ፒያኒስትና ኮምፖዘር ሳሙኤል ይርጋ የሙዚቃ ፍቅር ያደረበት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ የልጅነት ህልሙ ድምፃዊ መሆን ቢሆንም፣ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን በ16 ዓመቱ ከተቀላቀለ በኋላ ከያኖ ጋር ተሳስሯል፡፡ በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ከበርካታ ባንዶች ጋር ተጫውቷል፡፡ በመጀመሪያ አልበሙ ‹‹ጉዞ›› ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ሳሙኤል በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ሥራዎቹን የሚያቀርብበት ፕሮጀክት ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ በፕሮጀክቱና በሙዚቃ ሕይወቱ ዙሪያ ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት ‹‹ፕሮጀክት ዋን›› የተሰኘው ፕሮጀክትህ ይፋ ሆኗል፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ ምንድነው?
ሳሙኤል፡- የፕሮጀክቱ ዓላማ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችን ከፍ ያለ ደረጃ ባለው ዝግጅትና ማቅረብ ነው፡፡ ዋና ዓላማዬ ሰዎች ማድመጥ አለባቸው ብዬ የማስባቸውን የሙዚቃ ዓይነቶች ማድረስ ነው፡፡ አንድ የሙዚቃ ዓይነትን ዝነኛ ለማድረግ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በተለያየና ጥሩ በምለው መንገድ ለአገር ውስጥና ለውጭ ዜጎች ለማቅረብ አልሜያለሁ፡፡ ሕዝቡ ፕሮግራም አድርጎ በተከታታይ ማየት የሚችላቸው የሙዚቃ ዝግጅቶች በየወሩ ወይም በየሁለት ወሩ በስፖንሰሮች ድጋፍ የመቀጠል ዓላማ አለኝ፡፡ ክለብ ውስጥ መጫወት አቁሜ ኮንሰርቶችን መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ፕሮጀክቱን የጀመርኩት ሰዎች የሙዚቃ ዝግጅቶችን በጊዜ አይተው መግባት እንዲችሉ በማሰብ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ መነሻውን አዲስ አበባ ቢያደርግም ወደ ሌሎች ከተሞችም ትጓዛለህ፡፡ በዕቅድህ ያካተትካቸው ቦታዎች የትኞቹ ናቸው?
ሳሙኤል፡- ቦታዎቹ እስካሁን አልተወሰኑም፡፡ መጀመር የፈለኩት ከሸራን አዲስ ጋዝ ላይት ነበር፡፡ ሌላው ሐሳብ እዛው ሸራተን ላሊበላ ቦልሩም ውስጥ ማዘጋጀት ነበር፡፡ በሌላ በኩል አብዛኛው አድማጭ መምጣት የሚችልባቸውን ቦታዎች እፈልጋለሁ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በብሔራዊ ቴአትር፣ እንደ ፓርክ ባሉ ክፍት ቦታዎች ይካሄድና ከአዲስ አበባ ውጪ ሐዋሳ፣ ናዝሬት፣ ባህርዳር እያልኩ እቀጥላለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በውጭ ፌስቲቫሎች ላይ እንቀጥላለን፡፡
ሪፖርተር፡- የምታሳትፋቸው ሙዚቀኞች እነማን ናቸው?
ሳሙኤል፡- ‹‹ፕሮጀክት ዋን›› በተጀመረበት ዕለት የነበሩ ወጣት ሙዚቀኞች የተወሰኑትን ኮንሰርቶች አብረውኝ ይጓዛሉ፡፡ በየጊዜው ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ ችሎታ አለው የምለው የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ እንዲሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡ ታላላቅ የምላቸው ሰዎችም የሚካተቱበት ዝግጅት ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ቀን ሸራተን አብረውህ የተጫወቱት ወጣት ሙዚቀኞች ናቸው፤ ወጣቶችን ያካተትክበት ምክንያት ምንድነው? በምትሄዱባቸው ከተሞችስ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንፈጥራለን ብለህ ታምናለህ?
ሳሙኤል፡- ወጣቶቹ እንደኔው ሲጫወቱ የነበሩና በዓለም አቀፍ መድረክ የተሳተፉና ያልተሳተፉም ይገኙባቸዋል፡፡ ፕሮፌሽናል ሙዚቀኞችና ከብዙ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር ሲጫወቱ የቆዩ ናቸው፡፡ ዕድል ለመስጠት አይደለም ያሳተፍኳቸው፡፡ ለምሳሌ ጊታሪስቱ የዝነኛው መሐሪ ብራዘር ጊታር ተጫዋች ነው፡፡ ድምፃውያኑም አልበም አላወጡም እንጂ ብዙ የሠሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የመሐሙድ አህመድን በመዝፈን የሚታወቀው መስፍን (ቤቢ) ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ጋር አሜሪካ ውስጥም ብዙ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የፕሮጀክት ዋን ዓይነት መድረክ ግን ለእነሱ አዲስ ሊሆን ይችላል፡፡ በዕድሜ ትልልቅ የሆኑ ሙዚቀኞች አብረውን ይጫወቱ ነበር፡፡ በዝግጅቱ የተሳተፉት ወጣቶች መሆናቸው በአዲስ አበባና ክልል ያሉትን ወጣቶች ያበረታታል፡፡ ደረጃውን በጠበቀ መድረክ መሳተፍ ተሳታፊዎችን ያበረታታል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የሙዚቃ ዝግጅቶች ሲሰናዱ መረጃውን የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነሱም በአዲስ አበባ ይወሰናሉ፡፡ ወደ ክልል ከተሞች በመሄድ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ለማቅረብ ማሰባችሁ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል?
ሳሙኤል፡- የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሩ ነገር ይወድለታል፡፡ የምመኘውም ሁሌ የተለመደውን ነገር መሥራት አይደለም፡፡ ሕዝቡ ያለውን ጥሩ ነገር በተለየ መልኩ ማቅረብ እንደሚቻል ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ በፕሮጀክቱ መጀመሪያ ቀን ከጠራናቸው አምባሳደሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሙዚቃ አፍቃሪዎችና የሙዚቃ ኮንሰርት የማየት ዕድሉን የማያገኙም ይገኙበታል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም ብዙ ዕድሉን የማያገኙ፣ መክፈል እንዲሁም ካላቸው ሥራና ሕይወት አንፃር በቦታው መገኘት የማይችሉም አሉ፡፡ ስለዚህ በየትምህርት ቤቱ ወይም በየመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ተመሳሳይ ዝግጅቶችን በማቅረብ ሰዉ ስለሙዚቃ ያለውን አመለካከት መቀየር ይቻላል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሚዲያው በጣም የሚያተኩረው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉትም፣ ሙዚቃው ከለመዱት ውጪ አዲስ ስልት ቢኖረውም ሊያስደስታቸው ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሥራው በሙሉም ኢትዮጵያን መድረስ አለበት፡፡ እስካሁን ብዙ የተጓዝኩት ወደ ውጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያየኋቸው ከተሞችም ትንሽ ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ ሕዝቡን ማግኘት አለብኝ፡፡ የምንሥራውን መውደዱንና አለመውደዱን፣ በምን መልኩ እንደተረዳውም ማረጋገጥ አለብኝ፡፡ ዕድሉን ላላገኙ ሰዎች ዕድሉን በመስጠት፣ አመለካከታቸውን መቀየርና በሙዚቃው ዘርፍ መረጃ መስጠት ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት ፒያሳ ጎዳና ላይ ድንገት ሙዚቃህን አቅርበህ ነበር፡፡ መሰል የሕዝብ ትዕይንቶች በብዛት አይታዩም፡፡ አንተን ያነሳሳህ ምን ነበር?
ሳሙኤል፡- ለእኔም በዚህ አገር ውስጥ አዲስ ልምድ ነበር፡፡ ጥያቄው የመጣው ከእኔ ሳይሆን እንግሊዝ አገር ካለው ቻናል ፎር የተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ‹‹ራንደም አክትስ›› የተባለ ፕሮግራም አላቸው፡፡ ድንገት መንገድ ላይ ፒያኖ አውጥቼ ስጫወት በቴሌቪዥን የሚያውቁኝ ሰዎች ምን ይሰማቸዋል? ምንስ ምላሽ ይሰጣሉ? የሚለውን ለማወቅ ነበር፡፡ ሕዝቡ ማየት የሚፈልገውን ሰው ድንገት ሲያይ የተለየ ስሜት ይኖረዋል፡፡ ሌላው ነገር ሕዝቡን መድረሱ ነው፡፡ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ማቅረብ ሳይሆን፣ ብዙ ሙዚቃ የሚወድ ሕዝብ መድረስ ለእኔ አዲስና ደስ የሚል ልምድ ነበር፡፡ ሕዝቡም በጣም ተደስቶ እንደነበር አይቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው የኮንሰርቱ ጉዞ በስፖንሰር ወጪዎች ተሸፍኖ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ በነፃ እንዲያይ ነው የፈለግሁት፡፡ ለወደፊትም አዲስ አበባ ውስጥ በድንገት መንገድ ላይ እጫወታለሁ ብያለሁ፡፡ ያ ጥሩ ልምድ ስለነበረ የሚመች ቦታ ላይ አሁንም የማድረግ ዕቅድ አለኝ፡፡
ክፍለ ሀገር ስንሄድ አዳራሽ ውስጥ፣ ሜዳ ላይ ወይም ሆቴል ውስጥ ሕዝቡ በነፃ መጥቶ ያያል፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመሪያ አልበምህ ‹‹ጉዞ›› ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያተረፈ ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥስ ምን ያህል ተደማጭነት አግኝቷል?
