Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳሊኒ በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ጊቤ አራትን ለመገንባት ድርድር ጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግንባታ ውል ሳይፈርም በጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሲቪል ምህንድስና ሥራ የጀመረው የጣሊያኑ ግዙፍ ኩባንያ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ በመጨረሻ ግልገል ጊቤ አራትን በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ድርድር ጀመረ፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከአውሮፓ የገንዘብ ተቋማት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደሚያመጣ መተማመኛ በማቅረብ፣ ወደ ድርድር መግባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጊቤ አራትን በሚመለከት በሐምሌ 2007 ዓ.ም. የአዋጭነትና የዲዛይን ጥናቶችን ለማካሄድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈጽሟል፡፡

ሳሊኒ የፈጸመው የመግባቢያ ስምምነት የኃይል ማመንጫ ግንባታ ለማካሄድ ባይሆንም፣ ፕሮጀክቱ ካለበት አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች ሳሊኒ የአፈር ቆረጣ በመጀመር የሲቪል ምህንድስና ሥራ እያካሄደ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

በመግባቢያ ሰነዱ የተገለጸውም ሳሊኒ የግንባታ ድርድር መጀመር የሚችለው፣ ለፕሮጀክቱ የሚሆን ፋይናንስ ከውጭ የፋይናንስ ምንጮች የኢትዮጵያ መንግሥት ብድር እንዲያገኝ ማድረግ ከቻለ ብቻ ነው፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ከአውሮፓ የገንዘብ ተቋማት ለፕሮጀክቱ ማካሄጃ የሚያስፈልገው ብድር እንደሚያገኝ መተማመኛ በማቅረብ፣ ወደ ኮንስትራክሽን ድርድር መግባት መቻሉ ተመልክቷል፡፡

ካለፉት አሥርት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ በሚካሄዱ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ሳሊኒ በቆይታው ጊቤ አንድ፣ ጊቤ ሁለት፣ ጊቤ ሦስትና ጣና በለስ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ገንብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዓባይ ወንዝ ላይ እየተካሄደ የሚገኘው ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ሳሊኒ እነዚህን ግንባታዎች ያካሄደው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባካሄደው ድርድር ሲሆን፣ ቀጣዩ ማረፊያው ለማድረግ ያቀደውን ጊቤ አራት በተለመደው የድርድር መንገድ ለማሳካት ከጫፍ መድረሱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ያምናሉ፡፡

ሦስተኛውን የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ለመሳተፍ በሐምሌ 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የመጡት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዚ፣ ሳሊኒ የገነባውን የጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ግድብ መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት በጊቤ አራት ፕሮጀክት ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሳሊኒ ለዚህ ፕሮጀክት ፋይናንስ እንደሚያገኝ ለአቶ ኃይለ ማርያም መተማመኛ ሰጥተው እንደነበር በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኮሜርሻል መምርያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ብርሃኔና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኞች አልሆኑም፡፡

ጊቤ አራት በደቡብ ክልል በቱርካና ሐይቅ አቅራቢያ የሚገነባ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 1,450 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው ተብሏል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች