Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየ92 ዓመቱ የኢትዮጵያ ካርታ

የ92 ዓመቱ የኢትዮጵያ ካርታ

ቀን:

ይህ የኢትዮጵያ ካርታ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን በ1916 ዓ.ም. የነበረ ሲሆን፣ የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ ገጽታ ይመስላል፤ በወቅቱ አልጋ ወራሽ የነበሩት በልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ቤተ መንግሥት ውስጥ ተሰቅሎ ነበር፡፡ በብራና ላይ በተሣለው ካርታ ላይ የንግሥቲቱና የአልጋወራሹ ፎቶዎች፣ ሞአ አንበሳ (የአሸናፊው አንበሳ ምስል) ሲገኝበት፣ የካርታው መግለጫ የተጻፈው በአማርኛ ቋንቋ ብቻ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በሙሉ መጠሪያቸው በቅኝ የያዙዋቸው አገሮች ስም የታከለበት ነበር፡፡ በሰሜን የጣሊያን ግዛት ኤሪጥሪያ፣ በምዕራብ የእንግሊዝና የምስር ሱዳን፣ በደቡብ የእንግሊዝ የምሥራቅ አፍሪካ ግዛት፣ በደቡብ ምዕራብ የሱማሊ አገር የጣሊያን ግዛት፣ በደቡብ ምሥራቅ የሱማሊ አገር የእንግሊዝ ግዛት፣ በምሥራቅ የሱማሊ አገር የፈረንሳዊ ግዛት፡፡ ከ‹‹Vault Map Collection›› የተገኘ፡፡ (ሔኖክ መደብር)

****

ላንዲት መስቲካ ሻጭ ሕፃን

በደብተርሽ ምትክ

ትንሽ ሱቅ ታቅፈሽ

ካልፎሂያጅ እግር ሥር፤ እንደ

ድንቢጥ ከንፈሽ

ጋሼ ግዙኝ ስትይ፤ አንጋጠሽ

ወደ ላይ

ለጉድ ተጎልቸ፤ ምታረጊውን ሳይ

ራሴስ ይታመም፤ ምላሴን ምን

ነካው

ግራዋ ይመስል፤

መረረኝ ማስቲካው፡፡

አፈር ጠጠር ለብሶ ፤በዶዘር

ተድጦ

መስኩ ከነጎርፉ

ሰማይ ከነዶፉ

ለጌቶች ተሽጦ

አተር ነው እያሉ፤ አፈር ዘግኖ

መፍጨት

ገነት ነው እያሉ፤ መስክ ላይ

መፈንጨት

ጠበል ነው እያሉ፤ ተጎርፉ

መራጨት

ይህንን ማን ሰጠሽ

ገና በልጅነት፤ ልጅነት

አምልጦሽ፡፡

በምቢልታ በዋሽንት፤ በከበሮ

ታጥሮ

በክራር ተማግሮ

በቆመ ከተማ

እምባሽ ቅኝት የለው ፤ለሰው

አይሰማ

ጠዋት የፎከረ፤ ቀትር ላይ ሲረታ

ዛሬ ዝሎ ሲወድቅ ፤ትናንት

የበረታ

ኑሮን ያህል ሸክም፤ ያላንቀልባ

ሲያዝል፡፡

ምን ጸጋ ለብሶ ነው፤ ትከሻሽ

የማይዝል፡፡

(ከበእውቀቱ ሥዩም ፌስቡክ የተወሰደ)

****

ሐረር የምትጠራበት የተለያዩ ስሞች

ሐረር የታሪካዊቷ ከተማ ዋነኛ ስም ነው፡፡ የኦፊሴል መጠሪያዎም ሐረር ነው፡፡ የታሪክ ድርሳናትን ስታገላብጡ ግን ይህ ስያሜ በአዋሽና በዜይላ መካከል ላለው ጂኦግራፊያዊ ክልል በሙሉ የወል መጠሪያ ሆኖ ያገለግል እንደነበር ትረዳላችሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ከአዋሽና ከዋቢ ሸበሌ ወንዞች በስተምሥራቅ በኩል ያለው ክልል በጥቅሉ ሐረር እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡

*****

ከተማዋን ‹‹ጌይ›› እያሉ የሚጠሯት ሐረሪዎች ናቸው፡፡ እናንተም የሐረሪ ቋንቋን መናገር ስትጀምሩ ከተማዋን ‹‹ጌይ›› እያሉ መጥራቱንም እያደር ትለምዱታላችሁ፡፡ በጽሑፍ ጊዜ ግን ጥንያቄ ማድረግ ይገባል፡፡ (በእንግሊዝኛ ስትጽፉ ማለቴ ነው) በዚህን ጊዜ በርካታ ምሑራን እንደሚጽፉት ‹‹Gey›› ብላችሁ መጻፉን አትዘንጉ፡፡

ሐረሪዎች ከተማዋን ‹‹ጌይ›› ይሏታል፡፡ ከተማዋን በሙሉ ስሟ ለመጥራት ሲፈልጉ ደግሞ ‹‹ሐረር ጌይ›› ይላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በንግግር ወቅት ብዙም አያጋጥምም፡፡ ሆኖም በሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት የግቢ በር ቅስት ላይ ሐረር ጌይ በትልቁ ተጽፎ ይታያል፡፡

