ማንኛውም ወላጅ ልጁን በወግ አሳድጎ በትምህርት አንጾ ብቁ የአገር ዜጋ ለማፍራት ሌት ተቀን የሚያሳስበውና የሚመኘው ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ብቁ ዜጋ ለማፍራት የመኖሪያና የትምህርት ቤት አካባቢዎች ልጆችን በሥነ ሥርዓት ኮትኩቶ ለማሳደግ ተስማሚ መሆናቸውን ማረጋገጡ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡
ይህን ዓይነት ኃላፊነት በሚገባ መወጣት የወላጆች ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ በቅርብ የሚመለከታቸው የመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችና የኅብረተሰቡም ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡ በመጀመርያ በመኖሪያ ሠፈሮችና በየትምህርት ቤቶች አካባቢ እንደ አሸን የፈሉ የቀንና የምሽት መዝናኛ ቤቶች (የጥፋት ቤቶች) ለወጣቱ እንዲያም ሲል ለታዳጊ ሕፃናቶች ምን ዓይነት ትምህርት እያስተላለፉ እንደሚገኙ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
‹‹ቺቺኒያ›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የወጣቱን የቀንም ሆነ የምሽት ውሎ ለተመለከተ ‹‹ይህንን ከማየት ይሰውረኝ፤›› ያሰኛል፡፡ ከተማይቱ እንደ ሰዶምና ጎመራ ሕዝቧን ይዛ እንዳትጠፋ ያሠጋል፡፡ በወጣቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ዓይቶ እንዳለየ መሆን ከተወቃሽነት አያድንም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን መጥፎ በሽታ፣ በሕፃናቱና በጎልማሶች አካባቢ የተዘራው እኩይ አረም በእንጭጩ ሳይታረም ሥር ከሰደደ ጥሩ ዜጋ ለማፍራት የተሰነቀው ምኞታችን እንዳይመክን መጠንቀቅ ያሻል፡፡
በየክልል አገሩ ከተሞችና በአዲስ አበባ እጅግ ተስፋፍቶ የሚታየው የሲጋራ፣ የጫትና የአልኮል መጠጥ ሱስ፣ ከሕፃናቱ እስከ አዛውንቱ እየተዘወረ ያለውን አጓጉል ድርጊት ቆም ብለን ልናስብበት ይገባናል፡፡
ምንም እንኳ የቢራ ፋብሪካዎች ቢራ መሸጥ ያለበት አሥራ ስምንት ዓመት ለሞላው ሰው ነው ቢሉም፣ በአንፃሩ ምርቱን የሚያከፋፍሉት ለባለ ኪዮክስ ስለሆነና ለኪዮስኩ በአብዛኛው የጫት፣ የትምባሆና የሌላ ሌላውም ደንበኞቹ ወጣቶች ስለሆኑ አትግዙኝ ብሎ አይከለክሏቸውም፡፡ ተማሪው ከትምህርት ገበታው ሲመለስ ትምህርቱን ከማጥናትና የቤት ሥራውን ከመሥራት ይልቅ ጥድፊያው ወደ ሱስ ማስታገሻ ቤቶች ነው፡፡ ወላጅ ከቤቱ በጠዋት ወጥቶ ወደ ሥራው ያመራል፡፡ የሚመለሰው ወደ ማምሻው ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የልጆቹን ውሎ የሚከታተልበት ዘዴ የለውም፡፡ ወጣቶችና ታዳጊዎች በተለያዩ ዘዴዎች ወደ አገር የገባውን የመጥፎ ተግባር ፊልም እየተመለከቱ ወደ አስከፊ ድርጊት ወሲብ ያለዕድሜያቸው እየገቡ፣ ያለወሊድ ቁጥጥር ልቁን ስለሚፈጽሙ ይህ አድራጎት የሚያስከትለው ጉዳት ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ የጊዜው ሕመም እየተስፋፋ ነው፡፡ ሲጋራ፣ ጫትና ቢራ በመጠቀም ረገድ ታዳጊዎች እየተጠመዱበት፣ ሌላ ሌላውንም መጥፎ ተግባር በጨቅላ አዕምሯቸው እየቀሰሙ ተበላሽተዋል፡፡
ሆኖም በሕፃናቱና በጎልማሶች ላይ መፍረድም አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ወላጆች የእነዚህ ሱሶች ምርከኞች ናቸው፡፡ እንግዲህ ታዲያ ወጣቱ ማንን ዓይቶ ይህን ነገር ከማድረግ ይቆጠብ? አዛውንት የተባለው፣ ተማረ የተባለው፣ ባለሥልጣኑና ሌሎችም ሥልጣኔ ማለት በሱስ መጠመድ እየመሰላቸው ለወጣቱ መልካም ዓርአያ ከመሆን ይልቅ፣ ጫት በብብት፣ ሲጋራ በጣት፣ ጫት ያነበዘውን ጭንቅላት አልኮል ያስለቅቀዋል እየተባለ ሕዝብ ሲነሆልል ይታያል፡፡ ገበሬውም የሰብል እርሻውን ትቶ ወደ ጫት እርሻ እየገባ ነው፡፡ እሱም ጠፍቶ ሌላውንም አብሮ ገደል እያስገባ ነው፡፡ እነዚህን ሕፃናትና ወጣቶችን በከተማው ከተንሰራፋው እኩይ ተግባር አላቆ ለነገ አገር ተረካቢነት ኮትኩቶ ሊያሳድጋቸው የሚችለው ማነው? ይህን ችግር ኅብረተሰቡ እንደቀላል ነገር ቆጥሮት ከሆነ ያሳዝናል፡፡ ቢሆንም የተኛ ይንቃ፡፡ ነገ ዛሬ ሳይባል ወላጆች፣ ዕድሮችና የሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች እጅ ለእጅ ተያይዘው የጠነከረ አጋርነት ፈጥረው ወጣቱን ከጥፋት ጎዳና የመመለስ ኃላፊነት ስላለባቸው፤ እባካችሁ ኢትዮጵያን የጥሩ ዜጋ ማፍሪያ እንጂ የብልሹ ዜጋ መፍለቂያ እንዳትሆን የወደፊቷን የኢትዮጵያ ተረካቢዎች በጥሩ ባህል ኮትኩተን እናሳድግ፡፡ በዚህ በያዝነው የሁለተኛው የዕድገት ዘመን ለመልካም ፍሬ እናብቃ፡፡ ወጣቶችም ትምህርት ከራስ ነው የሚጀምረውና መጥፎውን መጥፎ፣ ጥሩውን ጥሩ በማለት እየለያችሁ የመንግሥትና የወላጆችን መልካም አስተሳሰብ ለፍሬ አብቁት፡፡
(እንድርያስ መንገሻ ቆቱ፣ ከአዲስ አበባ)
*******
ዳያስፖራውን መግፋት አይበጅም
በመስከረም 23 ቀን 2008 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም “የባንክና የኢንሹራንስ ባለአክሲዮኖችን ዜግነት የሚቆጣጠር መመርያ ወጣ” በሚል ርዕስ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለአክሲዮኖች ለባንኮች የቀበሌ ወይም ሌላ መታወቂያ ካላቀረቡ በቀር የትርፍ ድርሻ እንዳይሰጣቸውና የአክሲዮን ዝውውር እንዳያደርጉ ከልክሎ አድርገው ቢገኙም እንደሚቀጡ ያትታል፡፡ በዓመት 50,000 ብር የሚከፈላቸው የዳይሬክተሮች ቦርዶች አባላትም ይህን ደንብ ባያስፈጽሙ እንደሚቀጡ ያስገነዝባል፡፡ ይህ ደንብ ቢያንስ ሦስት አንደምታዎች አሉት፡፡ አንደኛው ዳያስፖራውን ይመለከታል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት መንግሥት ደገኛውን ከቆለኛ ሳይለይ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን 500 ዶላር እያስከፈለ ቢጫ መታወቂያ ሲሰጣቸው፤ ከደኅንነት መሥሪያ ቤት፣ ከመከላከያ ተግባራት፣ ከመምረጥና ከመመረጥ መብት ውጭ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያለው መብት እንዳላቸው ነግሯቸው ነበር ይባላል፡፡ በዚያው መሠረት በርካታ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በወቅቱ ለአገሬው ባልተከለሉ የንግድና የልማት ሥራዎች ላይ ሳይሰማሩ አልቀሩም፡፡ በ500 ዶላር የመታወቂያ ካርድ የሰጣቸው መንግሥት አሁን ደግሞ በባንክና በኢንሹራንስ ተቋማት ውስጥ ድርሻ በመያዝ የተሳተፉትን ‹‹እንዳላያችሁ›› ማለት የጀመረ ይመስላል፡፡ መንግሥት በወቅቱ የሰጠው ተስፋ የት ገባ? የዳያስፖራና የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ግንኙነት እያበቃለት ነው ወይስ ግንኙነቱ ከጥቂት ዳያስፖራያውያን ጋ ብቻ ነው?