ሳሙኤል፡- ለእኔ ዓለም አቀፍ ክብሩና ስኬቱ ትልቅ ነበር፡፡ ጠቅሞኛልም፡፡ አልበሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመሸጡ ግን ብዙ ሰው ያውቀዋል ብዬ አላምንም፡፡ ያወቁትና የሰሙት ሰዎች ግን አልበሙን መግዛት ባይችሉም በጣም ተደስተው እኔ ያለሁበት ቦታ ላይ መጥተው ለማየት ሞክረዋል፡፡ አንደኛው ኮንሰርቶች መኖር አለባቸው የምልበት ምክንያትም፣ አልበሙን መግዛትና ማግኘት ለማይችሉት በዚህ መልኩ መድረስ አለብኝ ብዬ ነው፡፡ የሰሙትም ጥሩ ምላሽ ሰጥተውኛል፡፡ ሥራውን ወደ ተሻለ ደረጃ ወስደኸዋል የሚሉ አስተያየቶችም ደርሰውኛል፡፡ እኔ ደግሞ ሰዎች ከሚሉት በላይ መሥራት ስምፈልግ ከዚህ በኋላ የምሠራቸው እያደጉና እየተሻሻሉ ይሄዳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚገረሙበት ሳይሆን፣ ዓለም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከፍ ያለ እንደሆነ፣ ችሎታ ያላቸው ሙዚቀኞች እንዳሉና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ልዩ መሆኑን ማረጋገጥ የሚችልበትን ዓይነት ኮንሰርቶች አዘጋጃለሁ፡፡ ሁለተኛው አልበም የሚታተመው ውጭ ቢሆንም ኢትዮጵያም መጥቶ እንዲሸጥ አልሜያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ሁለተኛው አልበም ተጠናቋል?
ሳሙኤል፡- ሙዚቃዎቹ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ሸራተን አዲስ ያቀረብኳቸው ናቸው፡፡ መቅዳት ግን ገና አልተጀመረም፡፡ እኔ ሌላ ፕሮጀክት ውስጥ ስላለሁ ካላለቀ መጀመር የምንችል አይመስለኝም፡፡ ካለቀ በኋላ ኢትዮጵያ ወይም አውሮፓ ይቀዳል፡፡ የሚያሳትመው የመጀመሪያው አልበም አሳታሚ ሪል ወርልድ ሪከርድስ ነው፡፡ ሦስተኛውን አልበም ከነሱ ጋር የመሥራት ዕቅድ አለኝ፡፡ የተፈራረምኩትም እስከ ሦስተኛ አልበም ድረስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከሪል ወርልድ ሪከርድስ ጋር መሥራትህ ምን አስተዋጽኦ አበርክቶልሃል?
ሳሙኤል፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም የተከበረ ነው፡፡ በእኔ የሙዚቃ ሕይወት እንዲሁም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ትልቅ ድጋፍ አለው፡፡ እዛ የታተመ አልበምን ዓለም መስማት ይፈለጋል፡፡ አልበሜ ከወጣ በኋላ ታላላቅ የዓለም ሚዲያዎች ዘግበውታል፡፡ ተደማጭ ለመሆን በሪል ወርልድ ሪከርድስ መታተሙ ብቻ ሳይሆን የሚወጣው ሥራ በጥራት፣ በቅንብር፣ በድርሰትም ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ሀያሲ ያለበት ዓለም ስለሆነ ከዛ ስለወጣ ብቻ አይጨበጨብም፡፡ ከፕሮዲውሰሬ ጋር በደንብ ሠርተናል ብዬ አምናለሁ፡፡ የስሙ ትልቅ መሆን ላይ ጥሩ ሥራ ተደምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሽፋን አግኝተናል፡፡ ይህም ጠቅሞኛል፡፡ ያለንበት ጊዜ ሲዲ ኮፒ፣ ከየድረገፆች ዳውንሎድ፣ የሚደረግበት ነው፡፡ ሲዲዎች ብዙ ጊዜ የሚሸጡት ኮንሰርቶች ላይ ነው፡፡ አውስትራሊያ በነበረኝ ኮንሰርት የቀረቡት ሲዲዎች በሙሉ ተሸጠዋል፡፡ በአፍሪካ ከኢትዮጵያ ከፍ ያለ ኮንሰርት መቅረብ እንደሚችል በሥራው አይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የምሠራው እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ብዙ ታላላቅ ሰዎች አሉ፡፡ የእኔና የእነሱ አንድ ላይ መሥራት ከእኔ በላይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡
ሪፖርተር፡- አልበሙ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ከኩባና ከሌሎችም አገሮች የተውጣጡ ታዋቂ ድምፃውያን ጋር በጥምረት ሠርተሃል፤ ተሞክሮህን ብታጫውተን፤
ሳሙኤል፡- ሙዚቃ ውስጥ መሆኔ ልመለከት የማልችላቸውን ነገሮች እንዳይ ረድቶኛል፡፡ አገር ማየት በራሱ ትምህርት ነው፡፡ እኔ በተጓዝኩ ቁጥር ለኢትዮጵያ የምመኘውን እንዳይ ነው ያደረገኝ፡፡ ከሙዚቃው ውጪ ያሉ ሰዎችን ማግኘትም ሌላው ነው፡፡ በአልበሙ በተለያየ አገር ሥራ እየሠሩ ካሉ ሙዚቀኞች ጋር ተጣምረናል፡፡ ከእነሱ ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ የእነሱ ሙዚቃ ከእኔ ጋር ተዋህዶ የፈጠረው ነገር ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ያስገረመ ነበር፡፡ በተለይ ‹‹አይ አም ዘ ብላክ ጎልድ ኦፍ ዘ ሰን›› የታወቀ ዘፈን ነበር፡፡ አሜሪካ፣ ቺካጎ ውስጥ ዝነኛ ባንድ የሠራውን ሙዚቃ በድጋሚ ስሠራው፣ ከኩባ ክሪዎል ኳየር፣ ናይጄሪያ ‑ እንግሊዛዊት ኒኮሌትና የኢራን ዘር ያላት እንግሊዛዊት ሜል ተሳትፈዋል፡፡ ሙዚቀኞቹ ከእንግሊዝ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያም በሳክስፎን ፈለቀ ኃይሉ ነበር፡፡ የእኔ የኢትዮጵያ ገጽታ ያለው ፒያኖ ተጨምሮበት ልዩ ስሜት ፈጥሯል፡፡ አልበሙ በመጀመሪያ እንዲሰማ መንገድ የከፈተው ይህ ሙዚቃ ነው፡፡ በሌሎቹ ሙዚቃዎችም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅና ማራኪ እንደሆነ ያዩበት ነበር፡፡ መጣመራችን በአልበሜ ውስጥ ጥበብ እንደፈጠረ አይቻለሁ፡፡ ሻዴ አልበሙ ላይ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበረች፡፡ አዲስ አልበም ለቃ ቱር እያደረገች የነበረበት ወቅት ስለነበር አልተቻለም፡፡ ፎንቴላ ባስም ፈቃደኛ ብትሆንም በወቅቱ ታመመች፡፡ ሆኖም የነበሩት ሰዎች የፈጠሩት ጥምረት ልዩ አልበም እንዲሆን አድርጎልኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ጉዞዎችህ ለአገሬ የምመኛቸውን ያየሁበት ነው ብለሃል፡፡ በሙዚቃው ዘርፍ ካየሃቸው ለአገሪቱ ምን ተመኘህ?
