Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ በሕግ ይጠየቁ!

  ዜጎች በሰላም ወጥተው ለመግባት፣ ሥራቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማከናወንና ነፃነታቸው ተጥብቆ እንዲኖሩ የሕግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ የሠፈሩት የዜጎች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶችም ይህንን ያረጋግጣሉ፡፡ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ በሕግ ከተደነገገው ውጪ ወንድም ሆነ ሴት ነፃነታቸውን አያጡም፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም፡፡ ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ እነዚህ ሁሉ ወርቃማ ቃላት የሠፈሩት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ነው፡፡

  ነገር ግን የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት በመተላለፍ በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ አሉ፡፡ አንድ ሰው በሕግ ጥፋተኝነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳለው፣ በሕግ ጥላ ሥር ያለ ዜጋም ምንም ዓይነት የሕይወትም ሆነ የአካል ጉዳት እንዳይደርስበት ተደንግጓል፡፡ ይህንን ወርቃማ የሕግ ትዕዛዝ እየተላለፉ ዜጎችን የሚደበድቡ፣ የአካል ጉዳት የሚያደርሱና ለሕልፈት የሚዳርጉ አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥሰው በሕግ የማይጠየቁ ከሆነ ግን የሕግ የበላይነት አለ ለማለት ያዳግታል፡፡ አንዳንድ ምሣሌዎችን እያነሳን እንነጋገር፡፡

  ፖሊስ ኅብረተሰቡ በሰላም ተንቀሳቅሶ የዘወትር ተግባሩን እንዲያከናውን ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ ፖሊሳዊ ሙያቸውን ለዚህ ለተከበረ ኃላፊነት አስገዝተው ግዴታቸውን የሚወጡ በርካታ የፖሊስ አባላት አሉ፡፡ ለሕዝብና ለሕግ ራሳቸውን አስገዝተው ሙያዊ ተግባራቸውን የሚወጡ በርካታ የፖሊስ አባላት ባሉበት አገር ውስጥ፣ በአደራ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚያውሉ ጥቂቶችም አሉ፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግለሰቦችን በሕጋዊ መንገድ ከማስተናገድ ይልቅ፣ በዱላ እየደበደቡ የሚያሰቃዩና አካል የሚያጎድሉ እነዚህ ጥቂቶች የብዙኃኑን ታታሪ ፖሊሶች ምግባር ጥላሸት ይቀቡታል፡፡ ሰሞኑን በአንድ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ለሕዝብ እንዲደርስ የተደረገው መረጃ፣ እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

  በቅርቡ ካዛንቺስ በሚባለው የከተማው ክፍል በአራት ፖሊሶች ያላግባብ ተይዞ፣ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ድብደባ ተፈጽሞበታል የተባለው ዜጋ ጉዳይ የፖሊስን ተቋም በእጅጉ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ በመረጃው መሠረት ፖሊሶቹ ግለሰቡ ለምን በመሀላችን አቋርጦ ያልፋል በሚል መታበይ፣ በአካባቢው በሚገኘው የኮሙዩኒቲ ፖሊሲንግ ጽሕፈት ቤት በጨለማ ፈጸሙበት የተባለው ድብደባ፣ ለቂርቆስ ፖሊስ መምርያ ሪፖርት የተደረገበት ነው፡፡ እነዚህ የፖሊስ ባልደረቦች ግለሰቡ ያጠፋው ነገር ቢኖር እንኳ፣ በሕጉ መሠረት ለሕግ ማቅረብ ሲገባቸው ‘ለምን በመሀላችን ትሄዳለህ?’ በማለት ፈጽመውታል የተባለው የማናለብኝነት ድርጊት የሕግ የበላይነትን የሚጋፋ ነው፡፡ የብዙኃኑን የፖሊስ ባልደረቦች የሥራ ፍሬ ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ ግለሰቡ እንደ አንድ ዜጋ ‘ፍትሕ የለም’ ብሎ እንዲደመድም የሚያደርግ ተግባር ነው፡፡ ፖሊስ ጉዳዩን ተከታትሎ ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ አለበት፡፡ ውሳኔውንም ሕዝቡ በግልጽ እንዲያውቅ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