መንግሥት ለመገደብ የፈለገው ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንጅ እነ ቢል ጌትስን ወይም እነ ዋረን ቡፌትን አይደለም የሚያስብል ዕርምጃ የወሰደ አስመስሎታል፡፡ እነዚህ የዓለም ቢሊየነሮች ቢለመኑም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የማይታሰብ ነው፡፡ ወፍራም እንጀራ ያበላቸውን ኢትዮጵያዊነትን ክደው ኤርትራዊነትን መርጠው ወደ ኤርትራ ሸምጥጠው ሄደው፣ ከዚያ ሆነው ኢትዮጵያን ሲያደሙ የቆዩ ሁሉ፤ ኑሮ ሳይመቻቸው ሲቀር፣ በአሜሪካና በሱዳን በኩል እንደገና አዲስ አበባ ተመልሰው በመምጣት ዛሬም አድራጊ ፈጣሪ የሆኑትን ኤርትራውያንንም አይደለም አዲሱ ሕግ የሚከለክላቸው፡፡ እነሱማ እናት አገራቸውን ቢከዱም መንግሥት በደስታ ተቀብሏቸዋል፡፡ የሕግ ክልከላው ይልቁን በፖለቲካና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት እንባቸውን እያዘሩ ተሰደው ‹‹ዛሬ ለአገራችን ትላንት ለሥጋችን፤›› ያሉትን የአገር ልጆች፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የተመለከተና በእነሱ ላይ የመጣ ነው፡፡
ባንኮቻችን በአውሮፓና በአሜሪካ ካሉት ጋር ሲወዳደሩ እጅግ ጥቃቅን ናቸው፡፡ ባለው የአክሲዮን ይዞታ ደንብ መሠረት በርከት እያሉ ቢመጡም ድርሻቸውን መቆጣጠር ግን ቀላል ነው፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ባንክ አቅሙ አለው፡፡ ለመሆኑ መንግሥታችን የኢትዮጵያ ባንኮች ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያ፣ ከግብፅና ከሌሎችም ትላንት ነፃ ከወጡ የአፍሪካ አገሮች ባንኮች አኳያ ሲወዳደሩ ጥቃቅን መሆናቸውን አያውቅም ማለት ነው? ባግባቡ ተቆጣጥሮ የልማት አጋርነታቸውን በማጠናከር ፈንታ፣ በር መዝጋቱ ለምን አስፈለገ?
ዳያስፖራው ቀርቶ አገር ውስጥ ያለው ዜጋም እኮ እንዲያው ዘሎ አክሲዮን መግዛት አይችልም፡፡ እያንዳንዱ ባንክ የራሱ ገደብ አለው፡፡ ብሔራዊ ባንክም ሌሎች ገደቦች አሉት፡፡ ታዲያ በየት አልፎ ነው ባንኮችን ዳያስፖራው ከአገሩ ዜጋ ቀምቶና በድርሻ በልጦ የሚቆጣጠረው? ወይስ ይህ አዲስ መርህ የግራ ዘመሞች የሻገተ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ቅሪት ነው? ከሆነስ እስከመቼ እንዲህ ሊሆን?