ሳሙኤል፡- መሥራት ያለብን ያለንን ዓይነት ሙዚቃ ነው፡፡ የአልበም አቀዳድ፣ ሚክሲንግ፣ ማስተሪንግና አጠቃላይ የአልበም ዝግጅት ደረጃው ኢትዮጵያ ውስጥ ከምመኘው አንደኛው ነው፡፡ ትዕይንት የሚቀርብባቸው መድረኮች ምን ያህል ኢንቨስት እንደሚደረግባቸውና ምን ዓይነት ዕይታ እንደሚጠቀሙ ሳይ ለኢትዮጵያ ተመኝቻቸዋለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ የምመኘው ሙዚቃ ብቻ አይደለም፡፡ በሌላ ዓለም ያለውን፣ የተሻለ የሚባለውንና የሚጠቅመንን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በሙዚቃ ሕይወትህ የገጠሙህ ፈተናዎች አሉ?
ሳሙኤል፡- በኢትዮጵያ አንዳንዴ ሙዚቀኛው የሚፈልገውን ነገር ቢያቀርብ ወዲያው ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከለመድነው ዓይነት አካሄድ ስንወጣና አንድ ወይም ውስን ሰዎች ብቻ ሲሞክሩ ለማሸነፍ ትግል አለ፡፡ አያሸንፉም ማለት አይደለም፡፡ በደንብ ያሸንፋሉ፡፡ እኔ በተለመደው ዓይነት ሕይወት ውስጥ መጓዝ ስላልመረጥኩኝ ፈትኖኛል፡፡ ውጭ አገር የገጠመኝ ፈተና ከምጠብቀው ያነሰ ነው፡፡ አልበሜን ሳወጣ ባይሰሙኝስ? እነሱ የሚመኙት ሙዚቃ ሌላ ቢሆንስ? ብዬ እጠይቅ ነበር፡፡ ምላሹ ግን ከጠበቅኩት በተቃራኒው ነው፡፡ በጣም ሲደሰቱ ነው ያየኋቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ስጫወትላቸው ይደሰታሉ፡፡ የእነሱን ሙዚቃ እንድጫወት አይፈልጉም፡፡ አፍሪካዊ ሆኜ አውሮፓ ውስጥ መገኘቴ አንዳንድ ሰዎችን ላያስደስት ይችላል፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች ምን የተለየ ነገር ስላለው ነው ካምፓኒ ያስፈረመው ብለዋል፡፡ እንግሊዝ ውስጥ ያለ የኦንላይን ጋዜጣ ያሞግሰኝና መልሶ ያጣጥለዋል፡፡ እስራኤል ውስጥ ለምን አስፈረመው ያሉ ቢኖሩም፣ ጀሩሳሌም ፖስትን ጨምሮ ትልልቅ ሚዲያዎች ቀና ነገር ጽፈዋል፡፡ እነዚህ አንድ አቅጣጫ ያሳዩኝ አስተያየቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ሊወደኝና አድናቂዬ ሊሆን አይችልም፡፡ የሚደግፈኝን እያመሰገንኩ የሌላው እይታም ትክክል ከሆነ እያየሁ እሄዳለሁ፡፡ ትክክል ካልሆነ በቀናው አቅጣጫ እሄዳለሁ፡፡ ለወደፊት ግን ብዙ ፈተና ሊገጥመኝ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አፍሪካ በአጠቃላይ ፈተና አላት፡፡ ሙዚቃ ላይ ሳይሆን ጉዞ ላይ ጥቁር በመሆኔ ፈተና ይገጥመኛል፡፡ ኤርፖርት ውስጥ ብዙ ጊዜ በደንብ ይፈትሹኛል፡፡ ጥቁር በመሆኔ፣ ፀጉሬ ድሬድ ስለሆነም ትግል አለ፡፡ መጽሔት ወይም ሲዲዬን ከያዝኩኝ አልያም ኢንተርኔት ሲያዩ ይቅርታ ብለው ይለቁኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሙዚቃ ትምህርት ቤቶች፣ ሙዚቃ ከሚቀርብባቸው ቦታዎችና ከአገሪቱ ፖሊሲ አንፃር የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን ይፈትናሉ የምትላቸው አሉ?
ሳሙኤል፡- ለኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ ያሉት ፈተናዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ምን ያህል ይታገላል የሚለው ለሙዚቀኛው የሚቀመጥ ጥያቄ ነው፡፡ መለወጥና መታገል ለሚፈልገው ሙዚቀኛ ያለው ፈተና ብዙ ነው፡፡ ሙዚቃ የሚቀርብባቸው ቦታዎች ማጣት አንዱ ነው፡፡ የሆነ ቤት ይከፈትና ብዙ ባንዶችን ያስተናግዳል፡፡ ዓላማው ግን የቢዝነስ እንጂ የሙዚቃ አይደለም፡፡ ገንዘብ ማምጣት የሚችል ሙዚቃ እንዲያቀርቡ ሙዚቀኞች ይጠየቃሉ፡፡ ፈጠራንና አዲስ አቀራረብን ብዙዎች አያበረታቱም፡፡ የእኔ የሙዚቃ ትግል የባለቢዝነሶቹና የእኔ ፍላጎት አለመመጣጠኑ ነው፡፡ እነሱ ቤቱን በአንድ ቀን መሙላት ይፈልጋሉ፡፡ የኛን ዓይነት ሙዚቃ አድማጭ እያደገ ይመጣል እንጂ አሁን ብዙ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ፈተና ከመንግሥት ጋር ነው፡፡ ብዙ ግንኙነት ቢኖረኝም ከመንግሥት ብዙ ድጋፍ አላይም፡፡ ወደዚህ አገር የሙዚቃ መሣሪያ ይዤ ስገባ እንድከፍል የምጠየቀው እንደ ቅንጦት እንጂ አስፈላጊ እንደሆነ ዕቃ አይደለም፡፡ የተሻለ መሣሪያ ይዘን ስንመጣ ከባድ ክፍያ ስለሚጠየቅ ብዙዎቹ ትተውት ይመጣሉ፡፡ ሙዚቀኛውም ውስን ነው፡፡ መሣሪያዎቹ ቢመጡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ለውጥ ያመጣል፡፡ ከታክስ ጋር ያለው ጉዳይ በጣም ትግል ነው፡፡ ሙዚቀኞች ገቢ የምናገኘው በየወሩ አይደለም፡፡ ሊገኝም ሊጠፋም ይችላል፡፡ ፈቃድ ለማውጣት ስንሄድ የፈቃዱ ዓይነት ከእኛ የሙዚቃ ሕይወት ጋር አይገናኝም፡፡ ለምሳሌ ቢሮ ያስፈልጋል ይባላል፡፡ አንድ ክለብ ውስጥ ለመጫወት እንዴት ቢሮ ሊኖረኝ ይችላል? ያላመዛዘኑ አካሄዶች አሉ፡፡ ሕጉ መውጣት ያለበት ብዙ ጥናት ተደርጎ ነው፡፡ የሙዚቀኛውን ፈተና ብዘረዝራቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የጥናት ቦታ በአጠቃላይ የለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ቦታ ይከራዩና በሰዓት ተከፋፍለው ይለማመዳሉ፡፡ ከዛ ውጪ እንደ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ ያሉ የባህል ማዕከሎችን በመለመን በሚገኙ ድጋፎች እንጂ በአዲስ አበባና በክልል መለማመጃ የለም፡፡ ፕሮፌሽናል ስቱዲዮዎች ለጊዜው የሉም፡፡ የተሻለ የምላቸው ሁለት ስቱዲዮዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ስቱዲዮዎች የቤት ናቸው፡፡ ለሕዝቡ የሚደርሰው ፕሮዳክሽን አነስተኛ ደረጃ ያለው ነው፡፡ ሕዝቡ እያወዳደረ ያለው ወጥቶ ከነበረው አልበም እንጂ፣ ማደጉን የሚያረጋግጥበት ደረጃ የለም፡፡
ሀብቱ ያላቸው ሰዎች፣ መንግሥትና የግል ድርጅቶችም ሙዚቃ ጥቅም ማምጣት እንደሚችል የተረዱት አይመስለኝም፡፡ ሙዚቃ የሚቀርቡባቸው ቦታዎች መኖራቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የባህል ጥቅም አለው፡፡ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ችግሩን ማስረዳት የሚያስችሉ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፡፡ በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ በመሥራት ሙዚቀኛው የሚቸገረው ድምፁ ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡ አካባቢውን ቢረብሽም ለሙዚቀኛው ግን ሕይወቱ ነው፡፡ ለሙዚቃው ራሱን የቻለ ቦታ ቢኖረው ፈጠራው ያድጋል፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማየት ብለው የሚመጡ ሰዎችም ሙዚቃው ትክክለኛው ቦታ ላይ ካልቀረበ ሄደው የኢትዮጵያን ስም ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ ሙዚቃ በቱሪዝሙ ዘርፍ መጥቀም ይችላል፡፡ ቀድሞ ከነበሩና ሙዚቃ ከሚቀርብባቸው ቦታዎች ብዙዎቹ የሉም፡፡ ከሌሉ የሚጎዳው ሙዚቀኛው ነው፡፡ ሙዚቀኛው ሲጎዳ ሙዚቃው ይጎዳል፡፡ ሙዚቃ ሲጎዳ ደግሞ አገሪቱ ትጎዳለች፡፡
ሪፖርተር፡- ሙዚቃዎችን ለመሥራት ምን ያነሳሳሃል?
ሳሙኤል፡- ለሙዚቃ የሚያነሳሳኝ ሙዚቃ ነው፡፡ በእርግጥ ለመነሳሳት አንድ ነገር የምመረኮዝ ሰው አይደለሁም፡፡ ራሴን ለማነሳሳት እሞክራለሁ፡፡ አገር ውስጥ ወይም ሌላ ዓለም ያሉ ሙዚቃዎችን እየሰማሁ፣ እነሱ ባይኖሩም እኔ በምፈጥረው ሙዚቃና በምመኘው ነገር እነሳሳለሁ፡፡ የአገሬ ሙዚቃ ለእኔ ልዩ ነው፡፡ ስሜታዊ ያደርገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቅኝት በውስጤ መግለጽ የማልችለውን ስሜት ይፈጥርብኛል፡፡ እስከ መቼም ሊሠራበት የሚችልም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለህ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ትመራመር ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ በነበረህ ቆይታም በተደጋጋሚ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብታችኋል፡፡ ጫናው ያሳደረብህ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተፅዕኖ አለ?
ሳሙኤል፡- ያሬድ ውስጥ ክላሲካል ሙዚቃ ይሰጠናል፡፡ ክላሲካል ትልቅ ሙዚቃ ቢሆንም የውጭ ነው፡፡ ወደ ራሴ መመለስ ካልቻልኩ የሌላ ዓለምን ሙዚቃ አጥንቶ መውጣት ጥቅም የለውም ባይ ነኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ከክላሲካል ወይም ጃዝ የቱ ሊመች ይችላል የሚለውን እሞክር ነበር፡፡ በዛ ሰዓት ከመምህራን ጋር ጦርነት ነበር፡፡ በትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ብዙ ድጋፍ አልነበረውም፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ንቀውት ቁጭ ያሉ ተማሪዎችም ነበሩ፡፡ ትልቅ ቦታ የሚሰጡትና የሚወዱት የሌላውን አገር ሙዚቃ ነው፡፡ እነሱ በሄዱበት መንገድ ምርምር ተደርጎ አሁን ያለው ደረጃ ላይ ተደርሶ ይሆናል፡፡ የእኛ ሙዚቃ ተራ አይደለም፡፡ አቀራረቡ ምርምር ይፈልጋል፡፡ ያለንን ነገር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የእኛ ሙዚቃዎችና መሣሪያዎቻችን የተዋወቁበት መንገድ ውስን ነው፡፡ ዓላማዬ የነበረው ውስንነቱን መቀየር ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች “አንተ የተሰማኸው ለውጭው ሕዝብ እንዲሆን አድርገህ ስላቀረብክ ነው፤” ይሉኛል፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በተለየ መንገድ አቀረብኩ እንጂ ለውጭው ሕዝብ አላደላሁም፡፡ ሌላውን ዓለም ያወቅኩት መጓዝ ስጀምር ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ የተመኘሁት ተማሪ እያለሁ ነው፡፡ አምባሰልን ተማሪ እያለሁ የሠራሁት እንጂ ውጭ ከሄድኩ በኋላ የተመራመርኩት አይደለም፡፡ ውጭ ፒያኖ ላይ ተጫወትኩት፡፡ የትምህርት ቤቱ መቃወም እልህ ውስጥ ከቶኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታላቅ ሲሆን ማየት ዓላማዬ ስለነበረ ነው፡፡
አንዳንድ ፈረንጆች የእናንተ ሙዚቃ እንደ ሌላው የአፍሪካ አገሮች ብዙ አይታወቅም ሲሉ ያናድደኛል፡፡ አንሰን ሳይሆን ሙዚቃውን የሠራንበት ደረጃ መውረድ ነው፡፡ አገር ውስጥና ውጭ ያለው አድማጭ የሚደነቅበት ሙዚቃ መፍጠር ነበር ዓላማዬ፡፡ ፈተናው ለእኔ ጥሩ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ሌሎች የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ያሬድ ትልቁ የሙዚቃ ተቋም ነው፤ ሥርዓተ ትምህርቱ መስተካከል አለበት ብለህ ታምናለህ?
