በመቀበል የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶለት ለታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
መምህር ግርማ በማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ለታሰሩበት ወንጀል የ50 ሺሕ ብር ዋስ፣ እንዲሁም ሐሰተኛ ሰነድ ተጠቅመዋል ተብለው በተጠረጠሩበት ወንጀል የ40 ሺሕ ብር ዋስ አስይዘው እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ የፈቀደ ቢሆንም፣ በነፍስ ግድያ በመጠርጠራቸው እንዳልተፈቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