Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክሚስጥርን የመጠበቅ የባንክ ግዴታ

ሚስጥርን የመጠበቅ የባንክ ግዴታ

ቀን:

ሕግ በሙያ ወይም በሥራ ምክንያት የታወቀ የደንበኛ መረጃ /ሚስጥር/ የመጠበቅ ግዴታ በተለያዩ አካላት ላይ ይጥላል፡፡ የእምነት አገልጋይ፣ የሕግ አማካሪ፣ ጠበቃ፣ ነገረ ፈጅ፣ የሽምግልና ዳኛ፣ ልዩ አዋቂ /ኤክስፐርት/፣ አስታራቂ ሽማግሌ፣ ውል አዋዋይ፣ ሐኪም ወይም ሌላ በሙያው ወይም በሥራው ምክንያት የተገለጸለትን ሚስጥር በሙያ ሥራው ላይ ሳለም ሆነ ሥራውን ከለቀቀ በኋላ መግለጽ ወንጀል ሆኖ በሕጉ ተደንግጓል፡፡ /የወንጀል ሕግ አንቀጽ 399/ የደንበኞች ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ካለባቸው አካላት ውስጥ ባንኮች ተቀዳሚ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ባንኮች በሕግ ያለባቸውን ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ፣ ሚስጥር፣ እንዲገለጽ የሚፈቀድባቸውን ሁኔታዎችና በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመዳሰስ ሙከራ ተደርጓል፡፡

የግዴታው ወሰን

የባንኮች ዋና ዓላማ ከኅብረተሰቡ ገንዘብ በተቀማጭ /Deposit/ መልክ በመሰብሰብ ለነጋዴ በማበደር በኢንቨስትመንት አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህ ዓላማ ገንዘቡ ባንክ የገባው በማናቸውም ዓይነት ሕጋዊ መንገድ ቢሆንም፣ ገንዘቦችን በአደራ የማስቀመጥ ውል፣ ተቀማጭ ለተደረጉት ገንዘቦች ባንኩን ባለሀብት ያደርገዋል፡፡ በውሉ በተመለከቱት ውለታዎች መሠረት የመመለስ ግዴታ ያለበት መሆኑ ሳይቀር፣ አስፈላጊ ለሆኑት ሥራው እንዲያገለግሉት ለማድረግ መብት ይሰጠዋል፡፡ /የንግድ ሕግ ቁጥር 896/ በሌላ በኩል አስቀማጮቹም በተመሳሳይ የባለቤትነት መብታቸውን አያጡም፡፡ ገንዘቡን ለመጠቀም፣ ለማስተላለፍ ወይም ለመውሰድ የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ በገንዘብ ላይ ያለ የባለቤትነት መብት ከሌሎች የንብረት ባለቤትነት መብት በተለየ መልኩ የመሸጥ፣ የመለወጥ ወይም የማውደም መብትን አያካትትም፡፡ ይህም የመገበያያ ገንዘብ መግዣ /Means of transaction/ እንጂ የሚሸጥ ዕቃ /Object of sale/ ባለመሆኑና ሕግ ከፍ ባለ የሕዝብ ጥቅም እንዳይቃጠል፣ እንዳይወድም፣ ስለሚደነግግ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በባንክ ገንዘብ ያስቀመጠ ሰው በባንኩ ውስጥ ስላስቀመጠው የገንዘብ መጠን፣ መቼና ምን ያህል ከሒሳቡ እንደወጣ፣ ከማን፣ መቼ፣ ምን ያህል ገንዘብ ገቢ እንደሆነለት፣ ወዘተ. ከእርሱና ከባንኩ ውጪ ማንም ሊያውቅ አይገባም፡፡ ይህ ሚስጥርን የመጠበቅ ግዴታ ባንኮች በሚሰጡት የብድር፣ የገንዘብ ማስተላለፍ ሥራ፣ የገንዘብ ምንዛሪ፣ የካዝና ኪራይ አገልግሎቶች፣ ወዘተ. በተመሳሳይ መልኩ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል የሚደረጉ ግብይቶች /transactions/ ግላዊ ባህርይ ያላቸው በመሆኑ የባንክ ሠራተኛ መረጃውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት የለበትም፡፡ ይህ የደንበኛው መብት /የባንኮች ግዴታ/ ከግላዊነት መከበር /The right to privacy/ የሚመነጭ ሲሆን፣ በተለያዩ ሕጎች ጥበቃ ያደርግለታል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 26 ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱ፣ ግላዊነቱ፣ የመከበር መብት እንዳለው በመደንገግ መሠረታዊ መርሁን ያስቀምጣል፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ ሌሎች ሕጎችም ስለ ሚስጥራዊነት የሚሉት ነገር አለ፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ባንኮችን የሚገዛው የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000 በአንቀጽ 28 በግልጽ የደንበኞችን መረጃ ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠትን ይከለክላል፡፡ በተጨማሪም ይህን ሚስጥር የመጠበቅ መብት በሕግ ከተፈቀዱ ምክንያቶች ውጪ ለሦስተኛ ወገን የገለጸ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ማንኛውም ባለሙያ /የባንክ ሠራተኛን ጨምሮ/ በወንጀል ኃላፊ ይሆናል፡፡ /የወንጀል ሕግ አንቀጽ 397፣ 399፣ 400፣ 606 እና 843ን ይመለከቷል፡፡/ በፍትሐ ብሔርም ቢሆን በተለያዩ ድንጋጌዎች ሚስጥር መግለጹ በደንበኛው ላይ ባስከተለው ጉዳት መጠን ባንኩ እና/ወይም ሠራተኛው ለደንበኛው ካሳ የመክፈል ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ /የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2031 እና 2035ን ይመለከቷል፡፡/

ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታን ከደነገጉ ሕግጋት ሊሰመርባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ፡፡ ቀዳሚው ሚስጥር መጠበቅ ሚስጥር ሆኖ ሊጠበቅ የሚገባውንና በሥራው ምክንያት ያወቀውን ማናቸውንም ዓይነት ሰነድ፣ መረጃ ወይም ፍሬ ነገር የሚያካትት መሆኑ ላይ ነው፡፡ የግላዊነት መብት ሰፊ እንደመሆኑ መጠን ሚስጥራዊነትም መገለጫው ሊሰፋ ስለሚችል መረጃ ሁሉ በጥንቃቄ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛው ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ያለበት ሰው ሥራውን ከለቀቀ በኋላ ቢሆን እንኳን መረጃውን እንዳይገልጽ ግዴታ አለበት፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 397 በግልጽ እንደሚደነግገው በሥራው ምክንያት ያገኘውን መረጃ ሥራውን ወይም ሹመቱን ከለቀቀ በኋላ ቢሆን እንኳን መግለጽ በእስራት ወይም በመቀጮ ያስቀጣል፡፡

ሚስጥር የማይጠበቅበት ልዩ ሁኔታ

ሚስጥር መጠበቅ ልዩ ሁኔታ ያለው በመሆኑ ሚስጥር መግለጽ የማያስጠይቅበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም የሚመነጨው መሠረታዊ የግላዊነት መርህ ፍጹማዊ ካለመሆኑ የሚመነጭ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 26 (2) አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደኅንነት፣ የሕዝብን ሰላም፣ ወንጀል በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ በመጠበቅ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት በማስከበር ዓላማዎች ላይ በተመሠረቱ ዝርዝር ሕጎች የግላዊነት መብት አጠቃቀም ሊገደብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 400 ሚስጥር መግለጽ የማያስቀጣባቸውን አጋጣሚዎች ይዘረዝራል፡፡ ከባንክ ሥራ ጋር የተያያዙ ልዩ ሁኔታዎችን በተከታዩ ክፍል ለማየት እንሞክር፡፡

ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ፍፁማዊ ባለመሆኑ በሕጉ በተቀመጡ ግልጽና ልዩ ሁኔታዎች /exceptions/ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ እነዚህ ልዩ ሁኔታዎች ከራሱ ከደንበኛው ፈቃድ፣ ለሕዝብ ጥቅም /public interest/ በሚደረጉ ገደቦች፣ ለባንኩ ለራሱ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜና በሕግ በግልጽ ከተፈቀዱ ሁኔታዎች ሊመነጩ ይችላሉ፡፡

የመጀመሪያው የደንበኛ መረጃ ለሦስተኛ ወገን መስጠት የሚፈቀድበት ደንበኛው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ /Implicit/ ፈቃድ የሰጠ ሲሆን ነው፡፡ ደንበኛው የባንክ ሒሳቡን እንዲያንቀሳቅስ ተወካይ ከወከለ፣ ደንበኛው ያለው ሒሳብ ተገልጾ ለሦስተኛ ወገን እንዲሰጥለት ከጠየቀ፣ ባንኩን ለንግድ ሥራው ዋቢ /Reference/ አድርጎ ከጠቀሰ ወዘተ. ባንኩ መረጃውን ለሦስተኛ ወገን እንዲሰጥ መፍቀዱን ያሳያል፡፡ ስለዚህ ባንኮች የሒሳብ ባለቤቱ ፈቃድ መኖሩን እስካረጋገጡ ድረስ የደንበኛውን መረጃ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ተጠያቂ አይሆኑም፡፡ የሒሳብ ባለቤቱ ፈቃዱን በቃል፣ በድርጊት፣ ወይም በጽሑፍ መግለጽ የሚችል ሲሆን በቀላሉ ለማስረዳት ግን ባንኮች ፈቃዱን በጽሑፍ እንዲገልጽ ቢያደርጉ መልካም ይሆናል፡፡ መረጃው ሲገለጥም ጠቅለል ባለ አነጋገሮች፣ ለሚመለከተው አካል ብቻ የሚሰጥና ሚስጥራዊ /Confidential/ መሆኑን ማስጠንቀቅ ይገባል፡፡ ያልተጠየቁ ዝርዝር መረጃዎችን መስጠት /ለምሳሌ የገንዘብ መጠን እንዲጠቀስለት ብቻ ለፈቀደለት ሰው የገንዘቡን ምንጭ /አስገቢውን ጭምር/ መግለጽ/ ሚስጥራዊነትን ይጥሳል፤ በተጨማሪም ከሚመለከተው አካል ውጭም መግለጽ እንዲሁ ተገቢ አይሆንም፡፡

 

የደንበኞች መረጃ የሚገለጥበት ሁለተኛው መንገድ ከፍ ያለ የሕዝብ ጥቅምን /Public interest/ ለመጠበቅ ወይም የአገር /የሕዝብ/ ደኅንነትን ለማስከበር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተለያዩ ሕጎች ባንኮች የደንበኞቻቸውን ሚስጥር ለሦስተኛ ወገን እንዲሰጡ የሚፈቀድበትን መርህ ይደነግጋሉ፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 22 ‹‹መረጃ የመስጠት ግዴታ›› በሚል ርዕስ የሽብርተኝነት ወንጀል ለመከላከል ወይም ምርመራ ለማከናወን ፖሊስ ለምርመራው የሚረዳው መሆኑን በሚገባ የሚያምንበትን መረጃ ወይም ማስረጃ ከማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ባለሥልጣን፣ ባንክ፣ የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል፡፡ መረጃ ወይም ማስረጃ የተጠየቀው ወገን መረጃውን ወይም ማስረጃውን የመስጠት ግዴታ አለበት፤›› በማለት ልዩ ሁኔታውን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኘነትን በገንዘብ መረዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 657/2002 በአንቀጽ 4 መረጃ የመስጠት ግዴታ ደንግጓል፡፡ እነዚህ ግዴታዎች ባንኮች የደንበኞችን ሚስጥር ሽብርተኝነትን /Terrorism/፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ /money laundering/ እና ሽብርተኘነትን በገንዘብ መርዳት /Financing Terrorism/ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ ፖሊስ ወይም የፍትሕ አካላት መረጃ በጠየቁ ጊዜ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ መረጃ የሚጠይቀው አካል ግን መረጃውን ለእነዚህ ወንጀሎች መከላከል ወይም መቆጣጠር ለመጠቀም የፈለገ ስለሆኑ ማስረጃ ሊያቀርብ ይገባል፡፡

እነዚህን አዋጆች ለማስፈጸም ብሔራዊ ባንክ እ.ኤ.አ ከማርች 4 ቀን 2010 ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን መመርያ /Customer Due Diligence of Banks Directive/ አውጥቷል፡፡ ይህ መመርያ ባንኮች ከደንበኞቻቸው ሒሳብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሪፖርቶች ለፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል እንዲልኩ ግዴታ ይጥላል፡፡ በዚህ ረገድ ባንኮች በደንበኞቻቸው ሒሳብ የገባው ገንዘብ ከወንጀል ተግባር ወይም ከሽብርተኝነት ወንጀል ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን በምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲያምኑ፣ ደንበኞች ወደ ሒሳባቸው የሚያስገቡት ወይም የሚያወጡት ገንዘብ ከብር 200,000.00 ወይም ከ10,000.00 ዶላር በበለጠ ጊዜና አጠራጣሪ ግብይቶች /suspicious transactions/ ሲኖሩ ለማዕከሉ ሪፖርት እንዲያደርጉ ያስገድዳል፡፡ መመርያው በሚስጥራዊነት ገደብ ላይ ተጨማሪ ሁኔታዎችን በማካታት ልዩ ሁኔታዎችን /exceptions/ አስፍቶታል፡፡

የሕዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ባንኮች ለብሔራዊ ባንክ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለሚገባው ሰው ወይም ብሔራዊ ባንክ ለፈቀደለት አካል የደንበኛን መረጃ/ማስረጃ ሊሰጡ እንደሚችሉ የባንክ ሥራ አዋጅ ቀጥር 592/2000 በአንቀጽ 28/4/ ላይ በግልጽ ደንግጓል፡፡ የእነዚህ ልዩ ሁኔታዎች አመክንዮ /Rational/ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን በመቆጣጠር የመምራትና ባንኮችን የፋይናንስ ጤናማነት ለማረጋገጥ የተሰጠውን ሥልጣን ተፈጻሚ ለማድረግ ሲሆን፣ ለፍርድ ቤት  መረጃ የሚገለጸው ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማገዝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባንኮች ብሔራዊ ባንክ ለሦስተኛ ወገን መረጃ እንዲሰጥ ሲፈቅድ ፈቃዱን በጽሑፍ እንዲሰጥ መጠየቅ የሚገባቸው ሲሆን፣ የሚሰጠው መረጃም በግልጽ በፈቃዱ በተገለጸው መሠረት መሆኑን በማረጋገጥ ሊያስተናግዱ ይገባል፡፡ በፍርድ ቤት በኩል የፍርድ ባለመብቶች፣ ውርስ አጣሪዎች፣ በመፍረስ ላይ ያለ ድርጅት አጣሪዎች ወዘተ. በጠየቁ ጊዜ መረጃ እንዲሰጣቸው ወይም ለፍርድ ቤቱ  እንዲላክ የሚጠይቅ ሲሆን ባንኮች የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ትክክለኛ /genuine/ መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፖሊስ ለተራ ወንጀል የደንበኛን መረጃ ከፈለገ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይዞ ሊቀርብ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ፖሊስ እያጣራ ወይም እየመረመረ ያለው ወንጀል ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ ከሆነ ግን ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባያመጣም መረጃው ይሰጠዋል፡፡ ባንኮች ማረጋገጥ የሚጠበቅባቸው እየተጣራ ያለው ወንጀል የሽብርተኘነት ወንጀል ወይም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀል መሆኑን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ ጊዜ ፖሊስ ለተራ ወንጀል የደንበኛን የባንክ ሒሳብ መጠን ለማወቅ ጥያቄ አቅርቦ ሲከለከል የሚታይበት ሁኔታ የሕግ መሠረት ያለው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሦስተኛው ልዩ ሁኔታ ባንኮች የደንበኛን መረጃ ለራሳቸው ጥቅም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሲጠቀሙበት ነው፡፡ ይህ ለባንኩ ጥቅም የሚደረግ መረጃን የመጠቀም መብት ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ባንኮች ደንበኛው ላይ ገንዘብ ለማስመለስ /በኦቨር ድራፍት ብድር፣ ያለአግባብ ወደ ሒሳቡ የገባን ገንዘብ ለማስመለስ/ ክስ ለመመሥረት የደንበኛውን የሒሳብ መረጃ መግለጥ ይገደዳሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ አከራካሪ የሚሆነው ራሱ የደንበኛው ሒሳብ ሊሆን ይችላል ወይም የባንኩ ቀለል ያለ ማስረጃ /Prima-facie evidence/ የባንክ ሒሳብ መግለጫ /Bank statement/ ሊሆን ይችላል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ተዋዋይ ወገኖች እርስ በራሳቸው በተካሰሱ ጊዜ ውሉን አቅርበው በፍርድ ቤት እንደሚከራከሩት ሁሉ ባንኮችም ከደንበኞቻቸው ጋር ክስ ሲኖራቸው መረጃውን ሊጠቀሙበት ግድ ይላል፡፡

አራተኛው ልዩ ሁኔታ የሕግ አውጭው አካል በተለያየ ምክንያት መረጃ የመስጠት ግዴታን በአዋጅ ሲደነግግ የሚኖረው የሚስጥዊነት መብት ገደብ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/2002 አንቀጽ 79 ማንኛውም ሰው የደንበኞችን መረጃ የግብር አስገቢው ባለሥልጣን እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በዚህ ረገድ ባንኮች መረጃ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ግለሰቦች በሕግ ተጠቃሚ መሆናቸውን ከገለጹ፣ ይህ መብታቸው የሕግ ድጋፍ መኖሩን በማረጋገጥ መረጃ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

ሌላው የንግድ ሕጉ ከአክሲዮን መረጃ ጋር በተያያዘ የሚደነግገው ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ የንግድ ሕጉ የአክሲዮን መረጃ ሕዝባዊ (public) መሆኑን መሠረት በማድረግ የአክሲዮን መረጃን ሚስጥራዊ አያደርገውም፡፡ ሕጉ በቁጥር 331 የአክሲዮን ማኅበራት  የባለአክሲዮኖችን ስም፣ አድራሻ፣ የአክሲዮኖች ብዛትና ቁጥራቸውን፣ በየአንዱ አክሲዮን የተከፈለውን ገንዘብ ልክና ባለአክሲዮኑ መዝገብ የገባባትን ቀን የሚያመለክት መዝገብ እንዲይዙ ያስገድዳል፡፡ በሕጉ ቁጥር 3 ባለአክሲዮን የሆነው ሰው ይህን መዝገብ ሳይከፍል ሊመለከተው እንደሚችል፣ ሌላው ሰው ሁሉ ደግሞ የተወሰነውን ገንዘብ ከፍሎ መዝገቡን ለማየት እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

ስለዚህ በአክሲዮን ማኅበር መልክ የተቋቋሙ ባንኮች ሦስተኛ ወገን የባለአክሲዮን መዝገብ ለመመልከት በጠየቀ ጊዜ ሚስጥር መጠበቅን መከላከያ በማድረግ ሊከለከሉ አይችሉም፡፡ የባለአክሲዮን መዝገብ ማኅበሩ ሲመሠረት በንግድ ጋዜጣ እንዲታተም የሚደረገውም መረጃው ሚስጥራዊ ባለመሆኑ ነው፡፡ በተግባር ግን በአክሲዮን ማኅበርነት የተቋቋመው ባንኮች ሦስተኛ ወገኖች የባለአክሲዮንን መረጃ በጠየቁ ጊዜ የባንክ ሚስጥርን (Bank Secret) ምክንያት በማድረግ ፈቃደኛ የማይሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕጉ በቁጥር 331 (4) ‹‹ማንኛውም ሰው የተወሰነውን ገንዘብ ከፍሎ የመዝገቡን ግልባጭ ወይም ባጭር የተወጣጣውን ጽሑፍ ለመቀበል እንደሚችል ከመደንገግ ባለፈ የጊዜ ገደብ ወስኗል፡፡ እንዲህ ያለ መረጃ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ድንጋጌው በባንክ ሥራ አዋጅ አንቀጽ 28 (4) መሠረት ባንኮች በሕግ ለተፈቀደላቸው ሰዎች መረጃ የመስጠት ኃላፊነታቸው ጋር የሚጣጣም በመሆኑ ሦስተኛ ወገኖች የባለአክሲዮን መረጃ ሊከለከሉ አይገባም፡፡

የግዴታው አተገባበር

 

