‹‹አረጋግተን እንዴት ትምህርት መጀመር እንዳለባቸው እየተነጋገርን ነው›› የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም፣ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሠልፍ ወጡ፡፡
ተማሪዎቹ በማስተር ፕላኑ ውስጥ ማንኛውም የኦሮሚያ ቦታ መወሰድ ወይም መካተት እንደሌለበት የሚያንፀባርቁ መፈክሮችን ይዘው ከዩኒቨርሲቲው ግቢ በመውጣት፣ ወደ ሐረማያ ከተማ ለመሄድ ባደረጉት ሙከራ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸው ታውቋል፡፡
ተማሪዎቹ እንቅስቃሴውን የጀመሩት ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ እንቅስቃሴውን በመስማቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመራ ለፀጥታ ኃይሎች መረጃው በመድረሱ የዩኒቨርሲቲው ፖሊሶች፣ የክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት መከላከል፣ የተማሪዎቹ ሠልፍ በቅጥር ግቢው መገታቱን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ተማሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን በሚመለከት ባለፈው ዓመት ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ የመንግሥት አካላት ትኩረት በመስጠት በተለይ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎችና ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት ከማርገባቸውም በተጨማሪ ስምምነት ላይ እንደደረሱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነገሩን እንደ አዲስ እንዴት ሊያነሱት እንደቻሉ ተማሪዎቹ ተጠይቀው እንደገለጹት፣ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ጉባዔ ጠርቶ ነበር፡፡ ከስብሰባው አጀንዳዎች አንዱ የከተማ ማስተር ፕላኖችን ማስተካከል ነው፡፡ በመሆኑም ባለፈው ዓመት ተቃውሞ ተነስቶበት በቂ ማብራሪያ ሳይሰጥበትና ስምምነት ላይ ሳይደረስ በዝምታ ታልፎ፣ አሁን ሊፀድቅ እንደሆነ በመገመት ሳይሆን እንዳልቀረ፣ የተቃውሞውን ምክንያት መገመታቸውን ተማሪዎቹ አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እየተዟዟሩ መፈክር በማሰማት ላይ እያሉ፣ ለተቃውሞው መነሳት ምክንያት ናቸው የተባሉ ቁጥራቸው የማይታወቁ ተማሪዎች መታሰራቸውንና የተወሰኑ ተማሪዎች ተደብድበው ጉዳት እንደደረሰባቸው ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ በወቅቱ ጥይት የተኮሰ ቢሆንም የተጎዳም ሆነ የሞት አደጋ እንዳልደረሰ አክለዋል፡፡ ቁጥራቸው የማይታወቅ ተማሪዎች ሠልፉ ከመደረጉ አስቀድመው ከግቢው በመውጣት ከዘመዶቻቸው ጋር መቀላቀላቸውንና ከተለያዩ ክልሎች የመጡም ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመመለስ በተለያዩ ቦታዎች ተደብቀው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ኅዳር 20 እና 21 ቀን 2008 ዓ.ም. (ኅትመት እስከገባንበት ምሽት ድረስ) በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሒደት መቋረጡም ታውቋል፡፡ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ተማሪዎች ስላነሱት ተቃውሞ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ፣ ተማሪዎቹ ተቃውሞ ማንሳታቸውን አረጋግጠው ‹‹አረጋግተን እንዴት ትምህርት መጀመር እንዳለባቸው እየተመካከርን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ተማሪዎቹ ኅዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ 2፡30 ሰዓት ድረስ፣ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ የአካባቢው አስተዳደር፣ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስና ፌዴራል ፖሊስ ወደ ውጭ እንዳይወጡ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
የተማሪዎቹ ተቃውሞ ከማስተር ፕላኑ ጋር ብቻ የተገናኘ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ እንዴት ስለማስተር ፕላኑ ሊያነሱ እንደቻሉ እሳቸውም እንዳልገባቸው አስረድተዋል፡፡ በሠልፉ ግርግር ትንሽ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች ሕክምና የተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ሦስት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ክሊኒክ እየታከሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ወደ ሰማይ ከመተኮስ ባለፈ ተማሪዎችን የሚጎዳ ድርጊት አለመፈጸሙን፣ ለረብሻው ምክንያት ናቸው የተባሉ ተማሪዎች ተይዘው በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ከፖሊስ፣ ከዩኒቨርሲቲውና ከተማሪዎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎችም መለቀቃቸውን አክለዋል፡፡
ተማሪዎቹ ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲጀምሩ እሳቸውን ጨምሮ መምህራኑ እየመከሩ መሆኑን ፕሮፌሰር ጨመዳ አስታውቀዋል፡፡ ለትምህርት ሚኒስትሩ ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤና ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማሳወቃቸውንም አረጋግጠዋል፡፡