Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመከላከያና የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚቴ አባላትን ፓርላማው በተአቅቦ ድምፅ አፀደቀ

የመከላከያና የብሔራዊ ደኅንነት ኮሚቴ አባላትን ፓርላማው በተአቅቦ ድምፅ አፀደቀ

ቀን:

የመከላከያና ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ልዩ ኮሚቴ አባላትን ፓርላማው በአንድ የድምፅ ተአቅቦ ሰየመ፡፡

በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. የፀደቀው የፓርላማው የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ፣ በደኅንነትና በመከላከያ ተቋማት ላይ የሚካሄደውን ክትትልና ቁጥጥር በበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የመከላከያና ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ልዩ ኮሚቴ እንደ አዲስ እንዲደራጅ ደንግጓል፡፡

የመከላከያና የብሔራዊ ደኅንነት ተቋማት በባህሪያቸው ከሌሎች ተቋማት ለየት ያሉ የበጀት፣ የፋይናንስና የአስተዳደር አሠራሮች ያሏቸው በመሆኑ ፓርላማው ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም ተቋማትን ለመከታተል ወስኗል፡፡

የፓርላማው የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ እንደሚለው የዚህ ልዩ ኮሚቴ ሰብሳቢ የፓርላማው አፈ ጉባዔ እንደሚሆኑ፣ ሰብሳቢውንና ምክትል ሰብሳቢውን ጨምሮ ልዩ ኮሚቴው ሰባት አባላት እንደሚኖሩትና በምክር ቤቱ እንደሚመረጡ ይገልጻል፡፡

በዚሁ መሠረትም አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የልዩ ኮሚቴው ዕጩ ምክትል ሰብሳቢና አምስት አባላትን ለምክር ቤቱ ማክሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. አቅርበዋል፡፡

በምክትል ሰብሳቢነት የታጩት በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አፅብሐ አረጋዊ ናቸው፡፡ በአባልነት የቀረቡት ደግሞ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ የሆኑት አቶ አማኑኤል አብርሃ፣ ወይዘሮ ሃሊማ አድባባ፣ አቶ ሲሳይ አሰፋ፣ ሻምበል ነጋሳ ደሬሳና አቶ ሽኩረን ማሊ ናቸው፡፡

በቀረቡት ዕጩዎች ዙሪያ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየት እንዲሰጡ አፈ ጉባዔው መድረኩን ክፍት ካደረጉ በኋላ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡ የቀረቡት ጥያቄዎች ትኩረት ያደረጉት በፓርላማው ረዳት የመንግሥት ተጠሪ የሆኑት ሁለት ግለሰቦች የልዩ ኮሚቴው አባል መሆናቸው፣ ካላቸው የሥራ ኃላፊነት ጋር የሥራ ጫናን አይፈጥርባቸውም ወይ የሚል ነው፡፡

በፓርላማው የተለመደ አሠራር መሠረት የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሥራ ኃላፊ የሆነ የፓርላማ አባል የቋሚ ኮሚቴ አባል አይሆንም፡፡ ሌላው ጥያቄ ያስነሳው የፓርላማው የአሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንብ አንድ የምክር ቤቱ አባል በሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ አባል መሆን አይቻልም ተብሎ ተደንግጎ፣ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሻምበል ነጋሳ ደሬሳ ለመከላከያና ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ልዩ ኮሚቴ በአባልነት በአፈ ጉባዔው የመቅረባቸው ተገቢነትን የተመለከተ ነው፡፡ አፈ ጉባዔ አባዱላ በሰጡት ምላሽ ሁለቱ የመንግሥት ተጠሪዎች የልዩ ኮሚቴው አባል መሆን የሥራ ጫና እንደማይፈጥር ገልጸዋል፡፡

የሻምበል ነጋሳ ደሬሳ በልዩ ኮሚቴው ውስጥ አባል መሆን ከአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንቡ ጋር ግጭት አይፈጥርም ወይ በሚል ለቀረበው ጥያቄ ግጭት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ የሰጡት ምክንያትም ደንቡ የሚለው አንድ አባል በሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ አባል አይሆንም እንጂ፣ የልዩ ኮሚቴ አባልነትን አይጨምርም የሚል ነው፡፡

በዚሁ ማብራሪያ መሠረት ወደ ድምፅ በተገባበት ወቅት ጥያቄውን ያቀረቡት የምክር ቤት አባልና ሌሎችም የድጋፍ ድምፅ የሰጡ ሲሆን፣ የትምህርት ሚኒስቴር የቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አድሃና ኃይሌ ግን ድምፅ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ ይህን መሰል ድምፀ ተአቅቦ የፓርላማውን መቶ በመቶ መቀመጫ ለያዘው ገዢው ፓርቲና አጋሮቹ ያልተለመደ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...