ከዚህ በላይ የተገለጹት ልዩ ሁኔታዎች /exceptions/ ከመብዛታቸው የተነሳ የሒሳብ አስቀማጭ ደንበኞች የግላዊነት መብት /privacy/ በጣም የተገደበ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ገደቦቹ በአብዛኛው ከደንበኛው ፈቃድ ውጭ በሚሆኑ ምክንያቶች የሚፈጸሙ በመሆናቸው መርሁ ልዩ ሁኔታ ሆኗል ለማለት ያስችላል፡፡ ገደቦቹ በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ አዋጆች ሊፈቀዱ መቻላቸው፣ ብሔራዊ ባንክ መረጃው ይገባዋል ለሚለው ማንኛውም አካል መረጃው እንዲሰጥ መፍቀዱ ቀጥሎ ከምናያቸው የተወሰኑ የአፈጻጸም ችግሮች መኖራቸው ጭምር ስለደንበኞቹ መብት በስፋት መናገር፣ መጻፍ ትርጉም እንዲያጣ እያደረገው ነው፡፡

ባንኮች ያለባቸውን የደንበኛ ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ የተግባር አፈጻጸም በተመለከተ ራሱን የቻለ ጥናት ቢያስፈልገውም፣ እንከን ሳይኖርበት እየተፈጸመ ነው ለማለት ግን አይቻልም፡፡ በግል ተሞክሮ ጸሐፊው ለመታዘብ እንደሞከረው በተለያዩ ምክንያቶች የግላዊነት /Privacy/ መብቱ ይጣሳል፡፡ ቀዳሚው ምክንያት ባንኮች ላይ የሚታይ የቸልተኝነት አልፎ አልፎም መብቱ መኖሩን ካለማወቅ የሚመጣ ጥሰት ነው፡፡ የባንክ ሠራተኞች ሥራቸውን ሲፈጽሙ በሚያደርጉት ውይይት ሳይታወቅ መረጃ ይወጣል፡፡ ስለግላዊነት መብት /privacy/ ያላቸው ዕውቀትም አናሳ መሆኑ ግዴታውን ጠንቅቀው እንዳይፈጽሙ ያደርጋቸዋል፡፡

ሌላው ምክንያት የመብት ጥሰቱ ባህርይ ነው፡፡ ባንኮች ወይም በሥራቸው የያዟቸው ሠራተኞች የደንበኞችን ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ ሲጥሱ ጥሰቱን ለማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ የአንድ ደንበኛ የባንክ ሒሳብ ቁጥሩ፣ መጠኑ፣ ወዘተ. ለሦስተኛ ወገን ከደረሰ በኋላ /መረጃውን ሦስተኛ ወገን ከተጠቀመበት በኋላ/ ስለሚታወቅ የጣሰውን ለመለየት ያስቸግራል፡፡ ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ በባንኮች አካባቢ ያለው ተሞክሮ እንዲያውም ጥሰቱን የሚያበረታታ ነው፡፡ ባንኮች በከተማ ውስጥ ያሉ ቅርንጫፎችን በኤሌክትሮኒክ መረብ /Electronic Networking/ ያያያዙ በመሆኑ የአንድ ደንበኛ የባንክ ሒሳብ ከተከፈተበት ቅርንጫፍ ውጭ ባሉ በሌሎች ቅርንጫፎች አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ሥርዓት የተፈጠረ ሲሆን፣ የባንኩ ሠራተኞችም የግለሰቡን የባንክ ሒሳብ /ወጪውን ገቢውን/ ለማየት ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ የባንክ ሒሳብ ውስጥ መጨመር፣ መቀነስ፣ ማግባት፣ ማውጣት የሚሠራን ሠራተኛ /Operating banker/ የሚለይ እንጂ መረጃውን የሚመለከትን ሠራተኛ ማንነት የሚገልጽ ባለመሆኑ፣ የግዴታውን ተፈጻሚነት ዋጋ ያሳጣዋል፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ባንኮች ሒሳቡን ከየትኛውም አቅጣጫ የተመለከተውን ግለሰብ ለመለየት የሚያስችል አሠራር /System/ መኖሩን አንዳንድ ሰዎች ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር በሌለበት ሁኔታ ግን ሦስተኛ ወገኖች መረጃን ከማን እንዳገኙ ለመለየት ስለሚያዳግት ሚስጥራዊነት ገደል ይገባል፡፡ ሦስተኛ ወገኖችም የደንበኛ ሚስጥር እንዲሰጣቸው የመጠየቅ መብት አለመኖራቸውን ባለማወቅ መረጃ በሚጠይቁበት አጋጣሚ በሚፈጠር ጫና የባንክ ሠራተኞች መረጃ ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኞችና ፖሊሶች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጋዜጠኞች በሚዘግቡት ዜና ወይም በሚያቀርቡት ሪፖርት የባንክ ደንበኛ ሒሳብ፣ የብድር ታሪክ፣ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ወዘተ. የሚጠይቁበት አጋጣሚ አለ፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ግን ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ የማግኘት መብት ቢደነግግም፣ የሦስተኛ ወገን የንግድ ሚስጥርና የፋይናንስ መረጃ ሊገለጽላቸው እንደማይገባ ስለሚደነግግ ባንኮች ጋዜጠኞችን በሕጉ መሠረት ሊያስተናግዱ ይገባል፡፡ ፖሊሶችም መረጃ በሕግ አግባብ በተፈቀደላቸው መልኩ መረጃ የሚያገኙ ካልሆነ ግላዊነት ይጣሳል፡፡ ፖሊሶች የደንበኛን መረጃ ለማግኘት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ከሆኑ ግን ያለ ፍርድ ቤት ፈቃድ መረጃ ሊሰጣቸው እንደሚችሉ ልብ ይሏል፡፡

በሌላ በኩል የባንክ ደንበኞችም የግል የባንክ ሒሳባቸው በሚስጥራዊነት  ሊጠበቅ እንደሚገባ ዕውቀቱ የላቸውም፤ ግላዊነት መብት እንዳላቸው ቢያውቁም ለመተግበር ቁርጠኛ አይሆኑም፡፡ ባለቤቱ የማያስፈጽመው መብት /in-exercisable right/ ደግሞ በወረቀት ላይ ከመኖሩ ውጭ ማኀበራዊ ፋይዳ የለውም፡፡ ይህ መብት በመጣሱ ምክንያት ለባንኮችም ሆነ ለፖሊስ አቤቱታ ያቀረበ ደንበኛ ስለመኖሩ ማስረጃ ማግኘት ከባድ ነው፡፡

የመብቱ ጥሰት መኖሩ በደፈናው ቢታወቅም እንኳን በፍርድ ቤት ጥሰቱ ስለመኖሩ በአሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ያስቸግራል፡፡ መብቱ በመጣሱ የተነሳ የደረሰውም ጉዳት እንደዚሁ ለማወቅና ለማስረዳት ያስቸግራል፡፡ በባንክ ውስጥ ያለው የመተማመን /Trust/ እና የመተባበር /Cooperation/ አሠራር ተቋማዊ ኃላፊነትን እንጂ ግለሰባዊ ኃላፊነትን ለማስረዳት አያስችልም፡፡

በአጠቃላይ በባንክ ሒሳብ የሚከፍቱ ደንበኞች ሒሳባቸው በሚስጥራዊነት  የመጠበቅ መብት ቢኖራቸውም፣ በሕግ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ገደቦችና በአተገባበር ለመፈጸም አዳጋች መሆናቸውን አስተውያለሁ፡፡ ባንኮች ለሠራተኛቸው የሥነ ምግባር መመርያ በማዘጋጀት ቢያሰለጥኑ፣ ብሔራዊ ባንክ የሚስጥራዊነት መብት መከበሩን በአግባቡ ቢቆጣጠር፣ በብሔራዊ ደረጃ የሚዘጋጁትም /National Payment System, Core Banking System/ ሆነ በባንኮች የውስጥ አሠራር የሚዘጋጁት ኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓቶች የግላዊነት መብትን /Privacy rule/ የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ቢደረግ፣ መብቱ ተጥሶ ሲገኝም ባለመብቶች በፍርድ ቤት መብታቸውን ቢያስከብሩ መብቱ ከወረቀት ያለፈ ትርጉም ይኖረዋል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...