ሳሙኤል፡- ተማሪ እያለን ያለው ከሆነ እስካሁን ያለው የሚጠቅሙም የማይጠቅሙም ነገሮች አሉት፡፡ እንማራለን ብለን ከተመኘናቸው ሥርዓተ ትምህርቱ ባለማካተቱ ያልተማርናቸው ነበሩ፡፡ ቢካተቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ብዙ ምርምሮች ይሠሩ ነበር፡፡ ተመርቀንም የተሻለ ሥራ መሥራት እንችል ነበር፡፡ መካኒሳ ሴሚናሬ ከያሬድ የሚመሳሰል፣ የሚለያይም ሥርዓተ ትምህርት አለ፡፡ ከሥርዓተ ትምህርቱ ውጪ ያሉ አካሄዶች ስላሉ ለየት ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ጃዝ አምባ ከሁለቱም የተለየ ነው፡፡ ብዙ ዓይነት የትምህርት ክፍሎች መከፈት አለባቸው፡፡ መሣሪያ ተጫዋች ሆኖ መውጣት ብቻ ሳይሆን፣ መምህር፣ ተመራማሪ መሆን የሚፈልግ ተማሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ተማሪዎች ውስጥ ያለው ፍላጎትና ችሎታ መታየት አለበት፡፡ በዚህ ዓመት አካል ጉዳተኞችን የሚያበረታታ አሠራር ተጀምሯል፡፡ ተማሪ እያለሁ ከተመረቅኩም በኋላ የማልስማማበት ነገር አካል ጉዳተኞቹን አለማሳተፍ ነበር፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ ሰላም ኢትዮጵያ ተሳትፎበት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን መቀበል ተጀምሯል፡፡
ሪፖርተር፡- በልጅነትህ የሙዚቃ ፍቅርህንና ዝንባሌህን የምትገልጸው እንዴት ነበር?
ሳሙኤል፡- መዝፈን በጣም እወድ ነበር፡፡ መሣሪያ ነክቼ አላውቅም፡፡ ግቢዬ ውስጥ በነበረኝ እንቅስቃሴ ከቤተሰብ ተቃውሞ ባይኖርም፣ ሙዚቃን እንደ ሙያ ለመያዝ ድጋፍ አልነበረኝም፡፡ የደረጃ ተማሪ ስለነበርኩኝ ትምህርቱ እንዳይጓደል ወደ ሙዚቃው እንድገባ አልፈለጉም፡፡ በልጅነቴ ግቢያችን ያለ ዛፍ ላይ ወጥቼ እዘፍን ነበር፡፡ አጠገባችን ያለ ክሊኒክ የሚመጡ ፈረንጆች ያዩ ነበር፡፡ ከ16 ዓመት ጀምሮ ስኬት ላይ መድረስ ብዙዎችን ያስገርማል፡፡ ልጅነቴ በዓለም ላይ ታዋቂ ዘፋኝና ፒያኖ ተጫዋች የመሆን ምኞት ነበረኝ፡፡ ወደ ህልሜም እየደረስኩ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ያዘጋጀሁት ሙሉ የዘፈን አልበምም አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ሙዚቀኛ ተስፋዬ ለማ ጎረቤትህ ነበሩ፡፡ በሙዚቃ ሕይወትህ ምን ዓይነት ሚና ተጫውተዋል? ሌሎች መነሻዬ የምትላቸው ሙዚቀኞች እነማን ናቸው?
ሳሙኤል፡- ተስፋዬ ለማ በልጅነቴ ታላቅ የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ሆኖ ስለማውቀውና አጠገቤ ስለነበር፣ ስለሙዚቃ እንድመኝ አድርጎኛል፡፡ በአካል ባንተዋወቅም አራተኛ ክፍል እያለሁ በእሱ የተጻፈ ሙዚቃ 80 ልጆችን እየመራሁ ተጫውቻለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ትልቁን ሥራ ሠርቷል የምለው እሱን ነው፡፡ የሚገባው ያህል ቦታ ተሰጥቶታል ብዬ ግን አላምንም፡፡ ለእኔ በታሪክ ቁጥር አንድ የሆነውን ሕዝብ ለሕዝብ ከሠሩት አንዱ ነው፡፡ ፒያኖ እንድወድ ያደረገኝ መጀመሪያ ማንነቱን ሳላውቅ፣ በኋላም አውቄ ኤልያስ ነጋሽ ነው፡፡ እዚህ አገር እንደ ፒያኒስት መጠራት ይቻላል ያስባለኝ ታላቅ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ነው፡፡ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ልዩ ሙዚቃ ሠርተዋል፡፡ በሕይወት መኖራቸውም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ እነ አበጋዝን ጨምሮ የብዙ ሰዎች ሥራዎችን ስሰማ ነው ያደግኩት፡፡ ብቻዬን ሳይሆን የብዙ ታላላቅ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ሥራ ያነሳሳኝ ነኝ፡፡ ትልቅ ሥራ ከሠሩት ሌላው ግርማ በየነ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ትልቅ ክብር እንዲሰጣቸው እፈልጋለሁ፡፡ ከውጭ የፒያኖን ነገር ውስጤ እንዳደርግ ያነሳሳችኝ አሊሽያ ኪስ ናት፡፡ ፕሮዲውሰሬ እንግሊዛዊ ኒክ ፔጅ እንደ አባት እያበረታታ ነው እዚህ ያደረሰኝ፡፡ ፕሮዲውስ ለማድረግ በመወሰኑ ክብር ይሰማኛል፡፡ ፒያኖ ያስተማረኝ እዝራ አባተ፣ ትክክለኛ ትምህርት ሰጥቶኝ የፒያኖ ተጫዋች ሆኛለሁ፡፡ ፈለቀ ኃይሉ እንደ ጓደኛ እያበረታታኝ ሥራዎቼን እንዳቀርብና እዚህ እንድደርስ አስተዋጽኦ ካደረጉ ሰዎች ትልቅ ቦታ እሰጠዋለሁ፡፡ ፒያኖ ባልነበረኝ ሰዓት ፋሲልና ህንደኬ ፒያኖ ያስፈልግሃል ብለው የሰጡኝ ናቸውና በሕይወቴ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ የደገፉኝ እንዲሁም ያልደገፉኝ ሰዎችም እንኳን እዚህ ለመድረሴ ምክንያት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ፒያኖ መማር ሲፈልግ ትምህርት የሚሰጠው ለአዕምሮው እንጂ ለጣቱ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ምንም ጣት ባይኖረው ፒያኖ መጫወት ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ተማሪ እያለህ ባንድ መሥርታችሁ ነበር፡፡ ከዛ በኋላም ከብዙ ባንዶች ጋር ተጫውተሃል፡፡ ጉዞህ ምን ይመስላል?