‹‹አደሪ›› ሶማሌዎች ከተማዋን የሚጠሩበት ስም ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን ይኼንን ስም የምትሰሙት ከአዛውንቶችና ከጎልማሶች አንደበት ነው፡፡ ወጣቱ የሶማሊ ተወላጅ ግን ሐረር ከሚለው ስም በስተቀር ‹‹አደሪ››ን የሚያውቀው አይመስልም፡፡

የሐረርጌ ኦሮሞ ደግሞ ‹‹አደሬ›› በሚለው ስም ነው ከተማዋን የሚጠራት፡፡ የሐረርጌ ኦሮሞ ከተማዋን በሙሉ ስሟ ሲጠራት ግን ‹‹አደሬ ቢዮ›› ይላታል፡፡ የኦሮሞ ሽማጌሌዎች ሁለቱ ቃላት (‹‹አደሬ እና ‹‹ቢዮ››) ኋላና ፊት ተደርገው ቦታ እንደተለዋወጡ ይናገራሉ፡፡ ትክክለኛው አጠራርም ‹‹ብዮ አደሬ›› ሊሆን በተገባ ነበር እንደ ሽማግሌዎቹ እይታ፡፡ ታዲያ በዚህ ዘመን ‹‹ብዮ አደሬ››ም እጥር ብሎ ‹‹አደሬ›› ብቻ ሆኗል፡፡ አብዛኛው ሕዝብም ይኼንን አጠራር ነው የሚያውቀው፡፡

  • አፈንዲ ሙተቂ፣ ሐረር ጌይ፣ 2004 ዓ.ም.

****

40 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች የቤት ውስጥ ጥቃት ይደርስባቸዋል

ፆታዊ ጥቃት በተለይም የቤት ውስጥ ጥቃት ሲነሳ ሁልጊዜም የሚወሳው ወንዶች ጥቃት ፈጻሚ፣ ሴቶች ደግሞ ተጠቂ ተደርገው ነው፡፡ ሴቶች ወንዶች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው የሚሰማ ቢሆንም፣ ጎልቶና ተጋንኖ የሚሰማው፣ ጥናቶች ይዘው የሚወጡትም የሴቷን ጥቃት ነው፡፡

ዘ ጋርዲያን ይዞ የወጣው ጥናት እንደሚያሳየው ግን፣ 40 በመቶ ያህሉ ወንዶች በሚስቶቻቸው ወይም በሴት ጓደኞቻቸው የሚደበደቡ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ፖሊሶች ጉዳዩን ችላ ብለውታል፡፡

‹‹ሜንስ ራይትስ ካምፔይን ግሩፕ ፖርቲ›› የብሪቲሽ የወንጀል ዳሰሳንና የስታትስቲክስ ቢሮን መረጃ መሠረት አድርጎ በሠራው ጥናት፣ እ.ኤ.አ. ከ2004/05 እና ከ2008/09 በነበሩ ዓመታት 40 በመቶ ያህሉ የቤት ውስጥ ጥቃቶች የተፈጸሙት በወንዶች ላይ ነበር፡፡ ከ2006/07 43.4 በመቶ፣ ከ2007/8 45.5 በመቶ እንዲሁም 2008/09 37.7 በመቶ ያህሉ ጥቃት የተፈጸመው በወንዶች ላይ ነው፡፡

ከአራት ሴቶች አንዷ ወይም ከዛ በላይ ማለትም 28 በመቶ፣ ከስድስት ወንዶች አንዱ ማለትም 16 በመቶው 16 ዓመት ከሞላቸው በኋላ የቤት ውስጥ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፡፡

ስድስት በመቶው ሴቶች እንዲሁም አራት በመቶ ወንዶች ባለፈው ዓመት የቤት ውስጥ ጥቃት እንደደረሰባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች እንዲሁም 600 ሺሕ ያህል ወንዶች የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ነው፡፡

የወንድ መብት ተሟጋቾቹ እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም በቤት ውስጥ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ብቻ ናቸው የሚለውና የወንዶች ጥቃት በማኅበረሰቡና በፖሊስ ትኩረት ማጣቱ የተሳሳተ አመለካከት ነበር፡፡

****

የ30 ዲግሪዎች ባለቤት

ሰዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን በመናገር ችሎታቸው ሲደነቁ የሚሰማውን ያህል በትምህርት ዘርፍ በሚያገኙት የዲግሪ መጠን ሲወሱ እምብዛም አይሰማም፡፡

30 የኮሌጅ ዲግሪዎችን ያገኘው ሚካኤል ኒኮልሶን ግን በአንድ ወቅት ኤቢሲ ኒውስን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ነበር፡፡

 ኒኮልሶን ከሁሉም አብልጦ የሚወደው የመጀመርያ ዲግሪው የሆነውንና በሃይማኖታዊ ትምህርት ያገኘውን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ትምህርቱ ካገኛቸው ተጨማሪ ዲግሪዎች በበለጠ ፈታኝ ስለነበር ነው፡፡

በአርት ማስተርስ፣ ከኢስተርን ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ፣ በኤዱኬሽን ዶክትሬት፤ ከዌስተርን ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ፣ በሄልዝ አድምኒስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ፤ ከግራንድ ቫሊ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ማስተርስ፤ ከዌስተርን ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ካገኛቸው 30 ዲግሪዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

እ.ኤ.እ. ከ1963 ጀምሮ ዲግሪዎችን ማግኘት የጀመረው የሚቺጋኑ ነዋሪ ኒኮልሶን፣ 73 ዓመቱን እስካከበረበት 2014 ድረስ፣ 30 የኮሌጅ ዲግሪዎችን ማግኘት ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...