በሥራ ላይ ያለውን የኅብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ በማሻሻል በድጋሚ የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ማክሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀረበ፡፡ ረቂቁ ማኅበራቱ ከገቢ ግብር ነፃ እንዲሆኑና መሬት በምደባ በመንግሥት እንዲያገኙ ይፈቅዳል፡፡
በሥራ ላይ ያለውን የኅብረት ሥራ ማኅበራት አዋጅ ቁጥር 147/1996 በማሻሻልና በርካታ አዳዲስ ድንጋጌዎችን በማከል በድጋሚ አዋጁን ለመደንገግ የተፈለገው፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ካሳያዩት ለውጥና ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ በተሻለ ደረጃ ለመስጠት ውስንነቶች በመታየታቸው ነው፡፡
በመሆኑም በኢንቨስትመንት ሕጉና በሌሎች ሕጎች የተፈቀዱ ማበረታቻዎች የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ማግኘታቸው የተጠበቀ ሆኖ ከገቢ ግብር ነፃ እንዲሆኑ፣ ሆኖም የማኅበራቱ አባላት ከሚያገኙት የትርፍ ድርሻ የገቢ ግብር እንዲከፍል በረቂቁ ተካቷል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራት መሠረታዊ ዓላማዎችን የሚደነግገው ይኼው ረቂቅ አዋጅ አባላት በተናጠል በመሥራት ሊወጧቸው የማይችሏቸውን የኢኮኖሚ ችግሮች በተባበረ ጥረት ለማምረት፣ የሚያስፈልገውን ወጪና የአገልግሎት ዋጋን በመቀነስ አባላት የሚፈልጉትን አገልግሎትና ግብዓት በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ ከዓላማዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡
በአንድ አካባቢ ከሚደራጁ መሠረታዊ ማኅበራት በተጨማሪ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን፣ ከእነዚህ ዩኒየኖች የሚመሠረቱ የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች፣ እንዲሁም በፌዴሬሽኖች የሚመሠረት በብሔራዊ ደረጃ አንድ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሊግ እንደሚኖር በረቂቁ ተካቷል፡፡
የኅብረት ሥራ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች ከመሠረታዊ ማኅበራት የላቀ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ፣ ከእነዚህም መካከል ኢንዱስትሪዎችን እስከ ማቋቋም ድረስ ይችላሉ፡፡
በመሆኑም የማኅበራት ኃላፊነት ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅም አኳያ፣ መሬት በምደባ ከመንግሥት የሚያገኝበት አንቀጽ በረቂቁ ተካቷል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ለአባላት ከሚሰጡት አገልግሎት ውጪ፣ መንግሥት ለዋጋ ማረጋጋትና ምርታማነትን ለማሳደግ በራሱ ወጪ የሚያቀርባቸውን ግብዓቶች እንዲያሰራጩ ሕጋዊ ኃላፊነት እንዲወስዱ በረቂቁ ተካቷል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እሴቶችንም አካቷል፡፡ በዚህም መሠረት የማኅበራቱ እሴቶች ራስን በራስ መርዳት፣ የግል ኃላፊነትን መወጣት፣ ዴሞክራሲያዊ ባህልን ማስፋፋት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነትና ወንድማማችነት መሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