ሳሙኤል፡- ተማሪ እያለሁ ከተመረቅኩም በኋላ ከብዙ ባንዶች ጋር እንሠራ ነበር፡፡ ከተመረቅኩ በኋላ ኮፊ ሐውስ ውስጥ ከራማዳስ ባንድና ከሌሎችም ጋር እሠራ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ውጭ አገር ካለው ደብ ክሎስስ ጋር መጫወት ጀመርኩ፡፡ ባንዱ ትልቅ ስም ያገኘ ነበር፡፡ በመጀመሪያው አልበማችን ለሶንግ ላይንስ አዋርድ ብንታጭም አላሸነፍንም፡፡ በሁለተኛው አልበም እኔ ለብቻዬ ቤስት ኒው ካመር ተብዬ ታጭቼ፣ ባንዱ ደግሞ ቤስት ኮላቦሬሽን ታጭቶ ባንዱ አሸንፏል፡፡ ባንዱ ለእኔ ትልቅ ትምህርትና ልምድ ነበር፡፡
ቀጥሎ ከነሔኖክ ተመስገን ጋር ኑቢያን አርክ ባንድ ተመሠረተ፡፡ ባንዱ ጥሩ ሆኖ እስከ ጃዝ አምባ ድረስ ሠርተናል፡፡ በተወሰኑ ነገሮች ስለማልስማማ ባንዱን ለቀቅኩ፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ሙዚቃ መሠረትን ማግኘት ዓላማ ያደረገ ጥናት እየሠራሁ ነው፡፡ በጥናቱ በተለያየ ሙያ ያሉ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ የጥናቱ ውጤት መሣሪያዎቹ ላይ መስተካከል የሚችሉ ነገሮችና ስለሙዚቃችን ያላየናቸውን ለማወቅ ያግዛል፡፡
ሪፖርተር፡- ሙዚቃዎችህን እንዴት ትገልጻቸዋለህ?
ሳሙኤል፡- ሙዚቃዎቼ የኢትዮጵያና የውጭ አገሮች ሙዚቃ አስተዋጽኦ ጥርቅም ነው፡፡ ሙዚቃዬ ውስን አይደለም፡፡ በሙዚቃዎቼ የምታየው እኔ ነኝ፡፡ በውስጤ የማሆይ ጽጌ ማርያም ፒያኖ፣ የተማርኩት ክላሲካል ሙዚቃ፣ የምወደው ጃዝና አር ኤንድ ቢ፣ ድሮ በሬዲዮ የምሰማው የባህል ሙዚቃ ውሁድ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከሙዚቃዎችህ በይበልጥ ይገልጸኛል የምትለው አለ?
ሳሙኤል፡- አምባሰል ላይ የተጫወትኩት እኔን ይገልጻል፡፡ እዛ ላይ ያለው የተረጋጋ ሳሙኤል ቢሆንም፣ ክለብ ውስጥ ስጫወተው የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ በውስጤ ያለውን ጥልቅ ነገር የሚገልጸው ዘ ብሉዝ ኦፍ ወሎ ላይ ያለው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ሙዚቀኛ የምትከተለው መርህ ምንድነው?
ሳሙኤል፡- ኃላፊነት ወስደን ለሙዚቃው ሕይወታችንን ብንሰጠው ጥሩ ነው፡፡ መቼ እንደምሞት ስለማላውቅ ጥሩ ሠርቼ መሞት እፈልጋለሁ፡፡ የሕይወት መርሔ ጊዜዬን በሙሉ መጠቀም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነቴን መወጣት እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንድትለወጥ ምክንያቱ ሙዚቃ ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህ ብቻ ሳይሆን ሌላ አገር ሆኜ ስለኢትዮጵያ ልታገል እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ራስህን እንዴት ትገልጸዋለህ?
ሳሙኤል፡- ብዙ ነገሬ የተረጋጋ ነው፡፡ ሰው እስክቀርብ ቁጥብ ነኝ፡፡ በሕይወት ያሉ ነገሮችን በሙሉ በቁም ነገር እወስዳለሁ፡፡ ለመዝናናት ተብለው የሚጀመሩ ነገሮች አልወድም፡፡ በቀን ውስጥ አንድ ነገር ካልሠራሁ ራሴን እወቅሳለሁ፡፡ ደስታዬ የማምንበትን ነገር ሳሳካ ነው፡፡