  ሕዝብ ፖሊስ የህልውናዬ አስተማማኝ ጠባቂ ነው ብሎ የሚያምነውና የሚተባበረው፣ ፖሊስ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶችን ማስከበር ሲችል ብቻ ነው፡፡ እግረ መንገዱንም የፖሊስን ተቋማዊ አሠራርና ብቃት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ሥነ ምግባር የጎደላቸውን አባላት ማረም፣ መቅጣትና ሲልም ማሰናበት አለበት፡፡ የኅብረተሰቡን ሰላም ከማስጠበቅ ይልቅ ሥጋት የሚሆኑ ግለሰቦች ለአገርም ሆነ ለተቋሙ አይበጁም፡፡ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት እየጣሱ ሕግ ማስከበር ስለማይቻል፣ በዜጎች ላይ ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር የሚፈጽሙ ሊጋለጡና ለሕግ ሊቀርቡ ይገባል፡፡ የፖሊስ ተቋምም ለምሥጉን ሠራተኞቹና ለተቋማዊ ተዓማኒነት ሲል እንዲህ ዓይነቶቹን ግለሰቦች በሕግ ማስጠየቅ ግዴታው ነው፡፡

  በሌላ በኩል በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ተሰግስገው ፀረ ሕገ መንግሥት ተግባራትን የሚፈጽሙ ግለሰቦችን አደብ ማስገዛት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ በፍትሕ ዕጦት ሲንገላታና መብቱን ሲነፈግ ዝም እየተባለ፣ አሁን እንደ አዲስ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ብዙ እየተባለበት ነው፡፡ ነገር ግን በየተቋማቱ የተሰገሰጉ ራሳቸውን ከሕግ የበላይ ያደረጉ ግለሰቦች አደብ ካልገዙ፣ የሚሠራው ሁሉ የእንቧይ ካብ ይሆናል፡፡ ዜጎች መብታቸውንና ግዴታቸውን አውቀው በሰላማዊ መንገድ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የሕግ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጉልበተኞች ሕጉን እየደረመሱ ሰብዓዊ መብት መጣሳቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ለአገር አደጋ ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚኖረው ዜጎች በነፃነት መኖር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ነፃነትን የሚጋፉ ተግባራት በበዙ መጠን የሕግ የበላይነት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ሕገወጦች ሕግ ፊት ይቅረቡ፡፡

  በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ይፈጸማሉ የሚባሉ የመብት ጥሰቶች ተጣርተው አጥፊዎች መቀጣት አለባቸው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች ሲቀርቡ ከማንም በላይ በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ያለበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ለሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ዜጎች ሥቃይ ደረሰብን፣ ያላግባብ ታሰርን፣ ንብረታችንን ተቀማን፣ በግፍ ተፈናቀልን፣ ወዘተ ብለው አቤቱታ ሲያሰሙ የመደመጥ መብት አላቸው፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕገወጦች መፈንጨት የለባቸውም፡፡ ሕግ የሚከበረው የእያንዳንዱ ዜጋ ነፃነትና መብት ሲከበር ነው፡፡ ይህ መብት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠ ስለሆነ ይከበር፡፡  

  ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ ተጠብቆ በአገሩ በነፃነት እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እስከሆኑ ድረስ በመካከላቸው ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በመሆኑም በብሔር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ ሠፍሯል፡፡ እነዚህን መብቶች የማስከበር ኃላፊነት ደግሞ መንግሥት ላይ ተጭኗል፡፡ በመሆኑም በሕዝብ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጽሙ ወገኖችን መከላከል ወይም ከለላ መስጠት ሕገወጥነት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ለሕግ ይቅረቡ!    

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

  በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ከአቶ ደመቀ መኮንን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...