የባንኮቻችንን አቅም ከሌሎች የአፍሪካ ባንኮች ጋር ለማስተካከል ካስፈለገንና ዳያስፖራውም ገንዘብ ካለው ለምን አንጠቀምበትም? ወይስ ትላንት ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡትና ከቀደሙን ጋር ለመስተካከል ሌላ 3,000 ዓመት መጠበቅ ሊኖርብን ነው? የመማር አቅምና ፍላጎት ካለን ከሌሎች መማር ያስፈልጋል፡፡ በባንኩ፣ በኳሱ፣ በልማቱ፣ በፖለቲካውና በሩጫው ወዘተ. በስንቱ ይቅደሙን? ከማይጨው ሽንፈት፣ ከ1977 ዓ.ም. ረሃብ፣ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ከደርግ የሥልጣን አያያዝና አገዛዝ ውድቀት ምን ተማርን? በዚሁ መሠረት ባንኮቻችንን ለማጠናከር ብዙ መማርና በዕወቀት ላይ ብቻ በመመሥረት ብዙ መሥራት እንዳለብን መገንዘብ አለብን፡፡
በአንድ ፊት በአገራችን ልማት እንዲሳተፉ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ ዳያስፖራዎችን ሲማጠናቸው ሰንብቶ፣ ዛሬ ላይ የዕድገት ሞተር በሆኑት ባንኮች ውስጥ የአንድ ከመቶ ድርሻ እንኳ እንዳይኖራችሁ ማለት እውነት ታስቦ የተደረገ ነው ወይ? ለመሆኑ ስንቱ ዳያስፖራ ከበርቴ ቢሆን ነው ባንኮቻችንን በአገር ካለነው ዜጎች ቀምተው የሚቆጣጠሯቸው? መንግሥት ገና ለገና እንዲህ ስለፈራው ዳያስፖራ በቂ ዕውቀት አለው ወይ? አምባሳደሮቻችንስ ዳያስፖራ በብዛት ከተሰደደባቸው ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምሥራቅ መረጃ አይልኩም ወይ? ስንት ከበርቴ ዳያስፖራዎች እንዳሉን ቢነግሩን ሌሎቻችንም ስደት በመሄድ ለከበርቴነት በተዘጋጀን ነበር፡፡
እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሌላ አገር ከበርቴ ዜጋ ናቸው የሚለውን የፈጠራ ወሬ ብንቀበል እንኳ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሕጋዊ መንገድ አክሲዮን ገዝቶ የሚሠራው ይቅርና፣ ምንም ጥፋት የሌለበትን የሌላ አገር ዜጋ ሀብትስ ዛሬ ብድግ ብሎ መቀማት፣ ወረድ ሲልም የውጭ ዜጎቸን ያገኙትን የትርፍ ድርሻ አትስጡ፣ አክሲዮናቸውን እንዳይሸጡ አድርጉ ብሎ ማወጅ፣ በሕግና ሥርዓት እመራለሁ ከሚል፣ አኩሪና ረጅም ታሪክ ያላትን አገር ለሚመራ መንግሥት የሚመጥን ዕርምጃ ይሆን? ሌሎች አገሮችስ ዜጎቻቸው የተቀሙትን ሀብት ዝም ብለው ሊመለከቱት ይችላሉ? የልማት አጋርነታቸውንስ አያዳክመውም?
የአሁኑ ዕርምጃ ከደርግ ዘመንኑ ጭፍን ‹‹የፍየል ወጠጤ›› መፈክር የሚለየው ቢኖር በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አለመዘፈኑ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እናት አገራቸውን የከዱ ኤርትራውያን እንኳ ስንት ዓመት ሲያደሙንና ሲያስደሙን ቆይተው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ንብረታቸውን ቸሩ መንግሥታችን እየመለሰላቸው ነው ይባላል፡፡ ዳያስፖራው ከእነዚህ ዜጎች ለምንና በምን ምክንያት አንሶ ታየ?
ሁለተኛው አንደምታ የሚመለከተው በአገር ኗሪ የሆኑ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እውነተኛና ጠንካራ ባለሙያ ለገንዘብ፣ ለዝና ወይም ለጽድቅ ሲል አይደለም የባንክም ሆነ የኢንሹራንስ ቦርድ አባል የሚሆነው፡፡ ምናልባት ዋናው ምክንያቱ ከሞላ ጎደል ነፃ አገልግሎት ለወገኑ ለመስጠት ሲል ይሆናል፡፡ ይህም ሲባል ግን በቦርድ አባልነት የሚያገኙትን የ50,000 ብር ክፍያ ፈልገው የሚገቡ አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ብቁ ባለሙያዎች ገንዘብ ቢፈልጉ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል መሆን ከዓላማቸው አንፃር ከንቱ ድካም መሆኑን በሚገባ ስለሚረዱ፣ በምንም መንገድ ወደ ቦርድ አባልነት አይመጡም፡፡
ስለሆነም ይህ መመርያ ለብቁ ባለሙያዎችም ‹‹ነፃ አገልግሎት የምትሉትን እርሱት፣ የመንግሥትን ደንቦች ባታስፈጽሙ አይቀጡ ቅጣት ትቀጣላችሁ›› እያላቸው ነው፡፡ ይህ የመንግሥት አድራጎት በርካታ ብቁ ባለሙያዎችን ከዚህ ወሳኝ የአገልግሎት መስክ ሊያባርራቸው ይችላል፡፡ ያሉትን ጥቂት ጠንካራ ዜጎች በማስፈራራት፣ ብቁ አመራር የማይኖራቸው ባንኮችና ኢንሹራንስ ድርጅቶችን በደካማ አመራር ሳቢያ ይበልጥ እየደከሙ መሄዳቸው የማይቀር ነው፡፡ መሃይምነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ቀርቶ፣ አሜሪካም የብቁ ቦርድ አባላት ዕጥረት እንዳለባት ምሁራን ደጋግመው የሚገልጹት ነው፡፡
ሦስተኛው አንደምታ የሚመለከተው በኢኮኖሚው ውስጥ የተንሰራፋውን መንግሥትን ነው፡፡ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ በያመቱ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ከቡናና ከሰሊጥ ኤክስፖርት ከሚገነው ድምር ገቢ ይበልጣል ይባላል፡፡ ከዚህ ገቢ ውስጥ አብዛኛው ለልማት እንደሚወጣ ጎንደርና መቐለ ይመሰክራሉ፡፡ ከዚህ የተረፈውም ጠንካራ የማኅበራዊ ዋስትና ሥርዓት በሌለባት አገራችን፣ ያለባትን ከፍተኛ የማኅበራዊ ዋስትና ቀዳዳ በመሸፈን ወሳኝ ሚና አለው፡፡ በዚህ ላይ ዳያስፖራዎች በተለያዩ የልማት መስኮች እየተሳተፉ ነው፡፡ ይህ የዛሬው የባንክ ባለድርሻነት ክልከላ እነዚህንም አስደንግጦ፣ ሊመጡ ያሰቡትንም ዝር እንዳይሉ አያደርግም ወይ?
አገራቸውን በከፍተኛ ደረጃ እስከ 40 ዓመት አገልግለው በጡረታ የሚገለሉ ዜጎች ከስድስት መቶ ብር እስከ 800 ብር በሚከፈላቸው ወርኃዊ የጡረታ ገንዘብ ግማሽ ኩንታል ጤፍ ካልሆነ ሌላ ሊገዙበት እንደማይችሉ በመንግሥትም በሚገባ ይታወቃል፡፡ በአንፃሩ ከፍተኛ ደመወዝ፣ ሰፊ ጥቅማጥቅምና መኖሪያ ቤት ለሚያገኙት የዛሬው ሹማምንት ጡረታ ሲወጡ በልዩ ታሪካዊ አዋጅ የ25 ሚሊዮን ብር ቤተ መንግሥት አከል ቪላ በመንግሥት እንደሚገነባላቸው እየተነገረን፣ ዳያስፖራውን ግን ደሃ ወገኑን እንዳይረዳ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሚገኝና በአንፃራዊነት አስተማማኝ በሆነ ተቋም ውስጥ ጥቂት አክሲዮን ገዝቶ ጥቂት የገቢ ምንጭ በመፍጠር እንዳይደጉም ተስፋ ማስቆረጥ የመልካም አስተዳደር ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ ገዥዎቻችን የነገ ጡረታቸውን በልዩ አዋጅ እያመቻቹ፣ ዛሬም ተንደላቅቀው እየኖሩ፣ ሳይበላ የሚያበላውን የተመዘበረውን ሕዝብ መርሳታቸው አይጠቅማቸውም፡፡ ዳያስፖራው የዚህ ሕዝብ አካልና አለኝታ ነው፡፡ በእዚያ ላይ ንብረቱ የተገደበበት ከበርቴ ዳያስፖራም ካለ፣ ከአጋርነት ወደ ከበርቴ የመንግሥት ተቃዋሚነት እየተገፋ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአገራችንም፣ ለሁላችንም አይበጅም፡፡
(ገመቹ ደሳለኝ፤ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ)